Wednesday, July 2, 2014

አንዳርጋቸውን ፍለጋ በየመን…ወዳጄ የሀገር ሰው የት ይሆን የታሰርከው?

July 1/2014
በግሩም ተ/ሀይማኖት

ትላንት ነው አስደንጋጭ ዜና የሰማሁት፡፡ ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን መታሰር፡፡ ከምር በጣም ደንግጫለሁ፡፡ የመን ያለውን ሁኔታ ስለምኖርበት በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ የመን አሁን ያሉም በፊት የኖሩም በትክክል ያውቁታል፡፡ ድንጋጤዬን እንደያዝኩ በተለያየ ሀሳብ እና መላምት ስታትር፣ ነግቶ የት እንዳለ ለመፈለግ የት የት ሄጄ መፈለግ እንዳለብኝ ውስጤ በእቅድ ስነድፍ ቆየሁ፡፡ እቅዴ ተወስኖ ሳያልቅ ከተለያየ አቅጣጫ የሚያውቁኝ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሰዎች ተንቀሳቃሽ ስልኬ(ሞባይሌ) ላይ እየደወሉ ስለሁኔታው ይጠይቁኛል፡፡ የማውቀው እንደሌለ እና ምን ማድረግ እንደምችል ግራ እንደገባኝ ከመንገር ውጭ መልስ አጣሁ፡፡ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ለሚደወልልኝም መልስ አጠረኝ፡፡ ሌሊቱ እስኪጋመስ ድንጋጤዬ አለቀቀኝም፡፡ የድንጋጤዬ መንስኤ ሶስት ነገር ነበር፡፡

1ኛ፡- የመን እንደገባሁ ተይዤ እስር ቤቶቹን ስላየኋቸው፡፡ እኔን አንድ ጋዜጠኛ ወደ ሀገሬ ለመመለስ ‹‹ወኪል ኒያባ›› የሚባለው ፍርድ ቤት እስከማቆም የወያኔ ካድሬዎች ያደረጉትን በማሰብ…


2ኛ፡- ከኢትዮጵያ ውጭ የወያኔ ካድሬዎች እንደልብ ከሚንቀሳቀሱባቸው ሀገሮች የመን የመጀመሪያዋ እና በሺህ የሚቆጠሩ ካድሬዎች ያሉባት በመሆንዋ…


3ኛ፡- የመንና ኢትዮጵያ እ.አ.አቆጣር ከ2004 ጀምሮ በየአመቱ የሚታደስ ወንጀለኛ የመለዋወጥ የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸው በመሆኑ ነው ድንጋጤዬ ልክ ያጣው፡፡


ባሰብኩት መሰረት ፍለጋዬን ለመቀጠል በዛሬው እለት ጠዋት…የኢሳቱ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ጋር በመደወል መታሰሩን ሲሰሙ የታሰረበትን እስር ቤት ሰምተው እንደሆነ ጠየኩኝ፡፡ ምንም ፍንጭ የለም ትራንዚት ሲያደርግ መያዙን ብቻ ነው የሚያውቁት፡፡ ፍለጋዬን ከሚግሬሽን እስር ቤት ጀመርኩ፡፡ ሞባይል ስልኬ ግን በሁኔታው የተጨነቁ ሰዎች ሲደውሉ ተጨናንቆ ዋለ፡፡ ኢሚግሬሽን እስር ቤት አስፈልጌ የለም፡፡ ወደ ኤርፖርት በመሄድ እዛው ባለው ጊዜያዊ እስር ቤት ታስሮ ከሆነ አስጠየኩ፡፡ የለም፡፡ በመቀጠል የደህንነት ቢሮ በእነሱ አጠራር ‹‹አምንስቲያሲ..›› ሄጄ የሚታወቅ ነገር እንዳለ ጠየኩ፡፡ የረመዳን ጾም በመሆኑ የፍጡር ሰዓት ደርሷል እና ከፈለክ ክፍጡር በኋላ ካልሆነም ነገ ጠዋት መተህ ጠይቅ አሉኝ፡፡ ምን አስችሎኝ ነገ ድረስ ልቆይ…ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ሄጄ ባስፈልግም የለም ሆነ ያገኘሁት ምላሽ፡፡


‹‹..ወዳጄ የሀገሬ ሰው የት ይሆን የታሰርከው?..›› የሚል እሳቤ ውስጤ ተላወሰ፡፡ ለነገሩ የታሰረበትን ባውቅስ ምን ማድረግ እችል ይሆን? የሚል እሳቤም ሰቅዞ ያዘኝ፡፡ በእርግጥ የመን ከታሰረ ያለው ሁኔታ በጥሩ መንፈስ አይሸትም እና ሁላችንም ተላልፎ እንዳይሰጥ ድምጽ እንድናሰማ ለራሴ አሳሰብኩኝ፡፡…ፍለጋው አያልቅም ነገ ቸር ያሰማኝ ይሆን?...ፍለጋው አያልቅም ነገ ቸር ይገመኝ ይሆን?

No comments: