Monday, July 29, 2013

የዘመኑ መንፈስ (በእውቀቱ ስዩም)

July 29, 2013
በእውቀቱ ስዩም
Bewketu Seyoum is a young Ethiopian writerባገራችን ባሁኑ ጊዜ ብዙ ተከታይ ያለው ሃይማኖት ብሄርተኝነት ይባላል፡፡የብሄርተኝነት ምእመን ከሆንክ የነፍስ አባት ይኖርሀል፣በጭፍን የምትቀበለው ቀኖና ይኖርሀል፣ነገ የምትገባባት የተስፋ ምድር ይኖርሀል፣ከሁሉ በላይ ደግሞ ብርቱ ችግርህን የምትደፈድፍበት የመስዋእት በግ ይኖርሀል፡፡

ሃይማኖቶች ምእመናንን ብቻ ሳይሆን መናፍቃንንም ያፈራሉ፡፡ብሄርተኞች በስሜት የሚነድደውን ምእመን ብቻ ሳይሆን የኔ ቢጤውን መነፍቅም እንደሚያፈሩ አንርሳ፡፡በነገራችን ላይ ሃይማኖትን መካድ ማለት ሃይማኖት የሚያነሳቸውን አብይ ጥያቄዎች መካድ ማለት አይደለም፡፡እንዲሁም፣ ብሄርተኝነትን መካድ ማለት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ህልውና መካድ ማለት አይደለም፡፡በዚህ ጉዳይ ፣መናፍቅ መሆን ማለት፣ የብሄርተኛ ነቢያት ሰለ ጭቆና ስለ ነጻነት ብሎም ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀርቡትን አጉል እምነት መጠራጠር ማለት ነው፡፡

ከኢትዮጵያዊነት እንጀምር፡፡

ከዘመናችን የብሔርተኝነት ነቢያት አንዱ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ከእንቁ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ላይ ስለኢትዮጵያዊነት የሚከተለውን ይላል፡፡

‹‹…ኢትዮጵያን የመሠረታት የሶሰትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡በአማራው፣በኦሮሞው፣በትግሬው ግብግብ ውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡በዚህ የተነሳ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭት እና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡…የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት የምንለው የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው››
ጃዋር የኢትዮጵያን መሠረት የሦስት ብሄረሰቦች የስልጣን ግብግብ አድርጎ ወስኖታል፡፡ በመጀመርያ፣ ሌሎች ብሄረሰቦች በግብግቡ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አድርጎ ማቅረቡ አንድ ጉድለት ነው፡፡

 ግን ዋናው ቁምነገር ይሄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የግጭት ውጤት ብቻ እንደሆነች አድርጎ ማቅረቡ ነው ትልቁ ስሕተት፡፡ ሲጀምር፣ የግብግብ ታሪክ መሠረት ይንዳል እንጂ መሠረት አይገነባም፡፡ እንደኔ ግምት፣የኢትዮጵያ መሠረት የሆነው ብሄረሰቦች ለጋራ ሕልውና ሲሉ የሚያደርጉት የመደጋገፍ ታሪክ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ፣ ታሪክ ከላሾች፣የብሄሮችን የ‹‹ግብግብ››ታሪክ ሞቅ አድርገው፣አኳሽተው ሲጽፉ፣የብሄሮች መደጋገፍ ታሪክን ግን ቸል ይሉታል፡፡ አለያም እጅግ በቀዘቀዘ ስሜት፣ በጥቂት መስመሮች ብቻ ጨረፍ አድርገው ያልፉታል፡፡ለነገሩ፣ከፋፋይነትን ብቸኛ ያስተዳደር ፈሊጥ አድርጎ የሚቆጥር ሰው በታሪክ ገጾች ውስጥ መመልከት የሚፈልገው ክፍፍልን ብቻ ነው፡፡ታሪክ ግን ብዙ በጎ የትብብር ገጠመኞችን መዝግቧል፡፡ለምሳሌ ጀግናው አጼ ዮሐንስ አራተኛ በበዛሬይቱ ኤርትራ የግብጽን ወራሪ ጦር ድል የነሡት የትግራይ ጀግኖችን ብቻ አሠልፈው አልነበረም፡፡ በዚህ ጦርነት ከግብጽ ጎን ሆኖ፣የተዋጋው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይ እንደመሠከረው ወልቃይቶች፣ጥልጣል የተባሉ የአፋር ንኡስ ክፍሎች፣የወረኢሉ ኦሮሞዎች ለንጉሰነገስቱ ድጋፍ ለማድረግ ተሸቀዳድመዋል፡፡በራስ ወሌ የሚመሩ የአማራ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡የጎንደር ቀሳውስት ለጦርነቱ ድጋፍ ለማድረግ አድዋ ገብተዋል፡፡ የጎጃሙ ራስ አዳል የደርሼልሀለሁ አለኝታቸውን አሳይተዋል፡፡ የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ሳይቀር በመቶ የሚቆጠሩ በቅሎዎችንና ማበረታቻ ልከዋል፡፡ ዝርዝሩን ማንበብ ለሚፈልግ Muslim Egypt Christian Abyssinia የተባለውን የዚህ ደራሲ ማስታወሻ ገጽ 291-292 ያንብብ፡፡ መጽሐፉን በኢንተርኔት ቤተ-መጻህፍት ውስጥ በብላሽ ማግኘት ይቻላል፡፡

ከተለያየ መአዘን የመጡ እኒህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ቃላት ይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደ አረቄ ይወጣል፡፡ ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹‹የአማራ ባህል ››ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለው አይመስለኝም፡፡
ጃዋር‹‹አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭትና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች›› በማለት ሳይወሰን ‹‹የኢትዮጵያ አገራዊ መለያ ማንነት የምንለው አማራ ብሄራዊ ማንነት ነው›› ሲል ይጨምራል፡፡ ጎበዝ ኧረ በህግ አምላክ!!! የኢትዮጵያ ባህልኮ ካንድ አለት የተጠረበ ሕንጻ አይደለም፡፡ ከብዙ የመዋጮ ጡቦች የተገነባ ነው፡፡ ጃዋር እያንዳንዱን ጡብ ቀርቦ ቢመረምረው እዚህ የደረሰበት እርግጠኝነት ውስጥ የሚደርስ አይመስለኝም፡፡

እስቲ ከደቃቅ ምሳሌ እንጀምር፡፡ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡና ስነ-ስራታችን ነው፡፡ አንዲት ጠይም ፣ባለሹርባ ሴት፣ያበሻ ቀሚስ ለብሳ ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስል በየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ይህ ችክ ያለ ምስል በስነ-ስእል ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ቢዮንሴና ጆን ኬሪ አገራችንን በጎበኙበት ሰአት የቡና ስነስርአት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡና ስርአታችንን እንደ ኢትዮጵየዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው፡፡ ለዋለልኝ መኮንን እና ለጃዋር መሀመድ ይህ የአማራ ባህል መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ እይታ ይመስላል፡፡ ጉዱ ዝርዝሩ ላይ ነው፡፡ የሴትዮዋ ሹርባ ከሐማሴን ወይም ከተንቤን ሴቶች ልማድ ጋር ስምም ነው፡፡ ያበሻ ቀሚሱን የሽሮሜዳ ጋሞ የሸመነው ሊሆን ይችላል፡፡ ጀበናው የጂማ ሙስሊም ኦሮሞዎች ያስተዋወቁት ነው፡፡ አቦል ቶና በረካ አረብኛ ወይም የተወላገደ አረብኛ የተገኙ ቃላት ናቸው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ትንሳኤ በአል በሉባንጃ የሚታጀብ ቡና የማያፈላ ክርስትያን ኢትዮጵያዊ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ከጥቂት መቶ አመታት በፊት ግን ቡና የእስላም ልማድ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ የቡና ትርኢት የሙስሊም አበው በኢትዮጵያ ባህል ላይ የጨመሩት በጎ መዋጮ እድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ጊዜ በተባለው አናጢ ከብዙ ጡቦች የተገነባች ናት የምንለው ለዚህ ነው፡፡

ጃዋር አማራው የራሱን ባህል በኦሮሞው ላይ እንደጫነ ሲያምን ተገላቢጦሹ ያለው አይታየውም፡፡ ኦሮሞ በረጅም ዘመን፣በሠፊ ምድር፣ ሰፍሮ የመኖሩን ያክል በጎረቤቶቹና በወደረኞቹ ላይ የባህል ተጽእኖ አላሳደረም ማለት ብርቱ ባህል የለውም ከማለት አይለይም፡፡ ባገራችን ዋና ዋናዎቹ የባህል ቀራጺዎች ጦርነትና ሐይማኖት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፣ጀግኖችን እና ነገስታትን አባ በዝብዝ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኘው አባ ነጋ ወዘተ እያሉ መሰየም ገናና ኢትዮጵያዊ ባህል መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ብዙዎቻችን የማናውቀው ይህንን ባህል ያስተዋወቁት ለግማሽ ምእተአመት ያክል ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ነው፡፡
ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ቼ በለው በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እንዲህ በማለት ያረጋግጣሉ-
‹‹ነገስታቱ በ‹‹አባ›› ወይም የእገሌ ባለቤት በሚል ቅጽል ስም መጥራት የጀመሩት የኦሮሞዎችን ወይም የወረሸሆችን ልምድ በመከተል ነው ከ1838 ዓም ወዲህ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ወትሮ ግን በተለይም 1474-1713 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ቅብዓ መንግሥቱ በሚደረግላቸው ሰአት ይወጣላችው የነበረው የግርማ ስም ወይም ስመ መንግስት ‹‹ሰገድ›› የሚል ኃይለቃል በመጨመር እንደነበር ቀጥሎ ያለው ያረጋግጣል፡፡ ወናገድ ሰገድ፣ አጽናፍ ሰገድ፣ አድማስ ሰገድ፣ መለክ ሰገድ፣አድያም ሰገድ ሉል ሰገድ››በማለት ይዘረዝራሉ፡፡

ከጥቅሱ ሦስት ፍሬ ነገሮችን መረዳት ይቻላል፡፡

1- ይህ ባህል ባንድ የዘመን ምዕራፍ ላይ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የመነጨ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡
2- ባህሉ ብርቱ ተጽእኖ ከመፍጠሩ የተነሳ አማራና ትግራይ ነገስታት ለረጅም ዘመን ይጠቀሙበት የነበረውን የስያሜ ዘይቤ ሽሯል፡፡
3- አማራው ታሪክ ጸሀፊ ለባህሉ አስተዋዋቂዎች የባለቤትነት እውቅና ሰጥተዋል፡፡

በሃይማኖት ረገድም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚገጥመን፡፡ ለምሳሌ አቴቴ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድ ሲተረጉሙ ‹‹ዛር፣በሴት ስም የምትጠራ፣ ውቃቤ ፣ አማሮች ከኦሮሞዎች የወረሷት ጨሌ የሚያጠልቁላት አቴቴ ጊንቢ ሐራ አቴቴ ዱላ እያሉ እንቀት የሚቀቅሉላት አምልኮ ባእድ፣ትርጓሜ ጠባቂ ማለት ነው››ይላሉ፡፡

‹‹አምልኮ ባእድ ››የሚለውን አሉታዊ ሐረግ፣የክርስትያን አድልኦ ያለበት ፍርድ አድርገን እንለፈው፡፡ ዋናው ፍሬ ነገር፣ የአሮሞው ባህል በአማራው ባህል ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ማወቃችን ነው፡፡ ይህም አንዱ ብሄረሰብ ሁልጊዜ ጫኝ ፣ ሌላው ብሄረሰብ ሁልጊዜ ተሸካሚ እንደነበረ አድርገው ሊነግሩን የሚፈልጉትን ሰዎች ያስተባብላል፡፡ በሁለቱ ግዙፍ ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ግኑኝነት የእኩዮች ልውውጥ ነው፡፡ የባህሎች ውርርስ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ የማንኩሳ ዘመዶቼ የሚያስደነግጥ ነገር ሲገጥማቸው ‹‹አቲቲን ወሰድከው›› ይላሉ፡፡ ቀልቤን ገፈፍከው ለማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ባህላዊ ተጽእኖ በወለጋ ድንበር ላይ ቆሟል ያለው ማነው?

ስለጉዲፈቻ ባህል ብዙ ሰዉ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ በጦርነት ወቅት ምርኮኞችን ባርያ ማድረግ ወይም መግደል በብዙ ማህበረሰቦች የተለመደ ነው፡፡ በኦሮሞ አበዋዊ ባህል ውስጥ ግን ምርኮኞች በልጅነት ይታቀፋሉ፡፡ ከሌላ ብሄረሰብ ቢመጡም የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚያገኘውን መብት ሳይነፈጋቸው ያድጋሉ፡፡ ይህንን ልማድ በአማራው ማህበረሰብ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡
 ለምሳሌ በጎጃሙ ንጎስ ተክለይማኖትና በወለጋ መሳፍንት መሀል በተደረገው ጦርነት የተማረከው ብላቴና ነገሮ ዋቅጅራን እንደልጅ አሳድገውታል፡፡ ክርስትና አስነስተው ተክለኢየሱስ አሰኝተውታል፡፡ ራሱ በጻፈው ማስታወሻ ‹‹በጠጅና በስጋ አደግሁ›› በማለት የመሳፍንት ልጆች ያገኙት የነበረውን ምቾት ሳይነፈገው ማደጉን ይመሰክራል፡፡ ነገሮ ፣ ከማእረግ ወደ ማእረግ እየወጣ የንጉሱ ጸሐፌ ትዝዛዝ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ተመሳሳይ መልኩ በሸዋ ምርኮኛው ቆሴ ዲነግዴ በቤተመንግስት እየተቀማጠለ አድጎ ሐብተጊዎርጊስ በሚል ስመ ክርስትና የኢትዮጵያ የጦር ምኒስትር እስከመሆን ደርሷል፡፡ ሰዎችን በልዩ ቋንቋቸው ምክንያት ባይተዋር ማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህል አልነበረም፡፡

እኩዋን ባህላችን አማርኛችን እንኳ የጉራማይሌነታችን ምስክር ነው፡፡ አሁን ኦሮምኛ ያልተነካካ አማርኛ ማግኘት ይቻላል?፡፡ እሰቲ ለናሙና ያክል ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› ከተባለው የዮሐንስ አድማሱ ምርጥ የአማርኛ ግጥም ውስጥ ጥቂት መስመሮች ልቆንጥር፡፡

1) ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ
2) ሜዳና ተራራ በመሐል ሸለቆ
ጨፌውና መስኩ በኒህ ተደብቆ
3) ሐቀኛ ጠፍቶበት በዋለበት መልቲ
ጌጥ ነው ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ
4) ብልጭ ብሎ ጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ የሐሳብ አንጋፋ
በመረጥኳቸው መስመሮች ውስጥ የሚገኙት ‹‹ይፋ፣ ጨፌ፣ መልቲ፣ ሎቲ፣ አንጋፋ፣›› የተባሉት ቃላት ኦሮሚኛ ናቸው፡፡ ካንድ የአማርኛ ግጥም ይህን ያህል ኦሮሚኛ ከተገኘ በሙሉ መዝገበ ቃላት ውስጥ ምን ያህል ሊገኝ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህን ያክል ነው የተዋሀድነው፡፡

የኢትዮጵያ ባህል የተውጣጣ ባህል እንጂ ጃዋር እንደሚለው የአማራ ባህል ብቻ አለመሆኑን በመጠኑም ቢሆን ያሳየሁ ይመስለኛል፡፡ ጃዋርን እዚህ ላይ ላሰናብትና ለማጠናቀቂያ የምትሆን አንዲት አንቀጽ ልጨምር፡፡

ባህልን ማክበር ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በስሜት ሚነድደው የብሄርብሄረሰብ ፖለቲካችን፣ ዜጎች ለባህል ያላቸውን ፍቅር ወደ ጭፍን አምልኮአዊ ፍቅር እያዘቀጠው ነው፡፡

ባባቶቻችንና በእኛ መካከል የባህል ፋይዳ ልዩነት ያለ ይመስለኛል፡፡ አባቶች ባህላቸውን ያገኙት በኑሮ ጣጣ አስገዳጅነት ነው፡፡ ለምሳሌ የኔ አያት ቁምጣ ሱሪ የሚታጠቀው ከሌሎች ብሄረሰቦች ለየት ብሎ ለመታየት አይመሰለኝም፡፡ በቂ አቡጀዲ ስላላገኘ ነው፡፡

 ወይም ለስራ እንዲያመቸው ባጭር መታጠቁ ይሆናል፡፡ እኔ ግን የብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ቁምጣ ለብሼ ራሴን በማስጎብኘት እንድኮራ ይጠበቅብኛል፡፡ ጉድ እኮ ነው!!! ጋቢ በጥንት ጊዜ የሙቀት ምንጭ ነበር፡፡ ዘንድሮ የኩራት ምንጭ ሊሆን ይቃጣዋል፡፡

የዛሬዎቹ ባህል አምላኪዎች ባህል ሲያስቡ ለውጥን ይረሳሉ፡፡ ባንድ ወቅት የሚያኮራው ያንድ ብሄረሰብ ባህል በሌላው ወቅት ይናቃል፡፡ ባንድ ወቅት የሚያስሸልመው በሌላ ጊዜ ያስቀጣል፡፡ ከጥቂት መቶ አመት በፊት ዝሆን መግደል በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የሚያጎናጽፍ ተግባር ነበር፡፡ ዝሆን የገደለ ልዩ አምባር ክንዱ ላይ ያጠልቃል፡፡ እስኪ ዛሬ ያባቶቼን ባህል ለማክበር ነው ብለህ ፓርክ ውስጥ አርፎ የተኛውን ዝሆን ግደል፡፡ በአምባር ምትክ ካቴና ይጠልቅልሀል፡፡

የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት የተባለውን የተደጋገመ ግን ያልታሰበበት ቃል ከዚህ አንጻር ቃኙት፡፡ ሲጀምር ፣ዛፍ እንኳ ቅርፊቱን በሚቀያይርበት ዓለም፣ብሄር ብሄረሰቦች በየጊዜው አልባሳታቸውን አይቀያይሩም ወይ?፡፡ የብሄረሰቡ አልባስ ሲባል በየትኛው ዘመን የሚለበሰው ነው? የእንዳለጌታ ከበደ እናት ሲነግሩን፣ ዛሬ በጉራጌ ዘፈን ላይ በቲቪ የምናየው የሴቶች ሻማ ቀሚስ በደርግ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ሸማ ነው፡፡ ከሸማው በፊት ደግሞ የቆዳ ቀሚስ ይለበስ ነበር፡፡

ሌላው፣ አንድ ማህበረሰብ አልባሳት በየማእረጉ ልዩ ልዩ ልብሶች ይኖሩታል፡፡ ወታደሩ ያባ ገዳውን ልብስ የሚለብስ አይመስለኝም፡፡ ባሮች ከጌቶች ልብስ ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንዲለብሱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ በፊውዳል ማህበረሰብ ከላይ አስከታች መልበስ መከናነብ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ ይህንን በሸዋና በትግራይ ብቻ ሳይሆን በቅድመ ምኒልክ ከፋ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ባንጻሩ፣ባሮች በከፊል ተራቁተው መታየት አለባቸው፡፡ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አለባበስ በበሄረሰብ ላይ ሳይሆን በመደብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ የብሄር አልባሳት የሚባለው እንደ ማንኛውም ሾላ በድፍን ሐሳብ በጥርጣሬ መታየት አለበት፡፡

ትውልዱ የባህል ፈጣሪ መሆን ሲገባው፣የባህል ሙዚየም ሆኖ ተተክሏል፡፡አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ባንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ካባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ፣ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል››

ማሳረጊያ

ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ያቆያት የነገስታቱ ጉልበት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያ የተሸመነችበትን ውስብስብ ክር ማየት ያልታደሉ ናቸው፡፡ዛሬ ኢትዮጵያን በታትነን ክልላችንን እናድናለን ብለው ባደባባይ ሳያፍሩ የሚናገሩ ሰዎችን የምናይበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ ማእበል ከበረታባት እንደ ታይታኒክ ትሰጥም ይሆናል፡፡ግን መርከቢቱ ስትሰጥም የመርከቢቱ ሳሎን ብቻውን አይንሳፈፍም፡፡የመርከቢቱ ጓዳ ብቻውን አይተርፍም፡፡ኢትዮጵያ ስትከስም ብሄሮች ተነጥለው ይለመልማሉ ማለት ተፈጥሮ አመሏን እንደ ግትቻ የትም ጥላለች ማለት ነው፡፡

No comments: