Friday, July 10, 2015

የሰሜን ግንባር እየታመሰ ነው!

July 10,2015
(ኢ.ኤም.ኤፍ) የግንቦት ሰባት አርበኛ ጦር በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የጦር እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ በህላ፤ በሰሜን ግንባር የትርምስ ዜናዎች ደርሰውናል። ከዚህ በታች አርበኞች ግንቦት 7 ህዝብ ግንኙነት ያገኘውን መረጃ ዋና ዋናዎቹን እናቀርብላችኋለን።
የአርበኞች ግስጋሴ
የአርበኞች ግስጋሴ
የዳባት ፖሊሶች ታስረዋል
በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት ውስጥ የከረረ ተቃውሞ በፖሊስ አባላቱ በመነሳቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች መታሰራቸው ተሰማ፡፡
ቅዳሜ ዕለት ሰኔ 27 2007 ዓ.ም ዳባት ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የከረረ ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን ተቃውሞውን ተከትሎ የበርካታ ፖሊስ አባላት እስር እና ከአካባቢው መሰወር ተከስቷል፡፡
በስብሰባው ላይ የተነሳው ተቃውሞ ዋነኛ ምክንያትና ሰበብ የፖሊስ ፅ/ቤቱ ዋና ኃላፊ ሆኖ የተሾመው ሰው ከትግራይ ክልል የመጣ የህወሓት አባል መሆኑ ነው፡፡
በስብሰባው ላይ ጠንካራ የተቃውሞ ድምፃቸውን ካሰሙት የዳባት ፖሊስ አባላት መካከል ካሳው ማሞ እና ሰጡ እጥናፉ የተባሉት ይገኙበታል፡፡ ካሳው ማሞ እና ሰጡ አጥናፉ “ተጠሪነታችን ለአማራ ህዝብ ሆኖ እያለ ለምን በህወሓት አባል እንመራለን? ተጠሪነታችን ለትግራይ ክልል ፖሊስ ሆኖ ከሆነ የተቋሙን ስም ቀይሩት፤ አለበለዚያ ከስራ አሰናብቱን… ዘረኝነት ይቁም…” በማለት ተናግረዋል፡፡
ከስብሰባው በኋላ ካሳው ማሞንና ሰጡ አጥናፉን ጨምሮ በስብሰባው ላይ የዘረኝነት አገዛዝ ተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙ በርካታ የዳባት ፖሊስ አባላት እግረ ሙቅ እያጠለቁ ወደ ዘብጥያ ወርደዋል፡፡ ሦስት ፖሊሶች ደግሞ ድንገት ከአካባቢው የተሰወሩ ሲሆን በህወሓት ይታፈኑ ወይንም አምፀው ወደጫካ ይውጡ እስካሁን ምንም የታወቀ ነገር የለም፡
በህወሓቶች ቤት ውስጥ ታላቅ ሽብር ነግሷል
ከወልቃይቱ /ቃፍታ መሲን፣ ኮርጃሙስ፣ ማይ ሰገን፣ በዋል፣ ንኳል ሳግላ እና ማይ እምቧ…/ የአርበኞች ግንቦት 7 ወታደራዊ እርምጃ በኋላ ማለስልጣናቱ እንደተነፈሰ ፊኛ በመልፈስፈስ ኩምትርትር ጭምትርትር ብለዋል፡፡
የጦርነት ደመና ካጠላበት የኢትዮጵያ ጠቁር ሰማይ ስር በፍርሃት ተሸብበው የሚገኙት የህወሃት ባለስልጣናት እና ጀነራሎች የጨነቃቸውን ያክል ሰራዊቱን ወዲያ ወዲህ በማተራመስና በማንጓለል በድሃ ልጅ ዥዋዥዌ በመጫዎት ላይ ናቸው፡፡ ኤታማጆር ሹሙ “ጀነራል” ሳሞራ የኑስ ሰራዊቱ ኋላቀር እንደሆነ ህወሓቶች ባደረጉት ምስጢራዊ ስብሰባ ላይ አምኗል፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ ከወራት በፊት ግን አገሪቱ በወታደራዊ አቅሟ ከዓለም አገሮች ጋር ተወዳድራ ከዓለም በ46ኛ ከአፍሪካ ደግሞ በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለው ያን የተለመደ የፕሮፖካንዳ ቱልቱላቸውን ነፍተው ነበር፡፡
አሁን ኋላቀር በማለት ያጣጣሉትን ለእርድ የተዘጋጀ ሰራዊት በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት እየበተኑት ይገኛሉ፡፡ የሰሞኑ ወደ ሰሜን የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ ትናንት ጠዋት ከአዋሳ በሀገረ ማርያም በኩል ወደ ሞያሌ እና ሌሎች ጠረፎች አካባቢ በርካታ ሜካናይዝድና እና እግረኛ ጦር እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፌደራል ፖሊስ ተጭኖ ተልኳል፡፡
የኦነግ ጎሬላ ተዋጊዎች፡
የሀገረ ማርያም ዓይን እማኞች 26 አሮጌ ታንኮች በሚንገራገጭ ድምፃቸው አካባቢውን በማወክ እንደ ኤሊ እያዘገሙ ሲያልፉ መቁጠራቸውን ለዜና ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ ወደ ዚህ አካባቢ ጦር በገፍ እየተጫነ የሚገኘው የኦነግ ጎሬላ ተዋጊዎች ጥቃት ለመክፈት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚያረጋግጥ መረጃ ስለደረሳቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
ከአፋር ነፃ አውጭዎቹ አርዱፍና ጋዲሌ ጋር በመቀናጀት ኦብነግ በአፋር ክልል ሰርጎ እንደገባ የሚያመላክት መረጃም ጭምር ስለደረሳቸው ወደ አፋር ክልልም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር እያጓጓዙ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ መተራመስና መታመስ ጋር ተያይዞ ጦር እየመሩ በየማዕዘናቱ በሚላኩት ወታደራዊ አዛዦችና የበላይ አለቆቻቸው መካከል የተካረረ ፀብ እየተፈጠረ መሆኑን ከመከላከያ ምንጮቻችን የደረሰን መረጃ ያረጋግጣል፡፡ የፀቡ መንስኤ እያንዳንዱ አዝማች “የተመደበልኝ የሰው ሃይል እንዲሁም ትጥቅና ስንቅ ያንሰኛል…” የሚል ሰበብ ማንሳቱ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም የሚያመላክተው የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች ወኔያቸውን መሽናታቸውን ነው፡፡
አፈናው ቀጥሏል
በሌላ በኩል ደግሞ የህወሓት ዘረኛ ቡድን ሰራዊት ከማተራመሱ ጎን ለጎን ህዝብ በገፍ እያፈነ ወዳልታወቀ ቦታ ይዞ መሰወሩን በርትቶበታል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር ጎንደር… በርካታ ሰዎች በታጠቁ ኃይሎች እየታፈኑ ወዳልታወቀ ቦታ በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የነበረውና ጎንደር መምህራን ኮሌጅ ውስጥ የሚያስተምረው መምህር አለላቸው አታለለ ትናንት ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ የህወሓት የታጠቁ ቡድኖች ወደ መኖሪያ ቤቱ ገብተው አፍነው ወስደውታል፡፡ መምህሩ እስካሁን ድረስ የት እንዳለ አይታወቅም፡፡
በተጨማሪም የጎንደር እና አካባቢውን ገበሬዎች የህወሓት ካድሬዎች ዋጋውን መቶ በመቶ ቅድሚያ ካልከፈላችሁ በማለት ማዳበሪያ እንዳይወስዱ ከልክለዋቸዋል፡፡ ገበሬው የባሰውኑ በህወሃት ልቡ ሻክሯል…

No comments: