Thursday, July 11, 2013

ጉዳዩ የመብት እንጂ የፖለቲካ አይደለም

ሐምሌ 4 ቀን 2005 ዓ.ም
we are oneእንደ ጆርጅያ፣ አላባማ፣ ሚሲሲፒና ቴክሳስ በመሳሰሉ የደቡብና የደቡብ ምዕራብ  የአሜሪካ ግዛቶች የጥቁር አሜሪካዉያን መብት በግፍ የሚረገጥበትና ወቅት ነበር። ነጮች የሚገቡበት ምግብ ቤቶችና ነጮች የሚማሩበት ትምህርት ቤቶች ጥቁሮች እንዳይገቡ ይታገዱ፣ በባስ ከተሳፈሩ ደግሞ ከኋላ ባሉ መቀመጫዎች ብቻ ነበር እንዲቀመጡ ይደረጉ ነበር። ድንገት ወደ መሃል ጠጋ ካሉና ሌላ ነጭ በባሱ ዉስጥ ከገባ ለነጩ መቀመጫ መልቀቅ ይጠበቅባቸዉ ነበር።

በዚያን ወቅት ነበር የሰብዓዊ መብት ትግል እናት፣ ሮዛ ፓርክ፣ በአርባ አራት አመታቸዉ የግፍና የዘረኛ  አገዛዙን «እምቢ» ያሉት። እኝህ እናት ያልተለመደና ጀግንነት የተሞላበት ታሪካዊ ሥራ ለመስራት ቻሉ። ነጮች ብቻ በሚቀመጡበት ቦታ «እኔም ሰዉ ነኝ።

እኔም ከማንም አላንስም» ብለዉ ለመብታቸዉ፣ ለነጻነታቸዉ፣ ለእኩልነታቸዉና ለክብራቸዉ ሲሉ  ተቀመጡ። ለነጮች ቦታ «አለቅም» ብለዉ አሻፈረኝ አሉ።

የባሱ ሹፌር «ተነሺ፣ ፈቀቅ በይ፣ ይህ  ቦታ ላንቺ አይነቱ አይደለም፣ አንቺ ከፊት ሳይሆን ከኋላ ነዉ መሆን ያላብሽ። ላንቺ ትራፊ ነዉ የሚገባሽ» ሲላቸዉ እኝህ እናት ግን «እግዚአብሄር ሰዉን ሁሉ አኩል አድርጎ ፈጥሯል። እምቢ ለዉርደት፣ እምቢ ለበታችነት፣ እምቢ ለባርነት» ሲሉ በተከለከለ  መቀመጫ ላይ ተቀመጡ።

በዚህ ወቅት ነበር በግሪንስቦሮ ደቡብ ካሮላይና በሚገኝ ምግብ ቤት፣ ዮሴፍ ማክኒል የሚባል ጥቁር አሜሪካዊ የኮሌጅ ተማሪ፣ ለነጮች ብቻ በተፈቀደ ምግብ ቤት ምግብ አዞ ለመመገብ ደፍሮ በወኔ የገባዉ። የምግብ ቤቱ ባለቤት ምግብ ለማቅረብ ፈቃደኛ ባይሆንም፣ ዮሴፍ ማክኒል ግን ተስፋ አልቆረጠም። በነጋታዉ ሌሎች ሶስት ጓደኞቹን ይዞ ተመልሶ መጣ። አሁንም የምግብ ቤቱ ባላቤት ምግብ አላቀርብም አለ። እንደገና መቀመጥ፣ እንደገና ምግብ መከልከል፣ እንደገና መቀመጥ እንደገና ምግብ መከልከል።
እነማክኒል ተስፋ ሊቆርጡ አልቻሉም። አላማቸዉን ከግብ ማድረስ ከባድ እንደሆነ ያዉቃሉ። ከፊታቸዉ ትልቅ ተራራ እንዳለ ያዉቃሉ። በፊታቸዉ የዮርዳኖስ ወንዝ ያጓራል። በፊታቸዉ ጥልቅ ሸለቆ አለ። ነገር ግን የተራራዉ ርዝመት አላስፈራቸዉም። የዮርዳኖስ ወንዝ ጩኸት አላስደነገጣቸዉም። የሸለቆዉም ጥልቀት ልባቸዉን አላቀለጠዉም።

በየቀኑ ለነጮች ብቻ በተፈቀደ ምግብ ቤት መቀመጣቸዉን ቀጠሉበት። ነገሮች ስለከረሩ ስፍራቸዉን ለቀዉ አልሄዱም። ትግሉን አልሸሹም። ነገር ግን እነርሱ መከራ እየተቀበሉ ለሌላዉ ምሳሌ ሆኑ። በአሥራ አምስት ቀናት ዉስጥ በየከተሞች ለነጻነት የሚደረግ የመቀመጥ ትግል ተጧጧፈ። በመቀመጥ ለመብት መቆም ተቻለ። ስጋ ተቀመጠ ልብ ግን ቆመ። ክፋት ስትበረታ፣ ትዕግስትም ልቃ በረታች። ጥላቻ ስትበረታ፣ ፍቅርም አይላ ወጣች።

አሁንም እኛ ኢትዮጵያዉያን በአገራችን ያለዉን ችግር ለመቅረፍ በቁርጠኝነት የምንነሳበት ጊዜዉ አሁን ነዉ ባይ ነኝ። አሁንም አገራችን ኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ላይ ነዉ ያለችዉ። ተስፋ የቆረጥን፣ የሰላማዊዉን ትግል የተዉንና የማያዋጣ በሌሎች በመተማመን ላይ ያተኮረ የትግል መንገድ የተከተልን አለን። ብዙዎቻችን በ«አይቻልም» መንፈስ ተሞልተናል።

ይሄ መቀየር አለበት። በራሳችን መተማመን አለብን። ከስሜትና ከንዴት በጸዳ መልኩ የሚጠቀመዉንና የሚበጀዉን የሰለጠነዉንና በሕዝብ ጉልበት ላይ የተመሰረትዉን መንገድ መያዝ ይኖርብናል። ከበረታን፣ ከተባበርን ከግብ የማንደርስበት ምንም ምክንያት የለም።

የሰማያዊ ፓርቲ በቅርቡ በጠራዉ አንድነትና መኢአድም በደገፉት የአዲስ አበባዉ ሰላማዊ ሰልፍ፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የፍርሃትን ካባ አዉልቀዉ ድምጻቸዉን ማሰማታቸው ይታወቃል። ሰሞኑን ደግሞ የአንድነት ፓርቲ በሌሎች አንጋፋ የኢትዮጵያ ከተሞች ሕዝብን እየቀሰቀሰ ነዉ። በጎንደርና በደሴ በመኪና ላይ ጡሩምባ በመንፋት፣ ወረቀቶችን በመበተን፣ በየመንደሩ ዜጎችን ፔቲሽን በማስፈረም፣ ሕዝቡ ቀና ብሎ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲነሳ እያደፋፈሩት ነዉ። በዚህም ምክንያት የአንድነት አስተባባሪዎች በመታሰር ላይ ናቸው።ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነዉ።

ነገር ግን የጨዋታዉ ሕግ ተቀይሯል። እንደ ትላንትና ፈርቶ መመለስ ቀርቷል። «ጽ/ቤቶቻችን እስኪዘጉና ሁላችንንም አስረዉ እስኪጨርሱ ድረስ ለመብታችን መጮሃችንን አናቆምም» እያሉ ነዉ አንድነቶች።

እንግዲህ  «ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን» እላለሁ። በደሴና በጎንደር የምንኖር ሁሉ በነቂስ እንዉጣ። በርቀት ያለንም እየደወልን፣ በፌስቡክና በኢሜል በጎንደርና በደሴ ያሉ ዘመዶቻችን ፣ ጓደኞቻችን እንዲወጡ እናበረታታ። በፓርቲዉ የተዘጋጀዉን ፔቲሽን  በመፈረም በመንፈስ የሰልፉ ተካፋዮች እንሁን። የምናወቃቸዉን ሁሉ እናስፈረም። ለትግሉም ያለንን አጋራነት በተግባር እናሳይ።

በመጨረሻ አንድ አስፈላጊ ጉዳይ ላንሳ። በአገር ቤት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ወጭ ይጠይቃሉ። እስከአሁን በብዛት ወጭዉ የሚሸፈነዉ፣  እዚያው አገር ቤት ካሉ፣ የኑሮ ዉድነት ቀንበር ወገባቸውን ካጎበጣቸው ወገኖቻችን  ነዉ። በዳያስፖራ ያለን በአካል ተገኝተን ሰልፍ መዉጣት ባንችልም፣ ቢያንስ በገንዘባችን ድጋፍ መስጠት መቻል አለብን። ኢትዮጵያን የሚወድ እንግዲህ አሁን ይነሳ! ብዙ አወራን ጊዜው አሁን የሥራ ነው!

አንዳንዶች ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቅ ነዉ ይላሉ። ነገር ግን ወገንቼ ይሄ ፖለቲካ አይደለም። ይሄ የመብት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት ጉዳይ ነዉ።

ፔትሽኖች ለመሙላት፣ በገንዘብ ለመደገፍ  እንዲሁም በአገር ቤት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በቅርበት ለመከታተል የሚከተሉትን ድህረ ገጾች ይጎብኙ !

http://www.andinet.org/

http://www.semayawiparty.org/

No comments: