Saturday, July 27, 2013

ታሪኩ ተፅፏል! (ድምፃችን ይሰማ)

July 27, 2013

ጆሮ ያለው ይሰማል! አይን ያለው ይመለከታል! ጆሮ ኖሮት የማይሰማ፣ ዓይን ኖሮት የማይመለከትስ?

Ethiopia Muslims Protestየኢቴቪ ከ‹‹ጥቂቶች›› ወደ ‹‹የተወሰኑ›› የቃል ሽግግር!

እያንዳንዷ ጁምአ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ የሚጻፍባት ገጽ ከሆነች ቆይታለች። ጁምአ የፍትሕ፣ የነጻነትና የህዝብ ድምጽ ቀን ናት ለእኛ። የዛሬዋ ጁምአ ደግሞ በበኩሏ ታሪካዊ ሆና ውላለች። እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በአለም አቀፍ ደረጃ አገሪቱ ውስጥ እየተፈጸመ ላለው የሃይማኖት ጭቆና ድምጹን አሰምቷል። ዛሬ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጠራው አለም አቀፍ ተቃውሞ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እለቱን ስለ ፍትህ በመጣራት ሲያሳልፉት ውለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሃይማኖት ነጻነት እጦት፣ ተደጋጋሚ ፖለቲካዊ ክሶችና እስሮች፣ ሙስሊሞች ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የህገ መንግስት ጥሰት፣ የመስጊድ ቅሚያ እና መታሸግ፣ በመንግስት ሚዲያዎች ሙስሊሞች ላይ የሚሰነዘረው የፕሮፖጋንዳ ጦርነት፣ የመሪዎቻችን እስርና ወዘተ የመብት ጥሰቶችን በአንድ አንደበት ግን በተለያዩ አሕጉራት ሆኖ ለመቃወም የተጠራው የዛሬው ተቃውሞ እጅግ ባማረና ባስደነቀ ትእይንቶች ታጅቦ ተካሄዷል፡፡ በዚህ ሪፖርታዣችን በአገር ውስጥ ብቻ የተካሄዱትን የተቃውሞ መርሐ ግብሮች አፈጻጸም የምናስቃኛችሁ ሲሆን በነገው ሪፖርታዣችን ከአገር ውጪ የተካሄዱትንና ዛሬ ምሽት እንዲሁም ነገ ቀጥለው የሚካሄዱትን የቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ተቃውሞዎች ሙሉ ዘገባ እናቀርባለን፡፡

አዲስ አበባ ገና ከማለዳው ነበር የተለመደ መንገዳቸውን ትተው ወደ ፒያሳው ኑር መስጂድ በሚፈሱ ሙስሊሞች መሞላት የጀመረው፡፡ ለወትሮው በአንዋር መስጂድ ጁምአን ለመፈጸም የሚሄደው ሙስሊም ህብረተሰብ በሚሊዮን ሆኖ የተቃጠረበትን ኑር መስጂድን በማሰብ ነበር ወደ ኑር መስጂድ የነጎደው፡፡ ኑር መስጂድ ከመርካቶ፣ ቦሌ፣ ልደታ ካዛንቺስ እና ፒያሳ አቅጣጫ የሚመጡ ሙስሊሞች ለመሞላት የጁምአ ሰላት መድረስ እንኳ አላስፈለገውም ነበር፡፡ ገና በጊዜ መስጂዱ ሞልቶ ጎዳና ላይ መፍሰስ የጀመረው ሙስሊም በፒያሳ፣ ተ/ሃይማኖት እና አንዋር መስጂድ አቅጣጫ መፍሰሱን ተያያዘው፡፡ ሕዝቡ እንደጉድ ይመጣል፤ ጎዳናውም መሙላቱን ቀጥላል፡፡ ከጁምአ ሁለተኛ አዛን በፊት ወደ ተ/ሃይማኖት የወረደው ሙስሊም በላይ ዋናውን ጎዳና ለመዳረስ ጥቂት ቀርቶት ነበር፡፡

የጁምአ ሰላት እንደተጠናቀቀም ሁሉም በየፊናው የያዘውን መፈክር ከፍ በማድረግ ‹‹አላሁ አክበር›› በማለትና አላህን በማተለቅ ተቃውሞውን አሀዱ አለ፡፡ አንድ ሁለት እያሉ መፈክሮች ተከተሉ፡፡ የአካባቢው ድባብም ተቀየረ፡፡ መብቱ የተነካው ሙስሊም ‹‹ኢ-ፍትሃዊነትን የምሸከምበት ትከሻ የለኝም!›› በማለት እየተፈጸመበት ያለው በደል እንዲያከትም፣ የመንግስት ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት እንዲያበቃ ደጋግሞ በመፈክሩ አስተጋባ፡፡ ደቂቃዎች እየነጎዱ፣ ጾመኛ የሆነው ሕዝብ ሀይልና ወኔ ግን እየጨመረ ነበር የሄደው – እስከ ተቃውሞው መጠናቀቂያ ወቅት ድረስ፡፡ ሙስሊሙ ተቃውሞውን አጠናቆም ዱአውን በማስከተል ወደየአካባቢው መመለስ ጀመረ፡፡ በአካባቢው የነበረው ሕዝብ ብዛት በታሪክ ያልታየና አካባቢውም ሆነ ኑር መስጂድ አስተናግዶት የማያውቅ እንደነበርም በብዙ የአይን እማኞች ምስክርነት ተሰጥቶታል፡፡ የአዲስ አበባውን የኑር መስጂድ ተቃውሞ ለታደመ መንግስት ባለበት ሃገር ዳግም ህዝባዊ ተቃውሞ መጥራት እንደማያስፈልግ ይረዳል። የህዝብ ሃላፊነት ድምፁን ማሰማቱ፣ የመንግስት ግዴታው ደግሞ የህዝቡን ድምፅ ማድመጡ ነውና። መቶ ሺዎች በአዲስ አበባ ብቻ ሲጠሩት ያልሰማ መንግስት የቱን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ይሆን? ህዝብስ መብቱን እንዴት እንዲጠይቀው እየገፋፋ ይሆን?

በህብረተሰብ ስብጥር እና በማህበረ ፖለቲካው ረገድ ትልቅ ግምት የሚሰጣት ሻሸመኔ በልዩ ትኩረት የምትታይ ነች። በዚህች ከተማ የሚኖር መልካምም ሆነ መጥፎ ተሞክሮ እጅግ በርካታ በሆኑ የከተማና የገጠር ቀበሌዎች ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ አለው። እናም ሻሸመኔዎች ድምፃቸውን የወታደር ከበባ ጥሰው ሲያሰሙ የሃይል እርምጃ ፈፅሞ እንደማያዋጣ እና መዘዙም የከፋ መሆኑን በዙሪያቸው ባሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ስም እያስደመጡ ነበር። በከተማዋ አል ሂከም መስጂድ ዛሬ የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ ፌደራል ፖሊሶች መሰጂዱን ከበውት የቆዩ ሲሆን ህዝበ ሙስሊሙ ያካሄደው ሰላማዊ ተቃውሞ ከተጠናቀቀ በኋላ መስጂዱን ለቆ ለመውጣት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ወደ ቤቱ ለመመለስ የሚወጣውንም ሕዝብ ፖሊስ ሲያፍን የነበረ በመሆኑ ሙስሊሙ እስከ አስር ሰላት ድረስ በመስጂዱ ለመቆየት ተገዷል፡፡ ከአስር ሰላት መጠናቀቅ በኋላ ህዝበ ሙስሊሙ በጋራ በመሆን ከመስጂድ ቢወጣም ፖሊስ ግለሰቦችን ነጥሎ ያስር እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

በሂላል መስጂድ የተሰባሰቡ የአጋሮ ከተማ ሙስሊሞች አንደባለፈው ሳምንት ተቃውሞውን ለሴቶች ብቻ ከመተው ይልቅ በወንዶች በኩል የሳምንቱን በደል ለመካስ ሲሰባሰቡ ሴቶች ማንም ዝም ቢል ዝም ላይሉና ታሪክ ለመድገም ቃል ተግባብተዉ ነበር የመጡት፡፡ ዉጤቱ ወንዶች በደላቸዉን ሲክሱ ሴቶችም ወንዶችን አንድ እርምጃ በመቅደም በጀግንነት መዝገባቸዉ ላይ ስማቸዉን በደማቅ ቀለም ለሁለተኛ ግዜ አስመዝግበዋል፡፡ የመንግስት ኢማሞች ሕዝቡን ለማስፈራራት ቢሞክሩም ‹‹መብቴን ተነጥቄ ዝም አልልም›› ያለው የአጋሮ ሕዝብ ከሰላት መጠናቀቅ በኋላ በተክቢራ የጀመረውን ተቃውሞ በሌሎች መፈክሮች ታጅቦ በሰላም አጠናቆታል፡፡ የአጋሮ ድምፆች በመላው ሀገሪቱ የተሰሙ የመብት ጥያቄ ድምፆችን ተቀላቅለው ኢትዮጵያዊ ህብር ሰርተው ከተማው ደምቆ ውሏል።

በኦሮሚያዋ መቱ የነበረው የተቃውሞ ትእይንትም ልዩና የአገሬው ሕዝብ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች እንደሚገኙት ሙስሊሞች ፍትህ መነጠቁን የመሰከረበትና ለፍትህ እንደሚሟገት ያሳየበት ነበር፡፡ በከተማዋ ዋና መስጂድ ነጃሺ የተገኘው በርካታ ሕዝብ በእልህና በንዴት በተናጠ ገጽታ መሪዎቻችን እንዲፈቱ፣ መንግስት ሕገ መንግስቱን እንዲያከብር፣ ሙስሊሞችን መጨቆን እንዲያቆም ጠይቋል፡፡ በመቱ የነበረው ተቃውሞም የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ድምፅ ሃገራዊ ጥሪ መሆኑን ለሚያስተባብሉ ሁሉ ተግባራዊ ምላሽ የሰጠ ደማቅ ተቃውሞ ነበር።

በደሌም ታላቅ ተቃውሞ አስተናግዳ ነበር፡፡ የኢሊባቡር ዞኗ በደሌ በረህማ መስጂድ ሲሆን በበደሌ ከተማ እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ በጣም ብዛት ያላቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ሰላማዊ ተቃውሞ አከናውነዋል፡፡ የዛሬው የበደሌ ተቃውሞ የተለያዩ መፈክሮች የተስተጋቡበት ሲሆን፤ ከግማሽ ሰዓታት በላይም ቆይቷል – እንደ ዘገባዎች፡፡ በኢሊባቡር ዞን በምትገኘውና ከበደሌ ከተማ 36 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ጮራ ከተማ ከረጅም ጊዜ ዝምታ በኋላ ተቃውሞ ተካሂዶባታል፡፡ የድምጽ ተቃውሞ በተካሄደባት በጮራ ከተማ ትዕይንቱ በሁለት ቀበሌዎች በሚገኙ በፈትህ እና በኑር መስጂዶች መካሄዱን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

በኢሊባቦር ዞን በገቺ ከተማም እንዲሁ ከጁምአ ሰላት በኋላ ከባድ ተቃውሞ ተደርጓል:: የገቺ ከተማ ህዝበ ሙስሊም ተቃውሞውን እንዲያቆም የከተማው የፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች የከተማውን ሽማግሌዎች እና የከተማዋን ህዝብ ለያይተው ስብሰባ በመጥራት ማስፈራራታቸው የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ጁምአ ግን ማስፈራሪያው ቦታ እንደሌለው በተግባር አሳይተዋል፡፡ በከተማዋ የፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች የተደረገው ማስፈራራት ሳይበግረው የገቺ ከተማ ህዝበ ሙስሊም እልህ እና ወኔ በተሞላበት ሁኔታ ከበፊቱ ይበልጥ በነቂስ በመውጣት ድምፁን ሲያሰማ መዋሉን ምንጮቻችን ዘግበዋል፡፡ የጁምአ ሰላት ከመሰገዱ በፊትም ለኮሚቴዎቻችን ዱአ የተደረገ ሲሆን በመስጂዱ የተገኘው ህዝበ ሙስሊምም በለቅሶ እና በእምባ ‹‹አሚን›› ሲል እንደነበር ተሰምቷል፡፡ በተካሄደው ተቃውሞ የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን የተለያዩ መፈክሮችም ተብለዋል፡፡

ጅማዎች በፖሊስ ተከበው በዋሉበት በዛሬው ጁምአ የፈጸሙት ጀግንነት በቃላት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በከተማዋ ፈትህ መስጂድ ከረፋዱ ጀምሮ ከቧቸው የነበረውን ታጣቂ ሀይል ሳይሰጉ ወደ መስጂድ አል ፈትህ ያመሩት ጅማዎች የሰላት መጠናቀቅን ተከትሎ በነፍስ ወከፍ ያዘጋጁትን መፈክር ከፍ አድርገው የድምጽ ተቃውሞአቸውን ጀመሩ፡፡ ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› ከሚለው መፈክር ተነስተው ‹‹አሻእቡ ዩሪድ ኢስቃጠል መጅሊስ›› የሚለውን መፈክር አቋርጠው ለታሳሪ ኮሚቴዎቻችን ጥብቅና እንደሚቆሙ ከፍ ባለ ድምጽ መስክረዋል፡፡ ‹‹መብትን በማሰር መንጠቅ አይቻልም!›› እያሉም ለመንግስት ግልጽ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የጅማ የመብት ታጋዮች የእነሱን፣ በዙሪያቸው ያሉ ከተማ እና ገጠር ቀበሌዎችን ድምፅ ይዘው ሲወጡ ድምፃቸው ሃገራዊውን ተቃውሞ በሚደንቅ ውበት ተቀላቅሎ ውሏል።

ብዙዎች ‹‹ያልተጠበቀ ጀግንነት ነው›› ያሉት የወልቂጤው አስደማሚ ተቃውሞ ደግሞ እጅግ ውጥረት በሞላበትና የጦር ቀጠና በመሰለ ከባቢ ውስጥ በድምቀት ተካሂዷል። ወልቂጤዎች በዲናቸው የማይደራደሩ መሆናቸውን ለሚያውቅ ግን ‹‹ታሪክ ራሱን ደገመ›› እንጂ ሌላ አይልም፡፡ ውጥረት ነግሶበት የተከናወነው የወልቂጤው ተቃውሞ ባልተጠበቀው የህዝብ ማዕበል የበድረዲን መስጂድ ሜዳ በከተማው ሙስሊም ተጨናንቆ የጁመዓን አለም አቀፍ ተቃውሞ በከፍተኛ ድምቀት አከናውኗል፡፡ የጁመዓ ሰላት እንደተጠናቀቀ በተክቢራ የደመቀው በድረዲን መስጂድ ወዲያው ነበር ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ልዩ ሀይሎችና ፖሊሶች የተከበበው፡፡ ከበባውን ተከትሎ የተቃውሞው ድምፅ ከመቼው ጊዜ በበለጠ ከፍ ብሎ መሰማት ቀጠለ፡፡ ‹‹ጥያቄው ይመለስ!››፣ ‹‹ኮሚቴው ይፈታ!››፣ ‹‹ድምጻችን ይሰማ!››፣ ‹‹በአቋማችን እንፀናለን!›› እና ሌሎች መፈክሮች ተስተጋቡ፡፡ በስተመጨረሻ ህዝቡ ተቃውሞውን አጠናቆ አካባቢውን ከበውት የነበሩትን ልዩ ሀይሎችና ፖሊሶችን በመሀል ሰንጥቆ በማለፍ ከመስጂዱ ወጥቷል፡፡ ሆኖም ወደ 10 የሚጠጉ ሙስሊሞች መታሰራቸው የተሰማ ሲሆን ከፊሎቹም ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተዘግቧል፡፡

ምእራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ በዶዶላ ወረዳ ስር በሚገኘው ሄረሮ ከተማ በሦስት መስጂዶች ዛሬ ከጁምዓ ሰላት በኋላ ከፍተኛ የሆነ የድምፅ ተቃውሞ መደረጉና በሰላም መጠናቀቁም ተነግሯል፡፡ ተቃውሞው የተደረገው በኡሙ ቱርኪ ትልቁ መስጊድ፣ በቢላል መስጊድና በሳፊ መስጊድ ሲሆን በተቃውሞው ላይ ጎልተው ከተሰሙት መፈክሮች መካከል ‹‹አላሁ አክበር!››፣ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!››፣ ‹‹ኮሚቴው ይፈታ!››፣ ‹‹መጅሊስ አይወክለንም!››፣ ‹‹ድራማው ይብቃ!››፣ ‹‹ህገ-መንግስቱ ይከበር!›› እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ሕዝቡ በተያዘው መርሀ ግብር መሰረት ተቃውሞውን አሰምቶም በሰላም ወደ መጣበት ተመልሷል፡፡

የሰሞኑ የፓሊስ እስር፣ ፍተሻ፣ ማስፈራራት፣ ዘመቻ እና የመንግስታዊው እስልምና ተከታታይ ፕሮፓጋንዳ ያልገደበው የወራቤ ሙስሊም የተቃውሞ መርሃ ግብሩን በብቃት አሳክቶ በድል ወደቤቱ ተመልሷል፡፡ በወራቤው ተቃውሞ ህጻን፣ አዋቂ፣ ሴት፣ ወንድ ሳይለይ በጋራ ‹‹ፍትህ ይከበር!›› ድምጹን ያስተጋባ ሲሆን የአካባቢው አስተዳደሮችም ሁከት በመፍጠር የተወሰኑ ሙስሊሞችን ለመያዝ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ነቀምቴዎችም በአለም አቀፉ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ እለት ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ጋር በዱዓ ተቃውሞ ተቀላቅለዋል። ከእነዚህ ከተጠቀሱት ከተሞች በተጨማሪ በሌሎች በርካታ ከተሞች ከበር መልስ የዱአ እና የመሰባሰብ ተቃውሞዎች ተደርገዋል፡፡

ይህ ህዝብ ድምጹን እንክን የለሽ በሆነና በሰለጠነ ሰላማዊ መንገድ እያሰማ ቢሆንም እስካሁንም ግን በመንግስት ባለስልጣናት ‹‹ጥቂት›› እየተባለ ከመሸርደድ፣ ‹‹አክራሪ›› እየተባለ ከመሸንቆጥ አለማለፉ ለብዙዎች የሚያሳዝናቸው እውነታ ሆኗል። ‹‹ጥቂት›› የሚለው ቃል ሌላ አዲስ ትርጉም የተበጀለት ይመስላል። በቀበሌ ካድሬዎች ማስፈራሪያ ተገደው ለሰልፍ የሚወጡ አንድ እፍኝ የማይሞሉ ሰዎችን ‹‹የእገሌ ከተማ ሙስሊም ህዝብ›› እያለ የሚያጭበረብረው ኢቲቪ የአዲስ አበባንና የሌሎች ከተሞችን ጎዳናዎች ሞልተው የፈሰሱና በየሳምንቱ ድምጻቸውን የሚያሰሙ ሚሊዮኖችን ግን ‹‹ጥቂት አክራሪዎች›› ለማለት አያመነታም። ዛሬ ደግሞ ይሄ ቃል ‹‹የተወሰኑ›› ወደሚል ቃል ተለውጦ አይተነዋል፡፡

መንግስት ሁለት አመት ሙሉ የሄደበትን የሀሰት አዘጋገብ በመከተል ሕዝቡን የተወሰነ ከማለቱ በተጨማሪ ሕዝበ ሙስሊሙን በጸረ ሰላምነትና ኢትዮጵያዊነት የማይሰማቸው ዜጎች አድርጎ ለማቅረብ ጥረት አድርጓል፡፡ ዛሬ በአንዋር መስጂድ የተቃውሞ ፕሮግራም ያልነበረ ቢሆንም የተቃውሞ ፕሮግራም እንደነበርና ሰላማዊው ህዝብ የመንግስትን ንብረት አወደመ ብሎ እጅግ አሳፋሪ ዜና ለሕዝቡ አቅርቧል፡፡ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ መሰሉ የሀሰት ዜና የማይደለል ቢሆንም መንግስት እውነታውን ከማውራት ይልቅ በዚህ አይነቱ ‹‹አልሰማም አላይም›› ሁኔታ መቀጠሉ እንደ አገሪቱ ዜግነታችን በጣም ያሳስበናል፡፡ አንድ መንግስት የህዝቡን ልብ ትርታ በትክክል ለማዳመጥ ከዚህ የተሻለ ምን እድል ሊያገኝ ይችላል? የህዝበ ሙስሊሙን ፍላጎት በትክክል ለማወቅስ ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ ይኖር ይሆን?

አዎን! የዛሬዋም ጁምአ ‹‹ህዝብን ማሸነፍ አይቻልም!›› የሚል መልእክቷን ነው ያስተላለፈችው! እናም ህዝብን ማሸነፍ አይቻልምና በከንቱ አትድከሙ። የሃይል እርምጃም ሆነ የግዳጅ ጠመቃ እንዳላዋጡ ለማየት የዛሬውን ተቃውሞ ብቻ ማየት ይበቃል። አዎን! እኛ ለምትወስዱብን የሃይል እርምጃ ምንዳችንን አናጣውም… ትግላችን ለፍትህና ለነጻነት እሴቶች ነውና! እናንተ ሰላማውያንን በመደብደብና በመግደል እያጣችሁት ያለው ተቀባይነትና እያተረፋችሁት ያለውን የህዝብ ቁጣ ግን በምን ታካክሱት ይሆን!?

አላሁ አክበር!

No comments: