September 25, 2018
ከኤርሚያስ ለገሰ
የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጄር ጄኔራል ደግፌ በዲ በወቅታው የመዲናይቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የሰጡትን መግለጫ ሰማሁት። ኮሚሽነሩን በተሰጣቸው ሃላፊነት እና ስልጣን የማክበር የዜግነት ግዴታ አለብኝ።እንደ አንድ ዜጋ እና ድምፅ አልባ ለሆነው አዲስአበቤ( በአዲስ አበባ በፍላጐቱ የሚኖር) እንደሚቆረቆር ሰው ደግሞ ቅሬታዮን የማቅረብ መብት አለኝ።
በመግለጫው ጄኔራሉ ላለፉት 27 አመታት የሰማነውን የመነቸከ አካሄድ እንደ ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ የህግ የበላይነት ሳይሆን የሕጉ የበላይ መስለው ታይተዋል። ሰውየውን ያለ ዛሬ አይቼአቸው ባላውቅም ከአንደበታቸው የሚወጣው አምባገነናዊ አቋምና እብሪት በተራዘመ ሂደት ስርአቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊወስደው ይችላል። በተለይም ጄኔራሉ እንደ ዛሬው በአክራሪዎቹ ተጠልፈው አይጥ በበላው ዳዋ እየፈለጉ የሚገድልና የሚያስሩ ከሆነ ለለውጥ ሀይሉ ከባድ ሸክምና እዳ መሆናቸው አይቀርም።
እዚህ ላይ የለውጡ መሪ ለሆነው ዶክተር አቢይ አንድ በጥሞና ማየት አለበት ብዮ የማስበውን ቁምነገር ላስገባ። የመጣጥፉም መዳረሻ ይሄ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው ከምርጫ 97 በኃላ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ጋር በተያያዘ አቶ መለስ ሶስት ትላልቅ አምባገነናዊ እርምጃዎች ወስደዋል። በቅርበት ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሠይጣናዊ እርምጃዎች መዲናይቱን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለዋታል። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው ችግር ፓለቲካዊ እና መዋቅራዊ በመሆኑ መፍትሔውም ፓለቲካዊ መሆኑ አይቀርም።
#የመጀመሪያው የአዲስ አበባና የአዲስ አበቤን ሉአላዊነት (በራሳቸው ህገ መንግስት አንቀፅ 49 የተጠቀሰውን) በመናድ የመዲናይቱን ፓሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለፌዴራል መንግስት አድርገዋል። በሌላ አነጋገር አዲስ አበባም ሆነ የህዝቡ ሉአላዊነት መገለጫ ተደርጐ የሚወሰደው “የከተማው ምክርቤት” የአዲስ አበባን ፓሊስ የማዘዝ መብት የለውም። በዳቦ ስም “የአዲስ አበባ ፓሊስ” ይባል እንጂ በግብር፣ በተጠሪነት እና ተጠያቂነት አዲስአበቤ አይደለም። እዚህ ላይ ሌላም አስገራሚ ነገር ልጨምር። ለነገሩ አስገራሚ ከምለው አስቂኝ ብለው እመርጣለሁ። ነብሷን ይማረው እና ወላጅ እናቴ ከአቅሟ በላይ የሆነ ነገር ሲያጋጥማት “ ወደው አይስቁ!” ትለን ነበር። ወደው አይስቁ! እናም አስቂኙ ነገር አዲስአበቤ ባለቤት ላልሆነበት፣ ተጠሪው ላልሆነ፣ ለማይጠይቀው “ የአዲስ አበባ ፓሊስ” በጀት ይመድባል። የሉአላዊነቱ አካል ያልሆነውን ፓሊስ ይቀልባል።
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር! መቼም የአለም ሶስተኛ የዲፕሎማሲ ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የኢትዮጵያውያን ዋና መናገሻ የምታዘው ፣ ተጠያቂ የምታደርገው ፓሊስ የላትም ብሎ እንደ መናገር የሚያሳፍር የለም። እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም እርሶም በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓለቲካ ቧልትና ጠላታዊ እርምጃ የሚሸማቀቁ ይመስለኛል።
በእርሶ የስልጣን ዘመን ይህን ውንብድና በማስተካከል በቀድሞው ስርአት ፓለቲካ ቁስለኛና ሰለባ የሆነውን አዲስአበቤ ከይቅርታ ጋር እንደሚክሱት ሙሉ እምነት አለኝ። በአዲስ አበባ ፓሊስና አዲስአበቤ መካከል የተጋረደውን መጋረጃ ቀዳደው ለመጪው በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለሚመጣው የአዲስ አበባ መንግስት እንደሚያስረክቡ ጥርጥር የለኝም።
#ሁለተኛው የአቶ መለስ የውስጥ መመሪያ የፓሊስ ምልመላና ስልጠናን የተመለከተ ነው። ከምርጫ 97 ጀምሮ ለነበሩት ሶስት አመታት የአዲስ አበባ ፓሊስ ለመሆን በሚደረገው ምልመላ ለአዲስአበቤ የሚሰጠው ኮታ 10 በመቶ በታች ነበር። በሂደትም ከሃምሳ በመቶ የሚበልጥ አይደለም። የተቀረው ግማሹ በኮታ ከሌሎች አካባቢዎች ተመልምሎ የሚመጣ ነው።ከኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ…ወዘተ። ከሌላ አካባቢ የሚመጡት ፓሊሶች ደግሞ ከከተሜው ባህሪ ጋር መላመድ ስለሚያቅታቸው ነዋሪው እንደሚንቃቸው ስለሚያስቡ በበታችነት ስሜት ይሰቃያሉ። በተበቃይነት ስሜት መንፈሳቸው ይረበሻል። ፈሪና ድንጉጥ ፍጡር ይሆናሉ። ፈሪ ሰው ደግሞ ሁሉንም ሰው ጠላት ያደርጋል።
በፓሊሱና በከተማው ነዋሪ መካከል ያለው ግንኙነትም የፋራና አራዳ ፣ የተታላይና አታላይ፣ የከተማ ቀመስና ከተሜ፣ የሰገጤና ጩሉሌ መሆኑ አይቀርም። በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ፓሊስ አባላትና አዲስአበቤ መካከል ያለው ግንኙነት ከፍተኛ የመተማመን እጦት ያለበት ሆኗል። ነዋሪው እንኳን በሲነርጂ አብሮ ሊሰራ ቀርቶ በመንደሩ ያስቸገረ ሌባን ለፓሊስ አሳልፎ መስጠት አይፈልግም። ፓሊስ በፓትሮል ለአሰሳ ሲመጣ “ ዛፓው! ሰገጤው! እየመጣላችሁ ነው ወደ ቤት ግቡ!” የምትለው የአራዶች ቃል በእናቶቻችንም ዘንድ የተለመደ ሆኗል።
የምልመላ መስፈርቱም የኢህአዴግ ሊግ አባል (60 ነጥብ)፣ የወጣት ፎረም አባል (20 ነጥብ)፣ የትምህርት ዝግጅት እና ሌሎች የጤና መመዘኛዎች (20 ነጥብ) ነበሩ። በሌላ አነጋገር አዲስአበቤ የኢህአዴግ የወጣት ሊግ ውስጥ መታቀፍ ካልፈለገ ፓሊስ የመሆን የልጅነት ህልም ቢኖረው እንኳን ፓሊስ መሆን አይችልም። በዚህ እኩይ ተግባር ሁላችንም የታሪክ ተወቃሾች ነን። የታሪክ ተወቃሽነት የሚያመጣው ድርጊቱን መፈፀም አሊያም አጋዥ መሆን ብቻ አይደለም። መጥፎው ውሳኔ እንዳይተገበር ለመከላከል ቁርጠኝነት አልፎ ሔዶም ማጋለጥ አለመቻል በዚህ ፈርጅ ይመደባል።
እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከላይ የጠቀስኩት አካሄድ እንዲሁ ቢቀጥል አዲስአበቤ ለእርሶ ያለው ድጋፍ ከተወሰነ በኃላ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይችላሉ። የመዲናይቷን ሰላም የሚያስጠብቀው ክፍል ውስጥ ባለቤቱ ከሌለበት እና ባይተዋር ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ በሂደት እርሶንም በባላንጣነት የሚመለከትበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በመሆኑም በእርሶ የስልጣን ዘመን ይሄን ያልተፃፈ የውስጥ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ያስቁሙ። የኦሮሚያ ክልል ፓሊስ አባላት በኦሮሚያ የሚኖሩ ዜጐች እንተደረገ ሁሉ፣ የአማራ ክልል የፓሊስ አባላት በአማራ ክልል እንደሚመለመሉ ሁሉ…ወዘተ በአዲስ አበባ ክልልም የሚመለመሉ ፓሊሶች አዲስአበቤ( በፍላጐቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ) ብቻ እንዲሆኑ አድርጉ። መመዘኛውም እንደ እርሶ ሙሉ ቁመና ያለው፣ ፓሊስ ሆኖ ማገልገል ፍላጐት ያለው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በፀባዩ ተቀባይነት ያለው/ ያላት ያድርጉ። የፓርቲ አባልነት እንደ መመዘኛ መወሰዱ ፀያፍ እንደነበር በአደባባይ ይግለጡ።
#ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር ጋር የተያያዘ ነው። አስቀድሜ እንደገለጥኩት ከምርጫ 97 በኃላ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር የሚመደበው ከፌዴራል ፓሊስና መከላከያ ሰራዊት ነው። በተለይም ቁልፍ ስራ የሆነውን አዛዥነት፣ ወንጀል መከላከል እና ምርመራ መምሪያ የሚያዘው ለፓርቲው ታዛዥ የሆኑ የፌዴራል ፓሊስና የመከላከያ መኮንኖች ናቸው። ይሄ በራሱ የፈጠረው ችግር አለ።
ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆንብኝ እንጂ የፓሊስ አመራር ሳይንስም ጥበብም ነው። ሳይንስ በመሆኑ ፕሮፌሽናሊዝም እና ምሁራዊ ግንዛቤ ይጠይቃል። ጥበብ በመሆኑ የሰዎችን አእምሮ የሚማርኩ ስልቶችን ማወቅ ይጠይቃል። የፓሊስ አመራር ከሌሎቹ ሙያዎች በተለየ ረቀቅ ያለ ጥበብ ይጠይቃል። በእውቀት፣ በችሎታ፣ በእምነትና ሕዝብ ለሚቀበለው መርሕ መቆምን ይጠይቃል። የሕግ የበላይነትን አምኖ መቀበል ይጠይቃል።
ስለዚህ የፓሊስ አመራር መሆን ያለበት እንደ ድሮው በፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ በከፍተኛ መኮንንነት የሰለጠነ ፕሮፌሽናል ሰው ሊሆን ይገባል። የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል ተመልሶ ፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ የአራት አመት ስልጠናውን ካልወሰደ በስተቀር ወደ ፓሊስ አመራርነት መምጣት የለበትም። አሁንም ድፍረት አይሁንብኝ እና አንድ የመከላከያ ሰራዊት መኮንን ስልጠናም ሆነ የአእምሮ ኦረንቴሽኑ ወታደርተኝነት ነው። ጠላትን የማንበርከክ ጀብደኝነት እና የጦረኝነት ዝንባሌ ነው።
ነብሱን ይማረው እና አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራሮችን ከመከላከያ ሲያመጣ አዲስአበቤን እንደ ጠላት፣ አዲስ አበባን እንደ ጦርነት አውድማ ስለሚቆጥራት ነበር። የአቶ መለስ የጦረኝነት ጽንሰ ሐሳብ የሚመነጨው መዲናይቱን መቆጣጠር የሚቻለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በታነፀ ወታደራዊ ኃይል ነው ከሚል እምነት ነው። በጠላትነትና በአደገኛ ቦዘኔነት የፈረጀውም አዲስአበቤ ወጣት ፀጥ ረጭ ማድረግ የሚቻለው በዚህ አይነት የጦር አመራር መሆኑን ያምናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርሶም በማወቅም ይሁን የቀድሞ አሰራር ትክክል መስሎት የፓሊስ አመራርን የቀየሩበት አሰራር ተመሳሳይ ነው። እርሶም ለአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽርነት የሾሙት የመከላከያ ሜጄር ጄኔራል ሆኗል። ሰውየው የፓሊስ አካዳሚ ገብተው ስልጠና መውሰዳቸውን ባላውቅም ከአነጋገር ለዛቸው ከወታደርተኝነት የተላቀቁ አይመስለኝም። ዶሮ ሶስት ጊዜ ሳትጮህ ጠርብ ጠርብ የሚያካክሉ ኩሸቶችን ሲያወሩ አንደበታቸው አልተደናቀፈም። መስከረም 4፣ መስከረም 5 የሰጡት መግለጫ መስከረም 14 ከሰጡት ጋር እርስ በራሱ ሲደባደብ ከመጤፍ አልቆጠሩትም( የእነዚህ ቀናት አስቂኝ ድራማ በሌላ ጽሁፍ እመጣበታለሁ።) ጆሮአቸውን በጥይት የደፈኑት እኝህ ጄኔራል ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ አይችሉም የሚለውን የህገመንግስት ቃል አንብበውት የሚያውቁም አይመስልም። በአመራር ሳይንስ ውስጥ ቅድሚ ለሚሰጥ ቅድሚያ እንስጥ በሚለው ጥበብ አጠገቡ ያለፉ አይመስልም። የጄኔራሉ አድርባይነት እና የስልጣን ብልግና ከወዲሁ ቁልጭ ብሎ ወጥቷል።
በመሆኑም እንዲህ አይነት ወታደርተኝነት ግርዶሽ የጣለባቸውን የጦር መኮንኖች ያለምንም ስልጠና ሕዝብ ውስጥ መቀላቀል ጦሱ ብዙ ነው።አዲስአበቤ በለውጡ ላይ ያሳደረው አመኔታ ይሸረሽራል። በነዋሪው አንድ “ወዴት እየሔድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በጠቅላላው አነጋገር በዚህ ዙሪያ የሚታየው ስህተት በቀላሉ የሚታረም አይደለም። የመጀመሪያው ድንጋይ ከመወርወሩ በፊት መሰረታዊ የሆነ የአመራር ስርአት ለውጥን ይጠይቃል። መሪ መለወጥም ግድ ይላል። ከእንግዲህ በኃላ አዲስአበቤዎች በቀቢጸ ተስፋ የሚኖሩ አይደሉም። እንደ ጥቁሩ አሜሪካዊ የመብት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ህልም አላቸው። አንድ ቀን አዲስአበቤዎች በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ራሳቸውን ያስተዳድራሉ።
No comments:
Post a Comment