Wednesday, April 30, 2014

የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

April 30/2014

-በዋስ ይለቀቁ የተባሉ አባላት በነፃ ካልሆነ አንወጣም አሉ

-በሊቀመንበሩ መሪነት ሰላማዊ ሠልፍ አደረጉ

ከአዲስ አበባ አስተዳደር ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ካገኙ በኋላ ቅስቀሳ ሲጀምሩ፣ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ

አመራሮችና (ከሊቀመንበሩ በስተቀር) ቁጥጥራቸው 28 የሚደርሱ አባላት ሚያዝያ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው የታሰሩት የፓርቲው የፖለቲካ አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻን ጨምሮ 14 አባላት በየካ ክፍለ ከተማ ቤላ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን፣ የብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢውን አቶ የሸዋስ አሰፋን ጨምሮ ስድስት አባላት ደግሞ ቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ ላዛሪስት ትምህርት ቤት አጠገብ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንደሻው እምሻው አስታውቀዋል፡፡ ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ የሕዝብ ግንኙነቱ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድና ስምንት አባላት የካ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አቶ ስለሺን ጨምሮ የተወሰኑት አባላት አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀበና ችሎት ሚያዝያ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርበው በአንድ ሺሕ ብርና መታወቂያ ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ያዘዘ ቢሆንም፣ የፓርቲው አባላት ግን ከእስር ቤት እንደማይወጡ ተናግረዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ፖሊስ ያሰረበትን ምክንያት ፍርድ ቤት ሲጠይቀው ለሰላማዊ ሠልፍ እያሉ ሕዝቡን ሲቀሰቅሱና ሲበጠብጡ በመገኘታቸው መሆኑን ገልጾ ቢያስረዳም፣ ፓርቲያቸው ሰላማዊ ሠልፉን አድርጐ ያለምንም ችግር በሰላም በማጠናቀቁ እነሱም በነፃ እንዲሰናበቱ መጠየቃቸው ነው፡፡

ላዛሪስት ትምህርት ቤት አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያና ቤላ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ የፓርቲው አባላት ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ የሰባት ቀን ተጨማሪ የምርመራ ቀን ጠይቆ ስለተፈቀደለት፣ ሚያዝያ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡

የፓርቲውን አመራሮቹና አባላቱን ለእስር የዳረገው የሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ እንደራሴ አካባቢ ከሚገኘው ቢሮ በተወሰኑ ደጋፊዎች ሊቀመንበሩ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በሚመሩት አባላት ጉዞውን ወደ ባልደራስ አድርጓል፡፡ ‹‹አትነሳም ወይ አትነሳም ወይ ይኼ ባንዲራ ያንተ አይደለም ወይ? ራበን፣ ጠማን፣ በጨለማ ተዋጥን፣ ኔትወርክ የለም፣ መንገድ የለም…›› የሚሉ መፈክሮችን አንግበውና በድምፅ ማጉያ በማስተጋባት ዓደዋ ድልድይ አደባባይ የደረሰው ሠልፈኛ ለተወሰነ ደቂቃ እንደፈለገው መሄድ አልቻለም፡፡ ከዓደዋ አደባባይ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ በሚያስወጣው መንገድ ሠልፈኛው ሊሄድ ሲሞክር፣ መንገዱ በፖሊሶች የጐንዮሽ ሠልፍ ታጥሮ ‹‹መሄድ ያለባችሁ ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ ነው፤›› በመባላቸው መግባባት ሳይቻል ቀርቷል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል በጉልበታቸው በርከክ ብለው እጃቸውን ወደ ላይ ሲዘረጉ አንዱ የፓርቲው አባል ሰላማዊ ሠልፉ ከየት ተነስቶ የት እንደሚያበቃ የሚፈቅደውን ወረቀት ለአንድ የፖሊስ ኃላፊ ሲያሳዩአቸው ‹‹መንገዱን ክፈቱት ይሂዱ›› የሚል ትዘዝ በመስጠታቸው በጥሩንባ፣ በፊሽካ፣ በድምፅ ማጉያና በጩኸት የታጀበው ሠልፍ በርከት ባሉ ፖሊሶች እየተመራ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ መውጫ አመራ፡፡ ‹‹We need Electricity, We need Water, We need Transportation, No Network, Free Reeyot, Eskindr, Wubshet, Muslim Brothers, Freedom, Freedom›› የሚሉ መፈክሮችን በእንግሊዝ ኤምባሲ መግቢያ በር ፊት ለፊት በጩኸትና የተለያዩ ድምፆችን ካሰሙ በኋላ፣ ጉዞአቸውን ሰላማዊ ሠልፉ የሚጠናቀቅበት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ድንበሯ የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል ጀርባ አድርጓል፡፡

መንግሥት ፖሊሲውን እንዲያሻሽል ወይም ሥልጣኑን እንዲያስረክብ፣ ዜጐች የመናገር፣ የመጻፍና ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር እንዲያደርግ፣ የሚሉ መፈክሮችንና ሌሎችንም በማንሳት ሰላማዊ ሠልፉ ተጠናቋል፡፡ ታስረዋል ስለተባሉት የፓርቲው አመራሮችና አባላትን በሚመለከት ፖሊስ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሪፖርተር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ሊሳካ አልቻለም፡፡    

No comments: