Tuesday, April 15, 2014

ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝቡ በሚያዝያ 19ኙ ሰልፍ በመውጣት የወቅቱን አሳሳቢ ጉዳይ እንዲናገር ጥሪ አቀረበ

April 15/2014


(ዘ-ሐበሻ) “ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን በመቀጠል የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልሳለን” በሚል ሰማያዊ ፓርቲ ባወጣው መግለጫው ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም በጃንሜዳ በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሕዝቡን ብሶት እናሰማለን አለ።

“ሰማያዊ ፓርቲ በመንግስት የሚፈጽሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች የሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ለመንግስት አካላት በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት እነዚህን ተከታታይ ጥሪዎች ተቀብሎ የማሻሻያ እርምጃ ከመውሰድና ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ ጉዳዩን ችላ በማለት ችግሮቹ የበለጠ እየተባባሱ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡” ያለው መግለጫው “በመሆኑም እነዚህ ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለማድረግ ሠማያዊ ፓርቲ እሁድ ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት የሚቆይ ከፓርቲ ጽ/ቤት እስከ ጃንሜዳ የሚደርስ ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ያዘጋጀ ሲሆን የሠላማዊ ሰልፉን ቀንና ሰዓትም በአዋጅ ቁጥር 031983 መሠረት ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ በማሳወቅ ሰልፉን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡” ብሏል።

“በዚህ ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ላይም ከዚህ ቀደም ተነስተው የነበሩ መንግስት በእምነት ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም፣ ዜጎች ከቀያቸው ማፈናቀሉ እንዲቆምና ዜጎቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ የሚሉ ጥያቄዎች የሚነሱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በገዢው ፓርቲ ስልጣን እንጅ ለህዝብ የማይጨነቁት ተቋማት ስራቸውን በሚገባ ባለመስራታቸው ሕዝብ ለከፈለው ክፍያ አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑም እያገኘ አለመሆኑም የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ ሲሆን በተለይ የውሃ የመብራት የቴሌ ኮሚኒኬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሕዝብን እያመማረረ መሆናቸው በሠላማዊ ሠልፉ ላይ የሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው፡፡” የሚለው ሰማያዊ ፓርቲ “ይህን ታላቅ ሠላማዊ ሠልፍ የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልስ ዘንድ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሲቪክ ማህበራትና ሚዲያው ከሚደረገው ጥረት ጎን መቆም ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጡ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡” በማለት ለዘ-ሐበሻ የላከውን መግለጫ ቋጭቷል።

No comments: