Thursday, July 31, 2014

የተደራጁ ወንበዴዎች ለመፍጠር እየፈለጉ ያሉትን ብዥታ ለማጥራት -ከዳንኤል ተፈራ

July31/2014
10150630_609195442498727_1046966781_nባለፉት ጥቂት ወራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነ ስራ ሲሰራ ነበር፡፡ እሱም ውህደት ነው፡፡ የአንድነት/መኢአድ ውህደት ወሳኝና መሰረታዊ ድርድሮችን አልፎ የቅድመ ውህደት ፊርማው ከተቀመጠም ከወር በላይ ሆነው፡፡ከፊርማው በኋላ ውህደት አመቻች ኮሚቴ ተዋቅሮ በአጭር ጊዜ ነገሮችን መልክ ለማስያስ የቻለ ሲሆን ውህደቱም የሁለቱ መስራች የጉባዔ አባላት በተገኙበት ነሐሴ 3 እና 4 ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ታዲያ ከመስራች ጉባዔው አስቀድሞ ሁለቱ ፓርቲዎች በተናጠል ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የውህዱን ፓርቲ ደንብና ፕሮግራም፤ ለውድድር የሚቀርብ እጩ ፕሬዘዳንት መምረጥ፣ አዲስ ስያሜ በመጠቆም እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎችን በመስራት ይጠናቀቃል፡፡ በነገራችን ላይ የተናጠሉ ጉባዔ ስራውን የሚጀምረው አዲሱን የጋራ ደንብ በማፅደቅ ይሆናል፡፡ አጠቃላይ ውህደቱን ተቀበለው የሚባለው ደንብና ፕሮግራሙን ሲያፀድቅ ይሆናል፡፡
በአንድነት ፓርቲ በኩል በምክር ቤት ደረጃና በተለያዩ መዋቅሮቹ የሀሳብ ክርክር ማድረግ የተለመደ እንጅ ብርቅ አይደለም፡፡ የሃሳብ ክርክር ሲደረግ ‹‹ተባሉ፣ ምናምን›› እያሉ የሚጮሁት ከክርክሩ ትርፍ ለመሸመት የተሰለፉ ባእድ ሃይሎች እንጅ አንድነቶች አይደሉም፡፡ ነገዳቸው የሃሳብ ክርክር ከማውቀው ጎራ ስለሆነ የአንድነት አባላት የሃሳብ ፍጭት ሲያደርጉ ይደነግጣሉ፡፡ በአንድነት በኩል እጩ ፕሬዘዳንቶችን አስመልክቶም የተለመደው ክርክር ተደርጎ፤ እጩ ፕሬዘዳንቶቹ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ ሄደው ከሦስቱ አንዱ እንዲመረጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በድምፅ ተወሰነ፡፡ የቀረቡት እጩ ፕሬዘዳንቶች ከታወቁ በኋላም ደጋፊዎቻቸው እከሌ ቢመረጥ ይሻላል የሚል ሀሳብ የማቅረብ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ እኔም እከሌ ቢመረጥ ፖለቲካውን የተሻለ ያንቀሳቅሰዋል የሚል መብት አለኝ፡፡ ይህንን መብት የሰጠኝ ማንም ሳይሆን አንድነት ነው፡፡
ሀቁ ይሄ ቢሆንም የአንድነት ወገን ያልሆኑ ስማቸውን የደበቁ ወሮበላ ተላላኪዎች ሶሻል ሚዲያውን በመጠቀም የአለቆቻቸውን ትዕዛዝ ለማስፈፀም መንፈራገጣቸው አልቀረም፡፡ ዘመቻ ከተከፈተባቸው መካከል ደግሞ አንዱ እኔ መሆኔ ፈገግ ያሰኘኛል፡፡ ብዥታውን ማጥራት ያስፈለገኝም ለምን ስሜ ተጠቀሰ ብየ ሳይሆን የሀሰት ዘመቻውን አንድምታና ከየት አቅጣጫ እንደተሰነዘረ ለመጠቆም ነው፡፡ ዘመቻው የውሸት ስሞችን በመጠቀምና ማስጃ አልባ የተቀነባበሩ ስድቦችን በማዥጎድጎድ ብዥታ መፍጠር ነው፡፡ በተለይም ስርዓቱ ምንደኛ የሆኑ ተላላኪ ግለሰቦች ‹‹አሉላ እንደገና፣ ሰለሞን ሳልሳዊ፣ የፍቅር ቃልና አፄ ልብነድንግል›› የሚሉ የተልኮ ስሞችን በመጠቀም ውህደቱ ከመደረጉ በፊት ክፍፍል ለመፍጠር ኢህአዴጋዊ ተልዕኮ ተሰጥቷዋቸው እየባዘኑ ይገኛሉ፡፡ አንድነት አበቃለት እያሉ ስማቸውን ደብቀው እንደተራበ ቁራ ያንቋርራሉ፡፡ እነዚህን ከሙታን የሚለያቸው በድን ተንቀሳቃሽ መሆናቸው ነው፡፡ ህሊናቸውን የሸጡ ርካሽ ፍጡራን ናቸው፡፡
ዋናው ቁምነገር ዘመቻው ለምን ተከፈተ የሚለው ነው፡፡ የሚጠበቅም ነበር፡፡ ዘመቻው በተለይም በእኔና ጓዶቼ ላይ የተከፈተው ስለለውጥ፤ የተቃዋሚ ጎራውን የማይናድ መሰረት ስለማስያዝና የተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ስለተናገርን ብቻ ነው፡፡ ስለሰራን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መስራትን ደግሞ የአንድነት ልጆች ይደግፉታል እንጂ አይቃወሙትም፡፡ የሚቃወመው ሃይል ‹‹ተቃዋሚው ማንሰራራት የለበትም፤ እግር ማውጣት የለበትም›› ብሎ የሚያምነው ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ የስም ማጥፋት ዘመቻው በቀጣይ አመት የሚካሄደው ምርጫ ላይ የሚኖረንን ተሳትፎና ትግል አጋጣሚውን ተጠቅሞ የመምታት ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የተቀስኳቸው የሀሰት ስም ተጠቃሚ ባንዳዎች ሀብታሙ አያሌው ላይ ተመሳሳይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተው ነበር፡፡ ስም በማጥፋት እንደማይበገር ሲያውቁ አሰሩት፡፡
አንድነት ካቀረባቸው ሦስት ጠንካራ እጩዎች መካከል የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊው አንዱን ይመርጣል፡፡ ዋናው የሂደቱ ዴሞክራሲያዊ መሆን ነው፡፡ ኢንጅነር ግዛቸውና አቶ ትዕግስቱ ለአንድነት እዚህ መድረስ ያደረጉት ትልቅ አስተዋፅኦና የከፈሉት ዋጋ ሳይዘነጋ ነገር ግን አሁንም የእኔ እምነትና ፍላጎት ሀቅን መካድ ስለማይቻል ለአንድነት ፓርቲ አሁን ያለበት ከፍታ ላይ መድረስ በላይ ፈቃዱ ዋናው ስለሆነ፤ ትግሉን ወደ ህዝቡ ለማውረድና ከቢሮ ለማውጣት በነበረው ትንቅንቅ ላይ እውቀቱን፣ ገንዘቡንና ጊዜውን ያለ ምንም ስስት ሲሰጥ ስላስተዋልኩ፤ በላይ ፍቃዱ የሚታወቀው ሀሳብ በማመንጨትና ያ ሀሳብም ተግባራዊ እንዲሆን ሳይደክም በመስራት ስለሆነ፤ ‹‹የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት›› የሚለው ወሳኝ ህዝባዊ ንቅናቄ ስያሜ በበላይ በኩል የቀረበ እንደነበር ስለማውቅ እንዲሁም በላይ ፈቃዱ ፓርቲያችን የማተሚያ ማሽን ሊኖረው ይገባል የሚል ሃሳብ በማቅረብና በመተግበር ውጤት ያሳየም በመሆኑና በአጠቃላይ የጀርባ ሞተር ሆኖ የቆየ ውድ የአንድነት ልጅ ነው ብየ ስለማምን ለበላይ ድጋፌን እሰጣለሁ፡፡
ታዲያ ይህ ግልፅ እምነቴ በድብቅ ስሞች ስም ለማጉደፍ በሚሯሯጡ በገዥው ፓርቲ ምልምሎች በኩል የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲከፈትብኝ አድርጓል፡፡ ልብ በሉ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› ነውና በወሬኞች ላለመፈታት እንጠንቀቅ፡፡ ስም አጥፊዎቹ የአንድነት ልጆች ቢሆኑ ኖሮ እንደዘረዘሩት የሀሰት ውንጀላ አንድ ቀን አናድርም ነበር፡፡ የውሸት ስም መጠቀም ሳያስፈልጋቸው ቢፈልጉ ፕሬዘዳንቱ ጋ አሊያም የምክር ቤት ሰብሳቢው ጋ በማምጣት ባቀረቡ ነበር፡፡ አድናቆቴ ከፍ ይል የነበረውም ይህንን ማድረግ ቢችሉ ነበር፡፡ አሁንም እስከነፃነት ትግሉን እንቀጥላለን፡፡

No comments: