Tuesday, July 16, 2013

የደብረብርሀን ነዋሪዎች ፍትህ አጣን አሉ

ሐምሌ ፱( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በሰሜን ሺዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ ኗሪዎች የመንግስት ሹማምንት የሚያደርሱባቸውን በደሎች በመዘርዝር ለመንግስት አቅርበዋል።


ክልሉ በቅርቡ በጀመረው የህዝብ ብሶቶችን መስሚያ መድረኮች ላይ ነዋሪዎች ” በአደባባይ እንደበደባለን ፤እንታሰራለን፤ በአገራችን በሰላም ለመኖር አልቻልንም” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡በተደጋማሚ በሚደርስባቸው በደል አገር ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች መበራከታቸውንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ሹመት የሚሰጠው በዘመድ ዝማድ ነው ያሉት አንድ ተናጋሪ ፣ ድርጊቱን በሚቃወሙት ላይ ደግሞ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል

ሌላው ተናጋሪ ደግሞ ” በዘመድ የተሾመ ባለስልጣን እና በ15 ቁጥር ምስማር የተመታ እንጨት አንድ ናቸው ፣ ሁለቱም አንዴ ከገቡ ለመንቀል ያስቸግራሉ” ካሉ በሁዋላ፣ “ክፉ የሚሰራው ይሾማል፣ ደጉ ደግሞ ይወረዳል ሲሉ አክለዋል።
“አመራሮችን የሚገመግሙ ሰዎች በግል ህይወታቸው ላይ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በስብሰባው ላይ የተሳተፉ ሌላ ተናጋሪ ገልጸዋል

ኢሳት በእንጅባራ፣ በደሴና ወልድያ የተካሄደውን ህዝባዊ ስብሰባ በድምጽ ማቀርቡ ይታወሳል። በሁለቱም ስብሰባዎች ላይ ህዝቡ በአስተዳደሩ ምሬቱን ሲገልጽ ተስተውሏል። አንድ ተናጋሪ ” የኢህአዴግ ባለስልጣናት በጡንቻቸው ስለሚያሰቡ ህዝቡን ለስቃይ ዳርገውታል በማለት በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን ችግር ገልጸውታል

በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱትን ስብሰባዎች በመቅረጽ ለላኩልን የደብረብርሀን፣ የእንጅባራ፣ የደሴና ወልደያ ነዋሪዎች ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።

No comments: