Thursday, July 25, 2013

በቸልተኝነት በፈረሰ ሕንፃ ሳቢያ አራት ሰዎች ሞተው 16 ቆሰሉ

-    ፖሊስ በሰው ሕይወት የማጥፋት ወንጀል ክስ ሊመሠርት ነው

በቸልተኝነት በፈረሰ ሕንፃ ሳቢያ አራት ሰዎች ሞተው 16 ቆሰሉ
     

ባለፈው ቅዳሜ መርካቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ አሮጌ ሕንፃ በቸልተኝነት ሲፈርስ በደረሰ አደጋ አራት ሰዎች ሞተው 16 ያህሉ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
ሥራ አጥነትን ለማጥፋት በሚል ምክንያት የአዲስ አበባ አስተዳደር በልማት ሰበብ ቤቶችን እንዲያፈርሱ ያደራጃቸው ወጣቶች፣ በአዲስ አበባ በጎጃም በረንዳ አካባቢ ዕድሜ ጠገብ ከሆኑት ሕንፃዎች መካከል፣ ቀድሞ ሐበሻ ባንክ ይባል የነበረውንና እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ‹‹አሰፋ ገለታ ሆቴል›› ተብሎ የሚጠራውን ሕንፃ ሲያፈርሱ ከጥንቃቄ ጉድለትና ከቸልተኝነት የተነሳ በመናዱ፣ ሁለት ሰዎች በናዳው ወዲውኑ ሲሞቱ አንዲት ሴት ሆስፒታል ከደረስች በኋላ ሕይወቷ አልፏል፡፡ ባለፈው ሰኞ ረፋድ ላይ ደግሞ አራተኛው ጉዳተኛ በሆስፒታል ሕክምና ላይ እያለ ሕይወቱ ማለፉን ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የአካል መጉደልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ጨምሮ 16 ሰዎች ሕክምና ተደርጎላቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር የአዲስ ከተማ ፖሊስ መምርያ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ምትል ሳጂን ሲራክ ኃይሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዕለቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ያለፈውን ሰዎች ጨምሮ፣ ከባድና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ከሕንፃው ፍርስራሽ ሥር በማውጣት ወደ ቅዱስ ጳውሎስና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመውሰድ ለማሳከም ተችሏል፡፡ አብዛኞቹ የጉዳቱ ሰለባዎች እግረኞች መሆናቸውን ያረጋገጡት ምክትል ሳጂን ሲራክ፣ ከ20 ዓመታት በላይ ሆቴሉ ደጃፍ ላይ ይተኛ የነበረ የቀድሞ ሠራዊት አባል በጦር ሜዳ ጉዳት የደረሰበት እግሩ በሰው ሠራሽ የተተካ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጉዳት የቀረውን እግሩን እንዳጣም አስታውቀዋል፡፡ በርካቶች የእግር መቆረጥና ሌላም የከፋ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ በዕለቱ ሕንፃውን ሲያፈርሱ ከነበሩ ወጣቶች ውስጥ በአንዳቸውም ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ምክትል ሳጂን ሲራክ አረጋግጠዋል፡፡

ፖሊስና የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉት ርብርብ የሞቱና ሕይወታቸው የተረፉ ሰዎችን ወደ ሕክምና ቦታ ማድረስ ቢቻልም፣ የአዲስ አበባ ድንገተኛ አደጋዎችን በአፋጣኝ የማስተናገድ ብቃትንም የፈተሸ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ እንዲህ ባለው የሕንፃ ናዳ ሳቢያ በፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት የሚረዱ ክሬንና መሰል መሣርያዎች ያልተገኙባት ወይም የሌሉዋት ከተማ መሆኗን አደጋው አመላክቷል፡፡ ምክትል ሳጂን ሲራክም በዚህ ይስማማሉ፡፡ በዕለቱ ፈጥነው ከመጡት አምቡላንሶች በቀር የሕንፃ ፍርስራሾችን ሊበረብር የሚችል መሣርያ አልነበረም፡፡ 

በመላ አገሪቱ እየተበራከተ የመጣው የሕንፃዎች አደጋ ከዚህ ቀደም ከግንባታ ጥራት ችግሮች አኳያ አብዝቶ ሲከሰት የነበረ ሲሆን፣ በጎጃም በረንዳ የተከሰተው ግን ሕንፃዎችን ከማፍረስ ተግባር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ አደጋው የአገሪቱን የሕንፃዎች ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ ክስተቶች አንዱና በቸልተኝነት ምክንያት ከሚከሰቱት ውስጥ ዋናው ሳይሆን እንደልቀረ ይነገራል፡፡

በጎጃም በረንዳ አጓጉል በሆነው ሕንፃዎችን የማፍረስ ተግባር (በመላ ከተማው የሚታየው ተመሳሳይ ድርጊት ነው)፣ ባለፈው ቅዳሜ ማለዳ ሐምሌ 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በደረሰው አደጋ ምክንያት አደጋውንና መንስዔውን ሲመረምር የቆየው የአዲስ ከተማ ፖሊስ መምርያ፣ በአደጋው ሊጠየቁ የሚችሉ አካላትን በቸልተኝነት የሰው ሕይወትን በማጥፋት ወንጀል ክስ ሊመሠርትባቸው እንደሚችል ምክትል ሳጂን ሲራክ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት የወንጀል ምርመራ ቡድን ሪፖርቱን አጠናቅቆ መዝገቡን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መላኩን አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደርና የአፍራሽ ግብረ ኃይል ወጣቶች ክሱ ሊመለከታቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡ ስለአደጋውና ስለሕንፃ ማፍረስ ሒደት የሪፖርተር ዘጋቢ የሚመለከታቸውን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚና ሌሎችን ኃላፊዎች ለማነጋገር ቢሯቸው ቢሄድም፣ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባሉ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አደጋው ከደረሰበት አካባቢ ጀምሮ በሌሎችም ሥፍራዎች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሕንፃዎች በቸልተኝነትና ያለጥንቃቄ መፍረሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሕንፃዎችን እንዲህ የሚያፈርሱት ወጣቶች የግንባታ ብረቶች ሳይበላሹ ለማውጣት በሚል ሰበብ ሲሆን፣ በማስረጃ ማረጋገጥ ባይቻልም እስከ 300 ሺሕ ብር የሚደርስ ገንዘብ ለማግኘት ጨረታ ወስደው እንደሚሠሩ በስፋት ይነገራል፡፡

በርካታ የሥነ ሕንፃና የምሕንድስና ጠበብት ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ የሚደመጠው፣ የአገሪቱ ሕንፃዎች በትክክለኛ ባለሙያዎችና የሕንፃ ግንባታ ሕግጋት መሠረት የማይከናወኑ በመሆናቸው፣ የሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፉ አደጋዎች ለመበራከታቸው ምክንያት ናቸው ይላሉ፡፡ የሲሚንቶ ቡኮ፣ የብረት መጠን፣ የቦታ አቀማመጥ፣ የአፈር ባህሪይ ጥናትና መሰል ተግባራት ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥና ኢሥነ ምግባራዊ ድርጊቶች የሕንፃዎችን መደርመስ እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡

 እንዲህ ባለው ሁኔታ በመሠራት ላይ የነበሩ ሕንፃዎች በሰዎች ላይ እየተናዱ የሞትና የአካል ጉዳት ሲያደርሱ ተዘግቧል፡፡ አሁን ደግሞ ነባር ሕንፃዎችን ምንም ዓይነት የሥራ ቦታ ደኅንነት መጠበቂያ በሌላቸው፣ እግረኞችና ተሽከርካሪዎች በሚበዙባቸው ሥፍራዎች ላይ፣ አፍራሽ ግብረ ኃይል የሚል መጠርያ የተሰጣቸው ወጣቶች በትልልቅ መዶሻዎች የሚፈረካክሷቸው ግድግዳዎችና ምሰሶዎች የራሳቸውን ሕይወት ጨምሮ በየአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች የሚገኙ ዜጎችን ለአደጋ እየዳረጉ ናቸው፡፡

No comments: