Thursday, April 3, 2014

የማለዳ ወግ … በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል …

April2/2014



ግፍ ከበዛበት ወህኒ የአክብሮት ስላምታየ ይድረሳችሁ!
እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ለአፍታ ያህል እድሉን አግኝቸ ወህኒ የመውረዴን እውነታ ላስረዳችሁ ግድ አለኝ ። ዛሬ አስረግጨ የምነግራችሁ ወህኒ የመውረዴ ምክንያት ሚስጥር ግምሽ እድሜየን ህግና ስርአቷን አክበሬ የኖርኩባትን የሳውዲት አረቢያን ህግ ተላልፊ አይደለም ! የስደተኛው ጉዳይ ያገባኛል በሚል የማቀርበው መረጃ ቅበላየ የማይመቻቸው ፣ ያመማቸው ከተሰረሰውና እየተሰራ ካለው ከእገታው ጀርባ ስለመኖራቸው አልጠራጠርም ። ... ዛሬ በዚህ ዙሪያ ብዙ አልልም!
አላወቁትም እንጅ ክፉዎች ጠቅመውኛል ፣ ያላየሁትን እንዳይ አድርገውኛል። መንገዱ የከፋ ቢሆንም በወሰዱኝ መንገድ ተመርቸ እሰማው የነበረውን የወገኖቸ የወህኒ የከፋ ኑሮና ህመም ፣ በተቆርቋሪ ጠያቂ ማጣት ፣ በፍትህ መነፈግ እይሆኑ ያሉትን ከመስማት ማየት ማመን ነውና በአካል ማየት ችያለሁ !
ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት በግፍ ለተደበደበው፣ ሁለት አይኑን ላጣውና " አይሆኑ ከሚሆን ቢሞት ይሻላል "ተብሎ የፎቶ መረጃው ሳይቀር በእጀ የገባውን ወጣት ምንዱብ የወህኒ ህይወትን ተጨባጭ ታሪክ ከአይን እማኞች ቃርሜያለሁ! እሱም ያለው ከታሰርኩበት የቅርብ ርቀት ነው ። ... አትጠራጠሩ አገኘውም ይሆናል !
በዚህ የጭንቅ ሰአት ከእኔና ከቤተሰቦቸ ጎን ሆናችሁ አለኝታችሁን ለገለጻችሁልን ምስጋናየ ከፍ ያለ ነው ! ዛሬ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ አንገባም ። በላይ በመላ አለም የምትገኙ ወገኖቸ ያሳያችሁኝ ድጋፍና መቆርቆር ከጨለማው ቤት ደርሶኝ ጽናት አጎናጽፎኝ ሰንብቷል። ይህም በአረብ ሃገር ስደተኛ ዙሪያ ሳቀርነው ለነበረው መረጃ ያገኘሁት ክብርና ሞገስ ሆኖ መከራውን አስረስቶኛል: ) ምስጋናየ አይለያችሁ!
ወገኖቸ ወዳጆች ፣ ዛሬ ሰላም መሆኔን ብቻ ተረዱ ብየ እንጅ በሰፊው ስለሚሆነው አቅም በፈቀደ መጠን እናወራለን ! ዝምታው ከናፈቅኳቸው ልጆቸ ፣ ከቤተሰቦቸና ከእናንተ ጋር የሚያደርሰው መንገድ ውል እንዲይዝ የሚደረገው ሙከራ ውል እንዲይዝ የሚተጉ ወገኖችን ሂደት ላለማደናቀፍ ብቻ ለመረጋጋት ሲባል ብቻ ነው !
በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል ፣ በንጋቱ ጮራ ታግዘን የምናወጋው የማለዳ ወግ ናፍቆኛል: ) ይህን ለማድረግ የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ደግሞ ልቤ ብርቱ ነው ...
ሰላም ለሁላችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት

No comments: