April 25/2014
የአቡነ ማቲያስ የግብጽ ጉብኝት ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል
የአቡነ ማቲያስ የግብጽ ጉብኝት ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል
ሃያ አምስት በመቶ እንደተጠናቀቀ የሚነገርለት የ“ህዳሴው” ግድብ በኢትዮያና በግብጽ መካከል ከፈጠረው የፖለቲካ ቁርቋሶ በተጨማሪ ወደ ሃይማኖት መንደርም እየዘለቀ ነው፡፡ ዛሬ (አርብ) ግብጽን ለመጎብኘት ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩት አቡነ ማቲያስ ከግብጽ በኩል እንዳይመጡ በተላለፈላቸው መልዕክት መሠረት ጉብኝታቸውን ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፈውታል፡፡
በግብጽና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የተለያዩ የዜና ዘጋቢዎች እንዳሉት ከሆነ መልዕክቱ ያስተላለፉት የግብጹ ፓትሪያርክ አቡነ ታዋድሮስ ዳግማዊ ናቸው፡፡ ፓትሪያርኩ ለአቡነ ማቲያስ ባስተላለፉት መልዕክት በበርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው የአባይ ግድብ የፈጠረው ሁኔታ እንዳለ ሆኖ ይህንን ጉብኝት ማካሄድ የግብጽን ቤ/ክ “የሚያሳፍር” ይሆናል በሚል ነው ምክራቸውን ለአቡነ ማቲያስ የለገሱት፡፡
ስማቸውን ሳይጠቅሱ መረጃውን ለግብጽ የሚዲያ አካላት የተናገሩት ባለሥልጣን እንደሚሉት ከሆነ ሁለቱ ቤ/ክናት ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ቢኖራቸውም ግድቡን በተመለከተ ይፋዊ ያልሆነ ሽምግልና የማካሄዳቸው ሁኔታ የማያዛልቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሁለቱ ከፍተኛ የቤ/ክ መሪዎች በሚገናኙበት ወቅት ይህ ጉዳይ ሳይነሳ እንደማይታለፍ የታወቀ ነው፡፡
አቡነ ታዋድሮስ “አሳፋሪ” ያሉትን ጉዳይ በዝርዝር አልገለጹትም ሆኖም የግድቡ መሠራት ግብጽን ክፉኛ ያሳሰባት ጉዳይ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ስትገባ ከመቆየት አልፋ ኢህአዴግን ለሚቃወሙ የመሣሪያና የመሳሰሉ ዕገዛዎችን ለማድረግ ስትንቀሳቀስ መቆየቷ የሚታወስ ነው፡፡
በሃይማኖቱ ዓለም ከፍተኛ ትስስር ያላቸው የግብጽና የኢትዮጵያ ቤ/ክናት ከ“ህዳሴው” ግድብ ጋር በተያያዘ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳቸው የውጥረቱን አሳሳቢነት የሚገልጽ ነው የሚሉ ክፍሎች ግብጽ መረጋጋት ስታገኝ የሚሆነውን ለመተንበይ ያስቸግራል ይላሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ለዕርቅና ሰላም መሥራት በሚገባቸው ጊዜ ከፖለቲካው በላይ መሆን አለመቻላቸው ሹመታቸውም ከዚያው የመነጨ ለመሆኑ ማስረጃ ነው፡፡ አገልግሎታቸውም ከፖለቲካው ሥልጣን በላይ መሆን ያልቻለ መሆኑን በግልጽ ያሳያል በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ያነጋገራቸው ባለሙያ እንደሚሉት የግድቡ ሥራና በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው ሁኔታ ሁሉንም ሊያሳስብ የሚገባ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ ኢህአዴግ የግድቡን ሥራ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ማዋሉ “አስከፊ ነው” ብለዋል፡፡ “አባይን የመገደቡ ጉዳይ አሁን የታሰበ ወይም የተጀመረ አይደለም፤ በንጉሡ ጊዜም ሆነ በደርግ ጊዜ የነበረ ነው፡፡ እኔ የፖለቲካ ተንታኝም ሆነ የታሪክ ምሁር አይደለሁም ነገር ግን በግድቡ ሥራ ላይ ባለኝ ሙያ በከፍተኛ ደረጃ እሳተፋለሁ፡፡ ህወሃት እና ኢህአዴግ ለራሳቸው ርካሽ ፖለቲካ መጠቀሚያነት ሲያውሉትና ሕዝቡን ከንቱ በሆነ አገራዊ ስሜት አስገብተው የራሳቸውን ፖለቲካ ለማራመድ የሚያደርጉትን ሁሉ በየቀኑ በሥራችን ላይ የምናየው አስከፊ ልምምድ ነው፡፡ እኔ የትግራይ ተወላጅ በመሆኔ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቴ አባይ ለዚህ መዋሉ ያስደስተኛል ነገር ግን ኅብረተሰቡ ሲጠይቅ “የግብጽ ደጋፊ ነህ፤ ጸረ-ልማት ነህ ወዘተ” ማለቱ የትም አያደርስም፡፡ በዚህ ላይ ከአገሪቷ ኢኮኖሚ አኳያ የግድቡ ወጪም ሆነ፣ የባለቤትነቱ ጉዳይ እንዲሁም ሌላ በርካታ ጉዳዮች ሊጠየቁ የሚገባቸው ጥያቄዎች ናቸው” ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የአቡነ ማትያስ የግብጽ ጉብኝት ላሁኑ ተላልፎ የነበረ ሲሆን የአቡነ ታዋድሮስ የመስከረም ወር የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውም በተመሳሳይ ምክንያት መሰረዙ ይታወሳል፡፡
No comments:
Post a Comment