Thursday, September 11, 2014

አንድነት ኃይል ነው፤ መበታተን ጥቃት ነው (ዶ/ር. አክሎግ ቢራራ)

Sep 11,2014
አስተያየት
 ዶ/ር. አክሎግ ቢራራ 
unityበመሳሪያ ኃይልና በውጭ መንግሥታት ድጋፍ የስልጣን እርካብ የተቆናነጠጠው፤ በጠባብ ብሄርተኛው በህወሓት ፍጹም የበላይነት የሚመራው፤ የኢህአዴግ መንግሥት ከተመሰረተበት ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ደህንነትና ነጻነት፤ የዘጠና አራት ሚሊዮን ሕዝቧ ሉአላዊዊነት፤ እውነተኛ እኩልነት፤ ማህበራዊ ጥቅም፤ መሰረታዊ ትብብር፤ ነጻነትና ዲሞክራሳዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተናግተዋል፤ ተገፈዋል። በማንኛውም የዘመናዊነት መስፈርት ቢፈረጅ፤ ኢትዮጵያን ከባሰ አደጋ፤ ሕዝቧን ከከፋ ድህነት እና የእርስ በርስ ግጭት፤ ወጣቱን ትውልድ ለሁላችንም ከሚያሳፍር ስደተኛነትና ውርደት ሊያድነው የሚችለው ተተኪ የአገዛዝ ስርአት (አማራጭ) በሕግ የበላይነት፤ በእውነተኛ የኢትዮጵይያውያን እኩልነት፤ በሕዝብ ስልጣን የተመሰረተ ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ብቻ ነው። ሰፊ ለም መሬት፤ ዝናብ፤ ወንዝ፤ ተስማሚ አየር፤ ከመሬት በታች ገና የማይታወቅ ሃብት ያላት አገር ለሁሉም አስተናጋጅ ለመሆን እንደምትችል አልጠራጠርም። ፍትህ-ርትእ ከሌለ ይኼን የማይገኝ ሃብት የሚጠቀሙበት የውጭ ኢንቬስተሮችና አጋር የሆኑ የውስጥ ሃብታሞች ሆነው ይቆያሉ። ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች የሚስማሙበት አንድ አበይት ጉዳይ አለ። ይኼውም ዲሞክራሳዊ አማራጭ አስፈላጊ ነው የሚል። ከጽንሰ ሃሳብ ባሻገር ግን ሁለቱም ወገኖች ዲሞክራሳዊ አሰራርን በተግባር አላሳዩም፤ ለማሳየትም የተዘጋጁ አይመስልም። አንዱ በሌላው እያመኻኘ ሃያ ሶስት ዓመታት አልፈዋል። የሚቀጥለው ምርጫ ዘጠኝ ወሮች ቀርተውታል። ሑኔታው ከቀጠለ የሚቀጥለው ምርጫ ከአሁኑ ተወስኗል ለማለት እንችላለን፤ የገዢው ፓርቲ የበላይነት ብቻ ይሆናል። መቶ በመቶ አሸነፍኩ ቢል አንገረም። የሚወዳደረው ከራሱ ጋር ይሆናል።
ገዢው ፓርቲ መከፋፈልን ወደ ሳይንስ ለውጦታል። ተቃዋሚው ይኼን ሳይንስ አልቀበም በማለት ፋንታ እርስ በርሱ መናከሱን ቀጥሎበታል። በተደጋጋሚ የሚታየው የራእይ፤ የግብ፤ የአደረጃጀትና የአመራር ደሃነት በቀላሉ አለመፈታቱ ተቃዋሚውን ፍሬ ቢስ አድርጎታል። በአገር ውስጥ ብቻ ያለው ሳይሆን በውጭም ያለው፤ በነጻነት ለመወያየትና አብሮ ለመስራት ገዢው ፓርቲ ሊቆጣጠረው የማይችለው። ቢቀበለውም ባይቀበለውም ተቃዋሚው የገዢው ፓርቲ አገልጋይ ሆኗል ለማለት ያስችላል። የምናውቀው የሃገሪቱን አስተዳደር በቋንቋ የቀየሰው አምባገነን መንግሥት ቆይታውንና የኢኮኖሚ ጥቅሙን ለማጠናከር ህዝብን እርስ በርሱ እንዲጋጭ፤ ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸው እንዲናከሱ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይኼ የመከፋፈልና ስልጣንና ሃብትን የማስተማመኛ ስልት ከታወቀ፤ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች በሰከነ መንገድ አስበው፤ ተፈላልገው፤ ተከባብረው፤ “ተናበው”፤ በዋናው ዓላማ ላይ ተስማምተው ለመስራት የገዢው ፓርቲ ፈቃድ አያስፈልጋቸውም ነበር። ችግሩ ጥበባዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ የማደራጀትና የመምራት ድክመትና ክፍተት መኖሩ ነው። ስርዓቱ  የራሱን መቆያ ያጠናከረውና የሚያጠናክረው የሃገሪቱን ባጀት፤ የተፈጥሮ ሃብትና ሌላ ጥሪት ለጥቂቶች አገልጋይ የሆነ ተከታታይ የብልጭልጭ እድገት በማሳየት፤ “እኔ እስካለሁ የእድገቱ ተጠቃሚዎች ትሆናላችሁ፤ እኔ ከሌለሁ፤ ትበላላችሁ” በሚል ዘዴ ነው።
ስርዓቱ የሚሰራውን ያውቃል ማለት ነው። የሚሰራውን የማያውቀው ተቃዋሚው ሆኗል። የተበታተነው ተቃዋሚ የሚለው በኢትዮጵያ እድገት የለም አይደለም። ፍትህ የለም። የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ታች በመሄድ ላይ ይገኛል፤ የኑሮ ውድነት የተራውን ዜጋ የመግዛት አቅም አስጊ በሆነ ደረጃ ቀንሶበታል። የወጣቱ ትውልድ እድል ተምሮ መሰደድ ሆኗል። በዘመነ ኢህአዴግ የሃገሪቱ ለም መሬትና ወንዝ ለውጭ ኢንቬስተሮች በእርካሽ ዋጋ ሲሰጥ ቆይቶ በአሁኑ ጊዜ አላሙዲ ብቻ የሚያመርተው በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን ሩዝ ለሳውዲ ገበያ ይቀርባል። እንደ ካሩቱሪ ያሉ የህንድ ኢኒቨስተሮችም የጋምቤላን ለም መሬት ተረክበው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እየተነገደባት ነው። ሳውዲዎች እየተመገቡ  ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ይራባሉ፤ አገሪቱ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለምግብ ግዢ ታወጣለች። ህይወቱ የተናጋው አብዛኛው ሕዝብ መብቱ ሰለታፈነ፤ ድምፁን ለማሰማት ስላልቻለ መከራውን ተቀብሎ ይኖራል ወዘተ የሚሉ ናቸው።
ስለሆነም፤ ተቃዋሚው የጠራ አማራጭ ለማቅረብ ነባራዊው ሁኔታ ይፈቅድለታል። የሚጎድለው የዓላማ አንድነትና የአመራር ብልሃት ነው። እርግጥ ነው፤ የገዢው ፓርቲ አቅም ከፍተኛ ነው። መንግሥትን ከተቆጣጠረ ባጀትንም እንደፈለገው ፈሰስ ለማድረግ ይችላል።

ስንቅ ብቻውን አቅም አይሆንም
የተቃዋሚው ክፍል አቅም ጠንካራ ሊሆን የሚችለው ከሕዝብ ከሚያገኘው ድጋፍ፤ ከመተባበሩ፤ ያለውን የቁሳቁስ አቅም በጋራ ከመጠቀሙ፤ በብልሃት ከመስራቱ፤ በአንድ ድምፅ ከመነሳቱ፤ ለዓላማው ጠንክሮ፤ በውስጥ አመራር ሳይበከል መስዋት ለመክፈል ፈቃደኛ ከመሆኑ ላይ ነው። በውጭ ያለው አገር ወዳድ፤ ዲሞክራትና የሰብአዊ መብቶች ጠበቃ ኃይል ያልተቆጠበ ድጋፍ ለማድረግ አቅምና ፍላጎት አለው። “ተባበሩ ወይንም ተሰባበሩ” እያለ ሲመክር ቆይቷል። ገንዘቡን፤ እውቀቱን፤ ድጋፉን ችሯል። ወደፊትም ይችራል የሚል እምነት አለኝ። ሆኖም፤ ስንቅ አቀባይነት ያለ ድርጅትና አመራር ብቃት ኢትዮጵያን አይለውጥም። ለዚህ ነው፤ ደጋፊዎች ተስፋ እየቆረጡ “ተቃዋሚ ነኝ” ማለቱን ቀልድ አታድርጉት፤ “ጩኸቱን ወደ ተግባር ለውጡት፤ በፍርሃትና በመጠላለፍ ዓለም መኖራችሁን አቁሙ፤ ነጻነት፤ ፍትህና ዲሞክራሳዊ ስርአት ያለ መስዋእትነት ስኬታማ ሊሆኑ አይችሉም። የእርስ በርስ ጦርነቱን አቁሙ። በውጭ ኃይሎች ማምለኩን አቁሙ። ድርጅት አፍርሳችሁ በድርጂት መተካቱን ተውት። አትጠላለፉ። መገናኛ ብዙሃኖችን ለእርስ በርስ ጦርነት አትጠቀሙ፤ አትወነጃጀሉ፡  የራሳችሁን የውስጥ አመራር ሳታጠናክሩ ሁሉን ነገር በገዢው ፓርቲና በሌላው ላይ አታመኻኙ፤ ተቃውሞ ብቻውን የማህበራዊ ጥቅም አይኖረውም” ወዘተ፤ ወዘተ የሚሉት።
በጀ፤ ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው?
ይኼ አጭር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስእል በተደጋጋሚ ያሳየው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተው ለሃገሪቱ ዘላቂነት እና ለመላው ሕዝቧ ደህንነት ሲባል መተባበር፤ ቢቻል መዋሃድ አለባቸው የሚለውን ባለፉት አስር አመታት በተደጋጋሚ ሁሉን በሚመለከት ያቀርብኩትን ምክርና ጥሪ ነው። ምክር እንጅ ትእዛዝ አይደለም። ማንም ግለሰብ ወይንም ቡድን ከውጭ ሆኖ ትእዛዝ ለመስጠት አይችልም። ትግሉ በአገር ቤት ካልተጠናከረ፤ አገር አቀፍና አሳታፊ ካልሆነ የፈለገው ጥረት ቢደረግ ዲሞክራሳዊ መሰረት ለመጣል አይቻልም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው አብሮና ተሳስቦ መኖርን ነው። ቂም በቀልነትን አይፈልግም። አንዱን አምባገነን በሌላ አምባገነን መተካት አይደፈልግም። ይኼማ ከሆነ ኢህአዴግ ምን አደረገ፤ የተካው ደርግ ምን አደረገ፤ አጼ ኃይለ ሥላሴስ ምን አደረጉ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ የስልጣኑ፤ የመንግሥቱ፤ የመሪዎቹ ባለቤት ለመሆን ይፈልጋል። ለዚህ ብዙ መስ ዋት ከፍሏል። ስለሆነም፤ ሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች በዓላማ እንድነት በመንቀሳቀስ ታሪክ የሚጠይቀውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው። ሕዝብን ካጎለመሱ ተመጣጣኝ አቅም ይኖራቸዋል። ወሳኙ ሕዝብ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ ዘጠና ሰባት ለቅንጅትና ለህብረት የሰጠው ያልተቆጠበ ድጋፍና የከፈለው መስዋእት እንዲያንሰራራ ከተፈለገ በአገር ቤትና ከአገር ውጭ የሚገኙ የፖሌቲካና የማህበረሰብ ድርጅቶች፤ የሞያ ስብስቦች፤ ግለሰሶብችና ሌሎች ከቡድን፤ ከፓርቲ፤ ከግል ዝናና ጥቅም በላይ ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ለመላው ስብጥር ሕዝቧ ደህንነት አብረው መነሳትና አምባገነኑን መንግሥት ማንበርከክ፤ ቢያንስ ለድርድር እንዲስማማ ማድረግ ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ የተቀነባበረ የሕዝብ አመፅ አገር አቀፍና ዘላቂነት ባለው ደረጃ ከተካሄደ ገዢው ፓርቲ ለመደራደር ይገደዳል።
ይኼን ትንተና ለማዘጋጀት የተገደድኩበት ዋና ምክንያት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት የለመደውን መንገድ እየተጠቀመ፤ ከመጭው ምርጫ በፊት በሰላማዊ መንገድና በሁለገብ ትግል የሚንቀሳቀሱና ተባብረው ለመስራት ፈቃደኛ የሆኑትን ተቃዋሚዎች ሁሉ ተባብረው እንዳይሰሩ በማሰብ በመከፋፈል ላይ ይገኛል። ይኼ አዲስ ነገር አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ጥሎበት የነበረው የመኢአድና የአንድነት ውህደት ሂደት አሳዛኝና ተስፋ በሚያስቆርጥ መልክ ስኬታማ አለመሆኑ ለገዢው ፓርቲ ቆይታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ይኼ ችግር የገዢው ፓርቲ ሳይሆን የተቃዋሚው ነው። በቅርቡ የተከሰተም ሌላ የተቃዋሚውን ክፍል ከጥያቄ ውስጥ ያስገባ አከራካሪ ጉዳይ አለ።
እንደማንኛውም አገር ወዳድ በ August 28, 2014 ሶስት በውጭ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶች በዜናና በድህረገጾች ያሰራጩትን፤ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡትን የጋራ መግለጫ በሰከነ መንገድ ተመልክቻለሁ።  መግለጫው እንዲህ ይላል። “ኢትዮጵዮጵያንና ሕዝቧን ካሉበት አዘቅት በማውጣት ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጋራ ትግልና መስዋእትነት የግድ የሚለን ደረጃ ላይ መድረሳችንን፤ የወያኔን ቡድን በሁለገብ ትግል እየተፋለምን ያለን ድርጅቶች ተጣምሮና አንድ ሆኖ መታገል እንዳለብን ካመንን ዓመታት አስቆጥረናል። ስለሆነም፤ ወደፊት ለመዋሃድ የተሰማማነው ድርጅቶች፤
  1. የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር
  2. የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ
  3. የአማራ ዲሞክራሳዊ ኃይሎች ንቅናቄ ነን” የሚል መግለጫ ወጥቶ ሲያነጋግር ቆይቷል።
ከአንድ ሳምንት በኋላ በ September 6, 2014, በኮሎኔል አለበል የሚመራው የአማራ ዲሞክራሳዊ ኃይሎች ንቅናቄ ማስተባበያ አውጥቶ “ከግንቦት 7 ጋር አልተዋሃድኩም” ብሏል።
በእኔ ግምትና እምነት ምንም እንኳን የጋራ ስምምነቱ በምን አጀንዳ ላይ እንደተቀረጸ ባላውቅም፤ አሰራሩ በግልፅነት፤ በሃላፊነት፤ በዲሞክራሳዊነት፤ በዘላቂነትና ሌሎችን በሚያበረታታ መንገድ የውህደቱ ድርድር እንዲካሄድ ያለኝን ተስፋና ምኞት ለማቅረብ እፈልጋለሁ። በተመሳሳይ፤ በአንድነትና በመኢአድም በውስጥና በመካከላቸው መካከል የተከሰቱ ልዩነቶችም በውይይት፤ በግልፅነት፤ በሃቀኝነት፤ በብልሃት፤ በዲሞክራሳዊ ስልት እንዲፈቱ የታሪክ አደራ እሰነዝራለሁ። ዛሬ ለፍትህ- ርትእ፤ ለህግ የበላይነት፤ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፤ አገርን ከአደጋ ለመከካለክ፤ ለእውነተኛ እኩልነትና ለዲሞክራሲ የሚታገሉ ኃይሎች “ኢህአፓ፤ መኤሶን፤ እሴፓ፤ ፓሪስ አንድ፤ ፓሪስ ሁለት፤ ኢዲዩ፤ እዴፓ፤ ቅንጅት፤ ህብረት፤ ታንድ፤ ኦነግ፤ መድረክ፤ አሬና፤ ግንቦት 7፤ አርበኞች፤ የአማራ ዲሞክራሳዊ ኃይሎች፤ አንድነት፤ ሰማያዊ፤ መኢአድ፤ አንድ ሁለትና ሶስት ወዘተ የሚሉበትና እርስ በርስ የሚወቃቀሱበት ዘመን አልፏል ለማለት የሚያስችሉ ብዙ ክስተቶች አሉ። የኼን ስል፤ ሁላችሁም ተዋሃዱ ማለቴ አይደለም፤ ብዙ ተሞክሮ አለተቻለም። ዲሞክራሳዊ ለውጥ ከተፈለገ ለመተባበርና ለመደጋገፍ ይቻላል። ይኼም ፈቃደኛነት ካለ ብቻ ነው። “አገር ትሸጥ ሲባል ስንት ታወጣለች” የሚል አዲስ ባህልና አዲስ ባለሃብት መደብ መፈጠሩን እያየን እርስ በርሳችን የምንናከስ ከሆነ ከትግሉ ዓለም መውጣት አለብን። አዲሱ ትውልድ ለራሱ ህይወት ሲል ይታገልበት ለማለት መድፈር አለብን። በምትካችን አዲስ ትውልድና አዲስ ዓመራር እየታገለ አመራሩን እንዲይዝ ቦታውን እንልቀቅለት። መሰናክል አንሁን። መቀበል ያለብን፤ እኛ ራሳችን ለመምከር ወይንም ለመመከር ስለማንፈልግ ሌሎች፤ በተለይ ፈረንጆች ለእኛ ተናጋሪ ሆነዋል። ለምሳሌ፤ ለኢትዮጵያ የሚለግሱ መንግሥታትና ድርጅቶች ደጋግመው የሚነግሩን በአንድ ላይ፤ በአንድ ድምፅ ለመናገርና አግባብ ያለው አማራጭ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማቅረብ እስካልቻላችሁ ድረስ ማንም አያዳምጣችሁም ነው። ሃቁ፤ ያለውን መንግሥት እንደግፋለን ነው የሚሉት። የተበታተነ ተቃዋሚ ውጤቱ ይኼው ነው። አንፈረድባቸው። የሚያኮራ ታሪክ እያለን የራሳችን ህብረተሰብ ለመታገድ ካልቻልን ሌሎች ያዙብናል። እያዘዙብን ነው። ከዚህ የበለጠ የጠነከረ ምክር መጠበቅ ራስን ማታለል ነው።
ለማጠቃለ፤ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች እንዲያስቡበት የምመኘውና አደራ የምለው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት እድሜውን ለማራዘም ለሚያደርገው ያልተቆጠበ ሴራና ሰለባ ምርኮኛ መሆን የለባችሁም/የለብነም የሚል ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውና የሚመኘው የእርስ በርስ መጠላለፍና ለስልጣን መሻማትን አይደለም፤ አብሮና ተባብሮ አምባገነኑን ስርዓት በዲሞክራሳዊ ስርዓት መተካትና ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው የእድገት በርና መሰረት እንዲከፈትለት ነው። ስለሆነም፤ የተቃዋሚዎች ሙሉ እምነት በኢትዮጵያ ሕዝብ አቅም ላይ ይሁን አላለሁ።

No comments: