Friday, September 19, 2014

አንድነት ፓርቲ መንግስት ሕገ መንግስቱን እንዲያከብር ታላቅ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ!

September 20,2014
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን በአደባባይ ሻማ ማብራት ፕሮግራም ለማሰብ የአዲስ አበባ አስተዳደርን በደብዳቤ መጠየቁንና የአስተዳደሩ የሕዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ለፕሮግራሙ የተመረጠውን ቦታ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ዕውቅና እንደነፈገው ፓርቲው አሳውቋል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱ የተለመደ የሕገ-መንግስታዊና የሕግ ጥሰት መሆኑን በመገንዘብ በጥልቀት ተወያይቶበታል፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ህብረተሰቡን በግዳጅ ስልጠና ወጥሮ በፈለገበት ቦታ ላይ በመሰብሰብ ከፍተኛ ኃብት እያባከነ ባለበት በአሁኑ ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲን አደባባይና ሜዳን መከልከል የለየለት አምባገነናዊ አሰራር በመሆኑ ድርጊቱን አጥብቆ ኮንኗል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አካላት በጉዳዩ ላይ ያደረጉትን ውይይት ሲያጠቃልሉ ቀድሞ ተይዞ የነበረውን የአደባባይ ሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት ፕሮግራም ከፍ ወዳለ የፖለቲካ እንቅስቀቃሴ መሸጋገር እንዳለበት በማመን ‹‹የአንድነት ንቅናቄ ለሕግ የበላይነት መከበር እና የህሊና እስረኞችን ማሰብ ›› በሚል ርዕስ መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እስከ 7፡30 ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ መወሰኑን ከፓርቲው ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ጽ/ቤቱ ጨምሮ እንዳስታወቀው የሰልፉ የዕውቅና ደብዳቤ ለአስተዳደሩ እንዳስገባ ጠቅሶ ቀደም ሲል ለአደባባይ ሻማ ማብራት የተቋቋመውን ኮሚቴ በሰው ኃይል እንዲጠናከር በማድረግ ዝግጅቱ እንዲቀጥል መወሰኑን ለፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል የደረሰን ዜና አመልክቷል፡፡

No comments: