Wednesday, September 24, 2014

ዳኞቹ የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ እንደሚገደዱ ገለጹ

September 24,2014
ከሳምንት በፊት በአቶ በረከት ስምኦን የተከፈተውና 15 ቀን የሚፈጀው የ‹‹ፍትህ አካላት›› ባህር ዳር ላይ እያደረጉት በሚገኘው ስብሰባ ላይ ዳኞች ቅሬታቸውን እንዳሰሙ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገለጹ፡፡
ልማታዊ መንግስት ግንባታ ላይ ያተኮረ ነው በተባለው ስልጠና ላይ የክልሉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ በክልሉ የሚገኙ ወረዳዎች የህግ ጉዳይ የስራ ሂደት አስተባባሪዎች፣ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች፣ ጸረ ሙስና እና ሌሎችም አስተዳደርና ጸጥታ ጋር የተያያዙ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ አካላት መሳተፋቸው ተገልጾአል፡፡
በስብሰባው በተለይም ዳኞች በዳኝነት ስርዓቱ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዳለና የገዥው ፓርቲ አባል ካልሆኑ መስራት እንደማይችሉ በመግለጽ ቅሬታቸውን እንዳቀረቡ ተገልጾአል፡፡
የክልሉ አስተዳደር የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሚመሩት በዚህ ስብሰባ ዳኞች አባል እንዲሆኑ እንደሚጠየቁ በመጥቀስ ‹‹አባል ሁኑ እየተባልን እንዴት ነጻ ዳኝነት አለ ይባላል?›› ሲሉ መጠየቃቸውን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ዴሞክራሲ፣ የፌደራል አወቃቀር፣ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስር የሚገኙ ድርጅቶች ሃብት፣ የመሬት ጉዳይና የዳኝነት ነጻነት የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየቶች ቢቀርቡም መልስ እንዳልተሰጠባቸው ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

No comments: