Thursday, April 17, 2014

በጭልጋ ወረዳ ተማሪዎች ባስነሱት ተቃውሞ ጉዳት መደርሱ ተሰማ

April 17/2014

 ኢሳት ዜና :-በሰሜን ጎንደር ዞን በጭልጋ ወረዳ በአይከል ከተማ ከቅማንት ብሄረሰብ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተነሳ የተማሪዎች ተቃውሞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በአድማ በታኝ ፖሊሶች ተደብድበው ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደ አካባቢው ሄዶ የተለያዩ መጠይቆችን በማድረግ በብሄረሰቡ ለቀረበው ጥያቄ መልስ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ችግሩ መነሳቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ፌዴሬሽኑ ጥናት በሚያደርግበት ወቅት ህዝቡን ታስተባብራላችሁ የተባሉ ከ68 ያላነሱ ሰዎች ከአካባቢያቸው ርቀው እንዲታሰሩ ተደርጓል። ከታሰሩት መካከል መምህራን የሚገኙበት ሲሆን፣ ለተማሪዎች ተቃውሞ መንስኤ የሆነውም የመምህራኖቻቸው ደብዛ መጥፋት ነው።

ተማሪዎቹ የታሰሩት የብሄረሰቡ መሪዎች ካልተፈቱ ትምህርት አንማርም በማለት ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ ሲያካሂዱት የነበረው ተቃውሞ ዛሬ ወደ ግጭት አምርቶ በርካታ ተማሪዎች እና የአይከል ከተማ ነዋሪዎች እንደተደበደቡና እንደታሰሩ ታውቋል።
ተማሪዎቹ  ጥያቄያቸውን በሰላም እያቀረቡ ባለበት ወቅት አድማ በታኝ ፖሊሶች አስላቃሽ ጪስ እንደተኮሱባቸውና አመጽ እንደተነሳ የአይን እማኞች ተናግረዋል። ግጭቱን ተከስቶ በርካታ ንብረትም ወድሟል::

አድማ በታኝ ፖሊሶች አሁንም ከተማዋን ተቆጣጥረው በመንገድ ላይ የሚያገኙትን ወጣቶች ሁሉ እየተደባደቡ መሆኑን እንዲሁም ከ10 በላይ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የወረዳውን ፖሊስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

No comments: