Wednesday, July 16, 2014

“አሸባሪ”ዎቹን ፍለጋ – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

June 15/2014
 (የሽብር – ዘፍጥረት ፫)
    ….በሁለት ተከታታይ ጽሁፎች የሽብርተኝነትን አነሳስ እና የአልሸባብን አፈጣጠር በደምሳሳውም ቢሆን መቃኘታችን ይታወሳል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባቱ ለምስራቅ አፍሪካው አደገኛ ቡድን መወለድ መንስኤ ስለመሆኑ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች እና ከሞቋዲሾ እስከ ኪስማዩ በደም ከተፃፈው የሠራዊቱ አባላት ገጠመኝ መረዳት ችለናል፤ ይህ ቡድን ዛሬ ከመንግስታዊ ተቋማት ይልቅ ንፁሀን ዜጐችን ዒላማ አድርጎ፣ የቀንዱን አገራት አካባቢ ወደ ሕግ-አልባ የጦር ቀጠናነት መለወጥ የሚያስችለውን ግዙፍ ኃይል አካብቶ አስፈሪ እየሆነ ስለመምጣቱ ማስተዋሉ አዳጋች አይደለም፡፡ ለርዕሰ-ጉዳያችንም መቋጫ የምናደርገው የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹ሽብር››ን እንዴት ለፖለቲካዊ ዓላማ እንደሚጠቀምበትና እነማንን በ‹‹አሸባሪ››ነት  ፈርጆ በመወንጀልና በማሳደድ እኩይ ተግባር ላይ መጠመዱን በጨረፍታ መመልከት በመሆኑ ወደዛው እናልፋለን፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
   የሽብር ድንበር…
የሽብር ድርጊትን ለዓላማቸው ማስፈፀሚያ መምረጣቸውን በይፋ አውጀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች፣ በአሰቃቂ አደጋዎች በሚመነዘሩ ጥቃቶች ንፁሃንን ለህልፈትና ለከባድ ፍርሃት በመዳረግ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በመገደብ ጥያቄዎቻቸውን በኃይል ለማስፈፀም መሞከራቸው የተለመደ ነው፤ ለዚህ ይቅር ለማይባለው ጭካኔያቸውም የድል ችቦ ለኩሰው ጮቤ ሲረግጡ በሀዘን ተመልክተናል፤ በቅርቡ በጎረቤታችን ኬኒያ ውስጥ የተፈፀሙትን ዘግናኝ የጅምላ ጥቃቶችና ፍንዳታዎችን ተከትሎ ቡድኑ የሰጣቸው መግለጫዎችም ይህንኑ ያስረግጣሉ፡፡ ከሁሉም በፊት ግን ‹‹የሽብር ድርጊት ምንድር ነው?›› የሚለው ጥያቄ ተፍታቶ መመለስ የሚኖርበት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በዳሰሳችን የምናገኘው ምላሽ ዓለም-አቀፍ ማሕበረሰቡን የሚያቀራርብ ቢሆንም፣ በተግባር ሲገለጥ ግን መጣረስ መኖሩን ማስረጃዎች ይጠቁማሉና፤ ስለዚህም የሽብርን አንድምታ ከየመንግስታቱ ባህርያት አኳያ በሁለት ምድብ ከፍለን እንመለከታለን፡፡
የመጀመሪያው በአንፃራዊነት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ማንበር የቻሉ አገራት እና ዓለም-አቀፍ ተቋማት ከሚሰጡት ብያኔ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በዚህ ምድብ ሽብርተኝነት የሚያቅፈው ትርጓሜም ሆነ አደጋውን ለመከላከል የሚወጡ ሕጎች በውስጣዊ የፖለቲካ ፍላጎት (በተለይ ሥልጣንን ከሕዝባዊ ሰላማዊ ተቃውሞ ለመከላከል) ያልተቃኙ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ‹የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ተቺዎችን ለማጥቃት ይውላሉ› ተብሎ አለመታሰቡ ከሞላ ጎደል ብዙሃኑን የሚያስማሙ (እንከን ባይታጣባቸውም በመግባባት የሚታለፉ) ተደርገው ይወሰዳሉ፤ የእነዚህ አካላት ብቸኛ ዓላማም አገርን እና ሕዝብን ከሰቆቃ መጠበቅ ላይ ያተኮረ እንደሆነ በመረጋገጡ ትርጓሜው ያን ያህል ሲያከራክር አይስተዋልምና ዝርዝር ነገር ከማተት ታቅበን፣ ወደ ሌላኛው ምድብ እንለፍ፡፡
በሁለተኛነት የምናነሳውና ዋነኛው ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወጥ-አምባገናዊ አገዛዝ በሚያስተዳድሯቸው አገራት የሚበየነውን የሽብር ድርጊት ነው፤ በእነዚህ ሥርዓታት ውስጥ ድርጊቱ አለቅጥ ከመለጠጡ በዘለለ፣ ለትርጉም አሻሚ የሆኑ አንቀፆች እንዲካተቱበት ስለመደረጉ ጉዳዩን ያጠኑ ምሁራን የደረሱበት ድምዳሜም ሆነ በተጨባጭ የታዩ የሐሰት ውንጀላዎች ያስረግጡልናል፡፡ ኩነቱን ከኢትዮጵያ አውድ አኳያ ካየነው ደግሞ ይሁነኝ ተብሎ የገዥው-ፓርቲን ስሁት ፖሊሲዎች እና አምባ-ገነናዊ ባህሪያት በድፍረት የሚተቹትን፤ እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅት አባላትን ለማጥቃት በ2001 ዓ.ም የፀደቀው የፀረ-ሽብር አዋጅ አንዳንድ አንቀፆች እንዲካተቱበት መደረጉን በማስረጃነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ በተለይም ከአረቡ ፀደይ በኋላ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ‹‹ለሥልጣኔ ያሰጉኛል›› በሚል የጠረጠራቸውን የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች፣ እንዲሁም ከኦሮሚያ በስመ-ኦነግ አፍሶ ካጎራቸው ንፅሃን እስከ የሙስሊም ኮሚቴዎች ድረስ በሐሰት እየወነጀለ ወህኒ ቤቱን ከአፍ እስከ ገደፉ ለመሙላት ያላዳገተውም በዚህ አስቀድሞ በዘረጋው ወጥመድ ይመስለኛል፡፡
  በርግጥ ይህን መሰሉ የገዥዎቻችን ብልጠት ዛሬ የተጀመረ አለመሆኑ አይካድም፤ ትላንት አርበኛው በላይ ዘለቀ እና ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያትን የመሳሰሉ የሀገር ባለውለታዎች፣ በአፄ ኃይለስላሴ አስተዳደር ‹‹አሸባሪ›› (ፀረ-ዘውድ) ተብለው የህይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን እናስታውሳለን፡፡ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ዘመነ-መንግስትም ቢሆን፣ ከጄኔራል አማን አምደሚካኤል እስከ ጄኔራል ተፈራ ባንቲ፤ ከኢህአፓ እስከ መኢሶን፣ ከኦነግ እስከ ህወሓት፣ ከጀብሀ እስከ ሻዕቢያ… ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ‹‹አሸባሪ›› (ፀረ-ሕዝብ) ተብለው ይሳደዱ፣ ይጨፈለቁና ይገደሉ እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት በተጨማሪ እውነታውን ይመሰክሩ ዘንዳ   በህይወት የሰነበቱ የዓይን እማኞች ያስረግጣሉ፤ ኢህአዴግም በምክር ቤቱ በኩል የያዘውን ሥልጣን በመጠቀም አካሄዱን ሕጋዊ ለማስመሰል በአዋጅ የደነገገው ይህንን የቀደመ ስልት በመኮረጅ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ስጋታችን ማነው?
አሸባሪ ቡድኖች ብዙውን ጊዜ የሚያቀነቅኑትን ፖለቲካዊ እና ኃይማኖታዊ አጀንዳዎችን ለማስፈፀም የየትኛውንም አገር ሕግ ከመጣሳቸውም በዘለለ ደም-አፋሳሽን በመሰለ አሉታዊ ገፅ የሚሸፈኑ መሆኑ እውነት ነው፤ ከዚህ ተነስተንም ስለጉዳዩ በምክንያታዊነት እንነጋገር ከተባለ፣ በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ቀንደኛው የስጋት ምንጭ ምንድር ነው? ብሎ ወሳኝ ጥያቄ ከማንሳት መጀመርን ግድ ይላል፡- በተጨባጭ ሀገሪቷን በታሪክ-አልባነት ለማፈራረስ ያንዣበበብን አደጋ የቱ ነው? ሥርዓቱ ያነበረው የጎሳ ፌደራሊዝም ወይስ እስክንድር ነጋ? የዕድገት ማነቆስ? አለቅጥ የተንሰራፋው መንግስታዊ ሙስና ወይስ እነርዕዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬ? አንገብጋቢው ችግራችንስ? በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሻቀበ ያለው ሥራ-አጥነት ወይስ እነአንዱአለም አራጌ እና በቀለ ገርባ? ተቻችሎ የመኖር እንቅፋትስ? የመንግስት በግላጭ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ወይስ እነአቡበከር መሀመድ? በርሃብ እንደ ቅጠል ለመርገፋችንስ? አስከፊው ድህነት ወይስ አንዳርጋቸው ጽጌ? የዲሞክራሲ ጋሬጣስ? ከአገዛዙ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት አራማጆችን በኃይል ማፈን ወይስ እነተስፋዓለም ወልደየስ? ለሕግ የበላይነት አለመከበርስ? ፍትህን በገንዘብ ሊገዛ ለከጀለ ባለጊዜ መቸርቸር ወይስ ‹በሰላማዊ መንገድ የሥርዓት ለውጥ እናመጣለን› በሚል የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ማሳደድ? …ለእነዚህና መሠል ጥያቄዎች አመክንዮአዊ ምላሽ ማግኘት ቀዳሚው ተግባር ይመስለኛል፤ ምላሾቹም ለአጠቃላይ አገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኃይማኖታዊ ችግሮች የማያዳግም መፍትሔ መስጠት
አይሳናቸውም ብዬ አስባለሁ፡፡
ማነው አሸባሪ?
ምንም እንኳ ጥያቄው ተራ ቢመስልም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተስተዋለው የሀገራችን ተጨባጭ እውነታ የሚነግረን ከሚታሰበው በተቃርኖው ነው፡፡ ጉዳዩን ያከረረው ገፊ-ምክንያትም አገዛዙ የሽብርን ትርጓሜ በፈለገ ወቅት ለጥጦ በመጠቀሙ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ በማንኛውም ሰዓት ሊወነጀልበት እንደሚችል እያሰበ በፍራሃት ተሸብቦ ሰጥ-ለጥ ብሎ እንዲያድር በማስገደዱም ጭምር ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት 7 እንደ አልቃይዳ እና አልሸባብ ሁሉ ‹‹አሸባሪ›› ድርጅቶች ተብለው መፈረጃቸው አይዘነጋም፡፡ ይሁንና እነዚህ አገር-በቀል ድርጅቶች ፖለቲካዊ ጥያቄዎቻቸውን የጦር መሳሪያ በማንገብ ለመፍታት የሚከተሉት መንገድ ‹ትክክል ነው፣ አይደለም›ን ጉንጭ አልፋ እሰጠ-እገባ ለጊዜው ወደጎን ብለን፣ የትጥቅ ትግል መስመርን ለምን መረጡ? የሚለውን የጨረፍታ ፍተሻ አናስቀድም፡፡
በቅድሚያም የኦሮሞ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ያለፈበትን ጥምዝምዞሽ ብንመለከት የምናገኘው እውነታ፣ ዛሬ በ‹‹አሸባሪ››ነት ከወነጀለው ኢህአዴግ ጋር በመተባበር የደርግ ሥርዓትን ለመቀየር ከመታገሉም በላይ በድሉ ማግስት የጋራ መንግስት መስርቶ፣ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ አካባቢ በጋራ ሀገር ሲያስተዳድር መቆየቱን የሚያስረግጥ ነው፤ ውሎ አድሮ አብዮታዊ ግንባሩ ‹ኦሮሚያን ያለከልካይ መቆጣጠር› የሚለውን ያደረ ትልሙን ለመተግበር፣ ትልቅ እንቅፋት የሆነበትን ኦነግን ከመንግስታዊው ሥልጣን ማባረር ቀንደኛ የቤት ሥራው በማድረጉ፤ ‹‹ሰላማዊና ሕጋዊ›› ተብሎ የተለፈፈለት የምርጫ ውድድር ሊካሄድ የቀናት ዕድሜ ሲቀሩት በስውር እጁ ጠምዝዞና አዋክቦ ከውድድሩ እንዲወጣ ማስገደዱን እንረዳለን፡፡ ይህንንም ተከትሎ ኦነግ የጣለውን ጠብ-መንጃ አንስቶ በኃይል ሥርዓቱን ለማስወገድ ‹‹ዱር ቤቴ!›› ብሎ ተመልሶ በርሃ መግባቱ ባይካድም፣ ወደዚህ ጠርዝ ለመገፋቱ ግን ዋነኛ ተጠያቂው (ኃላፊነት የሚወስደው›) ማን ነው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ቀላልና ግልፅ ነው፡፡    ሌላው በዚህ አውድ ሊጠቀስ የሚችለው ግንቦት 7 ነው፤ እንደሚታወሰው የዚህ ድርጅት ግንባር ቀደምት መስራቾች፣ በ1997ቱ ሶስተኛው ሀገር-አቀፍ ምርጫ ቅንጅቱን ወክለው ተወዳድረው እንዳሸነፉ ቢነገርም፣ ኢህአዴግ የቀድሞው ልምዱን በመጠቀም ‹‹ጨዋታው ፈረሰ፤ ዳቦ ተቆረሰ›› ብሎ ሁሉንም ከያሉበት ለቃቅሞ ወህኒ ቤት አጉሯቸው ሲያበቃ፤ እንዳሻው በሚቀልድበት ካንጋሮ ፍርድ ቤት አቅርቦ የዕድሜ ልክ እስራት ቅጣት ማስጣሉ የትላንት ትውስታችን ነው፡፡
እንግዲህ በዚህ አይነቱ በተቀነባበረ ሰው-ሰራሽ እሳተ-ጎመራ እንዲፈተኑ የተገደዱ ፖለቲከኞች፣ ያውም በቅድመ-ሁኔታ ከእስር ሲለቀቁ፣ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው ‹ለሀገራችን የሚበጅ ርዕዮተ-ዓለም አለን› ብለው ለትግል ከቆረጡ፣ የሚኖራቸው አማራጭ ምን ሊሆን ይችል ነበር? ብለን ብንጠይቅ፣ ሁላችንንም ሊያሳምን የሚችል ድምዳሜ ላይ መድረስ ቢሳነን እንኳ፣ ዛሬ ለመረጡት የትግል ስልት አሁንም ኃላፊነቱ ዞሮ ዞሮ መንግስታዊ ሥልጣን ከያዘው ኃይል ትከሻ ላይ እንደማይወርድ እሙን ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ ኢህአዴግ ሀገሪቷ የ‹‹አሸባሪ››ዎች ዒላማ መሆኗን ለማሳየት የሚጠቅሳቸው (ባለቤት ያላቸውም፣ የሌላቸውም)፣ በአዲስ አበባ አንዳንድ ሆቴሎች እና ሚኒባስ ታክሲዎች ላይ የተፈፀሙ ህይወት-ቀጣፊ አሳዛኝ ፍንዳታዎችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ጀምሮ ‹‹ፋክት›› መጽሔት ድረስ ባሉ የሚዲያ ውጤቶች በስፋት የተዘገቡ በመሆኑ መድገሙ አስፈላጊ አይደለምና አልፈዋለሁ፡፡ በግልባጩ የአልሸባብ አሸባሪነትንም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ያለው ብርቱ ፍላጐት ለማንም ስለማያጠራጥር፣ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ሀገሪቱንና ዜጎቿን ከየትኛውም አደጋ መጠበቅ በመሆኑ፣ ከዚህም በላቀ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለበት እገነዘባለሁ (ይህ ጥንቃቄ ጥልቅ ከሆነው ድህነታችን አንፃር በጥቅም ተማልለው በግብረ-አበርነት ሊሳተፉ የሚችሉ ወንድም-እህቶችንም በአይነ-ቁራኛ መከታተልን ያካትታል)፡፡ ምክንያቱም እውነተኞቹ የሽብር ኃይሎች (በመለስ ዜናዊ አገላለፅ ‹‹ፕሮፌሽናሎቹ››) የሰናፍጭ ታህል ቀዳዳ ካገኙ ዘግናኝ የሕዝብ እልቂት እና ከባድ የንብረት ውድመት ከማድረስ እንደማይመለሱ ከኬኒያ ክራሞት መረዳት ይቻላል፡፡
በተጨማሪም ከሥርዓቱ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ድርጅቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾችም ሆኑ ዜጎች… አልሸባብን የመሳሰሉ ኃይሎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት እኩል ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው አልዘነጋውም፡፡ ይህ ማለት ግን በተጭበረበረ ምርጫ ባሸነፉ የገዢው ፓርቲ አባላት የተሞላው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ የዓይኑ ቀለም ያላማረውን በሙሉ ‹‹አሸባሪ›› ብሎ እያሳደደ የሚፈርጀውን እንደወረደ በመቀበል ማውገዝ አለመሆኑን ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ በግሌም ከአልቃይዳ እና አልሸባብ በቀር፣ ሌሎቹ ድርጅቶች የሚከተሉት የትግል ስልት ሕጋዊና ሰላማዊ አለመሆኑ ባይካድም፣ የብሔራዊ ቡድናችንን እግር ኳስ ጨዋታ ለመመልከት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚሰበሰበው ዜጋን፣ አሊያም በሕዝብ የመጓጓዣ አገልግሎት ታጭቆ የሚጓዝ ንፁሃንን የጥቃት ዒላማ አድርገው ሲንቀሳቀሱም ሆነ ሲተግብሩ አለመታየታቸውንም፤ አለመሰማታቸውንም እመሰክራለሁ፤ በ‹‹ማኒፌስቶ››አቸውም ውስጥ ሲቪሉ ኢትዮጵያዊን በአሳቻ ቦታ ባጠመዱት ፈንጂ ስለማጋየት የሚያወራ ሽራፊ አንቀፅ አላነበብኩም፤ በአጠቃላይ ሰላማዊ ዜጋን በሽብር ድርጊት ለማመስ የቀመሩትን ‹‹ስትራቴጂ›› የሚያጋልጥ ጥናትም ሆነ የውስጥ-አወቅ መረጃ አጋጥሞኝ አለማወቁን  አልሸሽግም፡፡ …የሆነው ሆኖ በኢትዮጵያችን የ‹‹ሽብር›› ዘፍጥረት ቅድመ-ታሪክ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል ብዬ አምናለሁ፡፡
   በተቀረ የአል-ቃኢዳውን አይማን አልዘዋሀሪ፣ አሊያም የአልሸባቡን አህመድ አብዲ ጎዳኔ፣ ወይም የቦኮ-ሀራሙን አቡበክር ሼኩ የመሰለ በለዒ-ሰብ፣ ከኢትዮጵያውያን ‹‹አሸባሪ››ዎች መካከል ፈልገን የምናገኝ አይመስለኝም፤ ሌላው ቀርቶ ከሳሹ ኢህአዴግም የታሳሪዎቹን ንፅህና ከማንም በላይ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ሆኖም ሀገሪቱ ኢትዮጵያ ነችና፣ በደነበረና ምርጫ በተቃረበ ቁጥር ‹‹አሸባሪ›› በሚል የሀሰት ወንጀላ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን…  ለእስርና ስቅየት የሚዳርግበት በስዩመ ጠብ-መንጃ ሥልጣን ራሱን ከቀባ ከሁለት አስርታት በላይ ተቆጥሯል፤ መስከረም እስኪጠባም ድረስ ይኸው የነፍጠኝነት ዘመን መቀጠሉ አይቀሬ ይሆናል፡፡   በነገራችን ላይ እስከዚያው አቶ አንድአርጋቸው ጽጌ ሰሞኑን ከየመን ተይዞ ሞት ለፈረደበት የኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱን ሰምተናል፤ በርግጥ የመን ከዚህ የሰው ንግድ ገበያ ምን እንዳተረፈች የተገለፀ ነገር የለም (መቼም በደጉ ዘመን፣ አክሱማውያን ያስገብሯት የነበረችው ምድረ-አረብ፣ ይህ አይነቱን ያውም የራስን ሀገር ክብር የሚነካ ውለታን በብላሽ ፈፀመች ቢባል ማን ያምናል?) እንደዚያም ሆኖ ግን የአምባ-ገነኑ መሪያችን የአቶ መለስ ዜናዊን ህልፈት በሰማን ጊዜ እንደ ሰው እንዳዘንነው ሁሉ፣ እንዳርጋቸው ጽጌም ከአፄው ዘመን ጀምሮ በእምነቱ ፀንቶ ጉልበታም አገዛዞችን ሲገዳድር ከአርባ ዓመት በላይ ዋትቶ ዋትቶ፤ ዛሬ ሞቱን በሚሹ ሰዎች እጅ በመወድቁ ሊደርሰበት በሚችለው መከራና ስቀየት ከልብ ከማዘን ያለፈ የማደርገው ነገር ባይኖርም፣ ‹የኢትዮጵያ አምላክ ብርታቱን ይስጥህ› ማለትን
ወደድኩ፡፡
              እንደ መውጫ
ዘርፈ-ብዙ በሆኑ የግንኙነት ሰንሰለቶች እየተጠላለፈ ከመጣው የዓለም ገፅታ ተገንጥሎ ጉልበተኛ ሥርዓት ይመሰረትበት የነበረው የአምባ-ገነንነት ዘመን ጀምበር እየጠለቀበት ይመስላል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት እስከ ፖለቲካዊ ስምምነቶች ያሉ የትብብር ውሎችም አስገዳጅ በሆኑ ሕጋዊ ማዕቀፎች መጠፍነግን የመሰለ ጫና ስለማሳረፋቸው ከሁነቱ ለማፈንገጥ የሞከሩ ጥቂት የማይባሉ አገራትን የማታ ውድቀት ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በተለይም ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የተስተዋሉ ታሪካዊ ክስተቶች ዓለምን በማጥበባቸው፣ በተደጋጋሚ አምባ-ገነን አስተዳደርን ያስተናገዱ አገራት እንኳ ሳይቀሩ፣ በአዲስ ፖለቲካዊ ልምምድ እንዲቃኙ የዕድል በር ተከፍቶላቸዋል፡፡ ነገም  የለውጡን መንፈስ በመቃወም ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመንበርከክ አሻፈረኝ የሚሉ መንግስታትም፣ ከድንገቴው ፍርስራሾቻቸው ሥር ትውልዱ የነፃነት ብርሃን ይጎናፀፍ ዘንድ ዘመኑ ስለመፍረዱ ለመናገር ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ በእኛይቷ ኢትዮጵያም ተወደደም ተጠላ ከሁለት አስርታት በላይ እንደ ምርጊት የተጣበቀብን ኢህአዴጋዊ አስተዳደር የመጨረሻ ስንብት፣ በዚህ መንገድ ስለመበየኑ አስተማመኝ ፍንጮች መታየታቸውን በድፍረት እመሰክራለሁ፡፡ እልፍ አእላፍ እግሮችም ወደ የለውጥ አደባባዩ የማምራታቸውን ብልጭታ፣ የትኛውም ምድራዊ ኃይል ሊያጨልመው ይችላል ብሎ ማሰቡ ፈርኦናዊ መታበይ ካልሆነ በቀር አንዳችም ፋይዳ አይኖረውም።
ይሁንና አገዛዙ እንዲህ በውድቀቱ ዋዜማ ላይ ቆሞም በክፋት መፀናቱ ጥቂት ጥያቄዎችን እንድናሰላስል ይገፋል፡- ይህ አይነቱ የናዳ መዓት ተንከባሎ እስኪያደባየው ድረስ ስለምን በግትርነት ቆሞ ይጠብቃል? ሊገታው የማይችለውን ማዕበል በመጋፋትስ፣ በእናት አገር የእንባ ጎርፍ ውቂያኖስ መፍጠርን ስለምን መረጠ? እንዲህ የትውልድ ደም በከንቱ ለማፍሰስስ ስለምን አሰፈሰፈ? የሀገሪቱ ዕጣ-ፈንታ በጠብ-መንጃ ብቻ ይወሰን ዘንድ ስለምን ጨከነ? …ርግጥ ነው የእነዚህ ጥያቄዎች ምላሾች ሟርትም ይሁን ገድ፣ በሀገሬ ምድር አዲስ የታሪክምዕራፍ የመገለጡን አይቀሬነት ቅንጣት ጥርጣሬ ውስጥ አይከቱትም፡፡ በአናቱም ዛሬ አገዛዙን በትጥቅ ትግል ለመፋለም ከአስራ አንድ የማያንሱ ቡድኖች ‹‹ክተት›› አውጀው በርሃ መግባታቸው፣ የደርግን የመጨረሻዎቹ ቀናት ማስታወሱ አንዳች የሸሸገው ምስጢር አይኖረውም ማለት ታሪክን በቅጡ አለመረዳት ይሆናል፡፡
የሆነው ሆኖ የኢህአዴግ እምቢ-ተኝነት አውዳሚ ጥፋት ሊያደርስ ቢችልም እንኳ፣ በሂደቱ የምንሻገራቸው አደጋዎች፣ የምንወጣቸው አቀበቶች፣ የምንወርዳቸው ቁልቁለቶች፣ የምናቋርጣቸው ጫካዎች… የማታ ማታ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማዋለዳቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ትንቅንቅ መካከልም ለዘመናት የልዩነት መንስኤ የሆኑት፣ ከርዕዮተ-ዓለም እስከ ኃይማኖት፤ ከኢኮኖሚ ሥርዓት እስከ መሬት ይገባኛል ድረስ የሚመዘዙ ጥያቄዎች የሚያደርሱት ኪሳራ በሀገር ፍርሰት፣ በትውልድ እልቂት ሳይወራረድ በፊት፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይቻል ዘንድ የኢህአዴግን እጅ ከመጠምዘዝ ጎን ለጎን ብሔራዊ እርቅን አሳክቶ በድል ጎዳና በዝማሬ ለመትመም ሁላችንም የፖለቲካ ልዩነትን ለጊዜው ወደጎን ብለን በአንድነት እንድንቀሳቀስ ያስገድደናል፡፡ ይህንን ተልዕኮ ለማሳካትም ከክር የቀጠነው ብቸኛ አማራጫችን ደጋግመን የተነጋገርንበት ‹‹የሕዳሴ አብዮት›› ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments: