Thursday, August 29, 2013

ፓሊስ የሰማያዊ ፓርቲ አመራርን ነገ ሊያነጋግር ነው

ነሃሴ ፳፫(ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰማያዊ ፓርቲ የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ፓሊስ የፓርቲውን አመራሮች በመጥራት ለነገ ሊያነጋግራቸው ቀጠሮ መያዙን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ፡፡
ፓርቲው በበኩሉ ሊካሄድ የታቀደውን የተቃውሞ ሰልፍ በምንም አስገዳጅ ሁኔታ ሊሰርዝ እንደማይችል በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የፓርቲው አመራሮች ተናግረዋል፡፡
ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት ከሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ነገ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ የሰማያዊ ፓርቲ ፀሐፊን፣ ሊቀመንበሩንና የሰልፍ አስተባባሪዎችን ለማነጋገር ጥሪ እንዳቀረበላቸው ታውቋል፡፡
በፀጥታ ዙሪያ ልናነጋግራችሁ እንፈልጋለን የሚለው የፖሊስ መጥሪያ ፓርቲው የእሁዱን ስብሰባ እንዲሰርዝ ለማግባባት ያለመ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ፓርቲያቸው የእሁዱን ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ተናግረው፤ ምንም አስገዳጅ ሁኔታ ከያዙት አቋም እንደማያስቆማቸው ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
በታሪክ፣ በሞራልም ሆነ በህግ ተጠያቂ የሚያስደርገን ነገር ስለሌለ ሰላማዊ ሰልፉ የማይቀር መሆኑን የፓርቲው አመራር ተናግረዋል፡፡
በትላንትናው እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማህበራት ፍቃድ ጽ/ቤት የፓርቲውን ሰልፍ ህገወጥ ነው ማለቱን አስመልክቶ የተጠየቁት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ‹ሕጋዊ ወይም ህገ ወጥ› የሚባል ሰልፍ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው የሰልፍ አስተባባሪ ዝግጅት ክፍል ለእሁድ ሰልፍ የሚያደርገው ዝግጅት ከገዥው ፓርቲ የተለያየ ወከባ እየደረሰበት እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
መብራት በተደጋጋሚ የመጥፋት ተግባርና በመኪና ቅስቀሳ ለማድረግ የተደረገ እንቅስቃሴ በፀጥታ ሀይሎች ጫና እየተደረገበት እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የኢህአዴግ አባላት ቤት ለቤት በመሄድ ህዝቡ ለእሁድ የሀይማኖቶች ጉባኤ ሰልፍ እንዲወጣ ቅስቀሳ ማድረግ ላይ እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
መንግስት እያስተባበረ የሚገኘው የሀይማኖቶች ጉባኤ ሰልፍ ህዝቡ አክራሪነትን እና ጽንፈኝነትን ለማውገዝ በሚል የተጠራ ቢሆንም እየተካሄደ ያለውን የሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ሌላ አቅጣጫ ለማስያዝ ያለመ እንደሆነ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ሁለት ቀን ብቻ የቀረው የእሁዱ የመንግስትና የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በሀገሪቱ የፖለቲካ አካሄድ ከብዙ ዓመታት በኋላ ያጋጠመ ክስተት ተደርጎ ታይቷል፡

No comments: