Wednesday, April 23, 2014

እውቅና የተሰጠው የሚያዚያ 26ቱ የአንድነት ሰልፍ በደህንነቶች ትእዛዝ እውቅና ተነፈገ

April 23/2014

ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና እንደሚጠቁመው፣ የአንድነት ፓርቲ ሚያዚያ 19 ሰልፍ ለማድረግ ቢጠይቅም፣ የፖሊስ አዛዞች በዚያን ቀን በቂ ጥበቃ ማዘጋጀት አንችልም በማለታቸው፣ አስተዳደሩ ሚያዚያ 26 ቀን እንዲደረግ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ ለሚያዚያ 26 የእውቅና ደብዳቤ ለመዉሰድ ወደ አስተዳደሩ ጽ/ቤት ያመሩት የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች፣ የእውቅና ደብዳቤ ሳይቀበሉ መመለሳቸውን ያነጋገርናቸው የአንድነት አመራር አባል ገለጹ።
የአስተዳደሩ ሃላፊዎች፣ ከደህንነት ጽ/ቤት ለአንድነት ሰልፍ እውቅና እንዳይሰጡ በቀጥታ መታዘዛቸዉን የገለጹት የአንድነት አመራር ፣ አዲስ አበባ በከንቲባው ሳይሆን፣ የአዲስ ሕዝብ ባልመረጣቸው ከበስተጀርባ ሆነው በሚፈልጡና በሚቆርጡ ጥቂቶች መዳፍ ስር የወደቀችና በአምባገነኖች የምትገዛ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።
አንድነት ፣ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ፣ ሰልፍ ለማድረግ በአገዛዙ እውቅና ያልተሰጠበት የሚያዚያ 26 ቀኑ፣ አራተኛው ቀን ሲሆን፣ ከፋሲካ እሁድ ዉጭ ባሉ ሶስት እሁዶች ፣ መጋቢት 28፣ ሚያዚያ 5 እና ሚይዚያ 19 ቀንም ሰልፍ ለማድረግ ተጠይቆ በደህንነቶች ትእዛዝ እውቅና አለመሰጠቱ ይታወቃል።
ከሰልፍ ጋር በተገናኘም የአዲስ አበባ አስተዳደር ሚያዚያ 19 ቀን ሰልፍ ለማድረግ አንድነት ፓርቲ ጠይቆ እውቅና አልሰጥም ቢልም፣ ለአንድነት በተከለከለበት ቀን ለሰማያዊ ፓርቲ እውቅና እንዲሰጥ የደህንነት ሃላፊዎች መመሪያ መስጠታቸውን፣ በአዲስ አበባ ያሉ ምንጮቻችንን በመግለጽ መዘገባችን ይታወቃል።
በአንድነት ፓርቲ ላይ እየተደረገ ያለው ሕግ ወጥ እርምጃ፣ ከአስተዳደሩ ዉጭ ያሉ የደህንነት ሃላፊዎች፣ በቀጥታ የአስተዳደሩ የሰማያዊ ሰልፍ ፍቃድ ኦፊሰር የሆኑትን፣ አቶ ማርቆስን ፣ በማዘዝ እየፈጸሙት ያለ አሳዛኝ ተግባር እንደሆነ የገለጹት የአንድነት አመራር፣ ከከንቲባው ጽ/ቤት ሃላፊዎች ጋር የፓርቲዉ ከፍተኛ አመራሮች ችግሮችን ለመፍታት በስፋት እንደተነጋገሩ ገልጸዋል። አንድነት ሚያዚያ 19 ቀን ጠይቆ ፣ «ሌላ ዝግጅት አለ። በቂ ጥበቃ የለም» በሚል ሚያዚያ 26 ማድረግ እንደሚቻል እንደተነገራቸው የገለጹት የአንድነት አመራር፣ አሁን ሌሎች ድርጅቶች በሚያዚያ 19 ሰልፍ እንዲጠሩ እውቅና ለመስጠት መዘጋጀቱ፣ በቂ ጥበቃ ከየት ሊገኝ ቢችል ነው በሚል የአስተዳደሩን ሃላፊዎች ጠይቀዋል።
የአስተዳደሩ ሃላፊዎች ጉዳዩን ተከታትለው፣ ነገ ሚያዚያ 15 ቀን እንደሚያሳውቋቸው መግለጻቸዉን፣ የሚናገሩት የአንድነት አመራር አባል፣ አስተዳደሩ መጀመሪያ ለጠየቀዉ ፓርቲ፣ አስፈላጊዉን ቅድሚያ እንደሚሰጥና ሕግን አክብሮ በሕግ የተደነገገለትን ሃላፊነት እንደሚወጣ፣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በሃያ ሶስቱም የአዲስ አበባ ወረዳዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላትና ደጋፊዎች እንዳላቸው የገለጹት የአመራር አባሉ፣ አስተዳደር እውቅና ሰጠ አልሰጠም፣ በቅርብ ቀናት ዉስጥ ለሚያዚያ 19 ይሁን ሚያዚያ 26 ቅስቀሳ እንደሚጀምር አሳወቀዋል።
አገዛዙ የዜጎችን መብት ማፈን እንደማይችል ያስረዱት አመራር አባሉ፣ አንድነት በሰለጠነና በመግባባት ፖለቲካ ቢያምንም፣ ሕግ መንግስቱ የሚደነግግለት መብት ላይ እንደማይደራደር አረጋግጠዋል። «ሰልፉ ይደረጋል። ጥያቄዉ ፖሊስ ሕዝብን ይጠብቃል ወይንስ ከሕዝብ ጋር ይጋጫል? የሚለው ነው» ሲሉ ነበር የአንድነት ቁርጠኝነት ለማሳየት የሞከሩት።
ፓርቲዉ በዚህ ረገድ፣ እየትሰራ ያለዉን ደባ ለማጋለጥና ሕዝብ አጥርቶ እንዲያወቀው ለማድረግ፣ በመረጃ ላይ የተደገፈ መግለጫ እንደሚሰጥም ለማወቅ ችለናል።
የአዲስ አበባ አስተዳደርና አንድነት ከመግባባት ደረጃ ደርሰው፥ የታቀደው ሰልፍ ሕጉን በጠበቀ መልኩ ሚያዚያ 19 ይሁን ሚያዚያ 26 ይደረግ እንደሆነ፣ ያ ካልሆነ ደግሞ የአንድነት ፓርቲ ዉሳኔ ምን እንደሚሆን ተከታትለን ለማቅረብ እንሞክራለን።

No comments: