Wednesday, July 2, 2014

ሎሚ መጽሄት ከአብርሃ ደስታ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ

July2/2014
“ሕወሓት በ2007 ምርጫ እንደማይመረጥ አውቋል”
“ዓረናን ለማፍረስ ቢሞከርም አልተሳካም”
“ዓረና ሕወሓትን ያስደነገጠ እንቅስቃሴ አድርጓል”
===============================
አቶ አብረሃ ደስታ (የዓረና የፖሊት ቢሮ አባል)
የአረና ፖሊት ቢሮ አባል የሆነው አቶ አብረሃ ደስታ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሎሚ መጽሔት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቶማስ አያሌው ጋር እንደሚከተለው አውግቷል፡፡
ሎሚ መጽሄት የፊት ገጽ
ሎሚ መጽሄት የፊት ገጽ
ሎሚ፡- በአሁኑ ወቅት የአረና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አብረሃ፡- ዓረና ሦስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ ከህዝብ ጋር ለመገናኘት፣ ህዝብን ለመሰብሰብ፣ ለማስተማርና ለማደራጀት እንዲሁም ለነፃነቱ እንዲነሳ ለመቀስቀስ ባቀደው መሰረት በተሳካ ሁኔታ ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል። እስካሁን ድረስ በአስራ አምስት ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ ጠርተናል። በአስራ አንዱ የተሳካ ስብሰባ ሲደረግ በሽረ እንዳስላሴ፣ ዓዲግራት፣ ሑመራና ሐውዜን ግን በካድሬዎች ሴራ ተስተጓጉሏል። በሰባ አንድ የትግራይ ከተሞችና የገጠር መንደሮች የተሳካ ቅሰቀሳ ተደርጓል። የዓረናን አማራጭ ፖሊሲ የያዘ በራሪ ወረቀት ታድሏል። ዓረና ከምንም ግዜ በላይ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤ ተስፋም ተጥሎበታል። የህወሓት አባላትም ዓረናን ወደ መደገፍ የሚሸጋገሩበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ባጠቃላይ ዓረና ያደረገው እንቅስቃሴና እያገኘ ያለው የህዝብ ድጋፍ ህወሓትን አስደንግጦታል።
ሎሚ፡- በፓርቲያችሁ ውስጥ ልዩነት ስለመኖሩ ይነገራል፤ ካለስ ምክንያቱ ምንድነው?
አብረሃ፡- በዓረና ውስጥ ልዩነት አልተፈጠረም። ቅሬታ የሚያነሱ ግለሰቦች ግን አሉ። ቅሬታውም ከዓረና ዕቅድና ህወሓት በዓረና አባላት ላይ እያሳረፈው ካለው ጫና ይመነጫል። ዓረና ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲወስን ገና ከጅምሩ ያልተዋጠለት አንድ አባል ነበር። ዕቅዱ የአብዛኛውን ድምፅ አገኘና ፀደቀ። የዓረና አመራር አባላት ወደ ህዝብ ወርደው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተስማማን። በዚሁ መሰረት ሁሉም የማእከላዊ ኮሚቴና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት የየራሳቸው የስራ ድርሻ ተሰጣቸው።
ሁሉም የዓረና አመራር አባላት በተሰጣቸው የስራ መስክ ሲሰማሩ ሁለት አመራሮች ግን የተሰጣቸውን የስራ ድርሻ ሳይቀበሉ ቀሩ። ከሃያ አምስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንዱ ወደ ህዝብ ወርዶ የፓርቲ ስራ ለመስራት ፍቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ከሰባቱ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትም አንድ አባል ላለመስራት ወሰነ። ስለዚህ ከሰላሳ ሁለት ሰዎች ሁለት ብቻ የፓርቲ ስራ ለመስራት ፍቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። ሰላሳዎቹ ግን በየተመደቡበት የስራ ዘርፍ ተሰማርተው እነሆ ህወሓትን ያንቀጠቀጠ ዉጤት አስመዝግበዋል።
በዓረና ፓርቲ እንቅስቃሴ ለመሳተፍና የበኩሉን ለመወጣት ፍቃደኛ ያልሆነ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሺሻይ አዘናው ሲሆን፤ የቁጥጥር ኮሚሽኑ አባል ደግሞ ገብሩ ሳሙኤል ነው። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ከዓረና ጉባኤ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በማንኛውም የፓርቲ እንቅስቃሴ፣ ስልጠና፣ ስብሰባ ወይ የፓርቲ ስራ አልተሳተፉም። እንደ አባላት የፓርቲ ወርሃዊ ክፍያም አላደረጉም። በዚህ ምክንያት በጉባኤ ተመርጠው ሓላፊነት ተሸክመው የተሰጣቸውን ሓላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው በማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሊገመገሙና ለያዙት አፍራሽ ተልእኮ ሊከሰሱ ዕቅድ ተይዟል።
ሌላ ለችግሩ ምንጭ ነው ብለን የምንወስደው የህወሓትን ጫና መቋቋምህ አለመቻል ነው። ህወሓት በዓረና እንቅስቃሴ በመሸበሩ ምክንያት ዓረናን ለማዳከም፣ ከህዝብ ጋር እንዳይገናኝ ለማድረግ እንዲሁም ለማፍረስ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። የህወሓት ዋነኛ ጠላት ዓረና ሆኗል። በዚህ ምክንያት በመከላከያ ደህንነት አማካኝነት በዓረና አባላት ላይ ጫና ለመፍጠር እያንዳንዱ የዓረና አባል ተጠንቷል። ጥናቱ ምን ይፈልጋል? በምን ሊደለል ይችላል? ይፈራል ወይ? ቢታሰር ነው የሚሻለው ወይስ ቢመከር? ወይስ ቢደበደብ? ወዘተ በሚሉ ነጥቦች ላይ ያተኩራል።
እንደ ውጤቱም ብዙ የዓረና አባላት አባልነታቸውን ከለቀቁ ገንዘብና መሬት እንደሚሰጣቸው፣ ስልጣን እንደሚሰጣቸው ወዘተ ተነግሯቸዋል። ሌሎችም አባልነታቸውን ካላቆሙ እንደሚደበደቡ፣ እንደሚታሰሩ፣ እንደሚገረፉ፣ ከስራ እንደሚባረሩ፣ ንብረታቸውን እንደሚነጠቁ፣ እንደሚገለሉ፣ እንደሚገደሉ ተነግሯቸዋል። በተነገራቸው መሰረት ጥቅም ያገኙ አሉ። ከስራቸው የተባረሩ አሉ። የታሰሩና የተገረፉ አሉ። ሃብት ንብረታቸውን የተነጠቁ አሉ። ሲቀሰቅሱ በድንጋይ የተወገሩ አሉ። አሁን ብዙ የዓረና አባላት በእስር ላይ ይገኛሉ፤ ቃላቸውን በመጠበቃቸው እና በህወሓት ሊደለሉ ባለመቻላቸው።
ስለዚህ ጥቂቶች ህወሓት በሚፈጥረው ጫና ሲደናገጡ ብዙዎች ግን በቆራጥነት እየታገሉ ነው። አቶ ሺሻይ አዘናውና ገብሩ ሳሙኤል በዓረና እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ያልፈለጉበት ምክንያት ምናልባት በዓዲግራት በድንጋይ ስንወገር ስላዩ ይሆናል። ፍርሓትም አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በዓረና መርህ መሰረት አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል ግንባር ቀደም ሁኖ መሳተፍ ይጠበቅበታል። መፍራት የለበትም። በጥቅም ሊደለል አይገባም። ከህወሓት ጎን ተሰልፎ ዓረናን ለማፍረስ ጥረት ማድረግ የለበትም።
በፓርቲ ውስጥ ችግር ካለ በፓርቲ ስብሰባ ይገመገማል፤ ይጣራል፤ ይፈታል። በዓረና ፓርቲ የተፈጠረው የነ ሺሻይና ገብሩ በስራ ምክንያት አለመገኘት ችግር በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲነሳ ተወስኗል። ማንኛውም የውስጥ ችግር በውስጠ ደንብ ነው የሚታየው። ዓረና የነኚህ ሁለት የአመራር አባላት እምቢተኝነት በማዕከላዊ ስብሰባ አጀንዳ እንደሚሆን ሲነገራቸው ግን “ጉባኤ መጥራት እንፈልጋለን” የሚል ደብዳቤ ለዓረና ፅህፈት ቤት አስገቡ፡፡ ራሳቸው የፈጠሩትን ችግር ላማድበስበስ በፓርቲው ውስጥ ችግር እንዳለ አስመስለው አቀረቡ። “ጉባኤ እንጠራለን” የሚል ጥያቄያቸውም በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንደሚታይ ተነገራቸው።
እነሱ ደብዳቤ ሲያስገቡ ህወሓትም ዓረና እየፈረሰ ነው የሚል ወሬ መንዛት ጀመረ። በተመሳሳይ ግዜ አቶ ሺሻይ አዘናው፣ አቶ ገብሩ ሳሙኤልና አቶ አስገደ ገብረስላሴ “ፓርቲው እየፈረሰ ነው፣ አንባገነንነት እየሰፈነ ነው፣ የዓረና አባላት እየወጡ ነው፣ አስቸኳይ ጉባኤ እንድንጠራ ይፈቀድልን” የሚል መልእክት ያለው ቅሬታ ለዓረና ፅህፈት ቤት አስገቡ። “ጉዳያችሁን በስብሰባ እናየዋለን። እስከዛ ድረስ ግን እንደ አባላት በፓርቲው ስራ ተሳተፉ፣ መብታችሁን ለመጠየቅ ግዴታችሁን ተወጡ” የሚል መልስ ተሰጣቸው። አቶ አስገደ በፓርቲው ስራ ሲሳተፍ አቶ ሺሻይና አቶ ገብሩ ግን አሻፈረን አሉ።
ቀጥለውም ዓረና በተለያዩ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎችና ቅስቀሳዎች በሚያደርግበት ግዜ፣ የዓረና አመራር አባላት በስራ በተጠመዱበት ግዜ በስራ ከመሰማራት ይልቅ “ፓርቲው እየፈረሰ ነው፣ አስቸኳይ ጉባኤ እንጠራለን” የሚል ፅሑፍ ድጋሚ አስገቡ። ህወሓትም ተመሳሳይ አጀንዳ ፈጠረ። ዓረና እየፈረሰ ነው እያለ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ጀመረ። ጉዳዩ ሌላ ተልእኮ እንዳይኖረው በመጠርጠር መቐለ የሚገኙ የዓረና የስራ አስፈፃሚ አባላት ተሰብስበው “የአስቸኳይ ጉባኤ” ጥያቄ ለመመለስ ያህል ጥያቄው ፕሮሲጀሩን (Procedure) ጠብቆ መምጣት እንዳለበት ወሰኑ።
በዚሁ መሰረት ሦስቱ ቅሬታ አቅራቢዎች የዓረናን ህገ ደንብ አክብረው ህገ-ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ተነገራቸው። አቶ አስገደ ገብረስላሴ ተራ አባል እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም ጥያቄ ለመሰረታዊ አደረጃጀት ያቀርባል። መሰረታዊ አደረጃጀቱ ጥያቄውን መርምሮ ከተቀበለው ለክልል ፅህፈት ቤት ያስገባል። ስለዚህ አስገደ በዓረና ህገ-ደንብ መሰረት ጥያቄውን በመሰረታዊ አደረጃጀቱ በኩል እንዲያስገባ ተጠየቀ፤ ህገ ደንቡ የሚፈቅደው ይሄ ነውና። አስገደ ያለበት መሰረታዊ አደረጃጀት አባላትና ሐላፊዎች ግን የአስገደን ጥያቄ እንደማያውቁ፣ ቅሬታም እንዳላስገባላቸው መሰከሩ። ስለዚህ አስገደ ለሚመለከታቸው አካላት ቅሬታውን አለማቅረቡ ታወቀ። በህገ-ደንቡ መሰረት አንድ ተራ አባል መሰረታዊ አደረጃጀትን ሳያሳውቅ ዘው ብሎ ወደ ክልል ፅሕፈት ቤት አያስገባም። አንድ ተራ አባል አስቸኳይ ጉባኤ ለመጥራት የመሰረታዊ አደረጃጀቱ አባላት ሊቀበሉትና ሊያፀድቁት ይገባል።
አቶ ሺሻይ አዘናው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆኑ ጥያቄውን ለማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲያቀርብ ተነገረው። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል “አስቸኳይ ጉባኤ” ለመጥራት ከማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ቢያንስ አንድ ሦስተኛ ሊቀበሉት ይገባል። ከሃያ አምስቱ የዓረና ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ሺሻይ አዘናው አንድ ነው። አንድ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አስቸኳይ ጉባኤ የመጥራት ስልጣን የለውም፤ በህገ-ደንቡ መሰረት። የሺሻይ ጥያቄ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንደሚታይ ግን ተነግሮታል። የዓረና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በሁለት ሳምንታት ግዜ ውስጥ እንደሚካሄድም ተነግሮታል። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጥያቄ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ይፈታል።
ሦስተኛው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ገብሩ ሳሙኤል ደግሞ የቁጥጥር ኮሚሽን አባል በመሆኑ ቅሬታው ይሁን የአስቸኳይ ጉባኤ ጥያቄ ለሚሰራበት የቁጥጥር ኮሚቴ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ጥያቄው ለኮሚሽኑ ካቀረበ በኋላ የኮሚሽኑ አንድ አራተኛ አባላት ከተቀበሉት ጥያቄው ተቀባይነት ይኖረዋል። አቶ ገብሩ ሳሙኤል ግን ለቁጥጥር ኮሚሽን ያቀረበው ጥያቄ የለም። በመሆኑም የገብሩ ጥያቄ ወደ ቁጥጥር ኮሚሽን መሆን እንዳለበት ተነግሮታል።
የሦስቱም ጥያቄዎች በዓረና ህገ-ደንብ መሰረት procedure ጠብቀው መምጣት እንዳለባቸው ሲነገራቸው አቶ ሺሻይና አቶ ገብሩ “ጥያቄያችን ታፍኗል” ብለው የዓረናን ስም የሚያጠፋ ፅሑፍ በተኑ። “በፓርቲው ህገደንብ መሰረት አስገደ ወደ መሰረታዊ አደራጃጀትህ አስገባ፣ ሺሻይ ወደ ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አቅርበው፣ ገብሩ ሳሙኤል ደግሞ ወደ ቁጥጥር ኮሚሽን አቅርብ። ከዛ ጥያቄያቹ መስመራቸውን ጠብቀው ይፈታሉ” የሚል መልስ ሲሰጣቸው “ታፈንን” አሉ። በፓርቲው ብዙ ችግሮች እንዳሉ ተናገሩ። “ፕሮሲጀር (procedure) ተከተሉ” ማለት ጥያቄን ማፈን አልነበረም። ግን አደረጉት። ፓርቲ የፈረሰ አስመስለው ደጋፊዎቻችንን ለማደናገር ሞከሩ። ይህ ተግባር ህወሓት ከሚሰራው ጋር ይመሳሰላል። የዓረና ፓርቲ ችግሮች ያሏቸውን ዘረዘሩ። ግን እንዴት ማወቅ ቻሉ? ከፓርቲው እንቅስቃሴ ከተሰናበቱ ኮ ዘጠኝ ወራት አስቆጥረዋል። በምናደርገው ስብሰባም ይሁን ስልጠና ወይ ሌላ እንቅስቃሴ አይሳተፉምኮ። የፓርቲውን ውስጣዊ አሰራር ለመገምገም ኮ በፓርቲው እንቅስቃሴ መሳተፍ ግድ ይላል።
እንግዲህ ጥያቄያችሁን በአግባቡ አቅርቡ ስለተባሉ ነው “ታፍነናል” ብለው ፀረ ዓረና እንቅስቃሴ ያደረጉት። ዓረና ቢሆኑ ኑሮ ዓረናን ለማስተካከል ጥረት ባደረጉ ነበር። “በአስቸኳይ ጉባኤ ጥሪ” ስም ባለፈውም ዓረናን ለማፍረስ ተሞክሮ እንደነበር አውቃለሁ። አልተሳካም፤ አሁንም አይሳካም። ጉዳያቸው ግን በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ይታያል።
ሎሚ፡- የፓርቲያችሁ ፀሐፊ ፓርቲውን ለቅቋል፤ ምክንያቱ ምንድነው?
አብረሃ፡- አዎ! የፓርቲያችን የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊ የነበረው አቶ ስልጣኑ ሕሸ ከፓርቲው ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብቷል። እንደ ዓረና መርህ ማንኛውም ሰው ፖሊሲያችንና የፖለቲካ አቅጣጫችን እስከተስማማው ድረስ ወደ ፓርቲያችን የመግባት መብት አለው። በፈለገው ግዜም ከፓርቲያችን መልቀቅ ይችላል። መብቱ ነው። ያለ ፍላጎቱ ተጨቁኖ የሚኖር አባል መኖር የለበትም። አቶ ስልጣኑም መልቀቅ ፈልጓል። ለመልቀቅ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ግን መልቀቅ መፈለጉ በራሱ በቂ ምክንያት ነው። ፖለቲካ የህሊና ስራ ነውና።
አቶ ስልጣኑ ሕሸ በመልቀቁ ምክንያት ዓረና ብዙ ነገር አጥቷል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም አቶ ስልጣኑ ጠንካራና ጀግና ከሚባሉ የዓረና መሪዎች አንዱ ነበረ። ዓረናን ይመራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ወጣት ነበር። የስልጣኑን ጥንካሬ ግምት ውስጥ በማስገባት ያቀረበው የመልቀቅያ ምክንያት አሳማኝ ሊሆን አይችልም። በፓርቲው ስብሰባ ወይ ግምገማ ማቅረብ ይችል ነበር። እንደግፈው ነበር። የምናምነውና የምንኮራበት ጓዳችን ነበርና ነው። ስለዚህ መውጣት ፈልጓል። ምክንያቱን በግልፅ ስላልነገረን የመውጣት ፍላጎቱን መከልከል አልፈለግንም፤ አንችልምም። ግን እስካሁን ብዙ ነገር ሰርቷል፤ ብዙ አባል አፍርቷል፤ ብዙ አስተዋፅዖ አበርክቷል። የፓርቲውን ግዴታ በአግባቡ የተወጣ ጀግና ነው። ላበረከተው አስተዋፅዖ የምስጋና ደብዳቤም ያስፈልገዋል።
ሎሚ፡- አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አረና ውስጥ የሕወሓት ሰርጎ ገቦች ገብተዋል ይላሉ፤
አብረሃ፡- አዎ! ዓረና ውስጥ የህወሓት አባላት ሳይገቡ አልቀረም። የሚናገሩትና የሚሰሩት ዓረናን ለማፍረስ ያለመ ይመስላል። ግን አጣርተናል ብለን ነው የምናምነው። ህወሓት ሆነው ወደ ዓረና የገቡ፣ ዓረና ሆነው በጥቅም ተደልለው ለህወሓት የሚሰልሉ ቅጥረኞችም ይኖራሉ። መረጃው ቶሎ ይደርሰናል። አፋጣኝ መፍትሄ እናደርጋለን። ስለዚህ የህወሓት በዓረና መግባት ብዙ ችግር አይፈጥርብንም። ችግር እየፈጠረብን ያለው ጠንካራ አባሎቻችን መታሰራቸው ነው። ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። አሁን ያለውን የህዝብ መነሳሳት በአግባቡ ለመምራት ብዙ ቋሚ ሰራተኞች መቅጠር ይጠበቅብናል።
ሎሚ፡- ከአንድነት ጋር ልትዋሃዱ ነው የሚባለው ነገር ምን ያህል እውነት ነው?
አብረሃ፡- ለመዋሃድ ያሰብነው ከመድረክ አባላት ጋር ነው። በመድረክ ውስጥ ደግሞ አንድነት፣ ኦፌኮና ደቡብ ሕብረት ኢሦዴፓ እንዲሁም ሲአን አሉ። ስለዚህ ከተቻለ እነዚህ ፓርቲዎች በሙሉ ከዓረና ጋር ቢወሃዱ ምርጫችን ነው። ምክንያቱም አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረት ነው የምንፈልገው። ይህ ካልተቻለ ግን ከኦፌኮ ወይ ከአንድነት ወይ ከደቡብ ሕብረት ወይ ከሲአን ጋር እንወሃዳለን። አንድነቶች ከመኢአድ ጋር ለመወሃድ ጥረት እያደረጉ ነው። ውህደቱ ከተሳካ ጥሩ ነው። ዓረናም ተመሳሳይ አጀንዳ ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ጋር የመወሃድ ዕቅዱ ይተገብራል። ባጭሩ ባሁኑ ግዜ አንድነት ከዓረና ሳይሆን ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ ነው ጥረት እያደረገ ያለው። ዓረናም የአንድነትና የመኢአድ ውህደት ይደግፋል። ምክንያቱም ዓረና ጠንካራ ውሁድ ሀገራዊ የተቃውሞ ፓርቲ የማየት ራዕይ አለው።
ሎሚ፡- ፓርቲያችሁ በስፋት በሚንቀሳቀስበት ትግራይ ያለው ተቀባይነት ምን ይመስላል?
አብረሃ፡- ዓረና በትግራይ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሰፊ ድጋፍ እንዳለውም አረጋግጠናል። የትግራይ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ለውጥ እንደሚፈልግ ለማወቅ ችለናል። ህወሓትም ይህንን ጉዳይ በሚገባ ተረድቶታል። እናም ብዙ እንቅፋቶች ለመፍጠር እየሞከረ ነው። “ዓረና አያድናችሁም፣ ከፈለግኩ አስራቸዋለሁ ከፈለግኩ እለቃችዋለሁ” እያለ ህዝብን እያስፈራራ ነው። “ዓረና እየፈረሰ ነው። ዓረና አስፓልት መንገድ፣ ባቡር ሃዲድ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት ወዘተ ሰርቶ አያውቅም” እያሉ ህዝብን እያጭበረበረ ይገኛል። ስም የማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብናል። የህወሓት የደህንነት ሰዎች ራሳቸው አሳስረው ራሳቸው “እናስፈታችኋለን” እያሉ ህዝብን እያስደነገጡ ነው። ፍትሕ ግን ሊሰጡ አልቻሉም።
ሎሚ፡- አሁን ላይ ሆነህ ቀጣዩን የ2007 ምርጫ እንዴት ትመለከተዋለህ?
አብረሃ፡- የ2007 ምርጫ ከባድ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ህወሓት ምንም የህዝብ ድጋፍ እንደሌለው ከወዲሁ አረጋግጧል። ስለዚህ ፍትሓዊ ምርጫ ከተደረገ፣ የህዝብ ድምፅ ከተከበረ መሸነፉ አይቀርም። ህወሓት ግን ሽንፈቱን ለመቀበል ዝግጁ አይሆንም፤ ስልጣን መልቀቅ አይፈልግምና። ስለዚህ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላትን ማሰሩ አይቀርም። የምርጫ ታዛቢዎችን መከልከሉ አይቀርም። የምርጫ ኮሮጆውን በጠመንጃ መጠበቁ አይቀርም። ህዝቡ ግን ለውጥ ይፈልጋል። እኛ ለለውጥ ቀስቅሰን፣ አነሳስተን የህዝብ ድምፅ ሲታፈን ህዝቡ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ስለማይታወቅ ህወሓት ተጨናንቋል። ስለዚህ የህወሓት ጭንቀት ላልመረጥ እችላለሁ የሚል አይደለም፤ እንደማይመረጥማ አውቋል። የህወሓት ጭንቀት ህዝቡን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል የሚል ነው።
ዓረና እስከ 2007 ምርጫ አሁን ባለው መንፈስና ጥንካሬ መንቀሳቀስ ከቻለ ግን አብዛኞቹ የህወሓት ካድሬዎችም ጭምር የማሳመን ከፍተኛ ዕድል አለው። የምርጫን ውጤት ሊያጭበረብሩና ሊሰርቁ የሚችሉ ካድሬዎች በለውጥ ማዕበሉ ሰጥመው ለፓርቲ ሳይሆን ለሀገርና ህዝብ እንዲሰሩ የማድረግ አቅም አለን። በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ያገኘናቸው ካድሬዎች ፈጣን የሆነ የአመለካከት ለውጥ ታይቶባቸዋል። ስለዚህ የጨዋታ ካርዱ በህዝቡ አይደለም ያለው፤ በካድሬዎቹ ነው። ምክንያቱም ህዝቡማ ህወሓትን እንደማይመርጥ ተረጋግጧል። ጥያቄው የህዝቡ ድምፅ ይጭበረበራል ወይ የሚል ነው። ህወሓት የራሱ ካድሬዎች እንኳን የዓረናን እንቅስቃሴ አይተው እየካዱት ነው። ስለዚህ የ2007 ምርጫ ወሳኝ ነው።

No comments: