Friday, April 11, 2014

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የእሪታ ቀን ሰልፉን ከሶስት ሳምንታት በኋላ ለማድረግ ወሰነ !

April 10/2014

መጋቢት 28 ቀን ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀዉ የአንድነት የእሪታ ቀን ሰልፉ ፣ «ሰልፍ እንዲደረግ በታሰበበት ቀን፣ ሌሎች ዝግጅቶች ስላሉ በቂ ጥበቃ ልናሰማራ አንችልም» በሚል እውቅና ባለመስጠቱ ለሚያዚያ 5 ቀን መተላለፉ ይታወቃል።
የሚያዚያ አምስቱን ሰልፍ በተመለከተ ምላሽ የሰጠው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በሚያዚያ 5 ቀን ፣ ሩጫ ስለሚኖር ሰልፉ ለቅዳሜ ሚያዚይ 4 ቀን እንዲደረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአንድነት ፓርቲ የላከ ሲሆን፣ የሚያዚያ አራቱን ቀን ፣ ቅዳሜ በመሆኑና ግማሽ ቀን ሥራ የሚኖራቸው በርካታ ዜጎችን ስለሚኖሩ፣ አስተዳደሩ በጠየቀው ቀን ሰልፉን ለማድረግ ፍቃደኛ እንዳልሆነም የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች በጉዳዩ ላይ መክረዉበት ፣ የሚቀጥሉት ሁለት እሁዶች የባህል ቀናት እንደመሆናቸው፣ ከሶስት ሳምንታት በኋላ ሰልፉን ለማድረግ ማሰባቸውን ያነጋገርናቸው ከፍተኛ የአንድነት አመራር አባል ገልጸዉልናል።
ያንን በተመለከተ አስፈላጊዉን የማሳወቅ ደብዳቤ ለአስተዳደሩ የሚያስገቡ ሲሆን፣ በዚህ ሂደት፣ የተለያዩ ሩጫዎችን ለማስተናገድ ሲባል፣ መንገዶች ሲዘጉ፣ የትራፊክ መጨናነቅና የልማት ሥራ መደናቀፍ ሲፈጠር፣ ያላሳሰበው፣ የአዲስ አበባ አስተዳደሩ፣ ሕዝቡ ሕግ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ድምጹን ለማሰማት ሲዘጋጅ ይጨናነቃል፣ «የልማቱ ሥራ ይደናቀፋል፣ የትራፊክ መጨናነቅ ይኖራል» እያለ እውቅና አለመስጠቱ አሳዛኝ እንደሆነ የሚናገሩት የአመራር አባሉ ፣ «የኛን ሞራል ሞራል ለማዳከም የሚያደርጉት አሳዛኝ እንቅስቃሴ፣ ዉጤት እንዳመጣላቸው፣ ይልቅስ የበለጠ በቁርጠኝነት እንድንነሳ የሚያደርግ መሆኑን አውቀው፣ ከሶስት ሳምንት በኋላ አስፈላጊዉን ትብብር ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለኝ» ሲሉ በፓርቲያቸው ዘንድ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
የአንድነት ፓርቲ መጋቢት 28 ቀን በደሴ ከተማ እጅግ ታልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ይታወቃል። ፓርቲዉ ከደሴና ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዋሳ፣ ድረዳዋ፣ አዳማ በመሳሰሉት ወደ 14 በሚጠጉ ከተሞች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሆነም በስፋት ተዘግቧል።

No comments: