Saturday, August 27, 2016

በርከታ ከተሞች ራሳቸውን ከወያኔ አገዛዝ ነጻ አድርገዋል

August 27,2016
የዐማራ ሕዝብ ተጋድሎ – ሙሉቀን ተስፋው (ነሃሴ 20 ቀን 2008)
በበርከታ የጎጃም ከተሞች የዐማራ ተጋድሎ ተፋፍሟል፤ ራሳቸውንም ከወያኔ አገዛዝ ነጻ አድርገዋል
 በቡሬ ከተማ ከሠላሳ ሺህ በላይ ዐማራ ለተጋድሎ ወጥቷል፤ የኦሮሚያ ኢንተ. ባንክን ሕዝቡ ጥበቃ አድርጎለታል
 በጅጋ የተጋድሎ ሰልፉ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል
 ቋሪት ወረዳ ሙሉ በሙሉ በሕዝብ ቁጥጥር ሥር ሆኗል
 ማንኩሳ፣ ፍኖተ ሰላምና ጉንደወይን ሌሎች የዐማራ ተጋድሎ የተካሄደባቸው ከተሞች ናቸው
 በጎንደር ብዙ የዐማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባሎች ከሥራ ታግደዋል
 በደብረ ታቦር የሥራ ማቆም አድማ ሊጀመር ነው
 በወልቃይት የአማርኛ ሙዚቃ አትሰሙም በሚል ግጭት ተፈጠረ
 40 የዐማራና ኦሮሞ የጸረ ሙስና ኮሚሽን አቃቢ ሕግ ባለሙያዎች ከሥራ ተባረሩ
ቡሬ፤
በሬ ዛሬ የዐማራ ተጋድሎ ከተካሔደባቸው ከተሞች ዋነኛዋ ናት፡፡ ከጠዋቱ ሦስት ሰአት አካባቢ የጀመረው የዐማራ ተጋድሎ እስከ ምሽት 12 ሰአት ድረስ ቆይቷል፡፡ የተጋድሎ ሰልፉ ማዶ በሚባለው የከተማው ክፍል የተጀመረ ሲሆን ከሰላሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጋድሏቸው ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ ወልቃይት ዐማራ ነው፤ ኮ/ል ደመቀ እና የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሜቴዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ፤ መሬታችን ይመለስ፤ 25 ዓመት ታስረናል አሁን ግን በቃን፤ ዐማራነት ወንጅል አይደለም፣ ወያኔ ሌባ ነው፤ ብአዴን እኛን አይወክልም… የሚሉ መፈክሮች ገልተው ሲሰሙ ውለዋል፡፡ የወያኔ ደጋፊ የሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ትንሳኤ ሆቴል (ባለቤቱ ዐማራ ሲያስገድል የኖረ ሕወሓት ነው)፣ ቀበሌ 01 ጽ/ቤት፣ አብቁተ፣ የዓባይና የንግድ ባንኮች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክን ሊያወድሙ የሚፈልጉ ተላላኪዎችን ወጣቱ ዐማራ አክሽፎታል፡፡ ኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ መቆም አለበት ሲሉም የዐማራ ሕዝብ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡
በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ መኖሩን በተመለከተ ላቀረብነው ጥያቄ የዐይን ምስክር ሲናገሩ ‹‹እኔ በዐይኔ አንድ ለእረፍት የመጣ የዩንቨርሲቲ ተማሪ አጋዚ ሲገድለው አይቻለሁ፤ ሦስት ዐማሮችም በጥይት ተመተው ሆስፒታል ገብተዋል፤ በሕይወት ስለመኖር አለመኖራቸው ያወቁት ነገር የለም›› ብለዋል አንድ እማኝ በስልክ እንዳረጋገጡልን፡፡ የአጋዚ ወታደሮች ያቆሰሏቸው ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቡሬ ከተማ መግቢያና መውጫ በሮች ሙሉ በሙሉ በወጣቱ ተዘግተዋል፡፡
ጅጋ፤
የጅጋ ዐማሮች ዛሬ ለሦስተኛ ቀን የዐማራ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ የጅጋ ከተማ ሕዝብ ከነሃሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በየቀኑ ወደ አደባባይ እየወጣ ተጋድሎውን እያደረገ ነው፡፡ በጅጋ እስካሁን አንዲት እህታችን ተሰውታለች፡፡ ከተማዋንና አጠቃላይ ወረዳውን ዐማሮች ራሳቸው የተቆጣጠሩ ሲሆን ዛሬ ላይ የሃይማኖት አባቶች ወጣቱን ለመሰብሰብ ሞክረው ነበር፡፡ የዐማራው ወጣትም ከእንግዲህ በኋላ የዐማራ የመኖር መብት ሳይረጋገጥ ተጋድሎው እንደማይቆም እንቅጩን በአንድ ድምጽ ተናግረው ስብሰባው ያለስምምነት መበተኑን ከቦታው በስልክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በጅጋ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ምንም ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴም የለም፡፡ ሁሉም ዐማራ የተጋድሎ ጥያቄውን እያስተጋባ ነው፡፡ በስልክ ያነጋገርናቸው ወጣቶች ‹‹ከእንግዲህ በኋላ ዐማራነት ወንጅል ሆኖ የምንኖርበት ምንም ምክንያት የለም፤ የአባቶቻችን የአርበኝነት ታሪክ በዚህ ትውልድ ይደገማል›› ሲሉ በጎበዝ አለቃዎች ጭምር መመራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ቋሪት፤
በቋት ወረዳ ገነት አቦ ከተማ ትናንት ነሃሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የተጀመረው የዐማራ ተጋድሎ አድማሱን አስፍቶ የወረዳዋ ከተማ ገበዘ ማርያምም በሕዝብ ቁጥጥር ሥር ሆናለች፡፡ ገነት አቦ ከተማ ትናንት ከቀኑ ከ9፡00 እስከ 12፡00 የነበረውን የዐማራ ተጋድሎ ለማደናቀፍ ከወረዳው የወያኔ ተላላኪዎች የተውጣጡ የፖሊስና የሚንሻ አባላት ወደ ገነት አቦ ተላኩ፡፡ የገነት አቦ ዐማሮችም በአንድ ድምጽ ‹‹በመጣችሁበት መኪና አሁኑ ተመለሱ፤ አይ ካላችሁ ሕይወታችሁን ጠልታችኋል ማለት ነው›› አላቸው፡፡ ከመኪና ሳይወርዱ ተመለሱ፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ለዛሬ ጠዋት ቀጠሩ፡፡ በቃላቸው መሠረት ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ የተጋድሎ ሰልፉ ተካሄደ፡፡ የገበዘ ማርያም ከተማ ዐማሮችም ተጨመሩ፡፡ የከተማ ፖሊሶች ዝም አሉ፡፡ ከዞን የመጣ ሁለት መኪና የፌደራል ፖሊስም የቋሪትን ዐማራ መጋፈጥ አልቻለም፡፡ የፌደራል ፖሊሶች ልብሳቸውን ቀይረው ተደብቀው ዋሉ፡፡ ነፍጠኛው ዐማራ ጥይቱን ሲቆላው ዋለ፡፡ ለዚህማ ቋሪትን ማን ብሎት፡፡ በቋሪት ነገም የዐማራ ተጋድሎ ይቀጥላል፡፡
ማንኩሳ፤
በማንኩሳ የተጀመረው የዐማራ ተጋድሎ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉን ሰምተናል፡፡ በማንኩሳ ትናንት የተካሔደው የዐማራ ተጋድሎ መጠነኛ ቢሆንም ዛሬ ግን ወደ አደባባይ ያልወጣ የከተመዋ ነዋሪ አልነበረም ነው የተባለው፡፡ በማንኩሳ ዝርዝር ጉዳዮችን በስልክ መቆራረጥ ምክንያት ማግኘት አልቻልንም፡፡
ፍኖተ ሰላም፤
በፍኖተ ሰላም ከተማ የዐማራ ተጋድሎ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡ ትናንት የአንድ ዐማራ ወጣት ነፍስ ያጠፈው ቅጥረኛ ምንሻ ቤት መቃጠሉንም ሰምተናል፡፡ የፌደራልና የአጋዚ ጦር በፍኖተ ሰላም ከተማ ከመጠን በላይ መግባቱን ሰምተናል፡፡ ዛሬ ይህ ሪፖርት እስከተሠራበት ሰዐት ድረስ መንገዶች ሁሉ ዝግ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡
ጉንደወይን፤
በእነሴዎች አገር ጉንደወይን ትናንት ነሃሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ታላቅ የዐማራ ተጋድሎ ሰልፍ ተካሒዷል፡፡ የጎንቻ ሲሦ እነሴ ወረዳ ዐማሮች ትናንት ባካሔዱት ተጋድሎ የትግራይ የበላይነት ይብቃ፣ የማንነት ጥያቄያችን መልስ ይሰጥ፣ ዐማራነት ወንጀል አይደለም፣ የወንድሞቻችን ደም መፍሰስ መቆም አለበት… የሚሉ መፈክሮች መሰማታቸውን ዛሬ ከጉንደ ወይን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በተያያዘም ነሃሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በብቸና አንድ የአገዛዙ መሣሪያ የሆነ ሰው ተገድሎ መገኘቱንም ሰምተናል፡፡
ደብረ ታቦር፤ በደብረ ታቦር ከተማ ከነሃሴ 22 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀን የሚቆይ የቤት ውስጥ አድማ እንደሚደረግ መርሃ ግብሩ ያሳያል፡፡ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዳትወጡ የሚሉ ማስታዎቂያዎች ተለጥፈዋል፡፡ ይህን ተላልፎ በሚገኝ ሰው ላይም የዐማራውን ተጋድሎ እንደመተላለፍ ስለሚቆጠር ከህዝብ ጋር እንደተጣላ ይቆጠራል ተብሏል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ቅጥረኛ ካቢኒዎች ነጋዴዎችን ሱቆቻቸውን እንዳይዘጉ ያስጠነቀቀ ሲሆን የቤት ውስጥ ተጋድሎው አስተባባሪዎች ማንኛውንም ተቋም የሚከፍት ሰው ከወያኔዎቸ ጋር እንዳበረ ስለሚቆጠር የሚያስከፍለው ዋጋ የከፋ ነው ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ጎንደር፤
ጎንደር የቤት ውስጥ አድማው ለሦስተኛ ቀን ቀጥሏል፡፡ የቤት ውስጥ አድማው እስከ እሁድ ይደርሳል ተብሏል፡፡ ኮሎኔል ደመቀን የመውሰድ እቅዱ መክሸፉን የሰማን ሲሆን ትናንት ምዕራብ አርማጭሆ አብደራፊ አካባቢ አንድ ዐማራ የተሰዋ ሲሆን ሁለት የወያኔ ቅጥረኛ ፖሊሶች ዛሬ መገደላቸውን ሰምተናል፡፡
የጎንደር ከተማ ልዩ ኃይል ፖሊስ ምክትል አዛዥ መልካሙ የሽዋስ ጋርም ብዛት ያላቸው የፖሊስ አባላት በወያኔ ትእዛዝ መቀነሳቸውን ሰምተናል፡፡ የተቀነሱት የዐማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በሕዝብ ላይ ባለመተኮሳቸው ነው የተባለ ሲሆን ሁሉም የዐማራ ፖሊሶች በዐማራው ሕዝብ ላይ እንደማይተኩሱ ቃል ገብተዋል ሲሉ ምንጮቻችን ነግረውናል፡፡
አዲረመጥ፤ በወልቃይት ከተማ አዲረመጥ ትናንት ነሃሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የወልቃይት ዐማሮች የፋሲል ደመወዝን ‹‹ዐማራ ነኝ›› አዲስ ሙዚቃ ከፍተው ሲያዳምጡ የትግራይ ልዩ ኃይል ፖሊስ ‹‹አማርኛ ሙዚቃ ማዳመጥ አትችሉም›› በማለቱ በተፈጠረ ግጭት ከስድስት በላይ የሚሆኑ ፖሊሶች በከፍተኛ ሁኔታ ቆስለው አምልጠዋል፡፡ አንድ የወልቃይት ዐማራ በጥይት የተመታ ሲሆን ለሕይወቱ አስጊ እንዳልሆነ ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲስ አበባ፤
40 የዐማራና ኦሮሞ ተወላጅ የጸረ ሙስና ኮሚሽን አቃቢ ሕግ ባለሙያዎች ከሥራ ተባረሩ፡፡ ከአዲስ አበባ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በሙስና ወንጀል የተዘፈቁ የትግራይ ተወላጆችን መዝገብ ክስ የያዙ 40 የዐማራና ኦሮሞ የአቃቢ ሕግ ባለሙያዎች ከሥራ ተባረዋል፡፡ የተባረሩት የአቃቢ ሕግ ባለሙያዎች በሥራቸው የተመሰከረላቸውና አንቱ የተባሉ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው ተብሏል፡፡ ሆኖም የያዙት የሙስና ክስ መዝገብ የትግራይ ተወላጅ ሙሰኞችን በመሆኑ ሕወሓትን በከፍተኛ ሁኔታ ያዳክማል በሚል የዐማራና የኦሮሞ የሕግ ባለሙያዎቹ ከሥራ ገበታቸው ለመጨረሻ ጊዜ ተባረዋል፡፡ ወያኔ ከዚህ በፊትም እንደ ዳኛ ግዛቸው ምትኩ ያሉ ጠንካራ የዐማራ የሕግ ባለሙያዎችን የማባረር ልምድ መኖሩን ያስታውሷል፡፡

ሕዝባዊ ተቃውሞው ኢኮኖሚውን እየጎዳው ነው!

August 27,2016

“ጥብቅ እርምጃ እንወስዳለን” ህወሃት
protest business
ህወሃት ለማመን ባይፈልግም ለአስር ወራት የዘለቀው የኦሮሞ ተቃውሞ በክልሉ የንግድና ሌሎች ተቋማት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ከክልሉ ወደሌሎች የሚደረገው የንግድ፣ የዕቃ፣ የገበያ፣ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ፣ … ዝውውር በተቃውሞው ምክንያት በርካታ መስተጓጎሎች ደርሰውበታል፡፡ ከዚህም አልፎ አገሪቱ ለውጭ ንግድ በምታቀርበው ምርትና በምትሰበስበው ግብር ላይ የሚያስከትለውን ጫና ከክልሉ ስፋት አኳያ እጅግ ሰፊ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአማራው ክልል የተነሳው ተቃውሞ ችግሩን በይበልጥ እያባባሰው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ የቤት ውስጥ አድማ በሚመታበት ጊዜ የዜጎች እንቅስቃሴ ይገታል፤ ንግድ ይቀዘቅዛል፣ በየዕለቱ ለመንግሥት የሚሰበሰበው ግብር (ቫት) ይቀንሳል፤ የንግድ ተቋማት ሽያጭና ትርፍ ይቀንሳል፤ በዚህ ምክንያት መንግሥት ከንግድ ተቋማት የሚሰበስበው የትርፍ ግብር ይቀንሳል፤ … እንዲህ እያለ ተጽዕኖው በራሱ እየተቀጣጠለ ሌሎች ችግሮችን በመውለድ ኢኮኖሚውን እስከ ማሽመድመድ ይደርሳል፡፡
bure4
ቡሬ ጎጃም
ነውጥ አልባ የትግል ስልት የሚከተለው የኦሮሞ ተቃውሞ በትግሉ መርኽ መሠረት ሰሞኑን በኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠረ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ይፋ አድርጓል፡፡ ጳጉሜን 1 ይጀመራል የተባለው እርምጃ በምን መልኩ እንደሚደረግ ዝርዝሩን እንደሚያሳውቁ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በየትኛውም መልኩ ይደረግ የኢኮኖሚ ተቃውሞ ሥርዓትን በማሽመድመድ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር በኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠረው የኦሮሞ ተቃውሞ የህወሃትን ኮሮጆ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ካሁኑ እየተገመተ ነው፡፡ ተጽዕኖው ደግሞ በአንድና በሁለት ሳምንታት ብቻ የሚቋጭ ሳይሆን የበርካታ ጊዜያት ተደራራቢ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር ሐቅ እንደሆነ በሌሎች አገራት የተካሄዱት ተቃውሞዎች ምስክር ናቸው፡፡
በሙስና እና በዝርፊያ ለ25 ዓመታት ብቃቱን ያዳበረው ህወሃት/ኢህአዴግ በውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ይልቅ ዳያስፖራው ከሚልከው ዶላር የሚያገኘው እንደሚበልጥ የራሱ የገንዘብ መ/ቤት ይመሰክራል፡፡ ከ2003 ዓም በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት የውጪ ንግዱን በእጥፍ አሳድጋለሁ ብሎ ቃል የገባው ህወሃት/ኢህአዴግ አሁንም ያኔ ከነበረበት የ3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አለመነቃነቁን አዲስ አድማስ ዘግቧል፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን በዓመት ከዳያስፖራው የሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ የዛሬ አራት ዓመት 2.5ቢሊዮን ዶላር የነበረው በአሁኑ ጊዜ በዓመት 4ቢሊዮን ዶላር መድረሱ አብሮ ተዘግቧል፡፡ ከዚህ አንጻር ቀጣዩ የኢኮኖሚ ተቃውሞ በዚህ ዙሪያ ያጠነጠነ ቢሆን የህወሃትን አከርካሪ በመምታትና ዕድሜውን ወደማሳጠር በቶሎ ይደረሳል በማለት አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
እንደ አዲስ አድማስ ዘገባ ከሆነ ከአራት አመት በፊት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የውጭ እዳ ወደ 9 ቢሊዮን ገደማ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዕዳው ክምችት 20.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ለዕዳ ክፍያ የውጭ ምንዛሬ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ዕቃ ከውጭ ለማስመጣት የሚሰጠውን የዱቤ ፍቃድ እንዲቀንስ በማድረግ ወይም ረጅም ጊዜ እንዲወስድ በማድረግ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ በኢኮኖሚው ላይ ያሳድራል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ የተጠራው ተቃውሞ ሰልፍ አገዛዙን ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንደዳረገው ተሰምቷል፡፡ ቁጥሩን ለማረጋገጥ ባይቻልም እስከ 30 እና 40ሺህ ፖሊስ፣ ወታደሮችንና የስለላ ሰዎችን ያሰማራው ህወሃት ለእነዚህ ሁሉ ከአምስት መቶ ብር ጀምሮ የውሎ አበል ከፍሏል፡፡ ይኽም እስከ 10ሚሊዮን ብር ለሚሆን ወጪ እንደዳረገው ስሌቱ ያሳያል፡፡ የአዲስ አበባው ሰልፍ በተለያዩ ምክንያቶች እንደታሰበው ባይሳካም atnafበሥርዓቱ ላይ ጉዳት ከማስከተል አንጻር ዓላማው ግቡን እንደመታ ይነገራል፡፡
ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ይካሄዳል በሚል ፍርሃት ውስጥ የገባው ህወሃት አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ የቁጥጥር ሸክም መጫኑ ነዋሪዎች ይመሰክራሉ፡፡ በአማራ ክልል የተነሣው ብረት አከል ተቃውሞ ወደ አዲስ አበባ ይዛመታል በሚል ፍርሃቻ ሆቴሎች ቁጥጥሩ ጠብቆባቸዋል፡፡ የዞን 9 ጦማሪ የሆነው አጥናፍ ብርሃኔ በትዊተር በለቀቀው መልዕክት “ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የሚያርፍ እንግዳ ካለ በ24 ሰአት ውስጥ ለፖሊስ እንዲያሳውቁ ትእዛዝ ለየሆቴሎቹ ተላልፏል” በማለት ትላንት መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡፡
በየማኅበራዊ ድረገጹ ላይ አፍቃሪ ህወሃቶች አሠራሩ በቀድሞ አገዛዞችም ሲሠራበት የኖረና የተለመደ ነው ብለው ለማስተባበል ቢፈልጉም ሁኔታው ግን ከዚያ የተለየ ነው፡፡ በእርግጥ ሆቴሎች እንግዶቻቸውን ለፖሊስ ማሳወቅ የተለመደ አሠራር ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች  የአሁኑ ትዕዛዝ ግን ለየት ያለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ የሚያሰጋ ነገር ሲከሰት ህወሃት ተመሳሳይ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ መቆየቱን የሚናገሩ ወገኖች ከዚህ በፊት በኦነግ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ፍርሃቻ በነበረበት ጊዜ ትዕዛዙ መተላለፉን ያስታውሳሉ፡፡ ከዚያም በሶማሌ ክልል ተመሳሳይ አለመረጋጋት በነበረበት ወቅት ከክልሉ የሚመጡ ተስተናጋጆችን ወዲያውኑ ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዙን የሆቴል ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡ ያሁኑ ደግሞ ከአማራው ክልል በሚመጡ ላይ መደረጉ በክልሉ የተነሳው ተቃውሞ በህወሃት ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ ያሳያል፡፡
ethflagበተያያዘ ዜና ለዘመናት የኦሮሞንና የአማራን ወገኖች በመከፋፈል እርስበርስ እንዲናቆሩ በሰፊው የሰራው ህወሃት የሁለቱ ጥምረት ኅልውናውን አደጋ ላይ መጣሉን የራሱ ሰዎች መናገራቸውን ባለፈውጎልጉል ዘግቦ ነበር፡፡ እነ አባይ ጸሃዬ ወደ አሜሪካ መጥተው ጥምረቱ ስጋት እንደሆነባቸው ለጌቶቻቸው አስረድተዋል፡፡ አሁንም ይህ ጥምረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በሚደረጉት ሰልፎች እና በየማኅበራዊ ድረገጾች ላይ በሚጻፉት እየተንጸባረቀ ነው፡፡
በኦሮሚያ ከህጻናት እስከ አዛውንት በደም ኩሬ ሲጠምቅ የነበረው ህወሃት ሰሞኑን እየከረረ የመጣውን ተቃውሞ ለማክሸፍ “ጥብቅ እርምጃ” እወስዳለሁ ብሏል፡፡ ሲገድል፣ ሲረሽን፣ ሲያስር፣ ሲያሰቃይ፣ … ወዘተ የቆየው ህወሃት አሁን ከዚህ የተለየ ምን “ጥብቅ እርምጃ” እንደሚወስድ ግልጽ አላደረገም፡፡ ስቃይና ሞት በተለያየ መልኩ ሲፈጸምበት የኖረ ሕዝብ ከዚህ በላይ ምንም እንደማይመጣበት በማወቅ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከአስተባባሪዎችና ከአገር ቤት ከሚሰሙት ድምጾች ለመረዳት ይቻላል፡፡
በመለስ ሞት ፊታቸውን ያዞሩት ምዕራባውያኑ የህወሃት አንጋሾች ይህንን የህወሃት አካሄድ ካለመደገፍ ጀምሮ እስከ ጀርባ መስጠት እያደረሳቸው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

Saturday, August 20, 2016

አዲስ አበባ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ናት – አሜሪካ በኢትዮጵያ ያሉ ዜጎቿን አስጠነቀቀችn

August 20,2016
Members of the Ethiopian army patrol the streets of Addis Ababa in 2005.
Members of the Ethiopian army patrol the streets of Addis Ababa in 2005.ኤፍ (ነሃሴ 14 ፥ 2008) የአዲስ አበባ ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ለመጭው እሁድ የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ በከተማይቱ የፍርሃትና የመረበሽ ድባብ መስፈኑን ከአዲስ አባባ የሚደርሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአነስተኛና ጥቃቅን፣ በአንድ ለአምስት ጥርነፋ እና በከፍጠኛ የስለላ መረብ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ህዝብ ግን የቀድሞ ፍርሃት እንደማይታይበት መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተቀጣጠለ ባለ ህዝባዊ እምቢተኝነት ውስጥ በመገኘትዋ አዲስ አበባም የዚህ ለውጥ ንቅናቄ አካል እንድትሆን ውስጥ ለውስጥ ከፍተኛ የማስተባበር ስራ እየተሰራ ነው። የሕምባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ህዝቡ በአብዮት አደባባይ በነቂስ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል። ምክንያቱም የአዲስ አበባው ህዝባዊ ንቅናቄ ለለውጡ ወሳኝ ስለሆነ።
በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ700 በላይ ወገኖቻችን መገደላቸው፣ በ10ሺዎች ደግሞ ለእስር እንግልትና መሰወር መዳረጋቸውን አስተባባሪ ኮሚቴው በመግለጫው አመልክቷል።
ትላንት ነሃሴ 13 እለት ቡሄ ነበር። ከቶውንም የቡሄ በአል ድባብ አልነበረውም። በአዲስ አበባ ከፍተኛ ውጥረት አለ። በተለይ በአንዋር መስጊድ አካባቢ ከፍተኛ ፍተሻ በመካሄድ ላይ እንደነበር መረጃዎች ጠቁመዋል። ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ እንዲሁም በየመስሪያ ቤቱ ህዝቡን እየሰበሰቡ በእሁዱ ሰልፍ ላይ እንዳትገኙ በማለት እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
በሰሜን ጎንደር በርካታ ከተሞች ህዝባዊ እንቢተኝነቱ ወደ ጦርነት መሸጋገሩን ከስፍራው የሚደርሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የህወሃት ባለስልጣኖች እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የኢትዮጵያን አንጡራ ሐብት በመዝረፍ ፣ ንብሮቶቻቸውን በመሸጥ እና በማሸሽ ላይ እንደሚገኙም ታማኝ ምንጮች ገልጸውልናል።
ሕዝባዊ አመጹ ያስከተለው የሃገሪቱ አለመረጋጋት በዚህ ከቀጠለ ባለስልጣኖቹ ሀገር ጥለው ለማምለጥ እቅድ መያዛቸው ተነግሯል።
ይህ በዚህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎቹ እንዲጠነቀቁ በትናንትናው እለት መግለጫ አውጥቷል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክልሎች መንግሥትን ላይ በሚካሄዱት ተቃውሞዎች ምክንያት አደጋ ሊኖር እንደሚችል በመግለጽ ዜጎቹን አስጠንቅቋል።
የስልክና የኢንተርነት አገልግሎት መቆራረጥ ምክንያት በኢትዮጵያ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ በሀገሪቱ ካሉት የአሜሪካ ዜጎች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት እንዳሰናከለበት መግለጫው ጠቅሷል።
የተቃውሞ ሰልፎቹ ካለፈው ዓመት ሕዳር ወር ጀምሮ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት እንዳስከተሉ መግለጫው ጠቅሶ፤ ተቃውሞዎቹ ሊቀጥሉና ሊስፋፉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለ አስፍሯል። በዚህም ምክኒያት በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ደህንነታቸውን እንዲጠብቁና የተቃውሞ ሰልፎችንና ሰዎች በብዛት የተሰባሰቡባቸው ቦታዎችን እንዲያስወግዱ አሳስቧል።

Wednesday, August 17, 2016

ጊዜዉ ደረሰ

Augest 17,2016
ፊዳ ቱምሳ
ዕንባ እየተናነቀኝ የዛሬዉ የኦሮሞ ትዉልድ እየከፈለ ያለዉን መስዋዕትነት ከእሱ ጋር ሆኜ ያለመካፈሌ እያንገበገበኝ ተከዝኩ፡፡ የነፃነት ቀን መቃረቡን ሣይ በአንድ በኩል እጅግ ተፅናናሁ፡፡ የነገዉን ነፃነት ሳያዩት ለመጪዉ ትዉልድ የተሰዉትን ጀግኖች በዓይኔ እየዳሰስኩ ኮራሁባቸዉ፡፡ የእነርሱ ደም የፈሰሰዉ በከንቱ እንዳልሆነ ስረዳ በእጅጉ ተፅናናሁ፡፡ በልጅነት ዕድሜአቸዉ ለዚህ ታላቅ መስዋዕትነት ራሳቸዉን መስጠታቸዉ ለትዉልድ መዘከር የሚገባዉ ታሪክ እንደሆነ ያለጥርጥር ከህሊናዬ ጋር ተስማማሁ፡፡ እንደገናም ወደኋላ ሄጄ ያለፍንበትን መንገድ እንድመለከት አዕምሮዬ ሞገተኝና ተጓዝኩ — የህሊና ጉዞ፡፡
Ethiopia, TPLF officials
“Whoever sows injustice will reap calamity.”
ጊዜዉ 1991 ዓ.ም. ነበር፡፡ የነበርኩት ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ዉስጥ ነበር፤ በጊዜዉ የኦሮሞ ከተማ!! የወያኔ ሠራዊት ጎጃምን ተሻግሮ ወደ ኦሮሚያ ሲገሰግስ ተቃወምን፣ አወገዝን፤ ቀጥሎም ነቀምት መግባታቸዉን ሲለፍፉ የተቃዉሞ ሰልፍ አዘጋጀን፡፡ የተቃዉሞ ሰልፉ መነሻ ነቀምት ከመግባታቸዉ ጋር የሰጡት መግለጫ ነበር፡፡ መግለጫዉን እንደማስታዉሰዉ “ወተት ጠጣን ጮማ በላን” የሚል እና በዚህ መንገድ ተስተናገድን የሚል መግለጫ ነበር፡፡ ይሄ መግለጫ ወደፊት ለታቀደዉ ብዝበዛና ምዝበራ ሀ ሁ መሆኑን ስለተገነዘብን ነበር ተቃዉሞ ያዘጋጀነዉ፡፡ እናም በተቃዉሞዉ ሰልፍ ላይ የሚሰራጭ ወረቀት እንዲዘጋጅ ተወስኖ አንድ ጓደኛችን ወረቀቱን አዘጋጅቶ አመጣ፡፡ በጽሑፉ ዉስጥ የተቀመጠዉ ምሳሌያዊ መልዕክት ዛሬ ይህን እንድጽፍ አስገደደኝ፡፡
ምሳሌያዊዉ መልዕክት እንዲህ ይላል:- “አንድ በበረሃ የተጎሳቆለ እባብ በጠርሙስ ዉስጥ ያለ ወተት አይቶ ወተቱን ለመስረቅ ዙሪያዉን ተጓዘ፤ አልቻለም፡፡ እናም ጠርሙሱ ዉስጥ ገብቶ ለመጠጣት በዚያ በከሣ አካሉ በጠርሙሱ አፍ ወደ ጠርሙሱ ገባ፤ ወተቱን እየጠጣም ወፈረ፤ ከጠርሙሱ ለመዉጣት የገባበት የጠርሙስ አፍ ከዉፍረቱ የተነሣ አያስወጣዉም፡፡ እናም ሁለት አማራጭ ብቻ ቀረዉ፤ ወይ ወተቱን ተፍቶ መዉጣት ወይ ጠርሙሱ ዉስጥ መሞት፡፡” እናም ያ ጽሑፍ ወያኔ ወደ ኦሮሚያ ገባ፤ ምርጫዉ የዚያ እባብ ምርጫ ብቻ ይሆናል ይላል፡፡ ለወያኔ የያኔዉ መልዕክት ሳትጠራ ወደ ኦሮሚያ አትግባ፤ ኦሮሚያ የራሱ አባት አለዉ፤ ባለቤት አለዉ የሚል ነበር፡፡ ከገባህ ደግሞ ዕጣ ፈንታህ የእባቡ ዕጣ ፈንታ ነዉ፤ ወይ እዚያዉ ትቀበራለህ፣ ወይ በመጣህበት ሁኔታ ወደመጣህበት ትመለሳለህ የሚል ነበር፡፡
ከሃያ-አምስት ዓመት በኋላ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ ተነስቷል፤ የኦማራ ሕዝብ ተነስቷል፡፡ ወያኔ በእነዚህ ሕዝቦች ተከቦአል፤ እባቡ በጠርሙሱ እንደተከበበዉ፡፡ ወተቱን ጠጥቶ እንደወፈረዉ እባብ ወያኔ ወፍሯል፤ ሀብት ዘርፎአል፣ ተንጠባሯል፡፡ እናም እንደእባቡ ሁሉ ጠርሙሱን ለመስበር ይንፈራገጣል፡፡ ጠርሙሱ ግን አይሰበርም፤ የተጠናከረ የተባበረ ሕዝባዊ ኃይል ነዉና፡፡ ጠርሙሱን የከበቡት የኦሮሞ የአማራና የሌሎች ህዝቦች የነፃነት ሃይሎች ኢሳት አቀጣጥለዋል …. ጠርሙሱም እየጋለ ነው ፤ የወያኔ ምርጫ እንግዲህ እንደ እባቡ ሁሉ የበላዉን ተፍቶ፣ የዘረፈዉን ትቶ መዉጣት፤ አለያም እንደበላ እንደወፈረ መቃጠልና መሞት ነዉ፡፡ መዉጫ ቀዳዳ የለም፡፡ በህፃናት ደም ተጨማልቆ፣ በእናቶች ደም ተጨማልቆ፣ በከበሩ አዛዉንቶች ደም ተጨማልቆ የደም ካሣ ሣይከፍሉ ወዴት ይኬዳል? ይዋል ይደር እንጂ የእባቡ ምሳሌ ጊዜዉ ደረሰ፤ ጠርሙሱም ከተሰባሪ ጠርሙስነት ወደ ብረት ጠርሙስነት ተሸጋገረ፤ እባቡም ተከበበ፡፡ እንደገናም ጊዜዉ ደረሰ፡፡
August 6, 2016 (አመሻሽ)

Friday, August 5, 2016

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለምን ፍርድ ቤት አልቀረበም ?

Augest 5,2015
ከሙሉቀን ተስፋው
በፍርሃት ውስጥ የተዋጠው የወያኔው መንግስት በአማራው ህዝብ ላይ ያለውን ጥርጣሬ እንደቀጠለ ውሎአል በዚህም ምክንያት ኮለኔሉን ወደ ፍርድ አልማቅረቡ ብዙዎቹንም አስቆጥቶአል። ለምን አልቀረበም የሚለውን የዜና ትንታኔ ሙሉቀን ተስፋው ከቦታው ያጠናቀረው አጭር ዘገባ ትንሽ ነገር የሚያጭር ሲሆን ፣ ወያኔ የጎንደር ህዝብን ሃያልነት እና አልበገሬነት እንደዚሁም የትግል ጦር ጃንደረባ እንደሆነ ስለሚያውቅ ብቻ ፍራቻውን ከመግለጽ ተቆጥቦ ከርሞአል ፣ ስለዚህ የህዝቡ አልገዛም ባይነት እና እንቢኝ መሬቴን አልነጠቅም የሚለው የጎንደር ህዝብ ትግል መጨረሻው የሃገሪቱን የትግል የነጻነት ጎራ ሊቀይስ ያሰበ ይመስላል ፣እንደዚህም ሆኖ የሁሉንም ህዝብ አንድነት በጋራ የሚጠይቅ እና በትግሉም አንድ ሆኖ አገር እና ህዝብን የማዳን ስራ ሊሰራ ይገባአዋል ብለው ብዙሃኑ ያምናሉ ።
በዚህም መሰረት በኦሮሞ ንቅናቄ ላይ ለሚመለከተው ሁሉ በጋራ የምንቀሳቀስ ሲሆን የኦሮሞ ተወላጆች ግን በግለኝነት የኦሮሞነትን ነጸብራቅ ይዘው የሚወጡ ከሆነ አላማ እና ሴራቸው ከወያኔ የማይተናነስ አገርን የማጥፋት ስራ ስለሆነ ከዚህ ተቆጥበው ትግሉን በጋራ አንድ በመሆን ፣ለአንድቷ ሃገራችን መታገል ይገባናል ሲሉ የጎንደር ህዝብ ጥያቄ አቅርበዋል ።
ኦነጋዊ ስርአትም ሆነ ወያኔአዊ ስርአት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ስርአት መገንባት ይኖርብናል።
በጎንደር የዐማራ ተጋድሎው ቀጥሏል፤ የኮሎኔሉ ፍርድ ቤት አለመቅረብ መነሻ ምክንያት ሆኗል
• ሁሉም የኮሜቴው አባላት ለነሐሴ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጧቸዋል
• ፖሊስ አስለቃሽ ጪስ እየተጠቀመ ነው

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፍርድ ቤት ቀርበዋል በሚል በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ዐማሮች በሰሜን ጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ረፋዱ ላይ ተሰባሰቡ፡፡ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በሌሉበት ሊመለከተው መሆኑን ያወቁት የጎንደር ሕዝብ ፍርድ ቤቱ ሳይዘጋ ኮሎኔል ከሳሽ ካለውም ይከሰስ ከሌለውም በቶሎ ወደ ቤተሰቦቹ ይመለስ የሚል ጥያቄ በፍርድ ቤቱ አቅራቢያ ጩኸት በረከተ፡፡
የአድማ ብተና ፖሊስ የፍርድ ሒደቱትን ለመከታተል በመጣው የዐማራ ሕዝብ ላይ የኃይል ርምጃ መውሰድ ሲጀምር የወጣቶቹ ቁጣ ገነፈለ፡፡ የፍርድ ቤቱ መስኮቶች በድንጋይ ረጋገፉ፡፡ ወያኔ ሌቫ፤ ወልቃይት ዐማራ… ወዘተ የሚሉ የዐማራ ተጋድሎ ድምጾች በመለዋ የጎንደር ከተማ ከጫፍ ጫፍ ተስተጋባ፡፡ ጎንደር የሚገኘውን የወያኔ ደኅንነት ቢሮ አካባቢ የተጋድሎ ሠልፍ በረከተ፡፡ ፒያሳና መስቀል አደባባይ በአንድ ሳምንት ብቻ ሁለት ጊዜ ዐማሮች ጩኸታቸውን ማሰሚያ መድረክ ሆኑ፡፡
እስከዚህ ሰዓት ድረስ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ ባይኖርም የአድማ ብተና ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ከመጠን በላይ በዐማሮች ላይ እየበተነ ነው፡፡ ከተጋድሎው ተሳታፊዎች መካከል አንድ ሰው ከፍተኛ አደጋ የደረሰ ቢሆንም አሁን ላይ በሙሉ ጤንነት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ኮሎኔል ደመቀ በሌሉበት ጉዳያቸውን እንዲታይ ወስኗል፡፡ ኮሎኔል ደመቀ ከማረሚያ ቤት ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ (ፕላስማ) ለፍርድ ቤቱ ከሳሽ ከቀረበባቸው ይከላከላሉ፤ ካልቀረበም ፍርድ ቤቱ ወሳኔ ይሰጣል የሚል መልስ ቢኖርም የጎንደር ከተማ ሕዝብ አሁንም ተቃውሞውን እያሰማ ነው፡፡
በተያያዘም በማእከላዊ ፍርድ ቤት ያሉት የታፈኑ የወልቃይት ጠገዴ ዐማራ ማንነት ኮሚቴ አስተባባሪዎችም ነሐሴ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ አዲስ አበባ ማእከላዊ ታፍነው የሚገኙት የኮሜቴው አባለት አቶ አታላይ ዛፌ፣ አቶ ጌታቸው አደመ፣ መብራቱ ጌታሁን፣ አቶ አለነ ሻማ፣ አቶ አዲስ ሰረበ እና አቶ ነጋ ባንቲሁን ናቸው፡፡
አዳዲስ ነገሮችን በየሰዓቱ እናቀርባለን፡፡
የዐማራ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!!









Tuesday, August 2, 2016

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በጎንደር የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን ሰጡ

Augest 2,2016
ኢሳት ዜና ፣ — በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢትዮጵያ መንግስት ከስልጣን እንዲወገድ የሚጠይቅ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እሁድ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል ሲሉ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘገቡ። ቢቢሲ እና ኣዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሰልፉን ከዘገቡት ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ነዋሪነታቸው በከተማዋ እና አካባቢዋ የሆነ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የተለያዩ መፈክሮችን በማስተጋባት በሃገሪቱ ኢፍትሃዊነት መንገሱን በተቃውሞ ሲያሰሙ መዋላቸውን አፍሪካ ኒውስ የተሰኘ መጽሄት አስነብቧል። gondar
ተገቢ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል በሃገሪቱ መንገሱን እና የመንግስት አፈናና ቁጥጥር መባባሱን በቁጣ ሲገልጹ የዋሉት ሰልፈኞች ሰልፉ እንዳይካሄድ የተላለፈን ውሳኔ በመጣስ አደባባ መውጣታቸውን መጽሄዱ ሰልፈኞቹን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አመልክቷል።
በመንግስት ላይ ያላቸውን የተለያዩ ተቃውሞዎች የገለጹት የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለ25 አመት በስልጣን ላይ የቆየው የመንግስት ከስልጣን እንዲወገድ ጥያቄ ማቅረባቸውንም አለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በአይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለው ይኸው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆምና የአማራው ክልል ታሪካዊ የድንበር ወሰን እንዲከበር ጥያቄ ማቅረቡንም አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ዘግቧል።
በጎንደር ከተማ ዕሁድ ሲካሄድ የዋለው ይኸው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉና በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ መሆኑንም የዜና አውታሩ በዘገባው አስፍሯል።
የብሪታኒያው የማሰራጫ ኮርፖሬሽን (BBC) በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ባቀረበው ሰፊ ዘገባው አስነብቧል።
በክልሉ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን ያወሳው የዜና አውታሩ፣ በሰልፉ የታደሙ ሰዎች በኦሮሚያ ክልል ያሉ ተመሳሳይ ችግሮችንና በእስር ላይ ተዳርገው የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮችን ጉዳት በማንሳት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ በቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
ኢንዲያን ኤክስፕረስ የተሰኘ የህንድ ጋዜጣ በበኩሉ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ጎንደር ከተማ በአይነቱ ልዩና ታላቅ የሆነ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ዘግቧል።
በተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የታደሙ ነዋሪዎች ከተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች ያሉ በርካታ ሰዎች በእግርና በተሽከርካሪ በመሆን ከዋዜማው ጀምሮ ወደጎንደር ከተማ መግባት መጀመራቸውንንና የተቃውሞ ትዕይንቱን እንደተቀላቀሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
“ወያኔ ከእንግዲህ አይገዛንም” ፣ “ወልቃይት አማራ ነው”፣ “በኦሮሚያ ክልል ያለው ግድያ ይቁም” ፣ “በመብታችን አንደራደርም” የሚሉ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ የነበሩት ሰልፈኞች መንግስት በህዝቡ ላይ የሚያደርገውን አፈና እንዲያበቃ አሳስበዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እሁድ ማለዳ በተለያዩ የከተማዋ ዋና ዋና ስፍራዎች ቀድመው በመገኘት የተቃውሞ ሰልፉን ለማደናቀፍ ጥረት ቢያደርጉም ህዝቡ አካባቢውን በሙሉ ተቆጣጥሮ መዋሉን እማኞች አክለው አስታውቀዋል።

Monday, August 1, 2016

ብአዴን በአማራ ህዝብ ብሶት ላይ ተሳለቀ!!

Augest 1,2016
በአማራነታችን እዬደረሰብን ያለው ግፍ አንገሽግሾን ወደ አደባባይ ወጥተን ድምፃችንን ያሰማንበትን ሰላማዊ ሰልፍ ክልሉን አስተዳድራለሁ የሚለው ብአዴን የሰጠው መልስ ሚሊዬን አማሮችን አስቆጥቷል። የአማራ ህዝብ ሳይወክለው የአማራን ህዝብ እያስተዳደረ ያለው ብአዴን የትናንቱ ሰልፍ ምክንያት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄ ነው ሲል በአማራነት ጥያቄ ላይ ተሳልቋል።
የሰላማዊ ሰልፉ ዋና አላማ በወልቃይት ምድር ላይ በሕወሓት ማንአለብኝነት በአማራነታችን ላይ የተጫነብንን ትግራዊነት ማውገዝ እና አማራነታችን ማፅናት ነው። በተጨማሪም የአማራነት ማንነታቸውን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ያሉ የወልቃይት አማራ ማንነት ጠያቂ ኮሜቴዎቻችን ላይ ህወሓት ያካሄደችውን አፈና መቃወም ነበር የሰላማዊ ሰልፉ አላማ ። በአጠቃላይ የጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ የአማራ ህልውናን የተመለከተ ሰልፍ ነው።በሕወሓት እና በተቀጥላዎቿ አማካኝነት በአማራነታችን እዬደረሰብን ያለውን ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ ለመቃወም እና ለማውገዝ ያደረግነውን ሰላማዊ ሰልፍ አማራን አስተዳድራለሁ የሚለው ብአዴን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው ብሎ መሳለቁ ምን ያህል ለአማራ ህዝብ ባዳ እንደሆነ እና የህወሃት ቅርብ ዘመድ እንደሆነ በግልፅ አይተናል ። በመግለጫው ላይ አንድም ቦታ‪#‎ወልቃይት‬ የምትል ቃል አለመግለፁ ብአዴን መቼውንም የአማራን ህዝብ ጩኸት ሊሰማ የማይችል ድርጅት እንደሆነ በድጋሜ አስመስክሯል።
ስለሆነም ሕዝባችን ድምፁ እስኪሰማ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል። የጎንደር አማራ ድጋሜ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት አስቧል። መላው አማራም ከጎኑ ይሰለፍ ። ሰላማዊ ሰልፉ በጎንደር ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ የአማራ ከተሞች ላይ እንደሚካሄድ የታመነ ነው።
ብአዴን ውስጥ ያላችሁ ትክክለኛ የአማራ ልጆች ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ አበክረን እንመክራለን!!
ድል ለአማራ ህዝብ!!