Saturday, April 29, 2017

ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ፤

April 29,2017
ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ፤
ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ፤
ሚያዚያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም፤ በባሕር ዳር የመስቀል አደባባይ በነበረ የዘፈን ኮንሠርት ላይ ምሽት 1፡30 አካባቢ በፈነዳ ቦንብ ዝግጅቱ ተቋርጦ የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊሶች ጥይት ይተኩሱ እንደነበር የመረጃ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የዳሽን ቢራ ስሙን ወደ ባላገሩ መቀየሩን ተከተሎ በባሕር ዳር ከተማ የዘፈን ኮንሠርት በማዘጋጀት ለሕዝብ የማስተዋወቅ የመጀመሪያ ሙከራው ሲሆን ኩኩ ሰብሰቤና አረጋኸኝ ወራሽ ነበሩ፡፡ ወንድሞቻችን እየተገደሉና እየታሰሩ ምንም ዓይነት ዘፈንና ጭፈራ አንፈልግም በሚል የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ወደ ኮንሠርቱ እንዳልሄደ ነው የነገሩን፡፡ የሥርዓቱ ደጋፊዎች የሆኑ ጥቂት ሰዎች በታደሙበት በዚህ ኮንሠርት ኩኩ ሰብስቤ ‹‹ቻልኩበት›› እያለች በመዝፈን ላይ ሳለች ድንገት ከፍተኛ የቦንብ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ በዚህም አደባባዩ ውስጥ የነበሩ ቁጥራቸውና የጉዳት መጠኑ በውል ያልታወቁ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
ኩኩ ዘፈኗን አቋርጣ መጠጊያ ፍለጋ ለመሸሽ ተገዳለች፡፡ መድረኩ ላይ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ዘፈኑን አቋርጠው የሸሹ ሲሆን ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ከፍተኛ ተኩስ ተከትሏል ብለውናል መረጃዎቻችን፡፡ አስተያየቱ የሠጡን ሰዎች ‹‹እኛ አገር አጥተን የምን ‹ባላገሩ› የሚል አተላ ሹፈት ነው›› ብለውናል፡፡ ይህን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ሰዐታት ብቻ ከመቶ ያላነሱ ወጣቶች በገፍ ታሥረዋል ብለውናል፡፡ በቀበሌ 15፣ 04፤03፣ 05፣ 06 አካባቢዎች የተገኘ ማንኛውም ሰው እየታሠረ እንደሆነ የመረጃ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአዲስ ዘመን እስከ አምባጊወርጊስና ትክል ድንጋይ ድረስ ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኦባንግ ሜቶ ከከፋ አደጋ ተረፉ!

April 29, 2017

  • “ዳግም የመኖር እድል ተሰጠኝ፤ ተማርኩበት፤ እናንተም ተማሩ”
“ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ በሁሉም ስፍራ፣ በየትኛውም አጋጣሚ ለሚፈልጋቸው ሁሉ “አለሁ” የሚሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ዘረኝነትን፥ ዘውገኝነትን፥ ጎሠኝነትን አጥብቀው ይዋጋሉ። ይጸየፉታል። ከዘር ቆጠራና ከቂም የጸዳች ኢትዮጵያን ማየት ህልማቸውና የመጨረሻ ግባቸው ነው።
ሰብዓዊነት ለአፍታም ከአንደበታቸው የማይለይ፣ በሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ የሚወደዱ፣ ግልጽ ተናጋሪነታቸው ልዩ የሚያደርጋቸው ኦባንግ በዚሁ ባህሪያቸው “አባ ነቅንቅ” የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። በስደት ለሚሰቃዩ የኢትዮጵያ ልጆች /እሳቸው ቤተሰቦቼ የሚሏቸው/ በጠሯቸው ቦታና ሁሉ በመገኘት ለሚያሳዩት ትጋት አቻ የላቸውም። ኢትዮጵያን በመወከል በከፍተኛ ቦታዎች የሚሟገቱ፣ ያዘነውን የሚጎበኙ፣ ለሴት እህቶቻችን ቀድመው የሚደርሱ እኚህ ውድ ሰው በድንገተኛ የመኪና አደጋ ተዓምር ሊባል በሚችል አጋጣሚ ከሞት የመትረፋቸው ዜና ስንሰማ ደንገጠናል። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አብሯቸው የነበረ ባልደረባቸውም ከዚህ ዘግናኝ አደጋ አምልጧል።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ሚያዚያ 14 2009ዓም /22.04.2017 ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ የደረሰባቸውን የመኪና አደጋ አስመልክቶ “ዳግም የመኖር ዕድል ተሰጠኝ፤ ተማርኩበት፤ እናንተም ተማሩበት። ዜናው የእኔ ከአደጋ መትረፍ ሳይሆን በቅጽበት የምትሰናበተውን ህይወታችንን በሚገባ ልንጠቀምበት እንደሚገባ መማሩ ላይ ነው” ሲሉ ነበር የገለጹት።
“አዎ” አሉ ጥቁሩ ሰው። “አዎ! ሞትን ለቅጽበት አየሁት። እንዳልወሰደኝ ስረዳ ሰዎች በቅጽበት ታሪክ እንደሚሆኑ በመረዳት በህይወት ዘመናቸው ደግ ለመስራት ለራሳቸው አለመማላቸው አሰብኩ” ሲሉ መልዕክታቸውን የጀመሩት ኦባንግ “እንኳን ነገ፣ በደቂቃዎች ምን እንደምንሆን ማስተማመኛ በሌለበት ሁኔታ ሰዎች ስለበቀልና ሌላውን ስለማጥፋት ስልት እየነደፉ ለመኖር መምረጣቸው አሳዘነኝ”።
ይህንን ሲናገሩ “የሚጸጽተዎ ነገር አለ እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረን ነበር። ኦባንግ ግን መልሳቸው ሌላ ነው። “እኔ ጸጸት ብሎ ነገር አላውቅም። የምጸጸትበት ነገርም ስለመፈጸሜ አስቤ አላውቅም። ነገር ግን ለወገኖቼ መሥራት የሚገባኝን እንዳልሰራሁ አስባለሁ። በተለያዩ ምክንያቶች ያስብኩትን ያህል አልተጓዝኩም። ይህ ከጸጸትም በላይ ነው። ምክንያቱም ዘረኝነትን ረግጠንና ቀብረን መጓዝ አለመቻላችን መድሃኒት የሌለው የቅዠት ተስቦ በሽተኛ አድርጎናል” ብለዋል። በውል የማይታወቅ ዘመን ወደኋላ በመሄድ ለአሁኑ ትውልድና ለአገራችን በማይጠቅም ጉዳይ ላይ ጉልበት፣ ሃብትና ጊዜ እየባከነ መሆኑንን የጠቆሙት ጥቁሩ ሰው “ከዚህ አዙሪት ሳንወጣ ሞት ይወስደናል፥ ለትውልድ የማይድን ቁስል ትተን፥ ትውልዱን መርዝ ወግተን እናልፋለን” ይላሉ።
ተፈጥሮ በጥድፊያ ወደ ሞት እየገፋችን ባለበት ሰዓት ሰው ሌላውን ስለመበቀልና ስለማጥፋት ዕቅድ ይዞ መስራቱ ከምንም ነገር በላይ ልብ የሚሰብር እንደሆነ ኦባንግ በሃዘኔታ ነው የገለጹት። “የማውቃቸውም ሆነ የማላውቃቸው በርካታ ወዳጅ ቤተሰቦች እንዳፈራሁ አውቃለሁ። ይህን ዜና ሲሰሙ እንደሚያዝኑ እረዳለሁ። ከዜናው በላይ ግን ለሚሰሙ ትምህርት እንዲሆን ይህንን መልዕክት ለማስተላለፍ ስል መናገርን መርጫለሁ። ዳግም የመኖር ዕድል ስለተሰጠኝ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ስል ከሞት መልስ የተማርኩትን አካፍያለሁ። ለሚሰማ ትልቅ ጉዳይ ነው” ሲሉ ማሳሰቢያ አዘል መልክታቸውን ኦባንግ አስተላልፈዋል።
ከዘርና ከዘረኛነት ቋት ወጥተው “ከጎሳ በፊት ሰብዓዊነት” በሚል አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልትተከልበት የሚገባውን መርህ የሚያቀነቅኑት ኦባንግ “መለስ ሲነገረው ቢሰማና ለአንድ ቀን ቀና ሰው ስለመሆን ቢያስብ፣ ብለን ብንመኝ ቢያንስ በቅርቡ ያለቁትን በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ነፍስ ማትረፍ፣ እየሰፋ የመጣውን የጎሳ በሽታ መቀነስ በቻልን ነበር። ግን ያሳዝናል በተቃራኒው ነው የሆነው። ያለመውንና ያሰበውን ሳያይ ህይወቱ በጥላቻና በዘረኝነት እንደመረረች ሄደ” ሲሉ የቀናነት እጥረት በሽታ ክፋት ያስረዳሉ።
የኮምፒውተር እቃ ለመግዛት አንድ መደብር ደረሰው ሲመለሱ የ18 ዓመት ወጣት ሴት በፍጥነት እያሽከረከች ሊያመለጡት በማይችሉበት ሁኔታ ተምዘግዝጋ ኦባንግ የሚያሽከረክሩትን መኪና በሳቸው በኩል ጎኑንን መታችው። ወጣቷ በከፍተኛ ፍጥነት ላይ ስለነበረች የኦባንግ መኪና ምቱ እንዳረፈባት ወደ ጎን ተገለበጠች። በመጨረሻም የአውራ ጎዳናው ጠርዝ መኪናዋን ያዛትና በቋፍ ተደግፋ እግሯን ሰቅላ ተገልብጣ ቆመች። የመውጫ በሮቹ በሙሉ ተቀርቅረውና ተጨረማምተው ስለነበር ዕርዳታ ሰጪዎች ባደረጉት ድጋፍ ኦባንግና ባልደረባቸው በኋለኛው በኩል ባለው የእቃ መጫኛ በር ሾልከው እንዲወጡ ተደረገ።
አደጋው ከደረሰ በኋላ አካባቢው ላይ የነበሩ ሰዎች እያነቡ ውስጥ የነበሩት እነ ኦባንግ ሲወጡ ሰላም መሆናቸውን ሲመለከቱ መገረማቸውን መስክረዋል። ፖሊስም ያለ አንዳች ጭረት፣ ደም፣ ስብራት፣ … ኦባንግና ባልደረባቸው መትረፋቸው “ድንቅ” ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ ተናግሯል። እንደ ፖሊስ ገለጻ መኪናዋ ከተመታቸበት ቦታ ትንሽ ወደ አሽከርካሪው ተጠግቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ኦባንግ “ከሞት መልስ ተማርኩ” ለማለት እንደማይበቁ ይሆኑ ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ ጥቁሩ ሰው “በፈጣሪ ኃይል ከሞት ተረፍኩ፣ ዳግም የመኖር ዕድል ተሰጠኝ ያልኩት ለዚህ ነው” ብለዋል።
አያይዘውም በቀናነት፣ በታማኝነት፣ በጸዳ ህሊና፣ በሃቅ፣ በመታመን፣ ለአገርና ለህዝብ ከመስራት የበለጠ የሚያኮራ ነገር እንደሌለ ተናገረዋል። በዘርና በጎሳ ተቧድነው፣ ጥላቻን መነሻ መሠረታቸው አድርገው፣ ሌላውን ለማጥፋትና ለመበቀል ዝግጅት እያደረጉ ላሉ፣ ዘመኑ በውል በማይታወቅ ጊዜ ወደኋላ ተመልሰው ቂምን የሚያራግቡና የክፋት ዘርን የሚረጩ ሁሉም ቆም ብለው በማሰብ ራሳቸውን ወደ መግዛት ብልኃትና ጥበብ እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
እሳቸው ከሞት አፋፍ መልስ የተማሩት ይህንን ነውና በግላቸው ከቀድሞው በላይ ራሳቸውን ለህዝብ እንደሚያስረክቡም ቃል ገብተዋል። ዜናውን አስቀድማ የነገረችን ምስክር “ኦባንግን ማጣት እንደ አገር ክስረት ነበር የሚሆነው። ኦባንግ ጀርባቸው የጸዳ፣ ለሚፈለገው ዓይነት ኃላፊነት የሚታመኑ፣ ታላቅ ራዕይ ያላቸው፣ ከነፈሰው ጋር የማይነፍሱ፣ ራሳቸውን ሆነው በነጻነት የሚኖሩ፣ የአንደበት ሳይሆን የተግባር ሰው የሆኑ … ኢትዮጵያዊ” ስትል ገልጻቸዋለች። አያይዛም “ከሚሠሩት ከፍተኛ ሥራ 10 በመቶውን ብቻ አደባባይ የሚያወጡ፣ ጊዜና ትውልድ በሰዓቱ ክብር የሚሰጣቸው ሰው እንደሆኑ አምናለሁ። የተረፉትም ለዚሁ ዓላማ ነው” ስትል ይህንን የተናገረችው የሚሰሩትን ሥራ ሁሉ በቅርብ ጠንቅቃ ስለምታውቅ መሆኑንንም አመልክታለች።
ኢትዮጵያን አስመልክቶ በከፍተኛ ቦታዎች በዝግ ስለሚሠሩት ሥራ ለምን በአደባባይ እንደማይገልጹ በተደጋጋሚ ኦባንግ ተጠይቀው “ገና ምን ሰራን፣ ሥራው ራሱ ሲገልጸው ማየት ይሻላል” የሚል መልስ በዚሁ ገጽ ላይ መመለሳቸው አይዘነጋም።
የመኪናውን አደጋ ያደረሰችው የ18 ዓመት ወጣት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ለመረዳት ተችሏል። የመኪና አደጋ ሲደርስ ሰዎች በአብዛኛው እርስበርስ ሲካሰሱና ሲሰዳደቡ በተደጋጋሚ የታየ ቢሆንም በዚህ አደጋ ወቅት ኦባንግ ልጅቷን በማረጋጋትና በማጽናናት የፈጸሙት ተግባር የልጅቷን ቤተሰቦችና ባካባቢው የነበሩትን ሁሉ ያስደመመ እንደነበር በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ለአቶ ኦባንግ፣ ለባልደረባቸውና ለልጅቷ፣ እንዲሁም ለወዳጆቻቸው ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ይላል።
ከጎልጉል የድረ ገጵ ጋዜጣ የተወሰደ

Thursday, April 20, 2017

የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንዳስታወቀው በክልሉ 66 ሽህ 102 ዜጎች በፍርድ እና ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።

Aptil 20,2017

ሚያዝያ ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንዳስታወቀው በክልሉ 66 ሽህ 102 ዜጎች በፍርድ እና ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።

በክልሉ የእስረኛው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ በመሄዱ የክልሉ ባለስልጣናት መፍትሄ እንዲሰጡበት ጠይቋል። እስረኞቹን ለማስተናገድ የተበጀተው በጀት ማለቁንም ኮሚሽኑ አስታውቋል። እስረኞቹ በአማካኝ ከ5 እስከ 10 ዓመታት በፍርድ ወይም ያለፍርድ በእስር እንደሚማቅቁ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ክልሉ ለ 22 ሺ 26 እስረኞች በቀን 9 ብር በድምሩ 203 ሺ 139 ብር፣ በአመት ደግሞ 73 ሚሊዮን 130 ሺ 40 ብር ወጪ ቢያደርግም፣ አሁን የእስረኞች ቁጥር በ3 እጥፍ በመጨመሩ ለማስተናገድ አለመቻሉን የክልሉ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ገልጿል፡፡

 የክልሉ ማረሚያ ቤት ለእስረኞች ህክምና ያወጣውን 2 ሚሊዮን 246 ሺ ብር ለመክፈል አልቻለም። የሁለት አመት ውዝፍ የህክምና ወጪ ለመክፈል ባለመቻሉም የጤና ተቋማት ለማስተናገድ ፈቃደኛ አንሆንም እያሉት መሆኑንም ገልጿል። እያንዳንዱ እስረኛ በአማካኝ 5 ዓመት በእስር ቤት ቢቆይ በጠቅላላው 1 ቢሊዮን 365 ሚሊዮን ፣ 200 ሺ ብር ምንም እሴት በማይጨምር ነገር ላይ ወጪ የደረጋል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጿል።

የእስረኞች ቁጥር በአንዴ ያሻቀበው በ2008 ዓም የታየውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ያለምንም የፍርድ ውሳኔ የታሰሩ ወጣቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ነው። ይህ አሃዝ በማረሚያ ቤት አስተዳደር ስር የሚገኙ እስረኞችን እንጅ በየወረዳው እና በየቀበሌው ታስረው የሚገኙትን ዜጎች ቁጥር አያካትትም። በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለአመት፣ ለወራት ወይም ለሳምንታት የሚታሰሩት እስረኞች ቁጥር ቢደመር በክልሉ የሚገኘው እስረኛ ቁጥር ከተጠቀሰው በብዙ እጅ ይልቃል። በአማራ ክልል ያለውን የእስረኞች ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ህጋዊ በሚባሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንደሚኖሩ ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።

ህዝብ ተፈናቅሎ እያለቀሰ ባለበት ሰአት የመሰረት ድንጋይ አላስቀምጥም

April 20,2017
ሚያዝያ ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 9 የሚገኝ 10 ሺህ ካሬ/አንድ ሄክታር/ ለሆቴል ግንባታ በካሬ 650 ሺህ ብር ሊዝ የገዙት የኳታሩ ባለሃብት ፣ አገዛዙ ቦታው ላይ የሰፈሩትን ነዋሪዎች በሙሉ አንስቶ ቦታውን አጽድቶ መጨረሱን በመግለጽ የመሰረት ድንጋይ እንዲያስቀምጡ ቢጋብዝም፣ ባለሃብቱ ግን ‹‹ህዝብ ተፈናቅሎ እያለቀሰ ባለበት ሰአት የመሰረት ድንጋይ አላስቀምጥም›› ማለታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ባለሃብቱን ለማግባባት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን፣ የኳታሩ መሪን የኢትዮጵያ ጉብኝት አስታኮ የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ቀይ አሸዋ አፍስሰው የተጠረበ ድንጋይና ስሚንቶ አዘጋጅተው ቢጠብቁም፣ ባለሀብቱ ባለመቀበላቸው ድንጋይ የማስቀመጥ ስነስርዓቱ አልተከናወነም። የአካባቢው ነዋሪዎች መረጃውን ከክፍለ-ከተማውና የወረዳው መስተዳድር አካላት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። የኳታሩ ባለሃብት ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ የአዲስ አበባ መስተዳድር “ከዚህ በፊት የቤት ግምቱ ይሻሻላል፣ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ምትክ ቦታ በስምምነታችሁ መሰረት ይሰጣችኋል ፣ ይህ እስኪፈጸም በግዳጅ መፈናቀል አይኖርም” በማለት ለህዝቡ በአደባባይ የገባውን ቃል አጥፎ፣ ህዝብን በመከፋፈል፣ የተሳሳተ መረጃ በመስጠትና አፍራሽ ወጣቶችን አሰማርቶ በግዳጅ ለማፍረስ ከጀመረው ድርጊት አለመቆጠቡን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። መስተዳድሩ ለተፈናቃዮች የተሰጠው ቤት ይህ ነው በማለት ለባለሃብቱ የልደታ ኮንዶሚንየምን ማሳየቱን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ “ከእኛ መንግስት ይልቅ የኳታሩ ባለሃብት ያሳዩት ‹ሰብዓዊነት› በልጦ መገኘቱ፣ ይህ መንግስት እንደ ዜጋው እየተመለከተን ነው ብለን ለመቀበል አስቸግሮናል ›› በማለት ያሉበትን አሰቃቂ ሁኔታ ገልጸዋል። ተከራይ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ፣ ባለይዞታዎች ደግሞ በአብዛኛው ቤታቸውን በላያቸው ላይ አፍርሰው የግንባታ እቃዎችን በነጻ እንዲወስዱ በተፈቀደላቸው ‹አፍራሽ ወጣቶች› ፈርሶ ከአካባቢው እንዲለቁ የተደረጉ ሲሆን፣ በተለያየ ምክንያት ያለቀቁ ባለይዞታዎች የትንሣኤ በዓልን ‹‹ሌባ ሲጠብቁ ›› ማሰለፋቸውን በምሬት ገልጸዋል፡፡ እነዚሁ ባለይዞታ ነዋሪዎች — ያሉበትን አደገኛ ሁኔታ ቀኑን በሙሉ እዚያው ለሚውሉ የፖሊስ አባላት ቢያስረዱም ‹‹ እኛ ከዋናው መንገድ ወደ ውስጥ ለመግባት አንችልም፣ እኛም ለራሳችን እንፈራለን፣ አልታዘዝንም ›› በማለት መልስ መስጠታቸውን፣ ‹‹አፍራሽ ወጣቶችም ፖሊሶችን አፍርሰው ከሚያገኙት የጥቅም ተጋሪዎች እንዳደረጓቸውና ምንም እንደማይደረጉ በድፍረት የሚናገሩ መሆኑን፣ በሌላ በኩል አንዳንድ ፖሊሶች ‹‹ ይህ ወጣት የተወለደበትንና ያደገበትን ሠፈር ከማፍረስ መከላከል ሲገባው፣ ይህን ዓይነት ድርጊት ሲፈጽም እያያችሁ እኛን ምን አድርጉ ትላላችሁ›› ሲሉ በወጣቶቹ ሁኔታ ማዘናቸውን እንደገለጹላቸው አስረድተዋል፡፡