Thursday, April 17, 2014

የእሪታ ቀን ሰልፍ በሚያዚያ 26 ቀን እንደሚደረግ አስተዳደሩ እውቅና ሰጠ !

April 17/2014
«ህግን አክብረን ለድርድር የማናቀርበውን ህገመንግስታዊ መብታችንን አሳልፈን አንሰጥም። ታላቁ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ‹‹የእሪታ ቀን ›› በሚል መሪ ቃል ሚያዚያ 26፣2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይደረጋል፡፡» ሲሉ የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው ገለጹ።
ፓርቲዉ ከአዲስ አበባ አስተዳደር አስፈላጊዉን እውቅና ያገኘ ሲሆን ፣ ከትንሳኤ በዓል በኋላ በሃያ ሶስቱም የአዲስ አበባ ወረዳዎችና በአዲስ አበባ አካባቢ ባሉ ቦታዎች ቅስቀሳ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል። የአዲስ አበባ ሕዝብ በዚህ ቀን፣ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ያሰማል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰልፉ ሊደረግ የታሰበው መጋቢት 28 የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ አስተዳደሩ ሕግን ባልጠበቀ መልኩ፣ አማራጭ ቀን ወይም ቦታ እንዲቀርብ ሳይጠይቅ በደፈናዉ እውቅና አልሰጠም የሚል ደብዳቤ መላኩ ይታወቃል። ለሕገ ወጥ እርምጃ እውቅና አንሰጥም በሚል፣ አንድነት የአስተዳደሩን ደብዳቤ እንደማይቀበል በማሳወቅ፣ የቅስቀሳ ዘመቻ ማድረጉን ፣ ከዚያም ጋር በተገናኘ 4 አባላት በፖሊስ መደብደባቸውን ፣ አምስት ደግሞ ለሳምንት መታሰራቸው ይታወቃል።
አስተዳደሩ የላከዉን ሕገ ወጥ ደብዳቤ በመቀልበስ፣ ለሚያዚያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ እንዲደረግ እውቅና እንዲሰጥ መደረጉ ፣ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ያደረጉት ትግል ዉጤት እንደሆነም የሚያመላክት ነው።
10173649_621015051316766_1061251165963443430_n

No comments: