Friday, September 26, 2014

ያልታተመው “የሎሚ አዘጋጆች አጣብቂኝ!” ዘገባ

September 26,2014
የሎሚ መጽሔት አዘጋጆች ከሀገር ከተሰደዱ አንድ ወር ያለፋቸው ሲሆን፤ ይህ ጽሁፍ ደግሞ ለመጨረሻ ጊዜ ማለትም ነሐሴ 17/2006 ዓ.ም ለህትመት ሊበቃ ከነበረው እና ከታገተው የመጨረሻ ዕትም (ከቁጥር 120) ላይ የተወሰደ ነው፡፡ ጽሁፉም መንግስት የመሰረተውን ክስ እና በወቅቱ የነበረውን ነባራዊ ስሜት የሚያንጸባርቅ ሲሆን፤ ለአንባብያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ አንባቢም ጽሁፉን በወቅቱ የነበረውን ስሜት ከግንዛቤ በማስገባት እንዲያነብ እንጠይቃለን፡፡
ሎሚ5
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ባለጠመንጃውን ወታደራዊ መንግስት በጠመንጃ ኃይል አሸንፎ የአራት ኪሎ ቤተ መንግስትን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ዜጎች በሃገሪቱ የይስሙላ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይዘረጋል የሚል ተስፋ አሳድረው ነበር፡፡ ሕዳር 29/1985 ዓ.ም የፀደቀው ሕገ መንግስት አንቀፅ 39ን ጨምሮ (መገንጠልን የሚፈቅደው) አወዛጋቢ ጉዳዮች የሰፈሩበት ቢሆንም፣ በአንቀፅ 29 የተካተተውን (ሃሳብን በነፃ የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት መብት) እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑ ይህንኑ ተስፋ ከፍ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የሀገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ መንግስቱ ሃገሪቱን በሚገዛው ፓርቲና በሹማምንቱ እየተጣሰ፣ አፋኝ አዋጆችና ሕጎች እየጸደቁ ሲሄዱ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ከእኛ በኋላ የዲሞክራሲ ጎዳና ጠረጋ የጀመሩት እንደ ቦትስዋና እና ጋና የመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት በትክክለኛው መንገድ በመጓዛቸው የትና የት ጥለውን ሲሄዱ ገዢዎቻችን ግን ዛሬም “ዲሞክራሲ ሂደት በመሆኑ በአንድ ጀንበር አይመጣም” የሚለውን የተለመደ ዜማ መቀየር አልቻሉም፡፡ መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ካስገባቸው መሠረታዊ የዲሞክራሲ ጎዳና ጥርጊያዎች አንዱ ሃሳብን በነፃ የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት አንዱ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ በመጣው የመብት ጥሰቶች እጅግ አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ ከገቡት መሀል መጽሔታችን “ሎሚ” እና አዘጋጆቿ ይጠቀሳሉ፡፡
ይህ ዕትማችን ከአንባቢያን ጋር የምንገናኝበት የመጨረሻው ሕትመት ባይሆን መልካም ነበር፤ “ሎሚ” መጽሔት ከተመሠረተችበት ነሐሴ 2003 ዓ.ም አሁን እስካለንበት ነሐሴ 2006 ዓ.ም፣ ብዙ ራዕይ ሠንቃ ለሕትመት በበቁ 120 ዕትሞቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጥራት ደረጃዋን ጨምራ ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ በጠበበው የነፃ ፕሬስ ምሕዳር ውስጥም ሆና የሚደርሱባትን ጫና ተቋቁማ ለሦስት ዓመት ዘልቃለች፡፡
“ሎሚ” የተለያየ አቋም ያላቸው ምሁራንና ባለሙያዎች በጥናት ላይ ተመርኩዘው ያቀረቧቸውን ትንታኔዎች አስተናግዳለች፤ ከራሱ ድምፅ ውጪ መስማት የማይፈልገው የገዢው ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊያቸው አቋማቸውን በሎሚ እንዲያንፀባርቁ የቀረበላቸውን ግብዣ በተደጋጋሚ ባይቀበሉትም ዜጐቹ አማራጭ መድረክ በመሆን አመለካከታቸውን፣ ሃሳባቸውንና አቋማቸውን በነፃ እንዲገልፁ ዕድል ፈጥራለች፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተነባቢነቷ በማደጉ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በወር ከ40 ሺህ ኮፒ በላይ ከሚያሳትሙ ሦስት የነፃው ፕሬስ ቀዳሚ መጽሔቶች ሎሚ አንዷ ሆናለች፡፡ ለ80 ሚሊዮን ህዝብ በወር 40 ሺህ ኮፒ ማሳተም ባያኩራራም፡፡
በነዚህ ጊዜያት በበርካታ ፈታኝ፣ አዳጋችና ተስፋ አስቆራጭ ሂደቶች ውስጥ አልፋለች፡፡ የባለስልጣናት ማስፈራሪያ፣ የደህንነቶች ማዋከብና ማሸማቀቅ፣ አዘጋጆቿ በተደጋጋሚ እየተከሰሱ ዋስትና እያስያዙ ከማዕከላዊ በሹማምንቱ በሚሰነዘር ዛቻና ሥጋት የተነሳ በማተሚያ ቤት እጦት መንገላታት… አብረውን የቆዩ በመሆናቸው “ተላምደናቸዋል” ማለት ይቻላል፡፡ ለአዘጋጆቹ በአንድ “የግል ባንክ በኩል የሚያማልል ዶላር በምንዛሪ በመላክ ከአሸባሪዎች ጋር ለማነካካት የተሰራውን ድራማ አዘጋጆቹ ለንዋይ ባለመንበርከክና ለሙያቸው ታማኝ በመሆን ገንዘቡን ባለመቀበል ፉርሽ ያደረጉበት አካሄድንም መጥቀስ አይከብድም፡፡ የመጽሔቱ አዘጋጆች ላይ ይደርስ የነበረው ማስፈራራት ውጤት ሳያመጣ ሲቀር ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ስልክ እየተደወለ “ይህን ሥራውን ካላቆመ ለሚደርስበት መከራ ተጠያቂ እንደሌለ እንድታውቁት” ዓይነት ዛቻዎች የፈጠሩት ሰቀቀንና ስጋትም እንደዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ለምርጫ 97 ኪሳራ የነፃው ፕሬስ ውጤቶችንና አባላትን ተጠያቂ ከማድረግ ቦዝኖ የማያውቀው ገዢው ፓርቲ በ1999 የግል ፕሬሶችን አንዴት “መዋጋት” እንዳለበት የያዘውን አቋም በሰነድ መልክ አዘጋጅቶ ለአመራሮቹ መበተኑ ይታወቃል፡፡ በገዢው ፓርቲ አመራርነት ውስጥ ቢገኙም የፕሬስ ነፃነት መሰበር ይኖርበታል ካሉ ከራሱ ሰዎች በደረሰን በዚህ ሠነድ ላይ “ጋዜጠኞችን ማሠር”፣ “ፕሬሱን ማገድ” በመፍትሄ አቅጣጫነት ሠፍሮ ተመልክተናል፡፡ ይህንንም ምርጫ 2007 ከመድረሱ በፊት “በአስተዳደራዊ” ውሳኔ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን ከደረሱን መረጃ ተገንዝበነዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፍትህ ሚኒስቴር፣ በብሮድካስት ባለስልጣናት፣ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳይ መ/ቤት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሎሚን ጨምሮ በስድስት የነፃው ፕሬስ ውጤቶች ላይ እየተወሰዱ ያሉ “ዘመቻዎች” ነገ የሚወሰደውን እርምጃ ከወዲሁ ጠቋሚ ናቸው፡፡ የቀደመውን ጊዜ አፈና ወደ ጎን ብለን ባለፈው ሐምሌ ወር የተወሰዱትን እርምጃዎች ብንቃኝ ከወዲሁ መልሱን በግልፅ እናገኘዋለን፡፡ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ባሰሙት ንግግር “ሁሉንም ነገሮች አፅድተን ወደ ምርጫው እንገባለን” ማለታቸው ምርጫው ከመድረሱ በፊት ከነፃው ፕሬስ ላይ እርምጃ የመውሰጃ የመጀመሪያ ፊሽካ ነበር፤ ሐምሌ 3/2006 ዓ.ም ምሽት ኢቲቪ “ዶክመንተሪ” ብሎ ባቀረበው “ድራማ” በነፃው ፕሬስ ላይ “ዘመቻ ፀሐይ ግባት” እወጃ ተጀመረ፡፡ በማግስቱ ጠ/ሚ/ሩ “በሕጋዊ ሁኔታ የተመሰረተ ፓርቲ አባል መሆን ወይም በጋዜጠኝነት ከለላ መንቀሳቀስ ከሽብርተኝነት አያድንም” በማለት የታሰረ ጋዜጠኛ በሌለበት ሁኔታ ምን ሊፈፀም እንደታሰበ ተጨማሪ ምንጭ ሰጡ፡፡
ሐምሌ 7/2006 ዓ.ም ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሠራተኞች “ያለ ንግድ ፈቃድ ነው መጽሔት የምታትሙት”፣ በድንገት “ያለፉትን ዓመታት የሂሳብ ሠነዳችሁን ልታቀርቡልን ይገባል” የሚል ሠበብ በመስጠት፣ ሆኖም ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ ከሃያ ባላነሱ መሣሪያ የታጠቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ታጅበው የ“ሎሚ” መጽሔት ቢሮን አሸጉ፡፡ ከቀናት በኋላ “ቢሮውን እንክፈት” ብለው ከመጡ በኋላም የሎሚ መጽሔትን ፋይል ወስደው መልሰው አሸጉት፡፡ ከቀናት በኋላ በየዕትሙ በመፅሔቱ ላይ ማስታወቂያ ያወጡ ድርጅቶች ለሎሚ ምን ያህል ብር ከፍለው ማስታወቂያ እንደሰሩ ከተጠቀሱት መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች እየተጠየቀ መሆኑን ገለፁልን፡፡ ከውስጥ አዋቂዎች በደረሰን መረጃም የግብር ቁልል እየተዘጋጀ መሆኑ ታወቀ፡፡ ሐምሌ 28/2006 ዓ.ም ደግሞ ፍትህ ሚኒስቴር ሎሚን ጨምሮ ስድስት የሕትመት ውጤቶች በፍርድ ቤት መከሠሣቸውን ገለጸ፡፡ የክስ መጥሪያ ሳይደርሳቸው የቆዩት አሳታሚዎችም የመዘጋጃ ጊዜ እንዳያገኙ በሚመስል መልኩ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ሁለት ቀን ሲቀራቸው መጥሪያው ደረሳቸው፡፡ ከነዚህ መሀልም የሎሚ መጽሔት አሳታሚ ዳዲሞስ ኢንተርቴይመንት እና ፕሬስ ሥራዎች ኃ.የተ.የግ. ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ ናቸው፡፡ ሌሎችም ተከሳሾች እንዳሉ ለአቃቤ ሕግ ተገለፀ፡፡
የሆነው ሁሉ እንደሚሆን ከአስተማማኝ ምንጮች መረጃ የደረሳት ሎሚ ሊፈፀም የታቀደውን በርዕሰ አንቀጿ በመጠቆም፣ መፍትሄው ግን ይህ እንዳይደለ ለማመላከት ጥራለች፡፡ ለአብነት ያህል ከአንድ ወር በፊት ሐምሌ 12/2006 ለንባብ የበቃችው “ሎሚ” በርዕሰ አንቀፅዋ የመንግስትን አቅጣጫ ተንብያ ነበር፡፡
አሁን የፕሬሱ ህልውናና የሎሚ አዘጋጆች አጣብቂኝ በሆነ አደገኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከአስተዳደራዊ ውሳኔ መፅሔቷ ከመታገድ፣ አዘጋጆቿም አስራ ስምንት ዓመት እና ከዚያም በላይ በሚያስፈርደው ፀረ ሽብርተኝነት ተከስሰው እንደሚቀጡ ከስጋት ያለፉ ምልክቶች በርክተዋል፡፡ ከገዢው ፓርቲ ጋር ቅርበት ያላቸው ውስጥ አዋቂዎችም “ሁለት ምርጫ” እንደቀረበልን፣ እስካሁን አለመረዳታችንም አሳስቧቸዋል፡፡ ምርጫው ሁለት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ “ጋዜጠኞቹ ታስረው የመፅሔቷ ሕትመት ይቋረጣል”፤ አሊያም ደግሞ “ወደ ስደት እንድታመሩ “የማርያም መንገድ” ተከፍቶላችኋል” የሚሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ሁለቱን መምረጥ አይቻልም፡፡ ምርጫው አንድ ነው፡፡ የሎሚ መጽሔት ክስ ዝርዝር የሚከተለውን ይመስላል፡-
ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወ/ችሎት
አዲስ አበባ
ከሳሽ፡- የፌዴራል አቃቤ ህግ
ተከሳሾች፡- 1ኛ/ ግዛው ታዬ ወርዶፋ
አድራሻ ጉለሌ ክ/ከተማ ቀበሌ 03
2ኛ/ ዳዲሞስ ኢንተርቴይመንት እና የፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር
አድራሻ ጉለሌ ክ/ከተማ ቀበሌ 03
1ኛ ክስ
ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ለ፣ 34/1/44/1/ እና 257/ሀ እና ሠ/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፡፡
የወንጀሉ ዝርዝር ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ወንጀሉና ወንጀሉ የሚሰጠውን ውጤት በመቀበል መንግስት የሚለወጠው ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መርህ በምርጫ ብቻ ሆኖ እያለ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ በአመፅ ስርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ 1ኛ ተከሳሽ ዳዲሞስ ኢንተርቴይመንት እና የፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር በስራ አስኪያጅነት፣ 2ኛ ተከሳሽነት በተጠቀሰው ድርጅት “ሎሚ” በሚል እየታተመ በሚወጣ መፅሔት በቅፅ 3 ቁጥር 109 በግንቦት 2006 ዓ.ም በወጣው ዕትም በገፅ 3 ላይ “በአለም በጨቋኝነቱ አቻ የማይገኝለት የሚዲያ ምህዳር በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በገፅ 3 ላይ ሰብዓዊ መብት የሚባል በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተረስቷል፡፡ የምንገኝበት አለም የመራጮች እና የለውጥ ማዕበሎች የሰፈነበት በመሆኑ ኢትዮጵያን በቀጣይ ዓመት በሚደረገው አገራዊ የአጠቃላይ ምርጫ በመንተራስ ለበርካታ አመታት ከዘለቀው የግፍ፣ የጭቆና አገዛዝ ለማላቀቅ የማይቀረውን የለውጥ ማዕበል ለማምጣት ራሳቸውን ለተጠናከረ ህዝባዊ አመጽ ማደራጀት መጀመራቸው ሊበረታታ የሚገባው ነው” በማለት በማሳተም 2007 ዓ.ም ምርጫ ከመካሄዱ በፊት አዋጪ የሚሆነው ለአመጽ መደራጀት፣ የኃይል ተግባር መፈጸም ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን በመጥቀስ ሕትመቱን ያሳተሙና ለህዝብ እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ፤ በአጠቃላይ ተከሳሾች ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ከሕገመንግስታዊ ሥርዓት ውጪ በአመጽ መንገድ ለማፍረስ
ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ለአመፅ የሚያነሳሱ ፅሁፎች አትመው በማውጣት በዋና ወንጀል አድራጊነት ቅስቀሳ ያካሄዱ በመሆኑ በፈፀሙት መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ መሰናዳት ወንጀል ተከስሰዋል፡፡
2ኛ ክስ
ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 (1) ሀ እና ለ፣ 34/እና 44/1፣ 486/ሀ እና ለ/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፡፡
የወንጀሉ ዝርዝር
ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን 1ኛ/ ተከሳሽ ዳዲሞስ ኢንተርቴይመንት እና የፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር ስራ አስኪያጅ በመሆን፣ 2ኛ/ ተከሳሽ በተጠቀሰው ድርጅት ሎሚ በሚል እየታተመ የሚወጣ መፅሔት ላይ በሃሰት ወሬዎችን በማሳተም ህዝብን ለማነሳሳት በማሰብ በቅፅ 3 ቁጥር 91 ከጥር 24 እስከ የካቲት 1 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው ዕትም በገጽ 6 ላይ “የአሸባሪነት ፈርጦች” በሚል ርዕስ ስር “ኢህአዴግም ከማን አንሼ በሚል ስሜት ተቃራኒ ሃሳብ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን፣ ለስልጣኔ /ለወንበሬ/ ያስጉኛል የሚላቸውን ጠንካራ ተቃዋሚዎችን እያደነ በአሸባሪነት ስም ወህኒ ያወርዳቸው ከጀመረ ሰንብቷል” በሚል የሀሰት ዘገባ በማሳተሙ እንዲሁም በገፅ 23 ላይ “የኢህአዴግ የሽብርተኝነት መመዘኛ ምንድነው” በሚል ርዕስ “ኢህአዴግ” የህዝብ ተቀባይነት ያገኘ አይመስለውም፡፡ ሕዝብ የተቀበለውና አምነዋለሁ የሚለው ሰው ለኢህአዴግ ጠላት ነው፣ ሽብርተኛ ተብሎ ይከሰሳል” በማለት በሽብር ሕግ ተከስሰው የተቀጡ ተከሳሾች በሕዝብ የሚወደዱ እና ለገዢው ፓርቲ ተቀናቃኝ በመሆናቸው ብቻ በግፍ የተቀጡ ንፁሀን እንደሆኑ የሚያስመስልና ሃሰተኛ ወሬ አትመው በማውጣታቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በሀሰት ወሬዎች ህዝብን ማነሳሳት ወንጀል ተከስሰዋል፡፡
የማስረጃ ዝርዝር
የሰነድ ማስረጃ
1. ሎሚ መፅሄት ቅፅ 3 ቁጥር 91 ገጽ 1፣ 6 እና 23 ገፅ 03 ገጽ ኮፒ
2. ሎሚ መፅሄት ቅፅ 3 ቁጥር 109 ገጽ 1፣ እና 3 03 ገፅ ኮፒ
3. ዳዲሞስ ኢንተርቴይመንት እና የፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግል/ ማህበር በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት የሰጠ የንግድ ፈቃድ ኮፒ 01 ገጽ ይላል ከፍትህ ሚኒስቴር የተላከልን የክስ ዝርዝር፡፡
የአፍርሮ ታይምስ ጋዜጣ እና የጋዜጠኛ ቶማስ አያሌው የክስ ዝርዝር ደግሞ የሚከተለውን ይመስላል፤
ለፌዴራል1 የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ወ/ችሎት
አዲስ አበባ
ከሳሽ፡- የፌዴራል አቃቤ ህግ
ተከሳሾች፡- 1ኛ/ ቶማስ አያሌው ተካልኝ፤
አድራሻ አራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 136
2ኛ/ ግዛውና ቶማስ ኢንተርቴይመንት የፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር
አድራሻ አራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 136
1ኛ ክስ
ወንጀሉ
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ለ፣ 34/1/44/1/ እና 486/ለ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፡፡
የወንጀል ዝርዝር
ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን አንደኛ ተከሳሽ ግዛውና ቶማስ ኢንተርቴይመንት የፕሬስ ኃ/ የተ/የግ/ማህበር ሥራ አስኪያጅ በመሆን በሁለተኛ ተከሳሽነት በተጠቀሰው ድርጅት አፍሮ ታይምስ በሚል እየታተመ በሚወጣ ጋዜጣ ላይ በሃሰት ወሬዎችን በማሳተም ህዝብን ለማነሳሳት በማሰብ ህዝቡ በሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ አመኔታ እንዳይኖረው፣ ጥርጣሬ እንዲገባው ለማድረግ በማሰብ በቁጥር 9 ሚያዝያ 21 እና 22 2006 ዓ.ም በወጣው የጋዜጣ ሕትመት በገጽ
1 ላይ “ልዩ ኃይሎችና መከላከያ ሠራዊት ተፋጠዋል” በሚል ርዕስ ስር “ቀደም ባሉት ጊዜያት በጋምቤላ ክልል ሰፍሮ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የፈለገውን ሰው ሲያስር፣ ሲገድል፣ ሴቶችን አስገድዶ ሲደፍር ቆይቷል፡፡ ይህም የሰራዊቱን ስርዓት አልበኝነት እና ሕገ-ወጥ ድርጊት ለማስቆም የሞከረ መንግስታዊ አካል አልነበረም” በማለት አገሩንና ሕገ መንግስቱን በመጠበቅ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ህብረተሰብ እና መንግስታት በመልካም ስነ-ምግባር ተግባሩ እያከናወነ ያለውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በህዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲያጣ፣ ጥርጣሬ እንዲገባው ለማድረግ ዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ሐሰተኛ ወሬዎችን በመንዛትና ሕዝብን በማነሳሳት ወንጀል ተከስሰዋል፡፡
የሰነድ ማስረጃ
የሰነድ
1.ቅፅ 1 ቁጥር 9 ሚያዝያ 21 እና 22 2006 ዓ.ም የወጣውን አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ 02 ገፅ ኮፒ፣

No comments: