Thursday, July 25, 2013

የሰማያዊ ፓርቲ እንቅስቃሴ የወያኔን ቁንጮዎች ስጋት ላይ ጥሏል

july 25, 2013


ህዝብን ለማስፈራራት በታቀደ መለኩ እንደተለመደው የወያኔ ባለስልጣናት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እጅግ ስላሰጋቸው የሰማያዊ ፓርቲ እንቅስቃሴ የሚከተለውን አስፍረዋል፣
ye semayawi party selamawi self
የሰማያዊው ፓርቲ ጥቁር ተግባራት
ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ያቀረባቸው ጥያቄዎች የተሰላፊዎች ጥንቅርና መሰረታዊ ዓላማ በእጅጉ አነጋጋሪ ለሆኑ ጉዳዮች መነሻና መንደርደሪያ ሆነውኛል።
ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድነት ፓርቲ ባለመስማማትና በልዩነት ራሳቸውን ያገለሉ፣ መርህ ይከበር በሚል ተሰባስበው የነበሩ ግለሰቦች የመሰረቱት ፓርቲ ነው፡፡ ወደ ኋላ ስንመለስም በ1997 ዓ.ም ቅንጅትን ከመሰረቱትና የከሸፈውን አመጽ በማስተባበርና በመምራት ከፊትና ከኋላ የነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ የቀድሞውን ማንነታቸውን ሳይለቁ በአዲስ መልክና በአዲስ ኮፍያ ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ያሉ ናቸው፡፡
አንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ሕገ መንግስቱ በሰጠው መብት በሰላምና በሕጋዊ መንገድ ሕጉንና ስርዓቱን አሟልቶ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ሰማያዊም ፓርቲ ሆነ ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውጭ ከሚገኘው ጽንፈኛና አክራሪ ኃይል ጋር በመቀናጀት በአረቡ ዓለም የታየውን አብዮት ወደ ኢትዮጵያ እናመጣለን በሚል ለረዥም ጊዜያት ውስጥ ውስጡን ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም እውነቱን የተረዳው ሕዝብ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይህንን ሊቀበላቸው አልፈቀደም፡፡
ከውጭ የአሸባሪው ግንቦት ሰባት ቴሌቪዥን ጣቢያ «ኢሳት» ባለፉት አመታትም ሆነ አሁን ሰማያዊ ፓርቲ የጠራውን ሕዝባዊ ሰልፍ አይነት እንዲካሄድ በዚህም ጠንካራ ጸረ-መንግስት እንቅስቃሴና አመጽ በአዲስ አበባና በክልሎች እንዲቀጣጠል፤ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑ፤ ሀገሪቷ ሰላሟ ደፍርሶ ወደ ሁከት፣ ብጥብጥና ስርዓተ አልበኛ ሁኔታ እንድታመራ፤ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልጫሩትና ለማቀጣጠል ያለኮሱት እሳት የለም፡፡ አሁንም ሕዝቡ የተረጋጋ ሰላማዊ ሕይወቱን፣ የሀገሩን ሰላምና ደህንነት አጥብቆ የሚፈልግ በመሆኑ ይኸው እኩይ ሙከራቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ካለፈው አመት ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ተቃዋሚዎች በርቀት ካለው ጽንፈኛው አክራሪ ሀይል ጋር በውስጣዊ ትስስር በመቀናጀት፤ አጀንዳ በመጋራት ሌላው የሴራ መንገድ አላዋጣቸው ሲል፤የሙስሊም ወንድሞቻችንን ትግል እንደግፋለን፤ ከጎናቸው እንሰለፋለን፤ መንግስት በሙስሊሞች ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል፣ የታሰሩት ይፈቱ፣ ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን በአገር ውስጥ ደጋፊዎቻቸው በጋዜጦች በዌብ ሳይቶች (በተለይም በአረቡ ዓለም መገናኛ ብዙሀንና ድረ ገጾች) በመጠቀም የፖለቲካ ድጋፋቸውን ለማስፋት በእጅጉ ደክመዋል፡፡አሁንም ገፍተውበታል፡፡
በአሜሪካና በሌሎች አገሮች የሚገኙ የጽንፈኛው ግንቦት ሰባት አክራሪ ቡድን አባላትና ደጋፊዎች በጅምላው የሙስሊሙን ጥያቄ እንደግፋለን በሚል ስብሰባ አካሂደዋል፣ ሰልፍ ጠርተዋል፡፡ ከሂጅራ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የገንዘብ እርዳታ አሰባስበዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ሸብ ረብ ሲያካሂዱ በኢትዮጵያ የአክራሪ እስልምና አደጋ መሰረት እየጣለና የሸረሪት ድሩን እያደራ መሆኑን እያወቁም ቢሆን ይክዳሉ፡፡
እነሱ የሚፈልጉት ምንም ሆነ ምን ከጎናቸው ተሰልፎ ኢሕአዴግን የሚጥል ሀይል ማበራከት በሚለው የጨለማ አስተሳሰብ የተቃኘ ነው፡፡ ስለዚህም ጥቂት አክራሪ ሙስሊሞች በየሳምንቱ የዓርብ ጁምአ ጸሎት፤ለስግደት በወጣው ሕዝበ ሙስሊም መካከል መፈክር በማሰማትና በማስተጋባት ሲያካሂዱት የነበረውን እንቅስቃሴ ተቃዋሚው ሀይል አይኑን ጨፍኖ ሕጋዊ ጥያቄ ነው በማለት ድጋፉን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህንኑ አንድነት፣ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ በአይዞአችሁ ባይነት እያጋፈሩና ስፖንሰር እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩ ኢሕአዴግን የመደገፍ ወይንም ያለመደገፍ ጉዳይ ሳይሆን የአክራሪ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ መከሰት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ሕልውናና የደህንነት ጉዳይ መሆኑን ከጥላቻ ወጥቶ ማስተዋል ያልቻለ ተቃዋሚ ይሏል ይህ ነው።
መንግስትና የኢትዮጵያ ሕዝብ የችግሩን መሰረታዊነትና አሳሳቢነት በውል የተረዳው በመሆኑ ይህንን አደጋ ለመቅረፍ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፣ ውጤታማም ሆነዋል፡፡ ምንም እንኳ ሰማያዊ ፓርቲ ያካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ ለሌሎች ጸረ ሰላም ኃይሎች አጀንዳ ማራመጃነትና መጠቀሚያነት ያገለገለ ቢሆንም። ሁከትና ብጥብጥ ሳይነሳ፤ በትዕግስት ማስጨረሱ የመንግስትን ብስለት በገሀድ ያረጋግጣል፡፡
ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ የወሰደው ጽንፈኛ ተቃዋሚ በድርጊቱ በመግፋት በክልሎችም ሰልፉን እያስተባበረ ይገኛል፡፡ መድረክ በመቀሌ ሰልፍ ለማድረግ ተከለከልኩ ሲል አንድነት ደግሞ ሁለት ወር የሚዘልቅ ሰልፍ በየክልሉ ለማድረግ ፕሮግራም አውጥቷል፡፡ የግብፆች እቅድ፤በአገር ውስጥ ተቃዋሚ በመጠቀምና በገንዘብ በመርዳት መንግስትን ማዳከም፤መወጠር የሚለው ስትራቴጂያቸው በገሀድ ነፍስ ሲዘራ እያየን ነው ማለት ነው፡፡ በመሰረቱ ሀገር በስራ እንጂ በሰልፍና በጩኸት አትለወጥም፣ አታድግምም፡፡ የውጭ ሀይሎች ተላላኪና መሳሪያ መሆን፤ የሀገርን ልማትና እድገት ለማጨናገፍ በፖለቲካ ሽፋን መንቀሳቀስ በሀገር ላይ የሚፈጸም ከባድ ወንጀል ነው፡፡ በሰማያዊው ፓርቲ ሰልፍ ላይ የታየው የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት ብቻ ሳይሆኑ በአብዛኛው ለአክራሪዎች ወግኖ የቆመው ኃይል ነው፡፡ይህም ሰማያዊው ፓርቲ አስቀድሞ ውስጥ ውስጡን የማስተባበር ስራ መስራቱን በገሀድ ያረጋግጣል፡፡ መካከለኛ እድሜ ላይ ያሉና አዛውንቶች ጭርሱንም በሰልፍ ላይ የሉም ማለት ይቻላል፡፡
የሰልፈኛው ቁጥር አናሳ ከመሆኑ አንጻር ያን ያህልም ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም፣ «ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ» ዓይነት ተረት ሆነና 100 ሺ ሰው ሰልፍ ወጥቷል ሲሉ የሰማያዊ ፓርቲ ኃላፊ ከእውነታው የተጣላ መግለጫ ለተለያዩ ሚዲያዎች ሰጡ፡፡ ኢትዮ ምሕዳር ጋዜጣም ይህንኑ በማስተጋባት ይሁን በራሱ ስሜት ተነሳስቶ እንደሆነ አይታወቅም በመጀመሪያ ገጹ ላይ «100 ሺ ሰዎች ሰልፍ ወጡ» ሲል ግነቱን በመድገም ዘገባ አቅርቧል፡፡ መልእክቱ አያሻማም፣ ለቀጣዩ ሰልፍ ሰዎች እንዲሰናዱ በኋላም ብዙ መቶ ሺዎች ወጡ ለማለት እንዲመች የተዘጋጀ የቅድመ ፕሮፖጋንዳ ስራ ወይም የቅስቀሳ ማስታወቂያ መሆኑ ነው፡፡
ሌሎቹም የውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ከ1997 በኋላ የነበረው ፍርሃት ተሰበረ በሚል በመቶ ሺዎች ሰልፍ ወጡ፤ መንግስት በሶስት ወራት ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ካልሰጠ ተቃውሞውና ሰልፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ተቃዋሚውም የበለጡ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማድረግ እቅድ እያወጣ ነው፣ ተባብሮ እየሰራ ነው የሚሉ ዘገባዎችንም አንብበናል፡፡
ለዚሁም ተግባራዊነት አሜሪካና አውሮፓ ከሚገኙ አክራሪ ተቃዋሚ ሀይሎች ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደና ከወዲሁም ለመንቀሳቀስና ለማስተባበሪያ የሚሆን ገንዘብ በተለያዩ ሽፋኖች ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በቀጣይም መሰል የተቃውሞ ሰልፎችንና የአደባባይ ስብሰባዎችን ለማደራጀት እንደሚንቀሳቀሱ እየገለጹ ይገኛሉ።
የአረቡ ዓለም ዓይነት አብዮት በመፍጠር በሁከትና በትርምስ መንግስትን በኃይል ለመጣል ይቻላል ብለውም ዕምነት ይዘዋል። ይህ ግን ኢ-ሕገመንግሥ ታዊና ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሊያስተናግደው የማይችል ከንቱ ምኞት ከመሆን የዘለለ አይሆንም።፡፡ እነሱ እንዳሰቡት ሕብረተሰቡ የስውር ሴራቸውና የአመጻቸው ተባባሪ ይሆናል ተብሎም ጭራሽ አይታሰብም። በዚህ ዓይነቱ ድርጊት ጀርባ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የእነማን እጅ አለ? የነማንን ጥቅም ለማስከበርና ዓላማ ለማሳካት ነው ይህ ሁሉ እየታሰበ ያለው? ለዚህ ዓላማ መሳካት ሲባልስ በተለያየ መንገድ ከውጭ የሚገባ ስውር ድጋፍ የለም ወይ? የተለያዩ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚራወጡ የተለያዩ የውጭና የውስጥ ኃይሎች የሉም ወይ? ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች አንስቶ በሚገባ መፈተሽ ተገቢ ይሆናል። የመንግሥትን ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በመንግስትም ሆነ በግል የገንዘብ ተቋማት በኩል ግዙፍ ገንዘብ በቀጥታ አይልኩም፡፡ ሽብርተኞች በውጭው ዓለም እንደሚያደርጉት ሁሉ እነዚህም ጨዋታውን የሚያካሂዱትና ገንዘብ የሚያስገቡት ሕጋዊ ባልሆኑ የተለያዩ ስውር መንገዶች ነው፡፡
ይህ ሁሉ ደፋ ቀና በእርግጥ በዚህች አገር የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን የሀገሪቷን ሰላም በማደፍረስ ወደ ሁካታና ትርምስ ማዕከልነት ለመለወጥ በዚህም ጥፋትና ውድመት መካከል በሚፈጠር የመርፌ ቀዳዳ በሚያህል ክፍተት ተሽሎክሉኮ በሕገወጥነትና በኃይል ሥልጣን መጨበጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ የቀን ቅዥታቸው ግን በምንም መንገድ ዳር የሚደርስ አይሆንም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከጀርባ ሆነው በፋይናንስ በመርዳት ለሚያደርጉት ርብርብ ውስብስቡን ገጽታቸውን ስለሚረዳው ፈጽሞ አይንበረከክም፡፡
የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎችን የተጀመሩ ፈጣን የልማት እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የሚራወጡት በተቃዋሚነት ስም ያሉ ሰማያዊ ፓርቲን የመሳሰሉና ሌሎች የሃይማኖትና የፖለቲካ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ በአንዳንድ የውጭ ሀይሎች ስለላና መረጃ እንዲሁም ቀጥተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ሊታገዙ እንደሚችሉ መገመት ከእውነታው የራቀ አይሆንም። ይህን ለማለት የሚያስደፍረውም በአቋም ደረጃ እያራመዱት ያለውና በተግባርም እንተረጉመዋለን የሚሉት ሁሉ ያለው ተመሳሳይነት ነው። የሰማያዊ ፓርቲ፣የአንድነትም ሆነ የመድረክ ሽር ጉድ ለሰላም፣ለዕድገት፣ለፍትሕና ለዲሞክራሲ መስፈን ሳይሆን በአቋራጭ ራሳቸውን ለሥልጣን ለማብቃት የሚያደርጉት የህልም እሩጫ ነው።
ለዚህም ሕዝቡን ለማነሳሳት፣በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ስም መነገድ፤የሕዝብ ስሜትን ይቀሰቅስልናል ብለው የሚያስቡትን የተዘጋና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውን አጀንዳ ሁሉ ከተቀበረበት አውጥቶ የሌለ ሕይወት ለመስጠት አቧራ ማስነሳት፣ በአሸባሪነት ተጠርጥረው ጉዳያቸው በነጻ ፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያሉ ሰዎችንና ቀደም ብሎም የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸውን በተመለከተ ከፍርድ ቤት ይልቅ ራሳቸውን ፈራጅ አድርገው በመሰየም ይፈቱ ማለትና በዚህም አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን መደገፍ ነው ስራየ ብለው የያዙት፡፡
ታላቅ የሆነ ሀገራዊ ጉዳይ እያለ ያንን ለማሰናከልና ለውጭ ሀይሎች መሳሪያ በመሆን ሕዝቡን ለመከፋፈል መሮጣቸው ማንነታቸውን ይበልጥ አጋልጦታል፡፡ ማንም በዚህ የሚዘናጋና የሚታለል አይኖርም፡፡ ጥሪያቸውም ሆነ ቅስቀሳቸው ተቀባይነት የለውም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነትና የመድረክ ጥቁር ተግባራት ሀገሪቷን ወደ ጥፋት አቅጣጫ ለመውሰድ ያነጣጠረ እንጂ ለሕዝብ ጥቅምና ክብር ከማሰብ የመነጨ አይደለም፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ግን የታሪክና የትውልድ ተጠያቂነትም እንደሚኖርባቸው ጠንቅቀው ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

ECADF

No comments: