April 23/2014
- ውይይቱ ቀጣዩ የአሰላለፍ ስልትና የምት አቅጣጫ የሚወሰንበት ሊኾን ይችላል
- ተሳታፊዎች ፍረጃዎችንና ክሦችን በመረጃና በሐሳብ የበላይነት ማጋለጥ ይገባቸዋል
(አፍሮ ታይምስ፤ ቅጽ ፩ ቁጥር ፯፤ ማክሰኞ እና ረቡዕ፤ ሚያዝያ ፲፬ – ፲፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ በሃይማኖት ይኹን በማንኛውም ሽፋን የሚደረግን የፖሊቲካ ግጭት ለመመከት በሚል በአዲስ አበባ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ከታቀፉ አባሎቹ ጋራ ውይይት በማካሔድ ላይ መኾኑ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ዐሥር ክፍለ ከተሞች 116 ወረዳዎች ካሉት ሰባት የግንባሩ አደረጃጀቶች ማለትም የሴቶች፣ ወጣቶች፣ መምህራን፣ የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ የአነስተኛ ጥቃቅን ተቋማት ከእያንዳንዳቸው የተውጣጡ ስድሳ፣ ስድሳ አባላትን ያሳተፈና ሦስተኛ ሳምንቱን የያዘ ውይይት በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡
‹‹የሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮች በሰላም አብሮ የመኖር ወርቃማ ተሞክሮና የማስቀጠል ፋይዳው››፣ ‹‹አዲሲቷ ኢትዮጵያና የሃይማኖት ብዝኃነት አያያዝ››፣ ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነት ከሕገ መንግሥታችን ጋራ ያለው የማይታረቅ መሠረታዊ ቅራኔና መፍትሔው›› በሚሉ ርእሶች በቀረቡ ጽሑፎች ላይ የተመሠረተው ውይይቱ ለአራት ተከታታይ ዙሮች እንደሚካሔድ ተመልክቷል፡፡
‹‹የመደማመጥ መድረክ›› የተሰኙት የመጀመሪያዎቹ ኹለት ዙሮች፣ ከቀረቡት ጽሑፎች ጋራ በተያያዘ የተዘጋጁ የመወያያ ነጥቦችን አስመልክቶ የተሳታፊዎች ግንዛቤና አቋም ምንድን ነው የሚለውን ለማወቅ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና አቋሞች በስፋት እንዲነሡና በዚህም ስልት በአባላት ውስጥ ያለውን ስሜት በቀጥታ ለማዳመጥ የታቀደበት መኾኑ ተገልጦአል፡፡
ባለፈው ሳምንት በተከናወኑት የውይይቱ ኹለተኛ ዙር መድረኰች÷ በአወያይነት በተመደቡት የወረዳ ጽ/ቤት ሓላፊዎች አማካይነት በየፈርጁ ተጠቃለው ለበላይ አመራር (ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር) ቀርበዋል ለተባሉት የተሳታፊዎች ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና አቋሞች የግንባሩና የመንግሥት አቋሞች፣ መረጃዎችና ዕቅዶች በምላሽነት እንደተሰጡ ታውቋል፡፡
በቀጣይ በሚካሔዱት ኹለት ዙሮች፣ በተናጠል ሲወያዩ የቆዩት የሰባቱ አደረጃጀቶች ስድሳ፣ ስድሳ ተሳታፊዎች በጋራ በመገናኘት በሥልጠና አመለካከታቸውንና ግንዛቤያቸውን ያስተካክሉበታል ተብሎ የሚጠበቅ የማጥራትና የመግባባት መድረክ እንደሚኾን ተጠቁሟል፡፡
በዚኽ መልኩ የሠለጠኑት የየወረዳው 420 የግንባሩ ‹‹የልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አደረጃጀቶች›› በቀጣይ በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ እንደሚጠራ በሚጠበቀው የብዙኃን መድረክ ከሕዝቡ ጋራ ተቀላቅለው በተለያዩ ስልቶች በመሳተፍ መድረኰቹ በታቀደው አቅጣጫ እንዲመሩና ወደተፈለገው መደምደሚያ እንዲደርሱ በማድረግ ድርጅታዊ ተልእኮዎቻቸውንና ስምሪቶቻቸውን እንደሚወጡ ተመልክቷል፡፡
‹‹ጠባብነት፣ ትምክህትና አክራሪነት›› የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች እንደኾኑና ከሕዝብ አቅም ግንባታ አኳያ ዋናው ርብርቡ በእነዚህ ላይ እንደኾነ መንግሥታዊ ጽሑፎች ይገልጻሉ፡፡ ሙስሊሙ ከጠባብነት፣ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኑ ከትምክህት ርእዮት ጋራ የመዳበል ባሕርያት እንደሚታይባቸው የሚገልጹት የመንግሥት ሰነዶች÷ በእኒኽ ባሕርያት በተቃኙ ‹‹ሃይማኖታዊ ርእዮቶች›› ላይ የተመሠረተ ሽብርተኝነትና ሃይማኖታዊ ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል ታሳቢ አድርጎ ርእዮቶቹን ‹‹በትምህርትና ሥልጠና፣ በዴሞክራሲያዊ አኳኋን›› መታገልና የለዘብተኝነትና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የተጠናከረ ሥራ መሠራት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
የመንግሥት የመልካም አስተዳደርና ልማት ጉዳዮች ተያይዘው በተነሡባቸው ባለፉት ኹለት የውይይት ዙሮች አንዳንድ የመድረክ አወያዮች ለስብሰባው አካሔድ ተቀምጧል ከተባለው ድርጅታዊና መንግሥታዊ አቋምና አቅጣጫ በተፃራሪ በኦርቶዶክሳዊው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያሰሙት ገለጻ፣ የውንጅላና የፍረጃ መንፈስ የተጠናወተው ከመኾኑም በላይ ያልተፈለገ አደገኛ ውጤት ሊያስከትልም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
በየካ፣ በቦሌ እና በልደታ ክፍላተ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች የተሳተፉ የአፍሮ ታይምስ ምንጮች ስምና ሓላፊነታቸውን ለይተው የጠቀሷቸው አወያዮች÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን መዋቅሩን አጥንቶ ፋይናንሱን እኔ ካልያዝሁትና ካልተቆጣጠርሁት ብሏል፤ ስለዚህ አክራሪ ነው››፤ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሰጠችው ደንብ ውጭ ይንቀሳቀሳል፤ ስለዚህ አክራሪ ነው››፤ ‹‹መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ለመኾኑ አስገራሚ አስገራሚ መረጃዎች አሉት›› የሚሉና የመሳሰሉ ክሦችንና ፍረጃዎችን መሰንዘራቸውን አስረድተዋል፡፡
የት/ቤት(መምህራን) አደረጃጀት አባላት እንዲሁም የስብሰባው ተሳታፊ ካህናት በበኩላቸው፣ በቅርበት ጠንቅቀው የሚያውቋቸው በርካታ የማኅበሩ አባላት መኖራቸውንና ፍረጃውና ክሡ በማስረጃ መደገፍ እንዳለበት አለበለዚያ ማኅበሩን ይኹን አባላቱን ይገልጻቸዋል ለማለት እንደሚያዳግት በመጥቀስ ተቃውመዋል፡፡
አወያዮቹ ማስረጃ እንዲያቀርቡና አነጋገራቸውን እንዲያርሙ በጥብቅ ያስጠነቀቁት ተሳታፊዎቹ፣ ውይይቱ በዚህ መንፈስ የሚካሔድ ከኾነ በተሳትፎ ለመቀጠል እንደሚቸገሩ በማሳወቅ ስብሰባውን ጥለው ለመውጣት ተነሣስተው እንደነበርና አወያዩ አካል መድረኩን መሪዎች በሌሎች በመተካት አስቸኳይ እርማት በማደረጉ በተሳትፏቸው ለመቀጠል እንደቻሉ ተጠቁሟል፡፡
ሌሎች የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ አጽድቃ በሰጠችው መተዳደርያ ደንብ መሠረት እንደሚንቀሳቀስና የፈጸማቸውን ዐበይት ማኅበራዊና የልማት ተግባራት፣ የአገልግሎቱ ዕሴቶችና ትሩፋቶች ያስገኙትን አገራዊ ጠቀሜታዎች በመዘርዘር አስረድተዋል፤ በተሰነዘሩት ፍረጃዎችና ክሦች አንጻርም እውነታውን በመግለጽ ፍረጃውና ክሡ ሕገ መንግሥታዊውን ሃይማኖት ነክ ድንጋጌ የሚጥስ ጣልቃ ገብነት ነው በሚል ኮንነውታል፤ በሕግ አውጭነት ሉዓላዊ ሥልጣኗ አገልግሎቱን የፈቀደችለት ቤተ ክርስቲያ እንኳ ያላለችውን ሕዝብን ሰብስቦ ማኅበሩን በአክራሪነት መወንጀል የማኅበሩን ገጽታ በማጠልሸት ከሕዝቡ ለመነጠልና ሕዝቡን በማኅበሩ ላይ ለማዝመት ተይዟል ብለው የሚጠረጥሩት ዘመቻ አካል ነው ብለው እንደሚያዩትም አመልክተዋል፡፡
‹‹ከመቻቻል በላይ በፍቅር እየኖርን ነው፤ ከሕጋዊነትም በላይ በፍቅር እየኖርን ነው፤›› በማለት በመድረኩ ‹መቻቻል› እና ‹የሕግ የበላይነትን ማስከበር› በሚል ከተገለጸው ባሻገር ሕዝቡ በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴቶቹን ጠብቆ በፍቅርና በመገናዘብ እየኖረ መኾኑን ይልቁንም በዚህ ረገድ ከአክራሪነትና ጽንፈኝነት ጋራ በተያያዘ የሚሰጡ ማብራሪያዎች አንዱን የድህነትና ኋላቀርነት ሌላውን የሥልጡንነት መለዮ የሚያስመስል ትርጉም እንዳያሰጡ ማስተዋልና ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተመክሯል፡፡
በተያያዘም ‹‹ታሪካችን ረዥም ነው የሚለውን ትምክህት መዋጋት›› በሚል ከመጀመሪያው ምእት ዓመት (34 ዓ.ም.) አንሥቶ የሚቆጠረው የቤተ ክርስቲያኒቱ ብሔራዊ ታሪክ በቅ/ሲኖዶስ አባላት ሳይቀር የመንግሥት ሓላፊዎች የተተቹበትና እንዲታረሙም የተጠየቁበት ኾኖ ሳለ ለውይይት በቀረቡት ጽሑፎች ውስጥ በአግባቡ አለመስፈሩ የመጽሐፍ ቅዱሱን እውነታ መቆነጻጸልና ጥንታዊነቷን የማደብዘዝ ውጥን እንዳለ የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡
እስልምና በሰላም ገብቶ እንዲስፋፋ ምክንያት ኾነዋል የተባሉትን ንጉሥ አርማህ ‹‹በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ›› ከማለት በቀር ስማቸውንና ክርስቲያናዊነታቸውን በመግደፍ የቀድሞዎቹ ነገሥታት በአጠቃላይ ብዝኃነትን እንደ አደጋ የሚመለከቱና የአንድ ሃይማኖት ፖሊሲ የሚያራምዱ ነበሩ ማለትም በአነስተኛው አነጋገር ቅንነት የጎደለው እንደኾነ ተሳታፊዎቹ ለአፍሮ ታይምስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የመድረኩ አወያዮች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ለሰነዘሯቸው ክሦችና ፍረጃዎች ቅሬታ አቅራቢ ተሳታፊዎችን በግልጽ ይቅርታ መጠየቃቸው ተገልጦአል፡፡ ፍረጃውና ክሡ ለውይይቱ ከተሰጣቸው ተሰብሳቢውን የማዳመጥ አቅጣጫ አልፈው የተናገሩት መኾኑን በማመን መሳሳታቸውን የገለጹትም ‹‹ማንንም እንዳትፈርጁ፣ ‘specific’ እንዳታደርጉ ተብለናል፤ የመላእክት ስብስብ አይደለንም፤ ሰዎች ነንና እንሳሳታለን›› በማለት ነበር፡፡
ይኹንና ይህ ነው የተባለ ማስረጃ ባይጠቅሱም መንግሥት በሕግ የሚጠይቃቸው አንዳንድ ግለሰቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳይጠቁሙ አላለፉም፤ መንግሥት በልዩነትና ግጭት ወቅት ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅ በሚል ካልኾነ በቀር በሃይማኖት ጣልቃ እንደመግባት ተደርጎ የቀረበውን አስተያየትም አልተቀበሉትም፡፡
የውይይቱ ዓላማ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከአባሉና ከአጠቃላይ ሕዝቡ አቋምና ግንዛቤ በመነሣት በትምክህትና ጠባብነት የሃይማኖት አክራሪነት ርእዮት አራማጅነት በሚፈርጃቸው ወገኖች ላይ በቀጣይ የሚይዘውን አሰላለፍና የምት አቅጣጫ ለመወሰንና ይኹንታ ለማግኘት የሚጠቅምበት ሊኾን እንደሚችል ብዙዎች ያምናሉ፡፡
በቀጣዮቹ ኹለት ውይይቶችና ከዚያም በኋላ በታቀዱ የሕዝብ መድረኮች የስብሰባ ጥሪ የተደረገላቸው ኹሉ እስከ አኹን እንደታየው መዘናጋት ሳይሆን በስብሰባ እየተገኙ አካሔዱን በሐሳብና የመረጃ የበላይነት ማጋለጥና ተገቢው አቋም ላይ እንዲደረስ መትጋት እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡
No comments:
Post a Comment