Thursday, July 27, 2017

በሙስና ከታሰሩ ባለስልጣናት መካከል የተወሰኑት ስም ዝርዝር ታወቀ | ይዘነዋል

July 27,2017

በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበውና ዜና አቅራቢው ፋኑኤል ክንፉ እንዳጠናቀረው  በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 34 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባለሀብቶችና ደላሎች፤ በትላንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢፌዴሪ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታወቀ::
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ 34 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኃላፊዎቹ ተጠርጥረው የተያዙት “በፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግና በፌደራልና አዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በተደረገ የማጣራት ስራ የሙስና ተግባር ውስጥ ተሳትፈው በመገኘታቸው መንግስት ሙስናን ለመከላከል በያዘው ቁርጠኛ አቋም ነው፤” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል::
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ  ኃላፊዎች ከተገኙባቸው የመንግስት  ተቋማት መካከል፤ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ጋር ይገኙበታል፡፡
የሰንደቅ ምንጮች እንደገለጽት፣ በስኳር ኮርፖሬሽ በኩል ተጠርጥረው ከተያዙ መካከል  የቀድሞው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አበበ ተስፋዬ እና የቀድሞው የተንዳሆ የፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ድምፁ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ እንዲሁም፣ አቶ በኃይሉ ገበየሁ የኮርፖሬሽኑ ንብረት አስተዳደር ዳሬክተር እና አቶ ኤፍሬም አለማየሁ የቀድሞ የኮርፖሬሽኑ፣ ግዢና ንብረት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዳሬክተር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ግዢ ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ግርማ፤ እንዲሁም ወ/ሮ ሠናይት ወርቁ እና አቶ ኃየሎም ከበደ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ታውቋል፡፡
አንድ የቀድሞ ሚኒስትር እና አንድ ሚኒስትር ዴኤታም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮቻች የጠቆሙን ቢሆንም፣ ከሚመለከታቸው አካላት ለማረጋገጥ አልቻልንም፡

Sunday, July 23, 2017

የግብሩ አመጽ – የፍጻሜው ጦርነት

July 23,2017
ክንፉ አሰፋ
የአስቸኳይ (የአፈና) ግዜ  አዋጁ ገና አልተነሳም። በአዲሱ የግብር ትመና ሳብያ ከዳር እስከዳር የተነሳው ሕዝባዊ አድማ እና አመጽ ግን አዋጁን ውድቅ ያደረገው ይመስላል። አንድ ስርዓት ራሱ ያወጣው ህግ በህዝብ ሲሻርበት - ያኔ ነው ያበቃለት!
        ከቶውን "የአለምን  ኢኮኖሚ እየመራች ያለች ሃገር" የበጀት ሸክሟን ለምን በህዝብ ላይ መጣል እንዳለባት ግልጽ አልሆነም። እውነታው ከነዚህ ሁለት እይታዎች ውጭ አይሆንም።  ይነፋ የነበረው የእድገት ቀረርቶ እና ይነገር የነበር ሁለት ዲጅት እድገት ቁጥር ሁሉ ውሸት ነበር፣  ወይንም ደግሞ የሃገሪቱ ሃብት በጥቂቶች እየተዘረፈ ነው።
        ጆሮን ያሰለቸው የ"እድገት እና ትራንስፎርሜሽኑ" ዘፈን ቀዝቀዝ ማለት ሲጀምር የ "ደብል ድጅቱ" የፈጠራ ተረት እንደ በረዶ እየነጻ መሄዱ አልቀረም። እድገቱ የህዝቡን  ህይወት አልለወጠም። ተጀምሮ ከሚቋረጥ ህንጻ እና መንገድ ውጭ ትራንስፎርሜሽኑም በተግባር አልታየም።  ይልቁንም ተሸፍኖ የነበረው ችግር አሁን ፈጥጦ ወጥቶ በህዝብ ጫንቃ ላይ ጉብ ሊል ዳዳው፣ ገበሬውን መሬት በመንጠቅ፣ ነጋዴው ላይ ደግሞ ሚዛናዊ ባልሆነ የገቢ ግምት - ከፍተኛ ግብር በመጫን።   ምላሹንም እንደምናየው ነው።  አድማ፡ ህዝባዊ አመጽ፣... ተቃውሞ!
        በዘንድሮው የበጀት አመት የህወሃት መንግስት 320 ቢሊዮን ብር ማጽደቁን አብስሮን ነበር።  ይህ በጀት የ100 ቢሊዮን ብር  (1/3ኛ) የበጀት ጉድልት ነበረበት። ይህ የ100 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ከብድር እና እርዳታ ይሸፈናል ተብሎ  ነበር የተጠበቀው። የ11 በመቶው እድገት ተረት - ተረት  ውስጥ የእርዳታው እና የብድሩ መጠን ተገልጾ አያውቅም። ሃገሪቱ በደፈናው እያደገች ነው አሉን። በፈጣን እድገት የአለምን ኢኮኖሚ የምትመራ ሃገር ተባለ።  ፈረንጆቹም አመኑ።
        እርዳታን  እንደ ስትራቴጂ የቀመሩት የህወሃት ጠበብቶች፣ ፈረንጆች ፊታቸውን ማዞር እንደማይሳናቸው እንኳን አላሰቡትም። በሶማሊያ ውስጥ የነሱን ቆሻሻ ጦርነት ስለተረከቡ ብቻ ጉዳዩን እንደ ይገባኛል መብት (for granted) አዩት። የሶማልያ ጉዳይ፣ የአልሻባብ ፖለቲካ ዲስኩር፣ የጸረ-ሽብር እንቶፈንቶ አሁን የለም። አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት ዜጎችን በአዋጅ እና በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አፍኖ የያዘው ስርዓት ጋር በረጅሙ እንደማይዘልቁ ግልጽ ነው። ታዲያ ከቻይናው የእድሜ-ልክ የእዳ ቁልል ውጭ የታሰበው የውጭ ገቢ ጠፋ። ማጠፍያው አጠረ። ለሰራዊቱና ለደህንነቱም ደሞዝ መከፈል አለበት።  ...ቀሪው ገንዘብ ከግብር እና ከሃገር ውስጥ የሚሰበሰብ ገንዘብ ብቻ ነው።
        እናም እዳው ሕዝብ  ላይ ተቆለለ። የቀን ገቢ በግምት እየታየ ተጫነ። በገቢና ወጪ ሳይሆን፣  በህዝብ ላይ በግምት ግብር ሲጫን በታሪክ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም። አዲሱ የግብር ትመና በንግዱ ህብረተሰብድ ከባድ ቁጣ ቀስቅሷል። ከጫፍ እስከጫፍ የተነሳው የሥራ ማቆም አድማ የት ላይ እንደሚቆም አይታወቅም። በአስቸኳይ ግዜ በምትተዳደር ሃገር የተነሳው ይህ አድማ ቀድሞ የተጀመረው የመብት እና የነጻነት ትግል ቅጣይ ይመስላል። ቀድሞ የተነሳው የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።  የህወሃት የአፈና ሰንሰለትም እንደቀጠለ ነው። ዛሬ ነጋዴው ህብረተሰብ የሰለባው ባለሳምንት ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሰረታዊ ችግር ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የግብር ፖሊሲ አይደለም። ችግሩ ስርዓቱ ራሱ ነው። ዛሬ የንግድ ቤቶች ቢዘጉ ሌላ የንግድ ቤቶችን የመክፈት አቅም ያላቸው የህወሃት ሰዎች በደስታ መፈንጠዛቸው አይቀርም። ...አሜካላው ሳይነሳ መፍትሄ አይታሰብም።
        ዋናው ነገር ወዲህ ነው። ግብር ለመክፈልም እኮ የህዝብ ውክልና ያለው ስርዓት መኖር ግድ ይላል። የሀዝቡን ይሁንታ ያላገኘ መንግስት፣ በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ግብር የማስከፈል መብት የለውም፣ ሕዝቡም ላልወከለው መንግስት ግብር ለመክፈል አይገደድም።    
        እ.ኤ.አ. በ1750ቹ እና 1760ቹ አስራ ሶስቱ የአሜሪካ ቅኝ ግዛቶች ይዘውት የተነሱት መፈክርን ያስተውሏል። "No Taxation Without Representation" ይላል። "ውክልና ከሌለ ግብር አይኖርም" እንደማለት ነው።  አሜሪካኖች በዚያ የነጻነት ትግላቸው ወቅት አቋማቸውን ለመግለጽ የተጠቀሙበት መሪ ቃል ነበር።  አመሪካውያኑ ይህንን መፈክር ይዘው በማመጽ የብሪትሽን ኤምፓየር እንዳናፈጡት የታሪክ ማህደር ያወሳናል።
         ህወሃት የህዝብ ይሁንታም የለው፣ መረጃም የለው። ሃይለማርያም ደሳለኝ በብሄራዊ ቴሌቭዥን ለይ ወጥተው እንዲህ አሉ። ስራችንን የምንሰራው፣ ውሳኔም የምንወስነው መረጃ ሳንይዝ እንዲሁ በግምት ነው። "መረጃ የሚጠናከርበት ስርዓት የለም።" አሉ።  እኚህ ሰው አንዳንዴ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ  እውነትን ይለቁልናል። ንግግራቸው እኝህ ሰው ነጻ ያለመሆናቸውን ይጠቁመናል።   ሃገሪቱ ነጻ መውጣት ካለባት በመጀመርያ ነጻነትን ማወጅ ያለበቸው እሳቸው ናቸው። እውነት ነው።  ህወሃት እየመራ ያለው በግምት እና በጥይት ነው።
        የሃይለማርያም ንግግር አጉልቶ የሚያሳየን ነገር አለ። ስርዓቱ ችግር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን፣ ስርዓቱ ራሱ ችግር መሆኑን ግልጽ ያደርግልናል።
        ትግራይ "ክልል" ፕሬዝዳንት እና የመቐሌ ከንቲባ ላይ ከሰሞኑ የተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ የሚሰብቀን ነገር ይኖራል። ከሰሞኑ በመቀሌ ስታድዮም የገባው ህዝብ በዝግጅቱላይ በተገኙ የህወሓት አመራሮችን "ሌባ ሌባ ሌባ .. ሃሳዊ (ውሸታም) መሲህ ሲሉ ተደምጠዋል። እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ራሱ ተወክያለው ያለውን አመራር "ሌባ ሌባ " ካለ ምን ቀረ?... እንደኔ ግምት የቀረ የለም። ሃገር እየተመራች ያለችው መረጃ በሌላቸው፣ ራዕይ በሌላቸውና የህዝብ ይሁንታ ባላገኙ ሌቦች ነው።
        ከትግራይ ውጭ ያለውም ሕዝብ እንዲህ ነው የሚለው። "ወያኔ ሌባ ነው! ለሌባ ግብር አንከፍልም!"  
        "ኢትዮጵያንና ህዝቧን በጉልበት አፍኖ ለያዘ ዘራፊ ቡድን አንገብርም!!" ብለዋል ጊንጪዎች። ይህ የግብር አመጽ የፍጻሜው ጦርነት ይሆን? እድሜ ከሰጠን እናየዋለን።
        ለዛሬ በዚህ ላብቃ በመጪው ጽሁፌ ስለ "ኳስ እና ፖለቲካ" የምለው አለኝ።

Saturday, July 22, 2017

በአዲስ አበባ ሳሪስ፣ ኮልፌ፣ ቡራዩ፣ ደምቢዶሎ፣ ነጆ፣ ነቀምቴ በሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው | ወደ ሰሜን ለሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ማስጠንቀቂያ ተላለፈ!!

July 22,2017

( ዘ - ሐበሻ) ሕወሓት መራሹ መንግስት የጣለውን አግባብ ያልሆነ ግብር በመቃወም የተጀመረው የሥራ ማቆም አድማ በተለያዩ ቦታዎች እየተስፋፋ ነው:: በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሳሪስ እና ኮልፌ አካባቢ ንግድ ሱቆች መዘጋጋታቸው ታውቋል::
ሳሪስ ሙሉ በሙሉ ዝግ ስትሆን በኮልፌ አካባቢ ግን አንዳንድ ነጋዴዎች የመንግስትን ማስፈራሪያ ተቀብለው መክፈታቸው ተሰምቷል:: ለነዚህ ሱቃቸውን በመክፈት መንግስትን ለተባበሩት ነጋዴዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ እንደተላለፈላቸው ለማወቅ ተችሏል::
በደምቢዶሎ ከተማ ትንስፖርት ቆሞ ሱቆች ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይባት ቡራዩ ከተማም ዛሬ ጭር ብላ መዋሏን የአካባቢው የህቡዕ ታጋዮች በፎቶ ግራፍና ቭድዮ አስታከው ከላኩት መረጃ ሌረዳት ተችሏል::
ነጆ ከተማም እንዲሁ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ዘጋግተው ቤት ቁጭ ያለ ሲሆን የመንግስት ኃይሎች ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉባቸው እንደሆነ ከሥፍራው የተገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል::
በሌላ በኩል በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በሰነበተችው ነቀምቴ ከተማ መንግስት የባጃጅ ሹፌሮችን ስራ አስፈትቶ ሥብሰባ እንዲቀመጡ ማድረጉ ታውቋል::
በሕዝባዊ እምቢተኝነቱ የቀጠለችው ነቀምቴ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴዋ እጅጉን መዳከሙን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት የባጃጅ ሹፌሮችን በስብሰባ ላይ የማትገኙ ከሆነ ታርጋችሁን እቀማለሁ በሚል አስፈራርቶ እንደሰበሰባቸውና በታክስ ስም ፕሮፓጋንዳውን እያስተማራቸው መሆኑን ከስፍራው የተገኘው ዜና ይገልጻል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚጓጓዙ መኪኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ት ዕዛዝ ተላለፈ:: በሕቡዕ ጉዳዩን እያደራጁ የሚገኙት ወጣቶች (ቄሮዎች) ያሰራጩት ማስጠንቀቂያ እንደሚከተለው ቀርቧል::
“ማስጠንቀቂያ… ማስጠንቂያ… ዛሬ በሱልታ፣ በጫንጮ፣ በጎርፎ፣ በዱበር፣ በሙከ ጡሪ፣ በደብረ ፅጌ፣ በፊቼና በገርባ ጉራቸው ከተሞች ውስጥ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ለ3 ተከታታይ ቀናት የማቆም አድማ ይደረጋል። ሱቆች፣ሆቴሎችና የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች በሙሉ ተዘግተው ይውላሉ። በመሆኑም ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልልና ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ይቋረጣሉ። ይህን ህዝባዊ ጥሪ አልፎ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርግ አካል ካለ ለሚወሰድበት እርምጃ ተጠያቂ ራሱ ይሆናል።”
ወጣቶች (ቄሮዎች) ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ

Saturday, July 15, 2017

የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት አጥረው ባስቀመጡ ኤምባሲዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ መቸገሩ ተገለጸ

July 15,2017
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ መሬት አጥረው ባስቀመጡ የተለያዩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መቸገሩን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡ በከተማዋ ለረዥም ጊዜ መሬት አጥረው ካስቀመጡ አካላት መካከል፣ የውጭ ሀገር ኤምባሲዎች፣ የሼህ ሁሰይን አሊ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ፣ የመንግስት ተቋማት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እነዚህ አካላት የከተማዋን አንድ ሶስተኛ ሊያክል ምንም ያልቀረው መሬት በመውረር ያለ ምንም ስራ አጥረው አስቀምጠዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብለት የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አሁንም ምንም ዐይነት እርምጃ አለመውሰዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ መሬት አጥረው ከያዙ አካላት ጋር ለውይይት ተቀምጦ እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወቃል፡፡ ሆኖም መረጃዎች እንደጠቆሙት ከሆነ፣ በወቅቱ የተደረገው ውይይት ምንም ዓይነት ውጤት አላመጣም፡፡ በዚህም የተነሳ ስማቸው የተጠቀሱት አካላት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የከተማዋን መሬት እንደወረሩ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ሳምንት ስብሰባውን ያካሔደው የከተማዋ አስተዳደር፣ በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዳደረገ ቢገለጽም፣ መሬት አጥረው የያዙ አካላትን በተመለከተ የረባ ሪፖርት አላቀረበም፡፡
አስተዳደሩ ሰፋፊ መሬት አጥረው ከያዙ ኤምባሲዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ይልቅ በትናንሽ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጸው፡፡ ለረዥም ጊዜ መሬት አጥረው ለያዙት ኤምባሰዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ግን ወደ ስራ እንዲገቡ በድጋሚ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ብቻ ተሰጥቷቸው ታልፈዋል፡፡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው ሲባል ይህ ለበርካታ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ህጋዊ ባለ ይዞታ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ድንገት ተነስቶ በማፈናቀል እና ቤት በማፍረስ የሚታወቀው የከተማዋ አስተዳደር፣ ኤምባሲዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ አቅም እንደሚያጥረው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ 

በከተማዋ 138 አካላት 150 ሄክታር መሬት አጥረው የያዙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚወስዱት የውጭ ኤምባሲዎች፣ ሚድሮክ ኢትዮጵያ እና የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡ ሆኖ,ም አስተዳደሩ እርምጃ ወሰድኩኝ ያለው ግንባታ ባልጀመሩ ትናንሽ ባለሀብቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ13 ባለይዞታዎች ላይ ክሰ መሰረትኩኝ ያለው የድሪባ ኩማ አስተዳደር፣ ከ43 ባለሀብቶች ጋር ደግሞ ያለውን ውል በማቋረጥ መሬታቸውን መንጠቁን አስታውቋል፡፡

Source: BBN News July 13, 2017

Thursday, July 13, 2017

አምቦ ውጥረት ላይ ትገኛለች ነጋዴው ህብረተሰብ ጩኸቱን እያሰማ ነው

July 13, 2017
የአዲስ አበባ የግብር መክፈያ ቦታዎችም በአቤቱታ አቅራቢዎች እየተጨናነቁ ነው
የእለታዊ ገቢ ግብር አሰራርን በመቃወም በአምቦ ከተማ ዛሬ ተቃውሞ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ አንድ የፌደራል ፖሊስ መኪና ሲቃጠል ፣ አንድ አውቶቡስና ሌሎች የመስሪያ ቤት መኪኖችም ተሰባብረዋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ 11 ሰአት ድረስ በከተማዋ ተኩስ ይሰማ ነበር። ወደ ወለጋ የሚወስደው መንገድም በድንጋይ ተዘጋግቷል። በከተማዋ ያሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የንግድ ቤቶችም ተዘግተዋል። 
በአዲስ አበባ ደግሞ የግብር መክፈያ ቤቶች በአቤቱታ አቅራቢዎች ተጨናንቀው ታይተዋል። የወያኔ ህወሃት መንግስት በነጋዴው ህብረተሰብ ላይ የጣለው የግብር ጫና ነጋዴው ከሚሰራው ሁለት እጥፍ በላይ ከመሆኑ ባሻገር ምንም ጥናትን የያዘ እን የነጋዴ ማህበረሰቡን ገቢ ያላገናዘበ መሆኑን ነጋዴዎች ይገልጣሉ ። የተለያዩ የመረጃ ማእከሎችም ከስፍራው እንደገለጹ በአዲስ አበባም ሆነ አምቦ አለበለዚያም በሌላ ክልሎች ከፍተኛ ውጥረት መነሳቱ፣ የሃገሪቱን መንግስት ቢያስጨንቅም ጠንካራ እና ለሃገር እና ለህዝብ የሚያስብ አማራጭ የፖለቲካ ባለመኖሩ ህዝቡን ይበልጥ ከኪሳራ ውስጥ ጥⶀል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
በየወረዳው የሚገኙ ጽ/ቤቶች በአቤቱታ አቅራቢዎች በመጨናነቃቸው ፣ ባለስልጣናቱ “የምትችሉትን ክፈሉና ሌላውን ቀስ ብላችሁ ትከፍላላችሁ” በማለት ለማረጋጋት ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል። ነጋዴዎች ግን በባለስልጣኖች በኩል የሚሰጠውን መልስ የሚቀበሉት አልሆነም።
በዲላ ነጋዴዎች ግብር አንከፍልም በማለት በአንድ ድምጽ እየተናገሩ ሲሆን፣ ድምጻቸውን ለማሰማት የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት የሚያደርጉትን ሙከራ ከንቲባው ለማጨናገፍ እየተሯሯጠ መሆኑን ወኪላችን ገልጿል።