April 23/2014
-ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ሒሳብ አለ
-785 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ወጪ ታይቷል
-ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ላለፉት በርካታ ዓመታት ለፓርላማ ሲያቀርበው እንደቆየው ሁሉ፣ ለብክነት የተጋለጠ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ሀብት መኖሩን ባለፈው ሚያዝያ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ለፓርላማው ይፋ አድርጓል፡፡ ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ሲሰማ የቆየው ፓርላማው ፈጣን ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የአንድ ዓመት ገደብን መስጠት መርጧል፡፡
በዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ምክንያት ሠራተኞችን ለማቆየት መቸገራቸውን የገለጹት የፌደራሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ራሳቸው ጭምር በቡድን መሪነት በተሳተፉበት የ130 የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የ2005 ዓ.ም. በጀት ኦዲት በማድረግ፣ እንዲሁም በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን የስምንት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በማሠራት፣ በአጠቃላይ የ138 መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በመተንተን የኦዲት ግኝቱን ለፓርላማ አቅርበዋል፡፡
ከቀረበው የፋይናንስ ሕጋዊነትን የተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ውስጥ አንድ ቢሊዮን 527 ሚሊዮን ብር ተሰብሳቢ ሒሳብ መኖሩን፣ ሕጋዊ ሥርዓቱን በልተከተለ መንገድ የተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች 785 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን፣ የተፈቀደው በጀት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት ደግሞ 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት መገኘቱን ይፋ አድርገዋል፡፡
ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በወቅቱ ካልተወራረደ ወይም ካልተሰበሰበ በቆየ ቁጥር የመሰብሰብና ወደ ሀብትነት የመለወጥ ዕድሉ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ፣ ኦዲት ከተደረጉት መሥሪያ ቤቶች 77 በሚሆኑት ላይ 877.1 ሚሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ሳይወራረድ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ከያዙት መካከል በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ሥልጠና ማስተባበሪያ 173.6 ሚሊዮን ብር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 149.5 ሚሊዮን ብር፣ የትምህርት ሚኒስቴር 100 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል፡፡
ዋና ኦዲተር የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰቡን ለማጣራት ባካሄደው ኦዲት 32.2 ሚሊዮን ብር ከገቢ ግብር፣ ከቀረጥና ታክስ እንዲሁም ከሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ ደንቦች መሠረት አለመሰብሰቡን አረጋግጧል፡፡
ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጀቶች አግባብ ባለው ሕግና ደንብ መሠረት የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት 326.7 ሚሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ አብዛኛው ይህ ውዝፍ ያልተሰበሰበ ገቢ የሚመለከተው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን እንደሆነ ከኦዲት ሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በጊዜያዊነት ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች የጊዜ ገደባቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የጊዜ ገደቡ በሕግ አግባብ እንዲራዘም ካልተደረገ በስተቀር በዋስትና የተያዘውን ገንዘብ የመውረስ መብት በሕግ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን በጊዜያዊነት ገብተው የመቆያ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ በድምሩ 222.5 ሚሊዮን ብር የዋስትና ገንዘብ አለመሰብሰቡን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
‹‹የሚሰበሰብ ገቢ መንግሥት ለሚያከናውናቸው የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋትና ለአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ሚና የሚኖረው በመሆኑ፣ የመንግሥት ሕግና ደንብ ተከብሮ መሠራት አለበት፤›› ሲሉ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ አሳስበዋል፡፡
ሕጋዊነት የጎደላቸው ወጪዎችን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት 785 ሚሊዮን ብር አግባብነት የጎደላቸው ወጪዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው በ25 መሥሪያ ቤቶች በወጪ ተመዝግቦ ነገር ግን የወጪውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ማስረጃ ሊቀርብበት ያልቻለ 202.6 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡
የግዥ አዋጁን እንዲሁም ደንብና መመርያን ያልተከተሉ ግዥዎችን በተመለከተ ደግሞ፣ 43 መሥሪያ ቤቶች 165.9 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ወጪ አድርገዋል ብለዋል፡፡ ሌሎች 41 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 76 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ክፍያ መፈጸማቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
ሒሳቦች በወጪነት የሚመዘገቡት የሚፈለገው አገልግሎት መገኘቱን ወይም የሚፈለገው ንብረት በአግባቡ በእጅ መግባቱ ሲረጋገጥ ቢሆንም፣ 13 መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቱን ወይም ንብረቱን ሙሉ በሙሉ ሳያገኙ የከፈሉትን የ234.8 ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያ በወጪ መዝገብ ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በመሆኑም የተፈለገው አገልግሎት ወይም ንብረት ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ በተሰብሳቢ መያዝ ይኖርበታል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በ104 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ለተለያዩ ግዥዎች አራት ሚሊዮን 471 ሺሕ ብር ያላግባብ በብልጫ መከፈሉን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም በአሥር መሥሪያ ቤቶች የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልቀረበለት 22.6 ሚሊዮን ብር ወጪ መኖሩን፣ በሌሎች ሰባት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር ቀረጥ የተከፈለባቸው ንብረቶች ገቢ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ቀረጥ ተከፍሎባቸው ንብረቶቹ ገቢ ለመሆናቸው ለማረጋገጥ ካልተቻለባቸው መሥሪያ ቤቶች ትልቁን ድርሻ የያዘው፣ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ሲሆን፣ በቀጣይነት ደግሞ ጤና ጥበቃና ትምህርት ሚኒስቴር ተጠቅሰዋል፡፡
በ23 መሥሪያ ቤቶች የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ 90.9 ሚሊዮን ብር መኖሩን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የፌደራል መንግሥት ግዥ አፈጻጸም መመርያ በግንባታ ቦታ ላይ ላሉ ዕቃዎች፣ ወይም ግንባታ ላይ ላልዋሉ ክፍያ መፈጸምን የሚከለክል ቢሆንም፣ 11 መሥሪያ ቤቶች ይህንን በመጣስ 168.6 ሚሊዮን ብር መክፍላቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ መንግሥት የግንባታ ዕቃዎችን በብድር ሲያገኝ የተገኘው ቁስ መጠን ተሰልቶ ከግንባታ ወጪ ላይ መቀነስ የሚገባው ቢሆንም፣ አራት መሥሪያ ቤቶች ግን 18.3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ በብድር የተገኙ የግንባታ ዕቃዎች ወጪን ሳይቀንሱና ለመንግሥት ካዝና ሳያስገቡ በኦዲቱ ተገኝተዋል፡፡
የተፈቀደላቸውን በጀት በትክክል ለሥራ አውለዋል ወይ የሚለውን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት ደግሞ፣ በ96 መሥሪያ ቤቶች 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል፡፡ ይህ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት የነበረ ቢሆንም፣ የፓርላማው አባላት በቁጭትና በእልህ እንዳለፈው ዓመት ሲናገሩ አልተስተዋሉም፡፡
ብቸኛው የፓርላማ የግል ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የኦዲት ሪፖርቱን አስመልክተው፣ ‹‹በዚህ አገር ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም የሚሉ ባለሥልጣናት ያሉ ይመስለኛል፡፡ እርስዎ እንደዚያ ያስባሉ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ዋና ኦዲተሩን አቶ ገመቹ ዱቢሶን ጠይቀዋል፡፡
አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ምላሽ፣ እንዲዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ፣ ነገር ግን ችግር መኖሩን እያወቁ የማያስተካክሉ ኃላፊዎች መኖራቸውን፣ አንዳንድ ጊዜ በሒሳብ ባሙያዎች የሚታለሉ ኃላፊዎች እንዳሉ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
መደረግ የሚገባውን በተመለከተ በዶ/ር አሸብር ለተነሳው ጥያቄ ዋና ኦዲተሩ የሰጡት ምላሽ በዋና ኦዲተርና በአፈ ጉባዔው መካከል በተደረገ ስምምነት በ2006 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት ላይ የሚገኙ የኦዲት ግኝቶች እስካሁን በነበረው ግዝፈት የሚቀጥሉ ወይም የማይሻሻሉ ከሆነ፣ ሕጋዊ ቅጣት በመሥሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎች ላይ ለመውሰድ ስምምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፓርላማው ቋሚ ከኮሚቴዎች የሚከታተሏቸውን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በይበልጥ መጠየቅ እንደሚገባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. የ2006 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ለማቅረብ በፓርላማው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ጥያቄ ይቀርብላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
No comments:
Post a Comment