Friday, April 11, 2014

ሒላሪ ክሊንተን ጫማ ተወረወረባቸው

April 11/2014

clinton


በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ እየተባሉ የሚጠበቁት ሒላሪ ክሊንተን ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ጫማ ተወረወረባቸው፡፡ ጉዳት ባይደርስባቸውም ዜናው ግን የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቧል፡፡
አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን በላስ ቬጋስ በተጠራ የመልሶ መጠቀም ኢንዱስትሪዎች (Scrap Recycling Industries) ስብሰባ ላይ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ ከአዳራሹ ጫማ ተወርውሮባቸዋል፡፡
ጫማው ሳይመታቸው ቢቀርም ወርዋሪዋ ግለሰብ አስተካክላ ብትወረውር ግን ክፉኛ ጉዳት ልታደርስባቸው ትችል እንደነበር የቪዲዮው ምስል ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አዳራሹ ጨለምለም ያለ በመሆኑ ክሊንተን ጫማው ከተወረወረ በኋላ ነው ያስተዋሉትና ደበቅ ለማለት የሞከሩት፡፡
ሒላሪ ክሊንተን በጉዳዩ ላይ ቀልድ በማከል አስተያየት የሰጡበት ቢሆንም የስብሰባው ኃላፊዎች ግን ታላቅ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ጫማ ወርዋሪዋ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የዋለች ከመሆኗ በላይ ማንነቷ ገና አልተገለጸም፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ሚስት ሒላሪ ከፍተኛውን የፖለቲካ ሥልጣን ለመቆናጠጥ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በነበሩበት አራት ዓመታት ያከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ደጋፊዎቻቸው ቢጠቀሱም የጋዳፊ ግድያ ከዚያም ጋር ተያይዞ የተከሰተው የቤንጋዚው ቀውስ እና የአሜሪካው አምባሳደር መገደል፣ በግብጽ የተካሄደው ለውጥና ከዚያም በአሜሪካና ምዕራባውያን ግፊት ለውጡ መቀልበሱ፣ በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን ላይ የወሰዱት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በአፍሪካ እንደነ መለስ ካሉ አምባገነኖች ጋር በመሞዳሞድ ግብረሰዶማዊነት እንዲስፋፋ አሜሪካ የተከተለችው ፖሊሲ፣ ወዘተ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሒላሪ ኪሊንተን በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚ/ርነት ዘመናቸው ስላከናወኑት የሚያወሳ “የሚኒስትር ማስታወሻ” በገበያ ላይ ያውላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
የዛሬ ስድስት ዓመት አካባቢ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በኢራቅ ከጠ/ሚ/ር ኑሪ አልማላቂ ጋር ንግግር ሲያደርጉ አገሩ በአሜሪካ ወራሪነት መፍረሷ ያናደደው ኢራቃዊ ጋዜጠኛ የጫማ ሚሳኤል ወርውሮባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

No comments: