Saturday, September 27, 2014

እንኳን ለልማታዊው የደመራ አከባበር አደረሳቹ!

September 27,2014
ከባህር ማዶ ነኝና ዛሬ የመስቀል በዓል እንደመሆኑ የአገር ቤት የደመራን በዓል በቀጥታ ለመከታተል እያቅለሽለሸኝም ቢሆን የወያኔን የቀጥታ ስርጭት መከታተል ጀመርኩ። ብዙም ሳልቆይ ግን ከወትሮው በተለየ አለባበስ ሁኔታ ለበዓሉ ድምቀት ከሚሰጡት ወትሮ ከምናውቃቸው የስንበት ትምህርትቤት መዘምራን በተጨማሪ የሃኪም ፣የኢንጅነር፣ የገበሬ፣ የተማሪ፣ የአስተማሪ፣የወዛደር... ምን የቀረ አለ?... ልብስ የለበሱ በርካታ ሰዎች በመዘምራኑ ተከበው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ተመለከትኩ። መልዕክቱ ወዲያው ገባኝ። እንደገባኝም አልቀረ ካድሬው ጋዜጠኛ የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ልማቱን ትደግፋለች፣ የሚደረጉትን ልማቶችን ትባርካለች፣ የመነኮሳት ልብስ ተላብሰው የሚታዩትም ስለልማቱ ሲጸልዩና ሲባርኩ ነው እያለ ሲደሰኩር... ሐይማኖታዊው የመስቀል ስርዓት መሆኑ ቀርቶ በደንበኛው የወያኔ እጅ የተቦካና የተጋገረ ልማታዊ የደመራ በዓል ስለሆነ ከዛ በላይ ማየት አላስፈለገኝም። ውስጤ ባዶ ሲሆን ተሰማኝ።

አማራና ኦርቶዶክስ ተዋህዶን አከርካሪውን እንሰብራለን ሲሉን፣ አይ አማራም አደለሁ እምነትም በልብ ስለሆነ አይጠፋም ብዬ ዝም አልኩ። አማራም እየታደነ ከነህይወቱ ወደገደል ተጨመረ፣ተገደለ፣ከቀየው ተፈናቀለ፣ ዘሩም አንዲመክን ተደረገ። አድባራትም ተቃጠሉ፣መነኮሳትም ተዋረዱ፣ ቤተክርስቲያንም ተሰደደች። በመቀጠል ኦሮሞው ላይ ዞሩ። የኦሮሞ ግንባር ሲፋቅ ኦነግ ነው እያሉ ገደሉት፣ አገር ጥሎ እንዲጠፋ አደረጉት፣ እስር ቤቶችን በኦሮሞ ልጆች ሞሉት። ኦሮሞ አይደለሁምና ዝም አልኩ። ማነው ባለሳምንት ብለው ደግሞ ሙስሊሙ ላይ ዞሩ። የተሻለና ዘመናዊ የሆነ እምነት አመጣንልህ ተቀበል፤ ካልተቀበልክ ደግሞ እየተባለ በየመንገዱ ደበደቡት፣ እንደውሻ አሳደዱት፣ ሽብርተኛ ብለው አሰሩት። ሙስሊም አደለሁምና ምን አገባኝ አልኩ። ማን ቀረ ከቶ፧ የጋምቤላና የሱማሌው ጭፍጨፋ፣ የአፋሩ፣ የደቡቡ ሁሉም በየተራ ተወረደበት። ከፋፍለውና ነጣጥለው መቱን፣ እርስ በርስ አባሉን፣አዳከሙን።

አንድ የቀረችኝ የማንነቴ መለያ የሆንችው እምነቴና እምነቴን የማሳይበት ባሕላዊ እሴት ብትኖረኝ እሷንም ዛሬ ተነጠኩ። ሲጀመር የጋራ የሆነውን የማንነት ታሪክ አበላሹት፣ ታሪክ አልባ አደረጉን። በመቀጠል ህዝብን ከህዝብ በማነሳሳት አለመተማመንን አብቅለው አንድነታችንን በማኮላሸት ነጣጥለው መቱን። ከዛ አቅም እንደሌለን ሲያውቁ አገሩን ለባዕዳን ቸረቸሩት። በገዛ አገራችን የበይ ተመልካች ሆነን ቁጭ አልን።

ከንግዲህ ምን ቀረኝ ? አገሬን፣ እምነቴንና ታሪኬን አጣሁ ማለት ነው። እንግዲህ እኔ ማነኝ ? የሚጣልለትን እየበላ የሚኖር እንስሳ ወይስ ከወደኩበት አቧራዬን አራግፌ በመነሳት እንደኔው ከተረገጠው ጋር ዘር ሃይማኖት ሳልል እጅ ለእጅ ተይይዤ ማንነቴን መመለስ፤ በተባበረ ክንድ የወያኔን ስርዓት አሽቀንጥሮ በመጣል በጋራ፣ በእኩልነትና በመቻቻል መርህ ኢትዮጲያችንን ከፍ በማድረግ ተከብረን መኖር ? ለመሆኑ ለመኖርና ላለመኖር ምርጫ ያስፈልገዋል እንዴ ?
ዋ... ኢትዮጲያዬ!
መጽሐፈ ሄኖክ፣ መስከረም ፩፮፣ ፪ሺ፯

No comments: