Saturday, January 21, 2017

ሳይጀመር የተጨረሰው የኢህአዴግ ውይይትና ድራማው!!! | የኢ/ር ይልቃል ተወካዮች ለምን ከእረፍት በኋላ ተባረሩ?

January 21,2017
ይድነቃቸው አዲስ

ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጋለው ካለበት ቀን ጀምሮ ስለ ጉዳዩ ያለኝን መረጃ ለጠየቃችሁኝ በሙሉ ነገሩን ከፈረሱ አፍ እንዲሉ እንደሚከተለው ላካፍላችሁ ወድጃለው።
ድራማው የሚጀምረው ጥር 9 2009 ዓ.ም ወደ 10፡55 አካባቢ ለኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በተንቀሳቃሽ ስልኩ ከኢህአዴግ ፅ/ቤት ስልክ የተደወለለት ዕለት ነበር። ደዋይዋ ስሟን ከተናገረች በኃላ የደውለችበትን ምክንያት ተናገረች። እንዲህ በማለት ” ኢህአዴግ ባዘጋጀውና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሊያደርግ ባሰበው ውይይት ላይ እርስዎ በሊቀመንበርነት የሚመሩትን ሰማያዊ ፓርቲን የጋበዝን ቢሆንም እስካሁን ድረስ በፓርቲው በኩል የሚሳተፉትን ሰዎች ስም ዝርዝር አላሳወቃችሁንም ስለሆነም ከውይይቱ በፊት መታወቅ ስላለበት ስም ዝርዝራቸውን ሊነግሩን ይችላሉ? ” ስትል አክብሮት በተላበሰበት ንግግር የደወለችበትን ምክንያት ገለፀች። በስልክ መልዕክቱ ግራ የተጋባው ይልቃል ጌትነትም ፓርቲው የደረሰው ምንም ዓይነት የተፃፈ ደብዳቤ እንደሌለ ገልፃ ለነገ ለሚደረግ ውይይት በዚህ ሰዓት መደወል አግባብ አለመሆኑን ይናገራል። ከኢህአዴግ ፅ/ቤት የደወለችው ሴትዮ “ምናልባት ደብዳቤው በስህተት ሌሎች እጅ ገብቶ ሊሆን እንደሚችልና ማንም እጅ ቢገባም እርስዎ የሚሰጡኝን ሁለት ተሳታፊ ሰዎችን ስም ልመዘግብ። እውነተኛ አመራሩን ከምርጫ ቦርድ አረጋግጬ ነው የደውልኩት ” ስትል ይቅርታ በሚጠይቅ ቅላፄ ዳግም ጥያቄዋን አቀረበች። የድምፅ ምልልሱ የይልቃል ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ይገኛል።
የእኔን እና የቀድሞው የፓርቲው ም/ሊቀመንበር እና የምርጫ ጉዳይ ሃላፊ የነበሩትን አቶ ስለሺ ፈይሳን እያቅማማ ቢሆንም አስመዘገባትና ንግግራቸው አለቀ። ወዲያው ተነጋግረን ከመቅረት ሄዶ አቋምን ማሳወቅ ተገቢ ነው የሚል መተማመን ላይ ደረስን። በማግስቱ ጥር 10 /2009 ዓ.ም የፓርቲያችንን አቋም ለማሳወቅ እኔ ይድነቃቸው አዲስ እና አቶ ስለሺ ፈይሣ ከጠዋቱ 2፡50 አካባቢ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ በር ተገኘን። ከመግባታችን በፊት አቶ የሺዋስ አሰፋ ከመኢአድ አመራሮች ጋር በሩ ላይ ተገኝቶ ስሙ እንደሌለና የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ያስመዘገቡት የሁለት ሰዎች ስም ዝርዝር ተነገረው። “የፓርቲው ሊቀመንበር እኔ ነኝ እዚህ ስማቸው ያሉ ሰዎች የተባረሩና የዲሲፒሊን ግድፈት ያለባቸው ሰዎች ናቸው” በማለት ተከራከረ። በሩ ላይ በፌደራል ፓሊሶች ተከቦ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን መታወቂያ እያየና ከተመዘገበው ሥም ዝርዝር ጋር እያመሳከረ መግቢያና ማለፊያ ባጅ የሚሰጠው ግለሰብ ምንም ማድረግ እንደማይችል በቁጣ ተናገረና፤ ምንም ማድረግ በማይችለው ጉዳይ ላይ ባይጨቀጭቀው መልካም መሆኑን በመናገር ወደ ኃላ ገሸሽ እንዲል አሳሰበው።
(ፎቶ መፍቻ) ከሕወሓት ጋር ድርድር ተቀምጠው የነበሩት ‘ተቃዋሚዎች’::

ይህ ሲሆን እነ ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ እና ፣ ከመንግስት ቀለብ እየተሰፈረላቸው የሚኖሩ የውሸት ፓርቲ ባለቤቶች አጠገባችን ነበሩ። ዘወትር ሳያቸው በስሙ የሚነግዱባት ህዝብ ፍዳ ፊቴ ድግን ስለሚል ደሜ ይፈላል። ስለሆነም አተኩሬ ማየት እንኳን አልፈልግም። በሰዓቱ አንድ ስሙን የዘነጋሁት የፎርቹን መፅሄት ጋዜጠኛ መግባት ተከልክሎ ፓርቲያችን ውስጥ ስለተፈጠረው ጉዳይ ጠይቆኝ እያወጋን ነበር። በስተመጫረሻም መግቢያ በሩ ላይ ስማችን እንደተመዘገበና መግባት እንደምንችል ተነግሮን እኔና ስለሺ ፈይሳ ወደ ውስጥ ዘለቅን። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መለስተኛ አዳራሽ ታደምን። ውይይቱ በግምት 3፡35 አካባቢ ይመስለኛል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ በሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ መድረክ መሪነት ተጀመረ። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የመክፈቻ ንግግር አደረጉ። ውይይት መልካም መሆኑን እና መንግስት በሠላማዊ መንገድ ተደራጅተው ካሉ ሃያ ሁለት አገራዊ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ገለፁ። ወደ ዝርዝር አጀንዳ ከመግባታችን በፊት በቀጣይ ስለሚኖረው ውይይት አካሄድ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ለመወያየት መድረኩን ክፍት አደረጉት። የመጀመሪያው ተናጋሪ ፕሮሬሠር በየነ ጴጥሮስ ነበሩ። ዘወትር በሚናገሩበት የቀዘቀዘ የድምፅ ቃና መድረኩን ኢህአዴግ መምራት እንደሌለበትና ባለፉት ወራቶች የሞቱት ወገኖቻችንን በማሰብ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት የህሊና ፀሎት ቢደረግ መልካም ነው በማለት ሃሣባቸውን ገለፁ። የመድረክ መሪው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባይፈቅዱም የውይይቱ ተሳታፊዎች በከፊል የፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስን አባታዊ ምክር ተቀብለን በራሳችን ፍቃድ ተነስተን ላተወሰኑ ሰኮንዶች ቆመን የህሊና ፀሎት አድርሠን ተቀመጥን።
በቀጣይ ስላለው አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታና ስለ ውይይቱ ከተሣታፊዎች ሃሣብ ተሠነዘረ። ብዙዎቹ አሠለቺና ተደጋጋሚ ነበሩ። መንግስት ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ለማዋል መጥራቱን ገና ከጅምሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለእነ አየለ ጫሚሶ ፣ ትዕግስቱ አወሉ እና መሠሎቻቸው ደጋግመው ዕድል ቸሩ። እነርሱም መንግስት በአገሪቱ ላይ አስከፊ ችግር ከመከሰቱ በፊት የማረጋጋት ስራ መስራቱን አደነቁ። የኢዴፓው ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ትንሽ የተሻለ ነገር መናገራቸውን አስታውሳለው። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በመጀመሪያው ዙር እጅ አውጥተን ዕድል የሰጡን ቢሆንም አውቀው ይሁን ሳያውቁት ዘለሉን። ሁለተኛው ዙር ላይ እንደምንም ብለን ዕድሉን አገኘን። ከውይይቱ በፊት የተስማማንበት ሃሣብ ተናገረን እንዲህ በማለት ” በመጀመሪያ ደረጃ ውይይት መልካም ነው ብላችሁ ከልባችሁ አምናችሁ ከሆነ የጠራችሁትን እኛም የምንፈለገው ነገር ስለሆነ ጥሩ ነው። ፓለቲከኛ ሆኖ ውይይትን መግፋት አይቻልም። ግን አይመስለንም! እኛም እንሁን ፓርቲያችን ኢህአዴግን የሚያየው በጥራጣሬ መነፀር ነው። ይሁን ተጠራጥረን የትም ስለማንደረስ የምናምነውን ለመናገር እዚህ ተገኝተናል። ፓርቲያችን በመጀመሪያ እራሱ ገዳይና ችግር ፈጣሪ ሆኖ መታደስ አለበኝ ያለ ድርጅት መድረክ ይዞ እራሱ አወያይ ሆኖ መቅረቡን አይደግፍም። ይህም ውይይት የጥልቅ ተሃድሶ አካል አድርጎ ድርጅታችሁ ኢህአዴግ የሚያየው ከሆነ መታደሱ ለእናንተ እንጂ ለእኛ አያስፈልገንም። ሲቀጥል መንግስት እውነተኛ መፍትፍሄ ጠቋሚ ውይይት ከፈለገ ውይይቱ ውጭ ከሚገኙ ጠብመንጃ ካነሱትም ጋር ሆነ በሠላማዊ መንገድ የሚታገሉ ድርጅቶችን አጠቃሎ ማካሄድ አለበት። ውይይት በአገር ደረጃ ውጤት የሚያመጣው ስርዓቱ ትክክል አይደለም ብለው በምናምንበት መንገድ ለውጥ እናመጣለን ብለው እየሠሩ ያሉ ድርጅቶችን በሙሉ መሰብሰብ ሲችል ነው።
እንደ 1997ቱ ከፀሃይ በታች በማንኛውም ነገር ላይ እንወያየለን ተብሎ ጊዜ እንደተገዛበት አይነት መሆን የለበትም። ይህ አለመሆኑን በቀጣይነት ለህዝባችን የሚታይና የሚዳሠስ ማረጋገጫ መሠጠት አለበት። ካልሆነ የህዝብ ውክልና የሌላቸው ፓርቲዎች እንደ አሸን በፈሉበት ሁኔታ በህዝብ ስም መወያየትና በአብላጫ ድምፅ አቋም መያዝ ቀልድ ካልሆነ በቀር ተገቢ አይሆንም። መንግስት አስከፊ ደረጃ ከመድረሱ መታደሡ ተገቢ ነው የሚሉትንና ማህተማቸውን በኪሳቸው እየያዙ የሚዞሩትንም ትንሽ ሸንቆጥ አደረግናቻው። አንድ ቀን ዋጋ እንደሚያስከፍላቸውም ጭምር። የሚል የመጀመሪያ የሰማያዊ ፓርቲ ሃሣብ ተነገረ። ውይይቱ ከዛ በኃላ ብዙም ሳይቆይ የመድረኩ መሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሻይ ሰዓት አልፎ ወደ አምስት ሰዓት እየተጠጋ ስለሆነ ለሻይ ሰዓት እንውጣ በማለት የመጀመሪያ ዙር ውይይቱ በሻይ ሰበብ እንዲቆም ሆነ። የሻይ ሰዓት ላይ ከእነ ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ ፣ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ፣ አቶ ገብሩ ገብረማርያም ጋር ውይይቱ ቀጠለ። እኛ ሰሚ ነበርን። ፕሮፌሠር በየነ በሽግግሩ ጊዜ የነበራቸውን የፓለቲካ ታሪክና የኢህአዴግ አታላይናትን አካፈሉን። በሰማያዊ ፓርቲ የቀረበውን ሃሣብም እንደሚደግፉት ለእኔና ለስለሺ ነገሩን። እንደውም በአራዳ ቋንቋ ህዝቡ በአሁን ሰዓት እኛን ከመንግስት ጋር እየተሞዳሞድን አድርጎ እንዳይስለን ስጋታቸውን አካፈሉን።

ትንሽ ፈገግ እንድንልም አደረጉን። ሻይ ቡናው ላይ ቆፍጠን ብለው ታዩኝ። ምናል መድረኩ ላይም እንዲህ ቢሆኑ ብዬ ተመኘሁ። የሻይ ሰዓቱ ስላለቀ በግምት ወደ አምስት ከሩብ አካባቢ ወደ አዳራሹ ገባን። ከመንግስት ሚዲያዎች በቀር የግል ህትመት ሚዲያዎች እንዲገኙ ስላልተፈለገ ይመስለኛል አልተጋበዙም። ለሁለተኛው ዙር ውይይት የቀድሞው ቦታችንን ያዝን። ድንገት በመሃል ከፍ ባለ ድምፅ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰማያዊን ወክላችሁ የመጣችሁ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አንድ ጊዜ ወደ ውጭ ኑልን” አሉን። የውይይቱ ተሣታፊዎች ትኩረት በሙሉ ወደ እኛ ሆነ፤ ዝምታ ቤቱን ዋጠው። በነገሩ ግራ የተጋባነው እኔ እና ስለሺ ምን አስበው ይሆን ? በሚል መንፈስ ከአዳራሹ በራፍ ተገኘን።
አቶ ሽፈራው ራቅ ብለው ከቆሙ ሶስት ጋርዶች ጋር ጠበቁን። እንደወጣን ለምን እንደተጠራን አቶ ሽፈራውን ጠየቅናቻው ። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ድምፃቸውን ቀንሰው “እናንተ እውነተኛው የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አይደላችሁም የሚል መረጃ ደርሶኝ ነው። ስለሆነም ከአሁን በኃላ በስብስባው መካፈል አትችሉም” አሉን። እኛም የመጣነው ለይልቃል ተደውሎላት እንደሆነና እኛም የፓርቲው የማዕከላዊው ኮሚቴ አባል እንደሆንን ገለፅንላቸው። “እሱ ስህተት ነው አሁን ከምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት ሃላፊ ድውዬ እንዳረጋገጥኩት እናንተ እውነተኛ አመራሮች አለመሆናችሁ ተነግሮኛል” በማለት እንድንወጣ አሳሰቡን። አርግ የተባሉትን ከሚያደርጉ ግለሠብ ጋር ብዙም ጊዜ ማጥፋቱ መፍትሄ እንደሌለው በመረዳታችን የግቢውን ቅጥር ግቢ ለቀን ወደ 5፡35 ወጣን። ይሁን እንጂ አቶ የሺዋሥ አሠፋና ግብረአብሮቹ ከወጣን በኃላ ተደውሎላቸው በጓሮ በር ገብተው መሣተፋቸውን አውቀናል። ህዝብ ምንግዜም አሸናፊ ነውና ህዝብን ማዕከል ያላደረገ ውይይት መጨረሻው ሽንፈትና ቅሌት ብቻ ይሆናል ብዬ አምናለው። የውይይቱም የመጨረሻ ገጽ ከቀድሞ የውይይት ታሪኮች የተለየ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ድል የህዝብ ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች !!