Tuesday, July 15, 2014

አብርሃ ደስታ ተደብድቦ ፍርድ ቤት ቀረበ

July 15/2014
 በትግራይ እየተካሄዱ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን በመዘገብ ይታወቃል። ለእውነት ሲቆም እንጂ፤ ለህይወቱ ሲሰጋ አይተነው አናውቅም። አብርሃ ደስታ ስራው መምህርነት ሲሆን፤ የአረና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊም ነው። የትግራይ ተወላጅ ሆኖ ስለትግራይ መጥፎ በመዘገቡ የተናደዱበት ይመስላል። ባለፈው ሳምንት ትግራይ ውስጥ ታፍኖ ወደ አዲስ አበባ ማእከላዊ ፖሊስ እስር ቤት መምጣቱን ዘግበን ነበር። እዚህ ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ብቻውን መታሰሩ እና በከፍተኛ ሁኔታ መደብደቡ አዲስ የደረሰን ዘገባ ነው።
አብርሃ ደስታ ጠያቂም ሆነ ጠበቃ የለውም። ከድብደባው የተነሳ በጣም መዳከሙ ነው የደረሰን ዘገባ የሚያመለክተው። በፍቃዱ ጌታቸው ከአዲስ አበባ እንደዘገበው ከሆነ፤ አብርሃ ደስታ እንዳይታይ በማሰብ ለሊት ነበር እስር ቤት ያስገቡት። ይህ ብቻ አይደለም። በሚገርም ወይም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከለሊቱ 6፡30 ለሱ በተሰየመ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ለማወቅ ያልቻልነው ነገር፤ የፍርድ ቤቱ ሂደት፣ የክሱ ጭብጥ እና ይዘት ምን እንደሚመስል ነው። ነገሩን እንደ አንድ ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን እንደሰው ስናስበው ትክክል አይመስልም። አንድን ሰው አፍኖ አምጥቶ፤ ደብድቦ እና አሰቃይቶ ፍርድ ቤት ማቅረብ የደረስንበትን የፍትህ ዝቅጠት የሚያሳይ ነው።
አብርሃ ደስታ በተደጋጋሚ ሲናገር “የትግራይ ህዝብ የህወሃት ደጋፊ አይደለም” ይል ነበር። ለነገሩ የህወሃት ታጋዮች የሞቱት እና የተሰዉት እንደአብርሃ ደስታ ያሉ ሰዎች በግፍ ታፍነው እየተደበደቡ ለፍርድ እንዲቀርቡ ከነበር ያሳዝናል። ህወሃትን እንደግፋለን የሚሉ የትግራይ ተወላጆች ጭምር “የመስዋዕትነት ውጤቱ ይህ ነው?” ብለው እራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው።
የአረና ፓርቲም አንድ አባሉ ታፍኖ እና ታስሮ ሲወሰድ በዝምታ መመልከት የለበትም። የመግለጫ ጋጋታ የታሰሩትን ባያስፈታም፤ አቋምን ማሳወቂያ መንገድ ነውና መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ነው። የይስሙላ ቢሆንም ለሰባዊ መብት ጠባቂ ድርጅትም ቢሆን ማሳወቅ ያስፈልጋል። ከምንም በላይ ግን አንድነት ፓርቲ እንዳደረገው በህገወጥ መንገድ ዜጎችን የሚያስሩትን ሰዎች ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል። ቢሰራም ባይሰራም የህጉን መንገድ ደጋግመን ልንሄድበት ይገባል። ለዛሬው እዚህ ላይ አበቃን።

No comments: