Tuesday, February 20, 2018

ለሕዝብ ፍላጎት መታዘዝ ያስከብራል!

February 20,2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው ከመሰማቱ በፊት  በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ፖለቲከኞች ተፈተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲደረግ በማሰብ ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸው፣ አገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ችግር ያመለክታል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ ከፊቱ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ተደቅነውበታል፡፡ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁሉንም ወገኖች በሚያግባባ ሰው መተካትና የተሻለ ምኅዳር መፍጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እንደካሁን ቀደሙ በነበረው ሁኔታ የሚያስቀጥል አምጥቶ ቀውሱን ማባባስ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ካለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ ጀምሮ አልበርድ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ እልባት የሚፈልግለት ከሆነ፣ በመጀመርያ በውስጡ የሚታየውን ሽኩቻ በማቆም ለሕዝብ ፍላጎት ራሱን ማስገዛት አለበት፡፡ ለአገር የሚያስብ ማንኛውም ኃይል በዚህ ወቅት ለሕዝብ ፍላጎት መንበርከክ ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ ሁኔታ እያደር ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነና አሳሳቢ ችግሮች ተጋርጠው፣ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ገብቶ ሒሳብ ለማወራረድ መሞከር የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ይከተዋል፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች አገርን ከቀውስ ለመታደግ ሲሉ በዚህ ቀውጢ ጊዜ በአንድነት ቢቆሙ ይበጃል፡፡ ሰላማዊና ሥልጡን የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣው በመተናነቅ ሳይሆን፣ ለሕዝብ በሚበጅ ሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡
አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣውና ብዙዎችን የሚያስማማው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ነው፡፡ ይህ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ደግሞ ኢሕአዴግን ጨምሮ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚገናኙበት ሁሉን አካታች መድረክ ሲፈጠር ነው፡፡ ይህ መድረክ እንዲፈጠር የተለያዩ ተግባራት መከናወን ሲኖርባቸው፣ ከምንም ነገር በላይ ከትርምስና ከውድመት የፀዳ ከባቢ መፈጠር አለበት፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለሌለ በመተማመን መንፈስ አገሪቱን ከገባችበት አረንቋ ማውጣትና የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት ምኅዳር ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ በመሆኑ፣ ሕግና ሥርዓትን ሳያዛንፉ መነጋገርና መደራደር የሚቻል ከሆነ ሥጋት ወደ ተስፋ ይለወጣል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ዕርምጃ መውሰድ እያቃተው፣ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ተጨናግፈዋል፡፡ አገሪቱ እዚህ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከመውደቋ በፊትም ሆነ በተከታታይ ባጋጠሙ አስከፊ ችግሮች ምክንያት፣ የሕዝብን ፍላጎት ያገናዘቡ ዕርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ብቻ ከቀውስ ወደ ቀውስ መሸጋገር ልማድ ሆኗል፡፡ ከእንግዲህ ዓይነቱ አዘቅት ውስጥ በቶሎ አለመውጣት የአገር ህልውናን ይፈታተናል፡፡ ውጤቱም አስከፊ ይሆናል፡፡
      ያጋጣሙ ዙሪያ ገብ ችግሮችን በመሸሽ ወይም በማድበስበስ ዙሪያውን ከመዞር፣ ከእውነታው ጋር ተጋፍጦ ለሕዝብ ፍላጎት ሸብረክ ማለት ያስከብራል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ በፖለቲካው ሠፈር ውስጥ ያሉ ወገኖች በሙሉ ሊገነዘቡት የሚገባው፣ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ጎዳና መምረጥ ቀውሱን ያባብሰዋል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ግራ በገባት ወቅት ሥልጣንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ንትርክና ንዝንዝ ለማንም አይጠቅምም፡፡ አሁን የሚፈለገው አገሪቱን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ጎትቶ ማውጣት የሚችል ነው፡፡ በሐሳብ ልዩነት በማመን የተሻለ አቅምና ሐሳብ ያለውን ዕድል በመስጠት ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፍጠር የግድ ነው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳሩን በአስቸኳይ በመክፈትና ከአጉል ጀብደኝነት በመላቀቅ፣ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሒደት እንዲጀመር ሁሉም ወገን ጠጠር ማቀበል እንዲችል ዕድሉ ይመቻች፡፡ ነውጥ በተነሳ ቁጥር ሕይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ የሚቀጠልበት ቀውስ ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ በተቻለ መጠን ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ሊያስማማ የሚችል አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ለሥልጣን ከሚደረገው ሽኩቻና መራኮት የምትበልጠው አገር ናት፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላው ቢቀር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከሠፈሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተጨማሪ፣ አስተዋዩና ጨዋው ሕዝብ ውስጥ ለዘመናት የኖሩት የጋራ መስተጋብሮች ለመነጋገርና ለመደማመጥ ትልቅ ፋይዳ ነበራቸው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን አንዱን አሳዳጅ ሌላውን ተሳዳጅ፣ አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ የሚያደርገው አታካችና አሰልቺ የዘመናት የልሂቃን ችግር እዚህ አድርሶናል፡፡ በሕግ የበላይነትና በማኅበረሰቡ ውስጥ በዳበሩ መልካም እሴቶች አማካይነት በመታገዝ ቅራኔዎችን ከመከመር ይልቅ፣ ለጋራ መግባባት ቢሠራ ኖሮ ኢትዮጵያ የት በደረሰች ነበር፡፡ መልካም አጋጣሚዎች እንደ ዋዛ አልፈው በቀውስ ማዕበል እየተገፉ ውሳኔዎች ማስተላለፍ የተጀመረው በዚህ ምክንያት መሆኑን ከልብ መቀበል የግድ ነው፡፡ አሁን ኳሷ በዋነኝነት ያለችው በኢሕአዴግ እጅ ላይ ቢሆንም፣ በፖለቲካው ጎራ ውስጥ ያሉ ኃይሎችም የራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ ይኼንን ሚና በአግባቡ መወጣት የሚቻለው ግን ቅድሚያ ለአገር ሰላምና ደኅንነት ማሰብ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ወጀቡን ተከትሎ በዕቅድ  የማይመራ ነውጥን ማበረታታትና ለትርምስ የሚረዱ ግብዓቶችን ማቅረብ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋትና ራስን ለቁጭት መዳረግ ነው፡፡ ፖለቲካ የሚፈልገው ብልኃትና ጥንቃቄን እንጂ መደነባበርን አይደለም፡፡
‹‹ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል፣ ሞኝ ልጅ ግን ምሳው እራቱ ይሆናል፤›› እንደሚባለው፣ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ በመላቀቅ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የሚረዳ ምኅዳር እንዲፈጠር ራስን ማዘጋጀት የወቅቱ ዋነኛ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝብን ለአመፅ የሚጋብዙ ውሳኔዎች ትርፋቸው ሞትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በሰከነ መንፈስ ማሰብ ያለባቸው፣ የሚፈለገው ነገር ሊሳካ የሚችለው አገር ስትኖር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከወቅቱ የሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚመጣን ውሳኔ ማሳለፍ ያለበትና ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ማዘጋጀት የሚኖርበት፣ ከምንም ነገር በላይ የሆነችው አገር ሰላም እንድትሆን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር የሚያግዙ የፖለቲካ ውሳኔዎች ታክለው ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ወደሚረዳ ምርጫ መንገድ ሲመቻች፣ የአገር ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ አማራጮች ሳይጠፉና ለዚህም የሚረዱ ፖለቲካዊ ማዕቀፎች ባሉበት በዚህ ዘመን፣ የኃይል ተግባር ውስጥ በመግባት አገር ማተራመስና ሕዝብን ማመሰቃቀል በታሪክ ፊት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ አገርን አውድሞ ሙሾ ማውረድ የሞኝ እንጂ የብልህ ተግባር አይደለም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አማካይነት በነፃነት በሚደረግ ምርጫ እንጂ፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች በሚሆንበት ኢዴሞክራሲያዊ አሠራር አይደለም፡፡ የአገሪቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በእኩልነት የሚወዳደሩበት ሕጋዊ ማዕቀፍ በማበጀትና ብልሹ አሠራሮችን በማስተካከል፣ በዚህች ታሪካዊት አገር ዴሞክራሲ ነፍስ እንዲዘራ መደረግ አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት በስኬት ስሙ የሚነሳው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የበለጠ መመንደግ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን እንኳን ኢኮኖሚው የአገሪቱ ዕጣ ፈንታም አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ዘለቄታዊ መሆን የሚችለው በሰላማዊና በአሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሒደት ነው፡፡ የወቅቱን ችግር ለመግታት ብቻ ዒላማ ያደረገ ውሳኔ የሚተላለፍ ከሆነ ግን ሰላም እንደ ኅብስተ መና ይርቃል፡፡ ከዚህ ቀደም አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ስትገባ የአሥር ወራት አስቸኳይ ጊዜ ቢታወጅም ዘላቂ ሰላም ግን አልመጣም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ችግሮች ተፈጥረው በርካቶች ሞቱ፣ ለአካል ጉዳት ተዳረጉ፣ ተፈናቀሉ፡፡ አሁንም ካጋጠመው ቀውስ በዘላቂነት ለመላቀቅ አስተማማኝ ሰላም ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ አገሪቱ ከገጠማት ፈተና ለመታደግ የሚቻለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያግባባ ውሳኔ ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ሲጣል ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ይሁንታውን ሲገልጽ ነው፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር ስለሌለ ለሕዝብ ፍላጎት መታዘዝ ያስከብራል!

Saturday, February 17, 2018

የኢህአዴግ ውስጣዊ ቀውስ ተባብሷል- ስራ አስፈፃሚው አስቸኳይ ስብሰባ ይቀመጣል

Febeuary 17,2018

ዋዜማ ራዲዮ-የበረታውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ገዥው ግንባር በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተውተረተረ ይገኛል። መሰረታዊ የፖለቲካ ማሻሻያ መደረግ አለበት የሚሉ ድምጾች በበረቱበት በአሁኑ ሰዓት ስባት ሚሊየን አባላት ያሉት ኢህአዴግ ራሱን አንድ አድርጎ መራመድ ተስኖታል። የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል። የመከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ሳሞራ የኑስ መልቀቂያ ያስገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲነሱ የቀረበው ሀሳብ ከምንግዜውም በላይ አጀንዳ ሆኖ እየተናፈሰ ነው። ከዋዜማ ራዲዮ አቅም በፈቀደ በገዥው ግንባር ሰፈር ያለውን መረጃ በግርድፉ ከተለያዩ ምንጮች አሰባስበን አቅርበናል አንብቡት።
በተቃውሞ እየተናጠ መረጋጋት የራቀው ኢህአዴግ ሰፊ የአመራር ሽግሽግ እንደሚያደርግ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ግምታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ለዋዜማ የግል አስተያየታቸውን በስልክ ያካፈሉ አንድ የቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ ባለሥልጣንና አምባሳደር እንደሚሉት ብአዴንና ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትላቸው ደካማ አመራር ‹‹ፍጹም ደስተኞች እንዳልሆኑ›› በይፋ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ቀደም ባለው ስብሰባ ስብሀት ነጋ ኃይለማርያም ላይ የሰላ ሂስ መስጠቱን አውቃለሁ፡፡ አልቻልክበትም ብሎታል፡፡…አሁን የቸገራቸው እሱን አንስተው ማንን እንደሚያመጡ ነው፡፡›› ይላሉ እኚሁ የቀድሞ ባለሥልጣን፡፡
በመሪዎች ደረጃ ለውጥ ይጠበቅ የነበረው ከወራት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ቢኾንም የሐዋሳው ጉባኤ የተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ላልተወሰነ ጊዜ በመገፋቱ የሥልጣን ሽግሽጉ ከተጠበቀው ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲካሄድ በአራቱም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ፍላጎት ታይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን አራቱ የፓርቲ አመራሮች ስብሰባ አቋርጠው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የተላለፈው መልዕክት ተሰርዞ በምትኩ ደኢህዴንና ብአዴን ስብሰባቸውን እንደጨረሱ አስቸኳይ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር፡፡
ትናንት ምሽቱን ደግሞ ዳግም ስብሰባው ዛሬ ሐሞስ እንደሚካሄድ እየተነገረ ነው። የስብሰባው የጊዜ ሰሌዳ መዘበራረቅ ፓርቲው በሀገሪቱ እየበረታ የመጣው ቀውስ ያስከተለው ስጋት መሆኑን ግምታቸውን የነገሩን አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግማሽ ካቢኔያቸውን ለመፐወዝና አዳዲስ አደረጃጀቶችንና መዋቅሮችን ለማስተዋወቅ በአዲስ መንፈስ ኮሚቴ አቋቁመው እየሰሩ እንደነበር እንደሚውቁ የጠቀሱት እኚህ የቀድሞ ሹምና አምባሳደር፣ ባለፉት ሳምንታት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ) የሚመሩት አንድ ቡድን አዳዲስ ተሽዋሚዎችን በመመልመል ተጠምዶ እንደነበር እንደሚውቁም ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ ተሸዋሚዎችን ያስተናግዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት መሐል በዶክተር ደብረጺዮን ይመራ የነበረው የመገናኛ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ቦታ ሲሆን የብየነ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳን) ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲመሩ የቆዩት ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደዓረጋይ ከቦታቸው ተነስተው የዶክተር ደብረጽዮንን የቀድሞ መሥሪያ ቤት እንዲመሩ መታጨታቸው ተስምቷል።፡፡ ኮሚቴው ከዚህም ባሻገር ሦስት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችንና ሁለት ኤጀንሲዎችን በአዲስ ለማዋቀር እየሰራ ሲሆን ዶክተር ነገሪ ሌንጮን የሚተካ እጩ አመራር በማፈላለግ ላይ እንደነበረም ተሰምቷል፡፡ ይህ የምልመላና የአዲስ መዋቅር እንቅስቃሴ የሀገሪቱ ቀውስ በመበርታቱ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፡፡
በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት የመከላከያና ደህንነት ተቋማትን የመከለስና ሹም ሽር የማድረግ ስምምነት ቢደረግም የደህንነት ተቋሙ ጉዳይ ገና አልተጀመረም። የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስን ለመተካት ሲደረግ የቆየው ምክክርም መቋጫ አላገኘም።
ከመከላከያ አካባቢ የወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች በቀጣዮቹ ሳምንታት ዉስጥ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ መልቀቂያቸውን እንደሚያስገቡ የሚጠበቅ ሲሆን ሲሆን ጄኔራል ሳዕረ መኮንን ይመር ቀጣዩ ጠቅላይ ኢታማዡር ሹም እንደሚሆኑና በሥራቸው የብሔር ውክልና ያላቸው ሦስት ጄኔራሎች እንዲኖሯቸው እንደሚደረግ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ጉዳዩን እናውቃለን ያሉ ምንጮች ነግረውናል። ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ሲባል እንዲሁም ወቅታዊ የፖለቲካ ሚዛኑን ከግምት በማስገባት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስን ሊተኩ ይችላል የሚል ግምት ከመነሻው ጀምሮ ሲናፈስ ቆይቶ የነበረ ቢኾንም ጉዳዩን የያዘው ኮሚቴ መካከል ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉም እየተነገረ ነው።
ይህ ጉዳይ በምደባ ኮሚቴው በኩል አወዛጋቢ ሆኗል። ለወቅታዊ ፖለቲካው ምላሽ ብርሀኑ ጁላ ተመራጭ ዕጩ ቢሆንም በልምድና በግዳጅ አፈፃፀም ሳዕረ ቢሆን ይሻላል ወደሚለው መደምደሚያ ተደርሷል። የዚህ ሳምንቱ የፖለቲካ ዝንባሌ ይህን ውሳኔ ሊያስቀይረው ይችላል የሚለው ግምትም እንዳለ ነው።
የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 23 ቀን ጀምሮ ስብሰባ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከደኢህዴን ቀደም ብሎ ለስብሰባ የተቀመጠው ብአዴን በሰሜን ወሎ በተፈጠሩ ግጭቶች አቋርጦት የነበረውን ስብሰባ ከጥር 27 ወዲህ እያካሄደው ይገኛል፡፡ ብአዴን ከፍተኛ አመራሮቹን ጭምር ሊቀይር ይችላል የሚሉ ግምቶች መሰማት የጀመሩት በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ሲሆን በተለይም በፓርቲው ዘንድ ፍዝ ሚና ያላቸውን ሊቀመንበሩን አቶ ደመቀ መኮንንን ሊያሰናብት እንደሚችል ሰፊ ግምት ተሰጥቷል፡፡ ከስልጣን እንዲለቁ የበረታ ግፊት አለ። በአባላት መካከል በተደረገ ግለ-ግምገማ አቶ ደመቀ መኮንን በስልጣን እንዳይቆዩ የሚያደርግ ብርቱ ትችት እንደቀረበባቸው ተሰምቷል። በተለይ የክልሉ ህዝብ ወኪል ሆነው በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ አንዳችም ተፅዕኖ መፍጠር ያለመቻላቸው በእናት ድርጅታቸው በኩል ከፍ ያለ ቅሬታ ፈጥሯል።
በሕወሓቶች ዘንድ የክልሉ ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለል እንዲሉ ከፍ ያለ ፍላጎት መኖሩም ይነገራል፡፡ ብአዴንና ደኢህዴን እንደተገመተው አመራሮቻቸውን ገምግመው የሚያሰናብቱ ከሆነ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትላቸው ስለመነሳታቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
ፕሬዚዳንቱን በሕዝበኝነት፣ ዋና ጸሐፊዉን በሥልጣን ጥመኝነት በቅርቡ የገመገመው ኦህዴድ ያልተጠበቀ የለውጥ ኃይል ኾኖ በወጣበት በዚህ ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ የአመራር ሽግሽግ መደረጉ የሚያጠራጥር እንዳልሆነ የሚናገሩት እኚህ ባለሥልጣን ‹‹መጪዎቹ ወራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ጊዜያት እንደሚሆኑ እምናለሁ›› ይላሉ፡፡