Monday, April 21, 2014

ከውጭ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ለመሥራት መቸገራቸውን ገለጹ

April 21 /2014

ከውጭ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ቢፈልጉም፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የቢሮክራሲ ችግሮች ፈተና እንደሆኑባቸው ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአገር ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የሙያ ዘርፎች ከተሰማሩ ተመላሽ የዳያስፖራ አባላት ጋር ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ፣ ከ500 በላይ የዳያስፖራ አባላት ተገኝተው ችግሮቻቸውንና ምሬታቸውን ለመንግሥት አሰምተዋል፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም፣ በንግድ፣ በማዕድን ፍለጋ ሥራና በትራንስፖርትና ማሽነሪዎች ኪራይ ላይ የተሰማሩ ከውጭ ተመላሽ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተሳተፉበት በዚህ ውይይት መድረክ ላይ፣ በተለይ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ሊያሠራቸው አለመቻሉን አስታውቀው፣ ፈቃድ ለማግኘት እስከ ሁለት ዓመትና አንዳንዶቹም ከዚያ በላይ እንደወሰደባቸው ተናግረዋል፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት በጐንደር ከተማ መሬት መውሰዳቸውን፣ የሆቴሉ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የአፈርና የዲዛይን ጥናት በውጭ ባለሙያዎች ለማሠራት ውጭ አገር ደርሰው ሲመለሱ መሬታቸው በአካባቢው አስተዳደር መወረሱን፣ አንድ ከአሜሪካ የተመለሱ ኢትዮጵያዊ ተናግረዋል፡፡

‹‹መሬቱን የወሰድከው በተጭበረበረ ዶክመንት ነው፡፡ ፎርጅድ ነው፡፡ አንተ ዳያስፖራ አይደለህም፡፡ እንዲያውም የሠራኸው ወንጀል በመሆኑ በሕግ ከመጠየቅህ በፊት ውጣ፤›› ብለው የአካባቢው የሥራ ኃላፊዎች ከቢሮ እንዳስወጧቸው እኚሁ ግለሰብ በምሬት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰላሳ ዓመት ከኖርኩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት ፎርጅድ ልሠራ ነው?›› በማለት መንግሥት እንዲፈርዳቸው ግለሰቡ ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ ያልሄዱበት እንደሌለና በፍርድ ቤት ፍትሕ ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም አለመሳካቱን የተናገሩት እኚህ ግለሰብ፣ ‹‹ወደነበርኩበት የሰው አገር ለመመለስ እየተሰናዳሁ ባለሁበት ወቅት ይህ ውይይት ተዘጋጅቷልና መፍትሔ ካገኘሁ ብዬ ነው የተገኘሁት፤›› በማለት የመንግሥትን ምላሽ ጠይቀዋል፡፡

ይህ መሰሉ አጋጣሚ ወይም መልኩን የቀየረ ሌላ ችግር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ተመልሰው ከመሥራት ይልቅ፣ አገራቸውን እየወቀሱ በሰው አገር መቅረትን እንዲመረጡ እያስገደዳቸው መሆኑ በተለያየ አጋጣሚ የተገለጸ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በተጠራው የውይይት መድረክ ላይ የተነሳውም ተመሳሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ሁሉንም ችግሮች ችለው በአገራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙትን ጭምር እየነካ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የገለጹ ሌላ አንድ በአውሮፓ ይኖሩ የነበሩ የሕክምና ባለሙያ፣ አገራቸው ከገቡ በኋላ በምግብ ይዘት የበለፀጉ እንክብሎችን በኔትወርክ ማርኬቲንግ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሁለት ሺሕ በላይ ሠራተኞች በሥራቸው እንደሚገኙና ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መመርያዎች ከንግድ ሥራቸው እንዳስተጓጐላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹መንግሥት መመርያ የሚያወጣው ለማስተዳደር እንጂ ማነቆ ለመፍጠር ለምን ይሆናል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹መንግሥት ያሉትን ችግሮች ለይቶ ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነ ውይይቶች ዋጋ የላቸውም፡፡ ዳያስፖራውም የኢትዮጵያ አንድ አካል በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ይሰጠው፤›› ሲሉ ተወያዮቹ ጠይቀዋል፡፡

በተለያዩ የዓለም አገሮች ከ2.5 እስከ ሦስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
አሁን በሥልጣን ያለው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከተቋቋመ ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን 2,947 ብቻ ነው፡፡ በውጭ ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመተው አንፃር በአገሪቱ ላለፉት 20 ዓመታት 2,947 የዳያስፖራ አባላት ብቻ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸው፣ መንግሥት ለዚህ ዕምቅ ሀብት የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ለመረዳት እንደሚችል የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ወደ ሥራ የገቡ የዳያስፖራ አባላት ሦስት ሺሕ አይሙሉ እንጂ፣ 22.3 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ 125,600 ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ቢሰጥ ሊፈጠር የሚችለውን ለውጥ የሚያሳይ ነው ይባላል፡፡

No comments: