Tuesday, July 15, 2014

በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችና በወጣቱ ሚና ላይ ውይይት ተደረገ

July 14/2014
በአንድነት ፓርቲ የወጣቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አዘጋጅነት ትላንት ሀምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም በፓርቲው ጽ/ቤት “የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና የወጣቱ ተሳትፎ” በሚል ርዕስ ውይይት ተደረገ፡፡
በፖለቲከኛና ደራሲ አስራት አብርሃም የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅራቢነት በተደረገው ውይይት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አበበ አካሉ ወጣቱ ኢህአዴግ እየፈፀመ ባለው እስር ሳይሸበር ትግሉን በቀዳሚነት መምራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አክለውም በቅርቡ መንግስት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማዳከም ወጣት ፖለቲከኞች ላይ የወሰደው የእስር እርምጃ የተቃውሞ ትግሉን እንደማያዳክመው ጠቅሰው፣ አንድነት አመራሮቹን አሳስሮ እንደማይቀመጥ ተናግረዋል፡፡
በመቀጠል ፖለቲከኛና ደራሲ አስራት አብርሃም መድረኩን በመረከብ በሁለት ምዕራፎች የተከፈለውን የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሰፋ ያለ ዳሰሳ ያቀረበ ሲሆን ኢህአዴግ ለ23 ዓመታት በማሰር ትግልን ለማስቆም የያዘውን ስልት እስርን ባለመፍራት ማስቀረት እንደሚቻል ተንትኗል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የወጣቱ ሚና ምን መሆን እንዳለበት በስፋት በመተንተን፣ ወጣቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቀዳሚ ተዋናይ መሆን እንዳለበት ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
የመነሻ ሃሳቡን ተከትሎ ሰፊ ውይይትና አስተያየት በተሳታፊዎች ቀርቧል፤ አቶ አስራት አብርሃምም ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ውይይቱን በመዝጊያ ንግግር የደመደመት የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባልና የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብባቢ ሻለቃ አርጋው ካብታሙ በፖለቲካ ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ወደትግሉ ጎራ እንዲመጡ ለወጣቶች የትግል ጥሪ አቅርበዋል፡፡10513386_753747781350640_4359503663936542591_n
10464310_753747681350650_1030084630847553487_n
10411918_753747584683993_8877538779629312379_n
10437722_753747528017332_8433801724925968086_n
10371435_753747864683965_500273631796680168_n

No comments: