Tuesday, July 1, 2014

የሽብር - ዘፍጥረት (ተመስገን ደሳለኝ)

July1/2014

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ንቅናቄ መፈጠሩን ያስተዋለ  አልነበረም፤ …ከሺህ ዓመታት በፊት በአገር አልባነት፣ በተለያዩ የዓለም አህጉራት የተበታተኑት አይሁዳውያን ይደርስባቸው ከነበረው መገለልና ጭቆና (ፀረ-ጽዮናዊነት) ነፃ ለመውጣት በፈረንጆች አቆጣጠር በ1896 ዓ.ም. ቴዎድሮ ሄርዘል በተባለ ሰው መሪነት የጽዮናዊ ንቅናቄን መሰረቱ፤ ዋነኛ ዓላማውም ለዘመናት ሲናፍቋት ወደቆየችው ‹‹ተስፋይቱ ምድር›› መመለስን እውን ማድረግ ሲሆን፤ ይች ዕለት ትቀርብ ዘንዳም ገና ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ‹‹ሃ-ቲካያ›› (ተስፋችን) የተሰኘውን ዝነኛ መዝሙር ሲዘምር የኖረው እያንዳንዱ አይሁዳዊ፣ ተደራጅቶ ለመታገል መወሰኑ ደስታውን ሰማይ ጥግ አደረሰው፤ ንቅናቄው ከተመሰረተ ከሁለት አስርታት በኋላም ባካሄደው የመጀመሪያው ኮንግረስ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ውሳኔ ላይ ደረሰ፤ በአውሮፓ አገራት ተበታትነው ይኖሩ ከነበሩ ጽዮናውያን መካከል የተወሰኑት በግል ገንዘባቸውም ሆነ ቡድናቸው በሚያደርግላቸው ድጎማ ወደ ፍልስጤም በተናጠል ሄደው መሬት እየገዙ እንዲሰፍሩ የሚል ነበር፤ ይህንንም ሂደት አካባቢውን ከአውቶማን ቱርክ ነጥቃ የምታስተዳድረው ታላቋ ብሪታኒያ እ.ኤ.አ. በ1917 ዓ.ም ባወጣችው ‹‹ባልፎር ዲክላሬሽን›› (Balfour Declaration) በመደገፏ፣ መንገዱን አልጋ በአልጋ አደረገው፡፡ ይሁንና ዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ ከመሳካቱ በፊት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀሱ እንደማይቀር እርግጠኛ የሆኑት አዶልፍ ሂትለር እና ዱቼ ሞሶሎኒ፣ በጦርነቱ ወቅት አረቦቹን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲሉ፣ ብሪታኒያ ለሰፈራው የምታደርገውን እገዛ በአሉታዊ ጎኑ እያጋነኑ ቅስቀሳ ማድረግ መጀመራቸው ከባድ ስጋት ውስጥ ጣላት፤ እናም ‹‹ኋይት ፔፐር›› (White Paper) በተሰኘ አዲስ ድንጋጌ አይሁዳውያን መሬት እንዳይገዙ ከለከለች፡፡ እነርሱም በውሳኔው እጅግ ከመበሳጨታቸው የተነሳ ‹‹ሃጋና›› (Hagana) የሚባል ህቡዕ ቡድን መስርተው የእንግሊዝ ንብረትና ጥቅም የሆኑትን በሙሉ በፈንጅ ማጋየት፣ ሰላማዊ ዜጎችን መግደልና መጥለፍን የቀን ተቀን ሥራቸው አደረጉት፡፡ …እነሆም የፖለቲካ ተንታኞች ይህን ሁነት ነው ‹በዘመናዊው ዓለም የሽብርተኝነት ጅማሮ› ሲሉ የሚጠሩት፡፡ በአናቱም የአሸባሪው ‹‹ሃጋና›› የአመራር አባል ከነበሩት መካከል ዳቪድ ቤንጎሪኦን እና ሌቪ ሸኮል በተለያየ ጊዜ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲመረጡ፤ የድርጅቱ ታጣቂዎችም እ.ኤ.አ. በ1948 ዓ.ም. ለተመሰረተችው አዲሲቷ እስራኤል የመከላከያ ሠራዊት እርሾ ሆነው ማገልገላቸውን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

 የሽብር መግፍኤ

ሽብርተኝነት ሰይጣናዊ ድርጊት መሆኑ ባይካድም፤ የአንድ ሐይማኖት አሊያም ብሔር መለያ አለመሆኑ መዘንጋት የለበትም፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ የጭቆና ውጤት መገለጫ ተደርጎ ሲበየን ይስተዋላል፡፡ ከዓለም አቀፉ አል-ቃይዳ እስከ አፍሪካ ቀንዱ አልሸባብ፤ ከናይጄሪያው ቦኮ ሐራም እስከ ማሊው አሳር ዲን፤ ከማግሪቡ ሙጃአን አቢዒ እስከ ሰሀል በረሀው አዘዋድ… የሚጠቀሱ ድርጅቶችም የመጀመሪያ አነሳስ መገለል፣ ጭቆና እና ወረራን የመሳሰሉ ገፊ-ምክንያቶች ስለመሆኑ ጉዳዩን ያጠኑ ምሁራን ያስረግጣሉ፡፡ ከቀዳሚው ‹‹ሃጋና››ን እስከ ዛሬዎቹ ድረስ ያሉ በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖች የሚከተሉት ስልት ከወታደራዊ ተቋማት ይልቅ፣ ሰላማዊ ዜጐችና የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ደግሞ፣ ዘግናኝ የጭካኔ ገፅታን አላብሶ እጅግ አስፈሪ ፍጡር አድርጓቸዋል፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጃፓን አየር ኃይል አባላት ፈንጅ የጫኑ የጦር አውሮፕላኖችን ቁልቁል አምዘግዝገው ከአሜሪካን የውጊያ መርከቦች ጋር በማላተም ይፈፅሙት የነበረው፤ በእነሱ አጠራር ‹‹መለኮታዊው የንፋስ ጥቃት›› ተብሎ የሚታወቀው የአጥፍቶ መጥፋት ተግባር፣ ከ1980ዎቹ መጨረሻ ወዲህ ለተመሰረቱ አሸባሪ ድርጅቶች ተመራጭ ሆኗል፡፡ በርግጥ ይህን መሰሉ ድርጊት በዓለም ማሕበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያሌለው በመሆኑ፣ ቡድኖቹ ከየትኛውም አገራትም ሆነ ሕጋዊ ተቋማት ይፋዊ ድጋፍ እንዳያገኙ እንቅፋት መፈጠሩ በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ እንዲሁም የሽብርተኝነት መነሾና አንድምታ ዛሬም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚያስማማ ብያኔ ባያገኝም፣ የፖለቲካ ውሳኔን ጨምሮ ከማሕበራዊና ኃይማኖታዊ ጭቆና ጋር መያያዙ አያከራክርም፡፡ ጥቂት የማይባሉ የወቅቱ ቡድኖችም አመሰራረታቸው የእስልምና ሕግጋትን በሥርዓተ-መንግስት ውስጥ በኃይል ማንበር መሆኑ፣ በብዙሃኑ ዘንድ የተዛባ ትርጉም ፈጥሮ፣ ድርጊቱን የኃይማኖት መገለጫ እንዲመስል እየገፋው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

 …የሽብርተኝነትን ታሪካዊ ዳራ ከእስልምና ይልቅ፤ ከአይሁዳውያን ጋር የሚጋመድ መሆኑን በደምሳሳው ከቃኘን ዘንዳ፣ ለኢትዮጵያችን አስጊ እየሆነ ወደመጣው አልሸባብ አፈጣጠር እና ኢህአዴግ መራሹ-መንግስት ሽብርን የሚመለከትበትን መነፅር ወደ መፈተሹ አቢይ አጀንዳችን እንለፍ፡፡

 ወረራ-ሶማሊያ 
 የ1998ቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዓመቱን ከማጠናቀቁ በፊት ከባድ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሶማሊያ ራሱን ‹‹የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት›› ብሎ የሚጠራው ስብስብ፣ ኢትዮጵያ ላይ ጅሀድ በማወጁ ምክንያት መከላከያ ሠራዊታችን ሞቃዲሾ ድረስ ገብቶ እንዲደመስሰው የሚጠይቅ አጀንዳ አቀረበ፡፡ ይሁንና በምክር ቤቱ ቅንጅትን እና ሕብረትን ወክለው የገቡት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ይህ ሁኔታ ለብሔራዊ ጥቅም ሳይሆን የአሜሪካንን ተልዕኮ ለማስፈፀም እንደሆነ በማጋለጥ እና ለወደፊቱም ሀገሪቷን ከባድ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል በማስጠንቀቅ በብርቱ ቢወተውቱም፤ ገዥው-ግንባር፣ ከአጋር ፓርቲዎች እና ከአቶ ልደቱ ኢዴፓ ጋ ተባብሮ በማፅደቁ (ባያፀድቁትም በመለስ የቀረበ አጀንዳ ከመፈፀም የሚያግደው ኃይል አልነበረም) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ ዘልቆ ይገባ ዘንድ ግድ ሆነ፡፡ የህወሓት መስራች የነበረው አውዓሎም ወልዱ ከጋዜጠኛ ዮናስ በላይ ጋር ቃለ-መጠየቅ ባደረገበት ወቅት ከኤርትራ ጋር በማያያዝ በተረት አስደግፎ የገለፀበት መንገድ ይህንን ሁነት ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳይ እዚህ ጋ ልጥቀሰው፡-

 ‹‹አንዲት ተረት ልንገርህ፡፡ በአንዲት ሀገር ውስጥ ሀገሪቷን ለመጠበቅ የተሰማሩ ውሾች ነበሩ፡፡ ሰዉ ደግሞ ይህን በጎ ምግባራቸውን እያየ ያቀርባቸው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ሰዉ ምን ብሎ ይወስናል፤ ‹ግዴታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ስላልሆነ እናባራቸው፡፡› ውሾችም ይህንን ሰሙ እና ስብሰባ ተቀመጡ፡፡ ‹ሰዉ ሁሉ እንዲህ ብሎ ወስኖብናልና ምን እናድርግ?› ሲሉም መከሩ፡፡ መጨረሻ ላይ ‹አንድም መኖር ነው፣ አንድም መሞት ነውና ሕጎቻቸውን አክብረን እንሰናበት› ብለው ወሰኑ፡፡ ትክክለኛዋ ስነ-ሐሳብ እቺ ነች፡፡ ቢሆንም ግን አንዱ እጁን አውጥቶ ምን ይላል? ‹ክፍት የተተወ ነገር ካገኘንስ ምን እናድርገው?› አለ፡፡ ‹ይህማ የራሱ የሰዉ ስህተት ነውና እንክት አድርገን መብላት ነው እንጂ› ብለው ወሰኑ ይባላል፡፡ እኛም፣ ወደ ኤርትራ ዘልቀን ስንገባ ‹ልዑላዊት ሀገር ናትና፣ በቃ ተመለሱ› ተባለ፤ እንደ ውሾቹ ውሳኔ ክፍት የሆነች ሶማሊያን ያገኘን እንደሆነስ? ክፍት የሆነች ሶማሊያን ካገኘንማ እንክት አድርገን እንበላታለን እንጂ ነው የተባለው፡፡›› 
(የትግራይ ሕዝብ፣ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ›› ገፅ 208)

 በዚህ መልኩ በቅጥረኝነት በዘመቻው እንዲሰማራ የተደረገው መከላከያ ሠራዊታችን መዳረሻው የሕብረቱ ጠንካራ ይዞታ ወደነበረው ሞቃዲሾ ሆኖ፣ በሶስት ግንባር የተከፋፈለ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያን ለታሪካዊ ስህተት ከዳረገ ከዚህ ዘመቻ 30 ቀናት ቀደም ብሎ (ሰኔ 4/ 1998 ዓ.ም.) መንግስት አንድም ከኋላው አደገኛ ጠላቱን ኦብነግን አስቀምጦ ወደፊት መገስገሱ ያልታሰበ ችግር የሚያመጣ በመሆኑ፤ ሁለትም ‹በሚሊኒየሙ ሽብርተኛ ድርጅቶችን በሙሉ እንደመስሳለን› በሚለው ዕቅዱ፤ ሶስትም ‹የኦብነግ የተወሰኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሶማሊያ በኩል ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል› የሚል መረጃ በመድረሱ፤ የዘመቻ ሠራዊቱ አባል የሆነው አግአዚ 6ኛ አሉላ ሻለቃ ‹‹ሀጂ ተራራ›› በተባለው ስፍራ የመሸገው ኦብነግን እንዲደመስስ ይታዘዝና፣ ገርብ ከሚገኘው የጦር ሰፈሩ ተንቀሳቅሶ ድንገተኛ ጥቃት ይሰነዘራል፤ እነርሱም ለመከላከል ባደረጉት ከፍተኛ ትንቅንቅ ውጊያው እየበረታ መጣ፤ የማታ ማታም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ግንባር ጥቂት ጣቶቹን ቢያጣም፣ ‹‹ቃታ ለመሳብ አንድ ጣት እስኪቀረኝ ድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መዋጋቴን አላቋርጥም›› እያለ ሲዝት ይሰማ የነበረው፣ ‹‹ዱብኬ›› በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የኦብነግ ተዋጊዎች አዛዥ ከመገደሉ በተጨማሪ፣ በአጠቃላይ የግንባሩ ታጣቂ ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ፣ ገሚሱ ድንበር አቋርጦ ወደ ሶማሊያ ሲሸሽ፤ የተቀረው ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በመቀላቀል ሰላማዊ ዜጋ መስሎ መሸሸጉን የ‹‹ፋክት›› ወታደራዊ የመረጃ ምንጮች ይስረዳሉ፡፡

 በኦጋዴን ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ጅምላ ጭፍጨፋ ፈፅሟል›› በሚል በዓለም አቀፍ መድረክ ውግዘት የቀረበበትም በዚሁ ውጊያ ሰሞን ከተከሰተ አንድ ጉዳይ ጋ ይያያዛል፡፡ ይኸውም ከላይ የተጠቀሰው የሻለቃ ጦር አባል የሆነ አንድ ሻምበል መንገድ ስቶ ይጠፋና በኦብነግ ሰዎች እጅ ይወድቃል፤ እነርሱም ህይወቱን በመንጠቅ ብቻ ባለመርካታቸው ነውረኛነት   በተጠናወተው ሁኔታ ምላሱን ጎልጉለው ካወጡ በኋላ አስክሬኑን ጎዳና ላይ ይጥሉታል፤ ይህም ሠራዊቱን ክፉኛ በማስቆጣቱ፣ ቀድሞውንም ‹‹ከአሸባሪዎቹ ጋር ትተባበራላችሁ!›› በሚል የሚወነጅለውን የአካባቢው ነዋሪ መኖሪያ ቤቶች በእሳት ከማቃጠሉም በላይ፣ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ሲገድል፣ ጥቂት የማይባሉ እንስቶችን ደግሞ አስገድዶ ደፍሯል መባሉ ነው የክሱ ጭብጥ ሆኖ የቀረበው፡፡

 በክልሉ ለሰፈረው ሠራዊት ከ15 ዓመት በላይ በመረጃ መኮንንነት ያገለገለው ሁንዴ ከበደ (ስሙ የተቀየረ)፣ መንግስት ነዋሪውን ከማሰቃየት አልፎ ኦብነግን ከሕዝብ ለመነጠል ያደረገው የረባ ጥረት አለመኖሩን ይናገራል፡፡ እንደመኮንኑ ትንተና የአካባቢው ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ ዘላን በመሆናቸው ተበታትነው (ተራርቀው) እንጂ አንድ ቦታ በቋሚነት ሰፍረው መኖር አይችሉም፤ ነገር ግን መንግስት አንድ ቦታ ላይ ሰብሰብ ብለው እንዲሰፍሩ ለማድረግ ጫና ሲፈጥር ይስተዋላል፤ ይሁንና እነርሱ ጥያቄውን ለመቀበል የሚያስችል መሰረተ ልማት (ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ የእርሻ መሬትና የመሳሰሉት) ባለመሟላቱ ፍቃደኛ አልሆኑም፤ ይህ እምቢተኝነታቸውም ወታደሩ ጎጆአቸውን በእሳት እንዲያጋይ፣ በርሃብ አለንጋ ይረግፉ ዘንድ ሩዛቸውን በትኖ ከአፈር ጋር እንዲደባልቅ፣ ሴቶቻቸውን አስገድዶ እንዲደፍርና መሰል ስቅየቶችን ወደማድረሱ ጭካኔ ገፍቶታል፤ በዚህም የአብላጫው ነዋሪ ልብ ወደ ኦብነግ መሸፈቱን ያምናል፤ ይህ ደግሞ ለድርጅቱ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው የሰው ሀይል፣ መሸሸጊያ፣ ቀለብ እና የሀገሪቱን ሠራዊት የተመለከተ መረጃ በቀላሉ እንዲያገኝ ያስችለዋል (ኦጋዴንና አካባቢውን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሠራዊት ሚናን እና ኦብነግን በተመለከተ ሌላ ጊዜ በስፋት መመለሴ ስለማይቀር፣ ይህን ሀተታ እዚሁ ጋ ገታ አድርገን የጀመርነውን እንቀጥል)

 …ወደ ሶማሊያ የተደረገው ዘመቻ በሶስት የተከፈለ ነበር፤ በመጀመሪያው ግንባር አግአዚ 6ኛ አሉላ ሻለቃ ኮማንዶ እና ከ44ኛ ክፍለ ጦር የወጡ ሁለት ኃይሎች፣ ከሰሜን ዕዝ እና ከአዋሽ አርባ ማሰልጠኛ ከተወጣጣ አንድ ሜካናይዝድ ጋር ተጣምረው በፍርፍር በኩል በለደወይኔን፣ ብሉ በርግን፣ ጀዋሀርን አልፈው ሞቋዲሾ መግቢያ አፋፍን ተቆጣጥረው እንዲቆዩ ሲታዘዙ፤ በሁለተኛው ግንባር ከ44ኛው ክፍለ ጦር የወጣ አንድ ሻለቃ እና አግአዚ ወጋገን ክፍለ ጦር የተመደቡ ሲሆን፤ ግዳጃቸውም ‹በጊልካ ሀዩ፣ ባይደዋን ተሻግራችሁ ሞቋዲሾ ግቡ› የሚል ነው፤ በሶስተኛው ግንባር ደግሞ ጉና ክፍለ ጦር እና ኡመር 5ኛ ሻለቃ በፑንትላንድ በኩል በለበልን አልፈው ሞቋዲሾ እንዲደርሱ ታዝዘዋል፤ በዚህ መልክ የተንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ሠራዊት፣ ሞቋዲሾ አፋፍ ላይ ከደረሰ በኋላ የነበረውን ሁኔታ ከሰሜን ዕዝ ሜካናይዝዱን የተቀላቀለ የአስር አለቃ እንደሚከተለው ይተርከዋል፡-

‹‹መጀመሪያ ከአገራችን ስንነሳ አዲስ የተመሰረተው የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ወታደር ከፊት እንደሚመራ፣ የእኛ ግዴታ ከኋላ ሆኖ ድጋፍ መስጠት ብቻ እንደሆነ የተነገረን ቢሆንም፤ እቦታው ስንደርስ የገጠመን እውነታ ግን በተገላቢጦሽ፣ እኛ ከፊት እነርሱ ከኋላ መሰለፋቸው ነው፤ በዚያ ላይ ቁጥራቸው እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ሌላው አስቂኙ ጉዳይ ደግሞ ሞቋዲሾ አፋፍ ደርሰን ደፈጣ ባደረግንበት ወቅት በእኛ መንግስት ተመድበው እንደቀረቡ የምጠረጥራቸው የሀገር ‹ሽማግሌ› ተብየዎች በአስተርጓሚ በኩል አክራሪውን ኃይል ወደከተማው ገብተን እንድንደመስሰው እንዲማፀኑ የተደረገበት ድራማ ነው፤ ለማንኛውም እኛም ወደ ከተማው ዘልቀን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረትን በውጊያ ድባቅ መትተን ከይዞታው አባረርነው ስናበቃ፣ በ‹ባሌ ባይደዋ› ፈራርሶ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ተቆጣጠርን፤ ቀጥሎም ቤተ-መንግስቱን ይዘን ባንዲራችንን ሰቀልን፤ በዚህ ግዳጅ ከእኛ በኩል ከ44ኛ ክፍለ ጦር የመጣ አንድ ሻለቃ ሙሉ በሙሉ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ከዋናው ውጊያ በፊት (በጉዞ ላይ ሳለን) ደግሞ ‹‹ብሉ በርግ›› በተባለ ቦታ ባደፈጡ የአክራሪው ኃይል አባላት ድንገተኛ ጥቃት ተሰንዝሮብን አንድ ወታደር ሲሰዋ፤ አንድ ቆስሎብናል፡፡››

የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ የማስገባቷ ክሽፈት ዓብይ ማሳያ በደካማው የእስላማዊ ፍርድቤቶች ሽንፈት ላይ እጅግ የበረታው አልሸባብ መፈጠሩ ብቻ አይደለም፤ ዘመቻው ሀገራዊ ተልእኮ የሰነቀ አለመሆኑም እንጂ፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ ከሚጠቀሱት መካከል፣ የአሜሪካን የጦር መኮንኖች ሞቃዶሾና ኪስማዩ ድረስ መጥተው ከሳተላይት የሚቀበሉትን መረጃ ተንተርሰው፣ ሠራዊቱን ‹በዚህ ቦታ አሸባሪዎች መሽገዋልና፣ ወደዚያ ተንቀሳቀስ›፣ ‹በዚህ ቦታ ጥቃት ሰንዝር› እያሉ ትዕዛዛት ከመስጠታቸው ባሻገር፣ በውጊያ መሀል የጦር አውሮፕላኖቻቸው ድንገት ደርሰው በአጋዥነትየመሳተፋቸው ምስጢር ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ መቶ አለቃ ዘላለም እጅጉ (ስሙ የተቀየረ) እንዲህ ሲል ያጠናክረዋል፡-

‹‹በ1999 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በኪስማዩ ጫካ ከመሸጉ የአልሸባብ አባላት ጋር ከባድ ውጊያ እያካሄድን ሳለ፣ ዘግይተን የአሜሪካን እንደሆነ ያወቅነው የጦር አውሮፕላን ሳይታሰብ ብቅ ብሎ በሰከንድ ውስጥ ሺ ጥይቶችን በሚተፋ ዘመናዊ  መሳሪያ አልሸባቦችን እንደቅጠል ያረግፉቸው ጀመር፤ ስለጉዳዩ አስቀድሞ የደረሰን መረጃ ባለመኖሩ አዛዣችንን ጨምሮ ሁላችንም ክፉኛ ደንግጠን፣ ‹ምን መጣ?› ብለንም መሬት ላይ ‹ፓንች› እስከማድረግ ደርሰን ነበር፤ ሁኔታው የመብረቅ ስብርባሪዎች ከሰማይ እምብርት ውስጥ እየተምዘገዘጉ ምድርን የሚያደባዩ እንጂ ከአንድ የጦር መሳሪያ አፈ-ሙዝ ውስጥ የሚንጣጣ የጥይት እርምታ በፍፁም አይመስልም ነበር፡፡››

 ‹‹ማሃ ሚገለገሌ?›› 

 መከላከያ ሠራዊታችን የእስላማዊው ፍርድ ቤቶች ሕብረት የተሰኘውን ስብስብ ኪስማዩ ድረስ ተከታትሎ አከርካሪውን ቢሰብረውም፤ ዘመቻው ከተጀመረ አንድ ወር እንኳ ሳይሞላው ከሕብረቱ ኃይል ፍፁም የላቀ፣ በቁጣ የነደዱ ወጣቶችን ማሰለፍ የሚችል ንቅናቄ ይነሳል ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሞቋዲሾን ጨምሮ የሶማሊያ ዋና ዋና ከተሞችን መቆጣጠሩ፣ በአርበኝነት መንፈስና አገር ነፃ በማውጣት ስም ‹‹አልሸባብ›› መመስረቱን፣ የቡድኑን ስነ-ተፈጥሮ ያጠኑ ምሁራን ያስረግጣሉ፡፡ መጀመሪያውኑም ‹‹ዘመቻው የአሜሪካንን ተልዕኮ ለማስፈፀም ያለመ ቅጥረኝነት ነው›› በሚል ከሀገር ውስጥ እስከ አለም አቀፍ መድረኮች ድረስ የተቀጣጠሉ ተቃውሞዎችን መስማት ያልፈቀደው የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ሠራዊት፣ በሶማሊያም የተደረገለት አቀባበል ‹‹ማሃ ሚገለገሌ?›› (ምን አገባችሁ?) በሚል ብርቱ የቁጣ ድምፅ የታጀበ ነበር፡፡

 ቆይታው ለሁለት አመት ያህል የተራዘመው ይህ ሠራዊት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ካደረሰው ሰቆቃ በተጨማሪ፣ የዓለም አቀፍ ስምምነትን ተፃራሪ ድርጊቶች ፈፅሟል ተብሎ ተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብበት እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የአንዱ ሻለቃ አስተባባሪ ሆኖ የተመደበው ኃይላይ ገ/መድህን (ስሙ የተቀየረ) ኩነቱን እንዲህ ይገልፀዋል፡-

 ‹‹በሶማሊያ በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጠሙን ቢሆንም፣ ግዳጃችንን ከባድ ካደረጉብን መሀል ዋነኛውን ልጥቀስልህ፣ አብዛኛው የሞቋዲሾ ቤቶች ከድንጋይ የታነፁ ናቸው፤ ለከተማ ውጊያ በብላቴን ስልጠና የወሰደው የእኛ ሠራዊት ደግሞ፣ ልምምዱን ያካሄደው ከጭቃ በተሰሩ ቤቶች ውስጥ ነው፤ በዚህም ምክንያት ከአንዱ ሕንፃ ወይም መኖሪያ ቤት በክላሽንኮቭ ለሚሰነዘርብን ጥቃት የምንሰጠው ምላሽ በታንክ አሊያም በሞርታር የተደገፈ በመሆኑ፤ ድርጊቱ ለከተማ ውጊያ ከባድ መሳሪያ መጠቀምን የሚያግደውን ዓለም አቀፍ ሕግ ከመጣሱም በላይ፣ ከሞቋዲሾ ነዋሪ ሀዘን ያልገባበት አንድም ቤት ተፈልጎ እንዳይገኝ ሰበብ ሆኗል፡፡››

  ኃይላይ ገ/መድህን እንደሚያስረዳው በርካታ መኖሪያ ቤቶች፣ ሕንፃዎች፣ መስጊዶች… በከባድ መሳሪያ ሲፈራርሱ የተመለከቱ አያሌ ወጣቶች፣ በአርበኝነት ስሜት በገፍ ወደ አልሸባብ መጉረፋቸውን ነው፤ አያይዞም ‹‹በዚህ አይነቱ ሰላማዊ ዜጎችን አብሮ በሚደመስስ ጅምላ ጥቃት የተማረሩ ሶማሊያውያን አልሸባብን ቢቀላቀሉ ምን ይደንቃል?›› ሲል ይጠይቅና፣ ሁኔታው ለድርጅቱ ጥንካሬ ገፊ-ምክንያት እንደሆነው አጽንኦተ በመስጠት ይከራከራል፡፡ በተጨማሪም ከምሽቱ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የተጣለው ሰዓት እላፊን ተከትሎ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም ሶማሊያዊ እርምጃ እንዲወሰድበት የተላለፈው ትዕዛዝ ሕዝቡን ለምሬት ዳርጎት ነበር፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚጠቀሰው ‹‹ሆርሞድ›› እየተባለ በሚጠራው የቴሌ አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤት ግቢ የሰፈረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከቆይታው በአንዱ ዕለት፣ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አንድ አውቶብስና አንድ ሚኒባስን ኦርሴዶ ፓስታ ፋብሪካ አጠገብ በላውንቸር መትቶ ሲጋያቸው፤ ከተሳፋሪዎቹ መካከል በፅኑ ቆስለው ከተረፉት አራት ሰዎች በቀር፣ አንዲት እርጉዝ ሴትን ጨምሮ ሁሉም ማለቃቸው ነው፡፡ …ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አልሸባብ ካላፈ ታሪክ ጋር በማዛመድ ‹‹ኢትዮጵያውያን በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ጓሮአችንን ይኮተኩቱ ነበር፤ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ጊዜ ጓዳችን ድረስ ገቡ፤ ዛሬ በኢህአዴግ ደግሞ ሚስቶቻችንን እስከመንጠቅ ደረሱ›› እያለ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ የሕዝቡን ስሜት እንዲያሸንፍ ከማገዙ በዘለለ፣ ትውልድ ተሻጋሪ አደጋን የተሸከመ ይመስለኛል፡፡
 ቀሪውን ሳምንት እመለስበታለሁ

No comments: