Thursday, September 25, 2014

ጥቃቅንና አነስተኞች ቀጣዩን ምርጫ ‹እንዲያሳኩ› ታዘዙ

September 25,2014
• ‹‹ቃላችንን ካጠፍን የመለስን ቀን ይስጠን›› ባለስልጣናቱ

ከመስከረም 10/2007 ዓ.ም እስከ መስከረም 12/2007 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተሰጠው የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የማጥመቅ ስልጠና በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኢህአዴግ እንዲመረጥ እንዲሰሩ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውና እቅዱን ካላሳኩ ሸዳቸውን መስሪያ ቦታውን እንደሚያጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡

ሰልጣኞቹ ‹‹ግብር በዝቶብናል፣ ደንብ አስከባሪዎች በየጊዜው እየመጡ ገንዘብ ይወስዱብናል፣ በየወረዳው የመልካም አስተዳደር ችግር መፍትሄ ልናኝ አልቻልንም፣ ስለዚህ እናንተን እንዴት ነው የምንመርጠው? በየምርጫው ቃል ትገባላችሁ? ካለፈ በኋላ ትረሱናላችሁ እንዴት እነመንላችሁ?›› ሲሉ ቅሬታቸውንና በገዥው ፓርቲ እምነት እንደሌላቸው መግለጻቸውን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በስልጠናው የተገኙት ባለስልጣናት ገዥው ፓርቲ ቃሉን እንደሚያከብርና በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁት ዜጎች የተባሉትን ስራ ካከናወኑ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ቃል ገብተውላቸዋል ተብሏል፡፡ ተሰብሳቢው በተደጋጋሚ ችግሮችንና ኢህአዴግ ቃል ገብቶ የማይተገብራቸውን ነገሮች በማንሳታቸው በስልጠናው ከተገኙት ባለስልጣናት መካከል አንዱ ‹‹ቃላችንን አናጥፍም፣ ቃላችንን ካጠፍን የመለስን ቀን ይስጠን›› ብለው እንደማሉ ሰልጣኞቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በስተመጨረሻም የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ቢሆንም የምስክር ወረቀቱ ላይ የሰፈረውና የሰለጠኑት ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል፣ ከስልጠናው በፊት በስልጠናው ያልተገኘ በሸድ ስራ እንደማይቀጥል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸው እንደነበር ሰነዱን አያይዘን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ

No comments: