Wednesday, July 17, 2013

የኢትዮጵያ ንግድ ባንግድ የአገልግሎት ስራ አስኪያጅ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

-    በትምህርት ቤት እምነት ያጎደሉ ግለሰብም በፅኑ እስራት ተቀጥተዋል

በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሻሸመኔ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ፣ በተመሠረተባቸው ከባድ የማታለል የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ የአሥር ዓመታት ፅኑ እስራትና 20 ሺሕ ብር ቅጣት ተጣለባቸው፡፡

ሐምሌ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቅጣቱን የጣለባቸው የቅርንጫፍ ባንኩ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰለ ዮሐንስ የሚባሉ ሲሆኑ፣ ከእሳቸው ጋር በመተባበርና በመመሳጠር የወንጀሉ ተባባሪ መሆናቸው በሰውና በሰነድ ማስረጃ የተረጋገጠባቸው እናታቸው ወይዘሮ ለምለም ካህሣይ በአራት ዓመታት ፅኑ እስራትና በሦስት ሺሕ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ከባድ የማታለል የሙስና ወንጀል፣ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ሊቀጡ የቻሉበት ድርጊት የተቀነባበረው በሥራ አስኪያጁ አቶ መሰለ ዮሐንስ መሆኑን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያስረዳል፡፡

ውሳኔው እንደሚያስረዳው፣ አቶ መሰለ የሌሎች የባንኩ ሥራ አስኪያጆችን የይለፍ ቃል ባልታወቀ ምክንያት በእጃቸው አስገብተዋል፡፡ ቀጥለው በባንኩ ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ የታገደን ሒሳብ እንዲቀንቀሳቀስ ያደርጋሉ፡፡ የሒሳቡን ባለቤት ስም በራሳቸው፣ በእናታቸው በወይዘሮ ለምለም ካህሣይ ስምና በሌሎች ስም ሲያቀያይሩ ከርመዋል፡፡ ቀጥለው ከሒሳቡ ላይ በራሳቸው ስም 21,600 ብር፣ በወይዘሮ ለምለም ስም ደግሞ 500 ሺሕ ብር ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ውሳኔው ይገልጻል፡፡

ቀደም ብለው በእጃቸው አስገብተው በነበረው የሌሎች ሥራ አስኪያጆች የይለፍ ቃል በመጠቀም፣ ለወይዘሮ ለምለም በሐዋላ የተላከላቸው በማስመሰልና ሐሰተኛ መልዕክትና የሴሪአ ቁጥሮችን በመጠቀም፣ በተለያዩ ጊዜያት ሁለት ሚሊዮን ብር አውጥተው በግል አካውንታቸው በማስገባት ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በሰው ማስረጃ ሲያረጋግጥ ወንጀሉን ፈጻሚዎቹ ሊያስተባብሉ አለመቻላቸውን ውሳኔው ይተነትናል፡፡

በአጠቃላይ ሁለቱም ግለሰቦች 2,521,600 ብር ከታገደው ሒሳብ አውጥተው ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ስለተረጋገጠባቸው ቅጣቱ መወሰኑን በውሳኔው ተገልጿል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የገዙት የመኖሪያ ቤት፣ የጭነትና የቤት ተሽከርካሪዎች እንዲወረሱ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታ አቅርቦ እየተጠባበቀ መሆኑም ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የሚሌኒየም ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤት፣ ረዳት የፋይናንስ ኦፊሰር ሆነው ሲሠሩ የነበሩት አቶ ሰመረ በለጠ የተባሉ ግለሰብ፣ በፈጸሙት የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል በአሥር ዓመታት ፅኑ እስራትና በ15 ሺሕ ብር ተቀጥተዋል፡፡

ግለሰቡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም. ከትምህርት ቤቱ የተለያዩ የውስጥ ገቢዎች ያሰባሰቡትን 224,823 ብር ለሚመለከተው አካል ገቢ ሳያደርጉ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ካቀረበው ክስና ማስረጃ ማረጋገጡን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

ከትምህርት ክፍያ፣ ከትምህርት ማስረጃዎች፣ ከተለያዩ ቅጣቶችና ከተመላሽ ደመወዝ የተገኘን ገቢ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ቅጣቱ መተላለፉን ውሳኔው ያስረዳል፡፡

No comments: