Saturday, September 27, 2014

መስከረም 25 ቀን ሰልፍ ተጠርቷል – ሰማያዊ፣ መኢአድና ሌሎች ሊቀላቀሉም ይችላሉ (አማኑኤል ዘሰላም)

September 27,2014
በአንድነት ፓርቲ ወጣቶች አነሳሽነት፣ በአዲሱ የ2007 ዓ.ም ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ወጣቶች ኮሚቴ እየተንቀሳቀሰ ነው። እንደለመዱትና እንደከዚህ በፊቱም ሕወአት/ኢሕአዴጎች የዜጎችን ነጻ የመስብሰብ መብት እየረገጡ ፣ ሕገ መንግስቱን እየሻሩ ፣ እነርሱ ከሚፈልጉት ስብሰባ በቀር ምንም አይነት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ጫና እያሳደሩ ነው።
የፓርቲው ብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቢሮ ዉስጥ በሚደረጉ ስራዎች ተጠምዶ፣ አዳማ እና ደብረ ማርቆስ ሰኔ 8 ቀን ከተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች በኋላ ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የሉም። የአዲስ አበባ የአንድነት ወጣቶች፣ «ትግሉ የመሪዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው። ሁሉም ዜጋ የድርሻዉን ማበርከት አለበት» በሚል መርህ፣ በራሳቸው አነሳሽነት በአራት ወይንም ስድስት ኪሎ ፣ ሕዝቡ ሁሉ የሚሳተፍበት፣ የታሰሩ እስረኞችን የሚያስብ፣ የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት አዘጋጅተው፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ለመስከረም 3 2007 ዓ.ም እውቅና እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። አስተዳደሩ «በአራት ኪሎና በስድስት ኪሎ መሰብሰብ አይቻልም» የሚል ምላሽ ይሰጣል። ወጣቶቹ አላስፈላጊ ግብግብ ላለመፍጠር ሌሎች አደባባዮችን እንደ ሌላ አማራጭ በማቅረብ ለመስከረም 11 ዝግጁት ለማድረግ አስተዳደሩን ያሳወቃሉ። አስተዳደሩ አሁንም ምላሽ ሳይሰጥ ይቀራል።
በዚህ በአስተዳደሩ ጸረ-ሕግ ተግባራት ያልተደናገጡት የአዲስ አበባ አንድነት ወጣቶች፣ መብታቸውን ለማስከበር የሻማ ማብራቱን ስነ-ስርዓት ወደ ሰላማዊ ሰልፍ ይቀይሩታል። መስከረም 25 ቀን በአዲስ አበባ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት ይጀምራሉ። አስተዳደሩንም በደብዳቤ ያሳውቃሉ። ነገር ግን አስተዳደሩ የደረሰኝ ደብዳቤ የለም በሚል ሰልፉ እንዳይደረግ ማከላከል ይጀምራል።
ከሰልፉ ጋር በተገናኘ፣ ሰልፍ የአንድነት ሰልፍ ብቻ ሳይሆን ፣ የመኢአድ ፣ ሰማያዊና ሌሎች ድርጅቶችም እንዲቀላቀሉት ትልቅ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ መረጃዎች አሉ። መኢአድ የቅድመ ዉህደት ስምምነት ሲፈረም በጋራ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎች በጋራ እንዲሰሩ ስምምነት በመፈረሙ የመኢአድ ሰልፉን መቀላቀል የሚጠበቅ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ወቅቱ ትብብርን ስለሚጠይቅ ከአንድነት ወንድሞቻቸው ጋር ይሰለፋሉ የሚል ትልቅ ግምት አለ። በአዲሱ አመት፣ ድርጅቶች ባይዋሃዱም፣ ድምጻቸውን በአንድ ላይ ለማሰማት መንቀሳቀሳቸው፣ ለለውጥ ፈላጊዊ ሕዝብ ትልቅ የምስራች ነው የሚሆነው።
ለአዲስ አበባ ወጣቶች በዚህ አጋጣሚ ያለኝን አክብሮት ለመገልጽ እወዳለሁ። ትግል ማለት ይህ ነው። አገዛዙ ዜጎችን መሰረታዊ መብታቸው እንዳይጠበቅላቸው ማከላከሉ አይቀርም። ሕወሃት/ኢሕአዴግ በባህሪው አምባገነን በመሆኑ ሁልጊዜ መሰናክሎችን ማስቀመጡ አይቀርም። ሰዉን ተስፋ ለማስቆረጥ፣ ታጋዮች እጅ ሰጥተው ከትግሉ ሜዳ በቀላሉ እንዲሸሹ ለማድረግ ፣ የዲሞክራሲ ካምፑን ለመከፋፈል ሌትና ቀን ነው የሚሰራው።
አገዛዙ እንደሚፈልገው፣ የአንድነት ወጣቶች አርፈው፣ «አሜን» ብለው፤ ባርነትንና የመሸማቀቅ ኑሮን መርጠው መቀመጥ ይችሉ ነበር። ነገር ግን አላደረጉትም። አለቆቻቸው በቢሮ በስብሰባ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ፣ ወጣቶቹ ወደ ሥራ ተሰማሩ። «ዜጎች፣ በአደባባይ፣ በነጻነት ድምጻቸዉን የማሰማት መብታቸው መከበር አለበት» በሚል የጸና እምነት ፣ ኢትዮጵያዉያን በጓዳና በድብቅ ብሶታቸውን ከመግለጽና ከማንሿከክ ወጥተው፣ በገሃድ፣ አለም ሁሉ ፊት፣ ድምጻቸውን ያሰሙ ዘንድ ሰልፍ ጠሩ። ከአስተዳደሩም ጋር ሙግት ጀመሩ።
እነርሱ ሟቹ መሪያቸውን ለመዘከር ለሳምንታት አደባባዮችን ዘግተው አልነበረም እንዴ ? ታዲያ እኛ የምንወዳቸውና የምናክበራችው፣ በላባችን ዉስጥ የተቀመጡ የሕሊና እስረኞችን ለማሰብ፣ ለነርሱ ያለንን አጋርነታቸውን ለመገልጽ እንዳንሰበሰብ ለምን እንከለከላለን ? ሕግ ከተባለስ፣ ሕጉ ለሁሉም እኩል ለምን አይሆንም ?
ሕወሃት/ኢሕአዴጎች መሳሪያ በእጃቸው አለ። ተቋማትን ሁሉ ተቆጣጥረው፣ ለራሳቸው ተግባራዊ የማያደርጓቸውን ሕጎች እንደ በትር በመጠቀም፣ በጉልበት የዜጎችን መብት እየረገጡ ነው። ለጊዜው ጎዝፈው ሊታዩና ሊያስፈሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነርሱ የሌላቸው እኛ ግን ያለን ትልቅ ነገር አለ። እርሱም የሕዝብ ድጋፍ። እነርሱ ጥቂቶች ናቸው፤ እኛ ሚሊዮኖች ነን። እነርሱ ፖለቲካቸው በዉሸትና በማስፈራራት፣ በሸፍጥ ላይ የተሞረኮዘነው። እኛ ግን የሰለጠን፣ ሁሉን የሚያሰባስብ ፖለቲካን እናራምዳለን። እነርሱ ሰው መግደል፣ ሰዉ ማሰር፣ ሰው ማንገላታት ስራቸው ነው። እኛ ግን ያለፉት ጠባሳዎች ላይ ከማተኮር፣ ኢትዮጵያዉይን በሰላም፣ በእክሉልነት፣ ሳይፈሩ፣ ሳይሸማቀቁ፣ በአገራቸው ተክብረውና ቀና ብለው እንዲኖሩ እንሰራለን።
መስክረም 25 ቀን የተጠራው ሰልፍ የሰላም፣ የፍቅር፣ የታሰሩትና የተጎዱትን የምናስብብት ሰልፍ ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለዚህ ሰልፍ መሳካት የበኩሉን ድርሻ ይወጣ። ግድየልም ወገኖች እዉነት፣ ፍቅር፣ አንድነት ሁልጊዜ ያሸንፋሉ !!!

No comments: