Saturday, April 26, 2014

ሰበር ዜና • የአዲስ ጉዳይ ጋዜጠኛ በፖሊስ ታሰረ

April 26/2014

• ምክንያቱ እስካሁን ግልጽ አልተደረገም
የአዲስጉዳይ መጽሄት ከፍተኛ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ እስካሁን ለመጽሔቱ ባልደረቦች ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ዛሬ ሚያዝያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም ማለዳ በፖሊስ ታስሯል።
በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ በከፍተኛ አዘጋጅነት የሚሰራው ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ ማለዳ ከቤቱ ሲወጣ በመኪና ሲጠብቁት በነበሩት ፖሊሶች ሲሆን በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራ ማዕከል በእስር ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ጉዳይ ስለባልደረባው የእስር ምክንያትና ሁኔታ ለማጣራት ባደረገው ሙከራ የተገነዘበው ነገር ቢኖር ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ ፖሊስ ክበብ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ወጥቶ በሰላም ወደስራው በመሄድ ላይ ሳለ በመኪና ቆመው ሲጠብቁት በነበሩትና ከማዕከላዊ ምርመራ እንደመጡ በተናገሩ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋሉን ብቻ ነው።
ቤተሰቦቹ እንደተናገሩት የፖሊሶቹ ቁጥር 9 የሚደርስ ሲሆን ከመካከላቸው አንዱ ብቻ ነው ዩኒፎርም ያደረገው። በብርበራው ወቅት ፖሊሶቹ ወደጋዜጠኛው ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት ማንም ሰው እንዳይገባም ሆነ እንዳይወጣ ከልክለዋል ብለዋል።
የአዲስ ጉዳይ ባልደረቦች ከቤተሰቡ እንደተገነዘቡት ከሆነ ጋዜጠኛ አስማማውን ፖሊሶቹ ማለዳ ላይ ይዘውት ከሄዱ በኋላ ረፋድ ላይ መልሰው ወደቤቱ ይዘውት መጥተዋል። ከዚያም መኖሪያ ቤቱን ከማለዳው 4 ሰዓት እስከ10 ሰዓት ድረስ ሲበረብሩ የቆዩ ሲሆን አራት ፌስታል የተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶችና ጋዜጠኛው የሚጠቀምበትን ላፕቶፕ ይዘው ሄደዋል።
በብርበራው ወቅት ቤተሰቦቹ ለጋዜጠኛው ምግብ ለመስጠት የጠየቁ ቢሆኑም ፖሊስ ግን ፍቃደኛ አለመሆኑን ተናግረዋል። ጋዜጠኛ አስማማው ብርበራው በተካሄደበት ወቅት በፖሊሶች በካቴና ታስሮ ቤት ውስጥ ነበር ብለዋል ቤተሰቦቹ።
በመጨረሻም ፖሊሶቹ ለምርመራ ወደማዕከላዊ ይዘውት እንደሄዱ ለቤተሰቦቹ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አዲስ ጉዳይ የደረሰው መረጃ የለም።
አዲስ ጉዳይ ጋዜጠኛውን ፖሊስ አነጋግሮ ይለቅቀዋል የሚል ተስፋ ይዞ እስካሁን ሰዓት ድረስ ቢጠብቅም የጋዜጠኛው ከእስር መለቀቅ አጠራጣሪ በመሆኑ ይህንን ሰበር ዜና ይፋ አድርጓል።
ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ በሮዝ መጽሄት (በአሁኑ አዲስ ጉዳይ) ከቅጽ 1 ቁጥር 1 ህዳር 1999 ዓ.ም የመጀመሪያ እትም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ7 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያው በመጽሄቱ ከፍተኛ አዘጋጅነት እያገለገለ የሚገኝና ጋዜጠኝነትን የሚሰራ የአዲስ ጉዳይ ጋዜጠኛ ነው።
አዲስ ጉዳይ በእስር ላይ የሚገኘውን የመጽሄቱን ከፍተኛ አዘጋጅ የእስር ምክንያት ከሚመለከታቸው አካላት በማጣራት ተከታትሎ መረጃውን ለህዝብ የሚያቀርብ መሆኑን ለማሳወቅ ይወድዳል።

No comments: