Friday, April 25, 2014

“የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴን በተመለከተ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላይ ያለን እምነት በመሟጠጡ ወደ አፍሪካ ኮሚሽን ወስደነዋል” – ዶ/ር አወል

April 25/2014
የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ወደ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶችና ህዝቦች ኮሚሽን ሂደው በመንግስት ላይ ክስ መመስረታቸው ይታወቃል። ይህንን በማስመልከትም በድር ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ቢቢኤን) የኮሚቴውን የክስ ሂደት በቅርበት ከሚከታተለው ዶ/ር አወል ቃሲም አሎ ጋር በዚሁ ጉዳይ ቆይታ አድርጓል። ዶ/ር አወል የአለም ዓቀፍ ህግ ምሁር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በLondon School of Economics የሰብዓዊ መብት Fellow ነው።

ቢቢኤን፡- የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጉዳያቸውን ወደ አፍሪካ ኮሚሽን ለመውሰድና ለመክሰስ ያሰቡት ለምንድን ነው? ጉዳያቸውን በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች መጨረስ አይችሉም ነበር?

ዶክተር አወል፡- አመሰግናለሁ። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ኮሚሽን ለመውሰድ የተገደደበት ምክንያት በኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ላይ ያለው እምነት በመሟጠጡ ነው። እነዚህ ፍ/ቤቶች እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ የህግ የበላይነትን፣ ህገ መንግስቱን እና የራሳቸውን ህሊና መሰረት በማድረግ ሊወስኑ ይችላሉ የሚለው ተስፋ በመሟጠጡ ነው። ይህ ክርክር ደግሞ በዋናነት የእውነት ጉዳይ ስለሆነ መንግስት ከዚህ በፊት ሚዲያውን እና የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን በአጠቃላይ እንደ መንግስት ያለውን ሙሉ ሀይል በመጠቀም መሬት ላይ ሲፈጥራቸው የነበሩ እውነታዎች እውነት እንዳልሆኑና ከዚያ በስተጀርባ ሌላ ነገር እንዳለ ይህም የተፈበረከ ነገር እንደሆነ ማሳየት የሚችሉት ገለልተኛና ዓለም አቀፍ የሆነ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ሌላ መንግስት ጫና ሊያሳድርበት የማይችልበት ተቋም ላይ በመሄድ ጉዳያቸውን አቤት ለማለት ነው ተከሳሾቹ ወደ አፍሪካ ኮሚሽን ሊሄዱ የቻሉት።

ቢቢኤን፡- እንግዲህ ይህን ጉዳይ ከመጀመሪያው ጀምረህ ስትከታተለው ነበርና የአፍሪካ ኮሚሽን ምን አይነት ድርጅት ነው? ምን ምን ጉዳዮችንስ ያያል?

ዶክተር አወል፡- በመጀመሪያ እኔ ጉዳዩን ከያዙት ጠበቆች አንዱ አይደለሁም። ለጠበቆቹ በተወሰነ ደረጃ የሰጠሁት እገዛ አለ፤ ጉዳዩን በቅርበት አውቀዋለሁ ነገር ግን ጉዳዩን ከያዙት ግለሰቦች አንዱ አይደለሁም። ወደ ጥያቄው ስንመለስ ኮሚሽኑ ምን ዓይነት ተቋም ነው ለሚለው የአፍሪካ ህብረት በውስጡ የተለያዩ ተቋማት አሉት ከነዛ ውስጥም አንዱ ይህ የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊና የህዝቦች መብት ኮሚሽን ነው። ይህ ኮሚሽን በ1987 በተፈረመው የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝቦች ቻርተር በሚል ሰነድ መሰረት የተቋቋመ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ነው።

ድርጅቱ ወይም ተቋሙ ሁለት መሰረታዊ ኋላፊነቶች አሉበት። የመጀመሪያው ይህን ሰነድ ፈርመው አባል የሆኑ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ማለት ነው በምን ዓይነት መልኩ የተጣለባቸውን የሰብዓዊ መብት ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሆነ፣ ምን ዓይነት የህግ ማውጣት፣ የዳኝነትና የአስፈፃሚ ተቋማትን እንደገነቡ መገምገም ነው። ስለዚህ ማንኛውም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነድ መንግስታት በዚያ ሰነድ ውስጥ የተቀመጡ ሰብአዊ መብቶችን ለማሟላት ይቻል ዘንድ አስተዳደራዊ የህግ ማውጣት እንዲሁም የዳኝነት እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይጠበቃል። ስለሆነም ኮሚሽኑ በዚህ በኩል የሚሰረው ስራ አገሮች ቻርተሩን ከፈረሙ በኋላ በዛ ቻርተር ውስጥ የተረጋገጡ መብቶችን በምን ዓይነት መልኩ ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑንና ምን ዓይነት እርምጃዎችንስ እየወሰዱ ነው የሚለውን ነገር ከአገሮች ሪፖርት እየተቀበሉ ያንን መመርመር ነው።

ሁለተኛው የተቋሙ ስራ ግለሰቦች የሚያቀርቡትን አቤቱታ ተቀብሎ ማየት ነው። በዚህ ሰነድ መሰረት መብት የተሰጣቸው ግለሰቦች መንግስቶቻቸው እዚያ ሰነድ ላይ የተረጋገጡ መብቶቻቸውን የሚጥሱ ከሆነ ለኮሚሽኑ አቤት ማለት ይችላሉ። ኮሚሽኑ አቤቱታቸውን ተቀብሎ የማየት ስልጣን አለው። በአጠቃላይ የኮሚሽኑ ስራ ይሄ ነው።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን በሚቀበልበት ጊዜ የሚያያቸው ነገሮች አሉ። እነዚህ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ሊያሟሉ የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ከነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ዋናው ግዴታ ምንድን ነው ከሳሾች ወደ ኮሚሽኑ ከመሄዳቸው በፊት ሀገሮቻቸው ውስጥ ያሉ የዳኝነት መፍትሄዎችን መጀመሪያ አሟጠው መጠቀም ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ይህ በ‘ሀገር ውስጥ ያሉ የዳኝነት መፍትሄዎች ከተሟጠጡ ብቻ ነው አቤቱታ የሚቀበለው’ የሚለው መርህ የሚሰራው እዚያ ሀገር ውስጥ ቀድሞውኑ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል የፍትህ ስርዓት ያለ እንደሆነ ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው እርከን /stage/ ይሄ admissibility የሚባለው ማለት የክሱ የተቀባይነት ሂደት /process/ ሲያልፍ ነው። ከነዚህ ውስጥ አሁን እንዳልኩህ ዋናው መስፈርት አገር ውስጥ ያሉ መፍትሄዎችን ማሟጠጥ መቻል ነው።

የኮሚቴዎቻችንን ጉዳይ /case/ ስንመለከት አገር ውስጥ ያሉ መፍትሄዎችን አሟጠዋል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም የክስ ሂደቱ እስካሁንም እንደቀጠለ ስለሆነ ማለት ነው። የክስ ሂደቱ ቢጠናቀቅና ቢፈረድባቸው እንኳ ተጠናቀቀ ማለት አንችልም። ምክንያቱም ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት መቻል አለባቸው። ስለዚህ መደበኛ በሆነው አካሄድ መፍትሄ ያለበት ሀገር ውስጥ ከሆነ ከሳሾች ወደ ኮሚሽኑ የሚሄዱት አገር ውስጥ ያለውን የይግባኝ እድሎች ካሟጠጡ በኋላ ነው። እዚህ አቤቱታ ላይ የቀረበው መከራከሪያ ምንድን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ effective እና practical የሆነ የሚሰራ መፍትሄ አካል ስለሌለ ኮሚሽኑ ሀገር ውስጥ ያሉ መፍትሄዎችን እንድናሟጥጥ መጠበቅ አይኖርበትም የሚል ክርክር ነው የቀረበው። ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ያለው jurispudence ምንድን ነው አንድ ሀገር የዳኝነት አካሏ ለተከሳሾች፣ ለሰብአዊ መብት ጉዳተኞች መፍትሄ መስጠት የማትችል ከሆነ እነዚያ ግለሰቦች ሀገር ውስጥ ያለውን መፍትሄ እንዲያሟጥጡ አይጠበቅም ብሏል።

በዚህ የኮሚሽኑ jurispudence መሰረትም ኮሚቴዎቹ እየተከራከሩ ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዳኝነት አካል ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ስለሆነና ምንም አይነት ተቋማዊ (institutional) አሰራርና ገለልተኝነት /functional independence/ ስለሌለው፣ የመንግስት ተለጣፊ ስለሆነ ባጠቃላይ ሀገር ውስጥ ልናገኘው የምንችለው ምንም አይነት መፍትሄ ስለሌለ ኮሚሽኑ ጉዳዩን ማየት መቻል አለበት የሚል ክርክር ነው ያቀረቡት። ኮሚሽኑ እዚህ ላይ በቅርብ ጊዜ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጲያ መንግስትም የኮሚቴዎቹ አቤቱታ ደርሶታል። መልስ እንዲሰጥ እየተጠበቀ ነው። በእርግጥ መልስ ይመልስ አይመልስ በአሁኑ ሰዓት እኔ መረጃ የለኝም። ነገር ግን እዚህ የመጀመሪያው step ላይ ኮሚሽኑ በቅርብ ጊዜ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ከዚያ በኋላ ነው ወደ merit ማለትም ወደ ዋናው case የሚኬደው ማለት ነው።

ቢቢኤን፡- ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩን አይቶ ለኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቦለታል ማለት ነው?

ዶ/ር አወል፡- ምንድን ነው እያልኩ ያለሁት ኮሚሽኑ አቤቱታውን ከተቀበለ በኋላ ያንን አቤቱታ ለተከሰሰችዋ አገር ይልካል። በእኛ ኬዝ ለኢትዮጵያ ማለት ነው። ከዚያም የኢትዮጵያ መንግስት ከሳሾች ላቀረቡት አቤቱታ መልስ ይሰጣል። መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው? በአሁኑ ሰዓት ተከሳሾች ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ መከራከርና ያለውን የፍትህ ስርዓት አሟጠው መጠቀም እንዳለባቸው፣ ለምን ኮሚሽኑ ይህንን ኬዝ ተቀብሎ ማየት እንደሌለበት ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው ስቴጅ እንዳልኩህ ክሱ ተቀባይነት ይኑረው ወይስ አይኑረው የሚል ክርክር የሚደረግበት stage ነው። ክሱ ተቀባይነት አለው የሚል ውሳኔ ኮሚሽኑ ከወሰነ የሁለተኛው stage የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግስት የሙስሊሙን ህብረተሰብና ኮሚቴ መብቱን ጥሷል ወይስ አልጣሰም ከተጣሰስ የትኞቹ መብቶች ናቸው የተጣሱት ወደሚለው ክርክር ይኬዳል ማለት ነው። ስለዚህ አሁን ያለነው የመጀመሪያው ስታጅ ላይ ነው። የኢትዮጽያ መንግስት ለኮሚሽኑ የገባው የከሳሾቹ አቤቱታ ግልባጭ ደርሶታል። መልስ እንዲሰጥም ይጠበቃል። በአሁኑ ጊዜ መንግስት መልስ ይስጥ አይስጥ እስካሁን የማውቀው ነገር የለም ግን አሁን ያለነው እዚህኛው stage ላይ ነው።

ቢቢኤን፡- በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ነፃ አለመሆኑን፤ ገለልተኛ አለመሆኑን ነው አቤቱታ እየቀረበበት ያለው። ስለዚህ ኮሚቴዎቹ በዚህ ፍርድ ቤት የማይተማመኑ ከሆነ ለምን አድማ በማድረግ በአፍሪካ ኮሚሽን ክስ ላይ ብቻ ትኩረት አልተደረገም? በሌላ በኩል በሀገሪቱ የፍትህ ስርዓት ፍትህ እናገኛለን ብለው የማያስቡ ከሆነ መጀመሪያውኑ እዚህ ክርክር ውስጥ በተለይ ከመንግስት ጋር በሚደረገው ክርክር ውስጥ ለምን ገቡ?

ዶ/ር አወል፡- እንደዚህ ዓይነት የመንግስት ፍላጎት ያለበት፣ አለመግባባቱ ቀጥታ በመንግስትና በተከሳሽ መሀከል በሚሆንበት የክስ ሂደት አንደኛው ፍርድ ቤቱ ነፃ አይደለም ስለዚህ የሚደረገውን የፍርድ ሂደት ክብር አለሰጠውም፣ legitimize አላደርገውም የሚባልበት አንዱ ሰትራቴጂ ከፍርድ ቤቱ ጋር ምንም አለመተባበር ነው፣ በክስ ሂደቱ ላይ አለመሳተፍ ነው፣ መከላለያ አለማቅረብ ነው. . . ወዘተ። ለምሳሌ ከ1997 ምርጫ በኋላ የቅንጅት መሪዎች በክስ ሂደቱ እራሳቸውን ለመከላከል የተጠቀሙት ስትራቴጂ ይሄ ነበር። ፍርድ ቤቱ ነፃነት ስለሌለው እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ነፃ ሁኖ በህግና በህገ መንግስቱ መሰረት ሊወስን ስለማይችል ውሳኔውም መጨረሻ ላይ የሚመጣው ከመንግስት ስለሆነ የፍርድ ቤት ሂደቱ ላይ መሳተፍ የለብንም የሚል ውሳኔ ነበር እነሱ የወሰኑት። ኮሚቴዎቹ የወሰኑት ውሳኔ ግን ለየት ያለነው።

የዳኝነት ስራ ፍርድ ቤት ግለሰቦች ስለሄዱ ብቻ የሚሟላ አይደለም። የዳኝነት ስራ መሰረት የሚያደርጋቸው መሰረታዊ ነገሮች አሉ። አንደኛው ፍርድ ቤቱ በተከሳሽና ከሳሽ በሆነው መንግስት መሀከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ መቻል አለበት። ተከሳሽ ማንኛውንም ነፃ መሆኑን ሊያሳዩ የሚችሉ መረጃዎችን የማቅረብ፣ የመከራከር፣ ዐቃቤ ህግ የሚያቀርባቸውን ማስረጃዎችና ምስክሮች ጥየቄ የመጠየቅና የመፈተሽ መብት አለው። እነዚህ መብቶች ሊጠብቅለት ይገባል። መንግስት ስንል በአንድ አገር ውስጥ ያለ መንግስት almost ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይችላል ማለት እንችላለን። በጣም አቅም ያለው ትልቅ (ኋይል ነው)። ግለሰብ ግን በየትኛው ዓይነት መልኩ በመንግስት በቀላሉ ሊጨፈለቅ የሚችል አካል ነው። ዳኝነትን ዳኝነት የሚያስብለው ዋናው ነገር፤ ፍርድ ቤትን ፍርድ ቤት የሚያስብለው፤ የእውነት መድረክ የሚያስብለው፤ የፍትህ መድረክ የሚያስብለው መንግስትን የሚያክል ትልቅ ነገርና ግለሰብን የሚያክል በጣም ትንሽ ነገር ሚዛናዊነታቸውን ጠብቆ ሁለቱንም በህግ መሰረት በሰብዓዊ መብት ድንጋጌች መሰረት፣ በህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች መሰረት እንዲከራከሩ እድል መስጠት ነው። በዛ ክርክር ሂደት እውነት እንድትወጣና በዛ እውነት መሰረት ፍርድ እንዲሰጥ ነው የክስ ሂደቱ ያለው። የዳኝነት ስራ ማለት ያ ነው። በርግጥ ፍርድ ቤት እነዚህን ግለሰቦች ምንም ዓይነት እራሳቸውን የመከላከል ዕድል ሳይሰጣቸው ዝም ብሎ ሊወሰን አይችልም። የሚወስን ከሆነ እራሱን ችግር ውስጥ ያስገባል ማለት ነው። እራሱን ችግር ውስጥ የሚያስገባው እንዴት ነው መጨረሻ ላይ ሂዶ ሂዶ ውሳኔው ከተወሰነ በኋላ ያ የወሰኑበት አካሄድ፣ የከለከሏቸውን መብት ምናልበት የህግ ስርዓቱ ዛሬ ተጠያቂ ላያደርጋቸው ይችል ይሆናል ነገር ግን በታሪክ ተጠያቂ ይሆናሉ፣ ይወቀሳሉ።

ቢቢኤን፡- ከኮሚሽኑ የፍርድ ሂደት በኋላ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ውሳኔ ምንድን ነው? ውሳኔውን እንዴት ነው ሊተገብር የሚችለው? ኮሚቴዎችን ከእስር ሊያስለቅቅ የሚያስችል የፖሊስ ኋይል አለው?
የዚህን ምላሽ በቀጣዩ ክፍል ይዘን እንቀርባለን።

No comments: