Sunday, April 20, 2014

“በዩኒቨርሲቲው መቆየት ካልቻልኩ የፖለቲካ ፓርቲ እቀላቀላለሁ” – ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

April 19/2014


በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮች በሚሰነዝሯቸው ጠንካራ ትችቶች ይታወቃሉ፡፡ ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት የነፃውን ፕሬስ ሁኔታ አስመልክቶ በሬድዮ ፋና በተዘጋጀው ውይይት ላይም ተሳትፈዋል፡፡ ጋዜጠኛ ናፍቆት ተስፋዬ ከዶ/ር ዳኛቸው ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ የገባበት ስለጠፋው የዩኒቨርሲቲ የኮንትራት ውል፣ ስለፍርድ ቤት ነፃነት፣“በኢትዮጵያ ውስጥ የመናገር ነፃነት የለም”— ስለማለታቸውና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በስፋት አነጋግራቸዋለች፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር የተዋዋሉባቸው ሰነዶች በሙሉ መጥፋታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?

ከዚህ ቀደም ባልሳሳት—ከአንድ ዓመት ከሁለት ወይም ከሶስት ወር በፊት ይመስለኛል “60 ዓመት ስለሞላህ ኮንትራት ያስፈልግሀል” ተብዬ የሁለት ዓመት ኮንትራት ፈርሜ ነበር፡፡ የዚህ ኮንትራት ግልባጭም ለእኔ የተሰጠኝ ሲሆን በተጨማሪም ለፍልስፍና ዲፓርትመንቱ፣ ለዲኑ ቢሮና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዲሁም ለፐርሶኔል ቢሮ በአጠቃላይ አምስት ቦታ ተላከ፡፡ ሆኖም አምስቱም ደብዳቤዎች ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ሌላው ቀርቶ እኔም ቢሮ የነበረው ሊገኝ አልቻለም፡፡ እንዲያውም የዲፓርትመንት ኃላፊው፣ የኮሌጁ ዲኑና፣ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሮም “ሲጀመርም ደብዳቤውን ስለማየታችን ትዝ አይለንም” የሚል መልስ ነው የሰጡት፡፡
ከዚያስ?

ከዚያማ ይሄ ሰውዬ ኮንትራት ሳይኖረው ከአንድ ዓመት በላይ አስተማረ እስከ ማለት ደረሱ፡

፡ እኔም በበኩሌ፣“ኮንትራትህ እድሳት ያስፈልገዋል ተብዬ ሂደቱ አራት ወር ስለወሰደ፣ ለአራት ወራት ደሞዜ ታግዶ ነበር፣እድሳቱ ሲያልቅ ደሞዜ መለቀቁ ምልክት አይሆናችሁም ወይ?” ብላቸው ያመነኝ ሰው አልነበረም፡፡ ፐርሶኔል ክፍሎች ግን ፍቃዱ ባይራዘምለት ከአራት ወር በኋላ ደመወዙን አንለቅም ነበር ብለው ተከራከሩ፡፡ ሆኖም የነሱንም ሀሳብ የሚያዳምጣቸው አላገኙም፡፡ አሁን ለጊዜው በዝርዝር ለማስረዳት ባልዘጋጅም፤በጥቅሉ ሰነዱ ባንዳንድ ሰዎች እርዳታ ፐርሶኔል ቢሮ ከሳምንት በላይ ተፈልጎ ተገኝቷል፡፡ይህ ኮንትራት ባይገኝ ኖሮ ምናልባት ከሥራ ለመሰናበት እደርስ ነበር፡፡ አሁን ግን የኮንትራቱ ውል በመገኘቱ ምክንያት እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ማስተማር እችላለሁ ማለት ነው፡፡ የኮንትራቱ ውል ከመገኘቱ በፊት ግን ደብዳቤ ፅፈውልኝ ነበር፡፡

ምን ዓይነት ደብዳቤ?

“በአንተ እጅ ያለውም ሆነ ሌላው ክፍል የነበረው የኮንትራት ውል ስለጠፋ፣ የተሰጠህን የዓመት ፈቃድ ለጊዜው ይዘነዋል” የሚል፡፡ የእኔ ክርክር ጭብጥ ሁለት መንገድ የተከተለ ነው፡፡ አንዱ የኮንትራት ውሉ ሲሆን ሁለተኛው የዓመት ፈቃዱ ነው፡፡ የኮንትራት ውሉ ተገኘ፡፡ በመጀመሪያ የዓመት ቃዱን የያዙት የኮንትራት ውሉ ስለጠፋ ነበር፡፡ ወረቀቱ ሲገኝ ደግሞ የዓመት ፈቃዱ መለቀቅ ሲገባው አሁን ሌላ ሰበብ አመጡ፡፡ እድሜህ ስልሳ ዓመት ስለሞላና የጡረታ ሂደቱ በደንብ ተካትቶ ፋይልህ ውስጥ ስለሌለ፣ የዓመት ፈቃድህን ሰርዘነዋል አሉኝ፡፡ አሁን “ከሰስፔንሽን” ወደ “ካንስሌሽን” ሄደዋል ማለት ነው፡፡ የዓመት ፈቃዴን ባለፈው ሳምንት ነበር የምጀምረው፣ እሱን ተነጥቄያለሁ እልሻለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ማለት አልፈልግም፡፡

ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በሬዲዮ ፋና ላይ በነፃው ፕሬስ ዙሪያ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ እርስዎም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የውይይቱ ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?

እንግዲህ አንድ የሬድዮ ጣቢያ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ ፋይዳውን የሚያውቀው ሬዲዮ ጣቢያው ራሱ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሰጡን ርዕስ ተነስቼ አንዳንድ ነገሮችን ለመገመት አያዳግተኝም፡፡ ርዕሱ እንግዲህ በኢትዮጵያ ያሉ የነፃው ፕሬስ ጋዜጦችና መፅሄቶች ምን ይመስላሉ? እንዴትስ ሊሻሻሉ ይችላሉ? የሚል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስመለከተው የግሉን (ነፃውን) ፕሬስ በተጠናከረ ሁኔታ መተቸት ይፈልጋሉ፡፡ ሁለተኛ ከመንግስት ጋር ያልተያያዝን ሰዎች በውይይቱ ብንሳተፍ፣ ትችቱ ይሰምራል የሚል አስተሳሰብም ነበራቸው፡፡ ሌላው እኔን በግሌ ብትጠይቂኝ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጆርናሊዝም እና ኮሚዩኒኬሽን ዲፓርትመንት በቅርቡ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ የመናገር ነፃነት (Freedom of Speech) የለም” ብዬ ሽንጤን ገትሬ ተከራክሬ ነበር፡፡ ይህም በዩቲዩብ እና በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች ስለተሰራጨ፣ ለዚህ ምላሽ በመስጠት ያንን የተሰራጨ ሃሳብ ለማምከን እቅድ የነበራቸው ይመስለኛል፡፡ እኔ በሁለት ፕሮግራሞች ላይ ነው የተሳተፍኩት፣ እነሱ ግን ቀደም ብለው የጀመሩት ይመስለኛል፡፡

ውይይቱ ላይ ተጋብዘው ነው ወይስ በራስዎ ተነሳሽነት?

የሬድዮ ፋናው አቶ ብሩክ ከበደ ጋብዘውኝ ነው የተገኘሁት፡፡

በውይይቱ ላይ“ዶ/ር ዳኛቸው ስሜታዊ ሆነው ነበር”የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚል ትችትም ተሰንዝሮቦታል፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

የስሜታዊነቱን ነገር ያመጡት እንኳን እነሱ ናቸው፡፡ ስድብና ዘለፋውን በመጀመር እነሱ ይቀድማሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” ለሚለው በእውነቱ በናፍቆት ደረጃ ፍትህ ናፋቂ ነኝ፡፡ዴሞክራሲና የህዝባችንን ነፃነት ናፋቂ ነኝ፡፡ የዱሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚሉኝ “አሁን ያለንበት ወርቃማው ጊዜ ነው” የሚሉ ዜጎች ናቸው፡፡ “ያለፈው ስርዓት ናፋቂ” የሚለው አባባል ሆን ብሎ ሰዎችን ለማሸማቀቅ የተፈጠረ ቃል ነው፡፡ በሌላ መልኩ የአሁኑ ስርዓት እኮ በጣም የተሻለ ነው ለማለት ነው፡፡ እኔ የዛሬ 40 ዓመት ወደ ኋላ ሄጄ ለማወዳደር የፈለግሁት አጠቃላይ ሥርኣቱን ሳይሆን የመናገር ነጻነትን በተመለከተ ርዕስ ብቻ ነበር፡፡ ይህንንም ለመናገር የዕድሜ ባለጸጋም ነኝ፡፡ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በሚባልበት ጊዜ አንድ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለሁ፡፡ ያኔ የተሻለ የመናገር ነፃነት ነበር ብያለሁ፡፡ ይህንን አባባሌን አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ “በአፄው ጊዜ የፈለግነውን ለመተቸት የዩኒቨርሲቲው ህግ ይፈቅድልናል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ መዲና ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተነስተሸ አንድ ፖለቲካዊ የሆነ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አስተያየት ብትሰነዝሪ ከጸጥታ ኃይሉ የሚጠብቅሽ ችግር ይኖራል፡፡” ስላልኩኝ ነው “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የተባልኩት፡፡ ይሄ አይነተኛ የሆነ የካድሬዎች ማስፈራሪያና በነፃነት የሚናገሩ ሰዎችን ማሸማቀቂያ መንገድ ነው፡፡ እኔ እኮ የድሮ ትዝታ አለኝ፣ ልናፍቅም እችላለሁ፡፡
ለምሳሌ ከድሮው ስርዓት ምን ምን ይናፍቅዎታል?

ለምሳሌ የእንግሊዝ ፈላስፋ ኤድመን በርክ “Familiarity” የሚል ስለ ትዝታ ያነሳው ሀሳብ አለ፡፡ “ፋሚሊያሪቲ” ምንድነው? መተዋወቅ፣ ያሳለፍነው ትዝታ፣ትውስታ ማለት ሲሆን፤እንደ አርሱ አቀራረብ በአንድ ጉዳይ ላይ ስለተዋወቅን ብቻ መናፈቅ፣ የሰው ልጅ ባህሪና ፀጋ ነው ይላል፡፡ ገባሽ? እኔ የጥንቱን የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ እናፍቃለሁ፣ የፖሊስ ኦርኬስትራንም እንዲሁ፡፡ ዛሬ አንድ ኪቦርድ አስቀምጠው የሚዘፍኑትን ከምሰማ የእነዚያን ኦርኬስትራዎች ሥራ ብሰማ እናፍቃለሁ፡፡ የፈረሱትን የድሮ ሲኒማ ቤቶች— እነ ሲኒማ አድዋን እናፍቃለሁ፡፡ የድሮውን የመድረክ ተውኔት እናፍቃለሁ፡፡ የድሮው የክብር ዘበኛ አለባበስ ከፈረሳቸውና ከነማዕረግ ልብሳቸው ትዝ ሲለኝ እናፍቃለሁ፡፡ እንዴ ብዙ ብዙ የምናፍቀው ነገር አለኝ— እሱን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ በሰፈሬ ሳልፍ አሁን የደረቀው ቀበና ወንዝ ከነሙላቱ ይናፍቀኛል፣ ድሮ ለምሳሌ ሆቴል ገብተን ክትፎ በ75 ሳንቲም “ቅቤ ይጨመር?” እየተባለ የምንበላው ይናፍቀኛ…..እንዴት ያለ ነገር ነው! ድንች በሥጋ ወጥ 15 ሳንቲም የነበረበት ጊዜ ይናፍቀኛል፡፡ የድሮዎቹ አስተማሪዎቼ ይናፍቁኛል፡፡ ታዲያ የድሮውን መናፈቅ ምን ነውር አለው? ምንስ አድርግ ነው የምባለው?
እርስዎም “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚለው አነጋገር የካድሬ ቋንቋ ነው ብለዋል፡፡ ምን ማለት ነው?

ካድሬዎች ሁልጊዜ ያለንበት ስርዓት ነው ወርቃማው ይላሉ፡፡ ያለፈው በጠቅላላው አይረባም ባይ ናቸው፡፡ ሲያስተምሯቸውም እንዲህ እንዲያስቡ ነው፡፡ እኔን “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” ያለኝም ወጣት በዚያ ስለወጣ ነው፡፡ በጣም ልጅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም በሌላ ፕሮግራም ላይ አግኝቼዋለሁ፡፡ ያን ጊዜ አቦይ ስብሀት ባሉበት በጣም ሀሳባዊ የሆነ፣ የአሁኑን ሥርዓት “ፍየልና ነብር የሚሳሳሙበት” ወርቃማ ጊዜ እንደሆነ አድርጎ ሲያወራ፣ “አንተ ልጅ እስኪ አቦይ ስብሀት ጋር ዝም ብለህ አንድ ሁለት ዓመት አሳልፍ፣ ያኔ ፖለቲካህ መሬት የረገጠ ይሆናል” በማለት መክሬው ነበር፡፡

በእርሶ እይታ አሁን ያሉት በጣት የሚቆጠሩ የግሉ ፕሬስ ውጤቶች ምን ይመስላሉ?

እኔ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ማስቀመጥ የፈለግሁት ጉዳይ ምን መሰለሽ? አንደኛ የአንድን አገር የፕሬስ ሁኔታ ለማየት ከፈለግሽ ወደ አወቃቀሩ ነው የምትሄጂው፡፡ አወቃቀሩ አሀዳዊ ነው ወይስ ብዝሀነትን ያስተናገደ ነው የሚለውንም ታያለሽ፡፡ በእኔ እይታ ከአፄ ኃይለሥላሴ እስከ ኮሎኔል መንግስቱና በአሁኑም ስርዓት ስትመጪ አወቃቀሩ አሀዳዊ ነው፣ አንድ ወጥና በአንድ አካል የሚታዘዝ ነው፡፡ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ የሚሰማው ዜና ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ ነው፡፡ ሁሉንም በሞኖፖል የያዘ ነው፡፡ ይሄ “Univocal” ይባላል፡፡ “Multivocal” የሚባለው ደግሞ ብዙ ውድድር ያለበት፣ በአማራጭ የተሞላ ዜና እና የዜና ምንጭ ያለበት ነው፡፡ አሜሪካ ስትሄጂ CNN አለ፣ ABC አለ፣ ሌሎችም መዓት የዜና አውታሮች አሉ፡፡ እዚህ ይህ አይነት አማራጭ የለም፣ ይመጋገባሉ እንጂ፡፡

ይመጋገባሉ ሲሉ እንዴት ነው?

ለምሳሌ የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ወሬ ነው የሚያወራው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አወቃቀሩ ተመሳሳይና የሚታዘዘው በአንድ አካል ስለሆነ ነው፡፡ ማንም ሰው ቴሌቪዥን ጣቢያ በግሉ የመክፈት መብትም የለውም፡፡ እንዲህም ሆኖ አሁን ትንሽ ለቀቅ ተደርጎ በጥቂቱም ቢሆን ትችትም እየተፃፈ ነው፣ ይህን አልካድኩም፡፡ “Freedom of speech” እና “Freedom of expression” ይለያል ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡

እስቲ የሁለቱን ልዩነት ያብራሩልኝ?

ይኸውልሽ “Freedom of speech” ብዙ ነገርን ያካትታል፡፡ ለምሳሌ የመሰብሰብን፣ ማህበራት የማቋቋም፣ ለተለያየ የመረጃ ነፃነት እድል የማግኘትን (“exposure” የሚለው ይገልፀዋል) —– ያካትታል፡፡ በተለያየ አይነት መንገድ መረጃ ክፍት ሆኖና ተፈቅዶለት እንዲያገኝ እድል የሚሰጥ ነው – “Freedom of speech” ማህበራትን ማቋቋምና የመሰብሰብ ነፃነትም በጣም ጠቃሚ ነገሮች ናቸው፡፡ “Freedom of expression” ደግሞ መናገርን (የአንደበትን) ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈቀዳል ግን ህዝቡ መረጃ ለማግኘት አማራጮቹ አልሰፉለትም ወይም ህዝቡ ለተለያየ መረጃ “exposed” አይደለም፡፡ ይሄ ነው ልዩነታቸው፡፡ ዋናው ልዩነቱ “Freedom of speech” የሚባለው ነገር ካለ፣ የመረጃ ስብጥሩ ነፃ ነው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡

እስቲ ለ “Freedom of speech” ማሳያ የሚሆን ምሳሌ ይስጡኝ?

በጣም ጥሩ! ለምሳሌ የአባይ ግድብን ሁኔታ ውሰጂ ፡፡ መንግስት የግድቡ 30 በመቶ ተሰርቷል አለ፡፡ በቃ! እኛ ይህንን ይዘን ነው ቁጭ ያልነው፡፡ አንቺም ስትፅፊ የሚመለከተው አካል የነገረሽን ነው። አማራጭ የመረጃ ምንጭ ቢኖር እኮ 40 በመቶም 45 በመቶም ሊሆን ይችላል የተሰራው፡፡ አሊያም 15 በመቶም 10 በመቶም ሊሆን ይችላል፡፡ ዜጋው የመንግስት አካል የነገረውን እንጂ ሌላ አያውቅም፡፡ አንድ ግብፃዊ ግን እጅግ በርካታ የሬድዮ፣ የጋዜጣና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስላሉት፣ ስለ አባይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ በብዙ እጥፍ የበለጠና የተሻለ መረጃ የማግኘት እድል አለው፡፡ ይሄ እንግዲህ ነፃ የመረጃ ምንጭ (Freedom of speech) ምን ማለት እንደሆነ ያሳያል፡፡ የፖለቲካ ፈላስፋዎች እንደሚሉት፣ የዜና አውታሩ የመረጃ ምንጩ በሞኖፖል ከተያዘ፣የህዝቡ አንደበት መናገሩ (Freedom of expression) ጥቅም የለውም፣ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውም ይሄው ነው፡፡
አሁን ያለው ስርዓት (መንግሥት) ራሱ ህግ አውጭ ራሱ ህግ ተርጓሚ ነው፣ ይህ ትክክል አይደለም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ህግ አውጭና ተርጓሚው መሆን ያለበትስ ማን ነው?

ዋነው የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ይሄ ነው። “Separation of Power” የሚለው አስተሳሰብ የመጣው ለአንድ መቶ ዓመት ህግንና ነጻነትን በሚመለከት በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት መካከለኛው ዘመን ወደ ነበረው የሕግና የሥነ-መለኮት ፍልስፍና እንሂድ፡፡ በዚያን ጊዜ “ህግ የሚገኝ እንጂ የሚረቀቅ አይደለም” የሚለው አስተሳሰብ በሰፊው ተንሰራፍቶ ነበር፡፡
ማነው የሚፅፈው? ማነው የሚያረቅቀው?

በዚያን ወቅት ከላይ በጥቂቱ እንዳልኩት፣ መንግስት ህግ የሚያገኝ አካል እንጂ አርቃቂ አይደለም ብለው ያምኑ ነበር፡፡
እኮ ከየት ነው መንግስት ህግ የሚያገኘው?

ጥሩ ጥያቄ ነው! ከተፈጥሮ ነው ህግ የሚገኘው። ህገ-ተፈጥሮ (Natural Law) ይባላል፡፡ ከዚያ ነው የሚገኘው፡፡ በ15ኛውና በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መንግስት ትልቅ እየሆነ እየተስፋፋ ሲመጣ ህግ ማውጣት ግድ ሆነ፡፡ ሆኖም ግን የተወሰነው የአውሮፓ የማኅበረሰብ ክፍል “በፍፁም ህግ ልታወጡ አትችሉም፡፡ ራሳችሁ ህግ አውጥታችሁ ራሳችሁ ልትዳኙን አትችሉም፣ ነጻነታችን አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ክርክር ተነሳ፡፡
ከተፈጥሮ በግልፅ ይገኛሉ የሚባሉት ህጎች ምንድናቸው?

ጥሩ! ሰው መግደል አይፈቀድም – ይሄ ተፈጥሯዊ ህግ ነው፡፡ ሰው የመናገር መብት አለው፡፡ ያጠፋ ሰው ይቀጣል፡፡ የእኛም ፍትሀ-ነገስት ላይ ያሉት እኮ ከተፈጥሮ ህግ የተገኙት ናቸው፡፡ ህገ-ተፈጥሮ ለምሳሌ ወላጅ ልጁን ማሳደግ አለበት፡፡ ልጅ አባቱን አይመታም፡፡ በሰው ልቦና ላይ የተቀረፁ የተፈጥሮ ህጎች እኮ አሉ፡፡ በኋላ የግድ ህግ ማውጣቱ ሲመጣ፣ ህግ አውጭውና ህግ ተርጓሚው ይለያይ ተባለ፡፡ የእነዚህ አካላት መለያየት ግድ የሆነው ከመቶ አመት ጭቅጭቅ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ እንዳልኩሽ የሴፓሬሽን ኦፍ ፓወር የመጣው ህግ አውጪውንና ህግ ተርጓሚውን በመለየት ለተቃውሞው ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት ማለት ለምሳሌ አበራሽ በአበራሽ ጉዳይ ላይ ራሷ ወሳኝ ናት አይደለችም? ነው ጥያቄው፡፡ መልሱ መሆን የለበትም ነው፡፡ የህግ የበላይነት ማለት ሌላ ሶስተኛ አካል በተነሳው ጉዳይ ላይ ነፃ ሆኖ ይዳኝ ማለት ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው ይዳኙ ነበር። ደርግ በራሱ ጉዳይ ላይ ይዳኝ ነበር፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፣አሁን ኢህአዴግ በራሱ ጉዳይ ላይ ይዳኛል ወይንስ አይዳኝም ብለሽ ብትጠይቂ፤ በእኔ እምነት ይዳኛል፣ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም። ህጉን ተመርኩዞ ነፃ ሆኖ የሚዳኝ ዳኛ የለንም እያልኩሽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጋዜጦችንና ሚዲያውን እንደያዘ ሁሉ፣ፍርድ ቤቶችንም ወጥሮ ይዟል፡፡

ፍርድ ቤቶቹ ነፃ አይደሉም እያሉኝ ነው?

ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነፃ ሆነው እየሰሩ አይደለም፡፡ ትቀልጃለሽ እንዴ? ከብርቱካን ሚዴቅሳ ወዲህ በዚህች አገር ፍ/ቤት ላይ ማን ነፃ ሆኖ ትክክለኛ ፍትህ ሰጠና ነው፡፡

እስቲ ለዚህ ስጋት እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት ካለ ይግለፁልኝ?

ለዚህ ማሳያ ላቅርብልሽ —- የፀረ – ሽብር ህጉን 90 በመቶውን ያመጣነው ከውጭ ቀድተን ነው ይላሉ፡፡

ከውጭ መቀዳቱ ምን ክፋት አለው ይላሉ?

ክፋት አለው ያልኩት እኮ እኔ አይደለሁም! እነሱው የቀዱባቸው አሜሪካኖችና እንግሊዞች ልክ አይደላችሁም በሚል ወጥረው ይዘዋቸዋል፡፡ ለምን ይመስልሻል? ዋናው ነገር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ የእነሱ ህግ በጣም ስለሚያምር ለጥቁር አይገባውም ብለው ይመስልሻል? አይደለም! “በአገራችሁ ነፃ የሆነ ዳኝነት ስለሌለ ሰው ይጎዳል፣ መጠበቂያ የሌለው ጠብመንጃ ነው” ነው ያሏቸው፡፡ “እኛ እኮ ይህን ህግ ያወጣነው መጠበቂያ ስላለን ነው፡፡ ነፃ ዳኝነት በሌለበት ይህን ህግ እንዴት ሥራ ላይ ታውላላችሁ” ነው ያሏቸው፡፡ ማሳያዬ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ማሳያ ትፈልጊያለሽ እንዴ?
ዶ/ር ዳኛቸው “መንግስትና ዩኒቨርሲቲውን ይዘልፋሉ፡፡ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲው እያስተማሩ ደሞዝ ያገኛሉ”የሚል ትችት የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ይሄ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው! ይገርምሻል እዚህ አስተሳሰብ ላይም ችግር አለ፡፡ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በሚል ርዕስ የዛሬ መቶ ዓመት በገ/ ህይወት ባይከዳኝ የተፃፈ መፅሀፍ አለ፡፡ ፀሐፊው ለአፄ ምኒልክ ምክር ያቀረቡበት አለ፡፡ በመንግስት ላይ አንድ ግድፈት ያየሁት የመንግስት እና የንጉሱ ንብረት ያልተለየ መሆኑ ላይ ነው ብለዋል – ገ/ህይወት ባይከዳኝ፡፡ የደጃዝማቾቹ ንብረትና የአገሬው ህዝብ ንብረት በትክክል መለየት አለበት ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ደጃዝማቾችና ሌሎች ሹማምንት በደሞዝ መተዳደር አለባቸው ብለዋል፡፡ የመንግስት ንብረትና የንጉሡ ንብረት መለየት አለበት እኔ አሁንም የምፈራው፣ የፓርቲ ንብረትና የህዝቡ ንብረት አልተለየም ብዬ ነው፡፡ ኢህአዴጎቹ እኛ ቀጥረነው እኛው ስራ ሰጥተነው ይላሉ፡፡
አንድ ነገር ልንገርሽ – አፄ ኃይለ ሥላሴና ራስ ካሳ ከዝምድናቸው ባሻገር የቅርብ ወዳጆች ናቸው፡፡ ቀልድ ይቀላለዳሉ፡፡ ሁለት ታሪክ ነው የማወራሽ። በጅሮንድ ተክለ ሐዋሪያት ተክለማሪያም ከተፈሪ ጋር ተጣልተው ራስ ካሳ ጋር ይሄዱና “ስራ ስጡኝ” ይሏቸዋል፡፡ ራስ ካሳ ግን “አንተ የተፈሪ አሽከር ስለሆንክ ስራ አልሰጥህም” ይሏቸዋል፡፡ ራስ ካሳ “እርሶ ምን ነካዎት? እኔ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰራተኛ እንጂ የተፈሪ አሽከር አይደለሁም” ይላሉ ተ/ሐዋሪያት፡፡ “እኔ አሁን ስራ ለቅቄያለሁ– ለምንስ አሽከር ይሉኛል” ሲሉ ራስ ካሳን ይሞግታሉ፡፡ አየሽ መንግሥትና ንጉሥን ራስ ካሣ መለየት አልቻሉም። ኢህአዴጎችም ከዚህ አስተሳሰብ ስላልተላቀቁ ነው “እኛ ስራ ሰጥተነው፣ እኛ ቤት ሰጥተነው፣ እኛ ደሞዝ እየከፈልነው እኛኑ ይሳደባል ይዘልፋል” የሚሉት፡፡ እኔ ግን ስራ የሰጠችኝ አገሬ ኢትዮጵያ እንጂ እነሱ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ “እስከዛሬ በክፉና በደግ ጊዜ ሳናይህ እንዴት መጣህ አላለችም፣ እንኳን ደህና መጣህልኝ ልጄ” ብላ ነው ስራ የሰጠችኝ፤ይህንን አስረግጬ እነግርሻለሁ፡፡ ስለዚህ ስራ የሰጠኝና ደሞዝ የሚከፍለኝ ማን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ከዚህ ቀደም ዶ/ር ዳኛቸው የብአዴን አባል ናቸው የሚል ነገር ተወርቶ በነበረበት ጊዜ ስጠይቅዎት “እንኳን የብአዴን የምወደው የኢህአፓ አባልም አልሆንኩም የየትኛውም ፓርቲ አባል የማልሆነው በአካዳሚክ ስራዬ ላይ ነፃነት እንዳላጣ ነው” ብለውኝ ነበር፡፡ ያስታውሳሉ?

በደንብ አስታውሳለሁ እንጂ!

ታዲያ በአሁኑ ወቅት በየፖለቲካ መድረኮቹ ላይ ፅሁፍ ያቀርባሉ፣ ትችቶችን ይሰነዝራሉ፡፡ ይሄ ነገር በስራዎ ላይስ ተፅዕኖ የለውም?

በጣም ጥሩ! ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ጋር በፍፁም ግንኙነት የለውም፡፡ በአካዳሚክ ስራዬም ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም፡፡ እንዴት የሚል ጥያቄ ካነሳሽ ደግሞ፤ እኔ እንደ አንድ ሲቪል ግለሰብ ነው እየተቸሁ ያለሁት፡፡ ሁለት አይነት ምክንያታዊነት አለ- አንደኛው ግለሰባዊ ምክንያታዊነት ይባላል፤ ሁለተኛው ደግሞ ማኅበረሰባዊ ምክንያታዊነት (public reason) ይባላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማህበረሰባዊ ምክንያታዊነቴን ተጠቅሜም እየተቸሁ ነው፡፡ ሁለቱ አብረው ይሄዳሉ፡፡ እንደግለሰብ ደግሞ እያስተማርኩ ነው፡፡ በሙያዬም እያገለገልኩ ነው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በፍፁም አይጋጩም፡፡ ምናልባት ሊጋጭ የሚችለው የፓርቲ አባል የሆንኩ እንደሆነ ነው፡፡

የፓርቲ አባል ቢሆኑ የአካዳሚክ ስራውና የፓርቲ አባልነቱ የሚጋጩበትን መንገድ ሊገልፁልኝ ይችላሉ?

ማስተማርም ሆነ የፖለቲካ ስራ የሙሉ ሰዓት ስራ እንጂ የትርፍ ጊዜ ስራ ስላልሆኑ ሁለቱም ራሳቸውን ችለው መሰራት ያለባቸው ነገሮች ናቸው፤ ይጋጫሉ የምልሽ፡፡

ግን እኮ እንደ እርሶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ የሚስተምሩ ሌሎች ምሁራን በአንድ በኩል እያስተማሩ ወዲህ ደግሞ ፓርቲ እየመሩ ነው፡፡ እንዴት ያዩታል?

እኔ በዚህ በፍፁም አልስማማም! ይሄ የራሴ አቋም ነው፡፡ በእኔ እምነት እነዚህን ስራዎች በአንዴ ስትሰሪ ከሁለቱ አንዱ ይጎዳል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ከበደችና ዘነበችን በአንዴ እወዳለሁ የሚለው ጉዳይ የማያስኬድ ፍልስፍና ነው፡፡ ከከበደችና ከዘነበች በጣም የምወደውን መምረጥ አለብኝ፡፡ አለበለዚያ አንዷን መጉዳቴ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ ማለት ወይ ትምህርቱ አሊያም ፖለቲካው ጉዳት ይደርስበታል ማለት ነው፡፡ ይህ የእኔ እምነት ነው። በበኩሌ በዩኒቨርሲቲው ለመቆየት ካልቻልኩ ወደ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ እቀላቀላለሁ፡፡ እያስተማርኩ ግን የየትኛውም ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም፡፡

በአንድ ወቅት ለሰማያዊ ፓርቲ ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት ከአንድ የጋዜጣ አዘጋጅ ጋር ተጋጭተው ስለነበር የዛ ጋዜጣ መቅረፀ ድምፅ ካልተነሳ ንግግር አላደርግም ማለትዎን ብዙዎች አልወደዱትም፡፡ ዶ/ሩ ምሁር ሆነው ቂምን ለትውልድ ያስተምራሉ በሚል ተተችተዋልና ምን ይላሉ?

አንድና አንድ ነገር ልንገርሽ፡፡ አንድ ሰው ድምፄን አልቀዳም የማለት መብት አለው፡፡ ምሳሌ ልጥቀስልሽ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል በቅርቡ 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር፤ ፕሮፌሰር ባህሩ ድምጽ መቅረጽ አትችሉም ብለው መቅረፀ-ድምፅ አስነስተዋል፡፡

እንደዚህ ኣይነት በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የእኔ ምን አዲስ ነገር አለውና ነው? እኔ በጎን እኮ አይደለም ይሄ ጋዜጣ እየሰደበኝ ስለሆነ መቀዳት አልፈልግም ያልኩት፡፡ ማንስ ቢሆን መሰደብ ይፈልጋል እንዴ፡፡ አሁን ያልኩሽ ጋዜጣ ወደፊትም ሊቀዳኝ አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች በዚህ ነገር ደስተኛ አይደሉም ላልሽው፤ እኔ እንዳንቺ እርግጠኛ ሆኜ ባልናገርም፤ ጓደኞቼ እንደነገሩኝ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አስተያየት ሰጪዎች በማህበረሰብ ሚዲያው በሰጡት አስተያየት፤ በዚህ ጋዜጣ ያለመቀዳት መብት እንዳለኝ ብቻ ሳይሆን ዘለፋቸው ከመስመር የወጣ መሆኑንም መስክረዋል፡፡ ቂም ለምትይው ቂመኛ አይደለሁም፡፡

እኔ እስከምረዳው ድረስ አንድ ሰው፤ በማስታወስና በቂም መካከል ያለውን ልዩነት በቅጡ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ማስታወስ ማለት ማቄም ማለት አይደለም፡፡ ስድስት ወርና አንድ ዓመት ያልሞላውን ጉዳይ ማስታወስህ ቂመኛ ያደርግሀል የሚለው አገላለጽ አግባብ አይደለም። አልቀበለውምም፡፡ ከዚህ በፊትም እንዳልኩት ሰዎች እንደዚህ ነህ፤ እንደዚያ ነህ ባሉኝ ቁጥር ራሴን ለመከላከል ምላሽ መስጠቱ ተገቢነቱን አላምንበትም፡፡

አዲስ አድማስ ሚያዚያ 11 ቀን 2006 ዓ.ም

No comments: