April5/2014
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የተሰማሩ የእንግሊዝ ኩባንያዎች በርካታ ችግሮች እያጋጠማቸው ነው በማለት የእንግሊዝ ኤምባሲ ቅሬታውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቀረበ፡፡
እንግሊዝ ኤምባሲ ሰሞኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩባንያዎቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በመዘርዘር በደብዳቤ አሳውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናትና ከእንግሊዝ ኩባንያዎች ተወካዮች ጋር ተነጋግረዋል፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንግሊዝ የንግድ አባላትን ለማነጋገር መፍቀዳቸው የሚያበረታታ ነው፡፡ ስብሰባው በአሁኑ ወቅት የሚታዩት ችግሮች ምን እንደሆኑ እንዲረዱ አስችሏቸዋል፡፡ አንዳንዶቹን ችግሮች ለመፍታት እንደሚሞክሩም አስታውቀዋል፡፡ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ለመሥራት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎትም ተረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ቆይታ እንዲኖራቸው ቆርጠው መምጣታቸውንም እንዲሁ፤›› በማለት በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ግሬግ ዶሪ በኢሜል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ18 በላይ የእንግሊዝ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን የገዛው ዲያጆ፣ ከዳሸን ቢራ ፋብሪካ ጋር በሽርክና ደብረ ብርሃን ላይ አዲስ የቢራ ፋብሪካ በመገንባት ላይ የሚገኘው ዱት፣ ኢትዮጵያ ቆዳ ፋብሪካን የገዛው ፒታርድስ፣ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማራው ኒዮታ፣ በደቡብ ኦሞ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማራው ታሎው ኦይል፣ የወጥ ቅመም የሆነውን ክኖር የሚያመርተው ዩኒሊቨር፣ በኦጋዴን በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማራው ኤጃ፣ በአፋርና በትግራይ ወርቅ ፍለጋ ላይ የሚገኘው ስትራቲክስ ኢንተርናሽናል ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች እየደረሱባቸው ካሉ ችግሮች መካከል የሎጂስቲክስ አገልግሎትና የትራንስፖርት ችግር፣ በጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም የቆይታ ጊዜ የተራዘመ መሆኑና በንግድ ሒደት የሚያጋጥም ከፍተኛ ወጪ ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ ችግሮች ቢፈቱ በቀላሉ የመንግሥትን ወጪ ከመቆጠብ ባሻገር የሙስና በር ይዘጋል በማለት ኤምባሲው አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ ለማውጣት ረዥም ጊዜ መወሰዱ፣ የነዳጅና ጋዝ ፍለጋ እየተፋጠነ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለመኖርና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መመርያ የውጭ ኩባንያዎች የገንዘብ አቅርቦት 50/50 እንዲሆኑ መደረጉ እንደ ችግር ተነስተዋል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት ጠቅላይ ማኒስትር ኃይለ ማርያም የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ይህንን ችግር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
እንግሊዝ በዓመት ለኢትዮጵያ 16 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ የምታደርግ ብቸኛ አገር ናት፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት በበርካታ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር የሚሠራ ሲሆን፣ የመከላከያ ሠራዊት ትራንስፎርሜሽንና የ25 ዓመት የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተር ፕላን ጥናቶችን ይሠራል፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ወደ እንግሊዝ ያደላ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩልም ዕድገት እያሳየ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም. እንግሊዝ ከኢትዮጵያ 48 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ ዕቃ ገዝታለች፡፡ ይህ ቁጥር በ2005 ዓ.ም. 70 ሚሊዮን ፓውንድ ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያ 77 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ ዕቃዎችን ከእንግሊዝ ገዝታለች፡፡ በ2005 ዓ.ም. ይኼ ገንዘብ 99 ሚሊዮን ፓውንድ ደርሷል፡፡
No comments:
Post a Comment