Friday, July 18, 2014

የዘንድሮ እስር ‹‹ጸበል ቅመሱ›› ሁነብኝ ጃል! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)

July18/2014

(የህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 30 ሳይሻር ተሽሮ ከሆነ መሻሩን ተቃዋሚዎች ይወቁት!)
========
የምንወዳት ኢትዮጵያ ሀገራችን በተለያዩ ሥርዓታት ውስጥ የተለያዩ የሰዎችን እስር አስተናግዳለች፤ ዛሬም እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
በ97 ዓ.ም ምርጫውን ተከትሎ የቅንጅት አመራሮች፣ የግል ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማኅበራት አመራሮች …ታስረው ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት በኋላ በይቅርታ፣ በነጻ …መፈታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጊዜም በኋላ፣ በተለይ አፋኝ በሆነው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ብዙዎች ታስረዋል፣ እየታሰሩም ይገኛሉ፡፡
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና
በዘንድሮ ዓመት ግን የምናየው እስር የተለየ ሆነብኝ፡፡ የሕገ- መንግሥቱን አንቀ ጽ 30 መሰረት በማድረግ ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና አባላቶቻቸው ለሰልፉ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት እየተያዙ ለቀናቶች ታስረው መፈታት የተለመደ ሆነ፡፡ (ወይ ይህ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 30 ሳይሻር ተሽሮ ከሆነ መሻሩን ተቃዋሚዎች ይወቁት!)
አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ይሄንን እርምጃ ዘንድሮ በደንብ አይተውታል ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያኖች፣ ፖለቲከኞችና በርካታ ዜጎች በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል፣ ክስም ተመስርቶባቸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንቡን በመፈረም የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የፊታችን ቅዳሜ ሜክሲኮ በሚገው የመብራት ሐይል አዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ አቅዶ ስድስት አባላቱ ዛሬ ቂርቆስ አካባቢ በመኪና ህዝቡን በመቀስቀስ ላይ እያሉ መታሰራቸውን ሰማን፡፡
ፖሊስም ‹‹የስብሰባ እንጂ የቅስቀሳ ፈቃድ አልያዛችሁም›› በማለት ጥዋት አካባቢ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዳሰራቸው እና የፓርቲው አመራሮች በፖሊስ ጣቢያ ድረስ በመገኘት ከኃላፊዎቹ ጋር ቢነጋገሩም ልጆቹ ቃላቸውን መስጠታቸውንና ፖሊስ ልቀቃቸው የሚል ትዕዛዝ ሲደርሰው እለቃቸዋለሁ ማለቱን ወዳቻችን ዳዊት ሰለሞን በፌስ ቡክ ገጹ ዛሬ አስነብቦን ነበር፡፡
እኔም እንደጋዜጠኛ ጉዳዩን ለማጣራት የቀድሞ የኢዴፓ ሊቀመንበር ወደሆኑት አቶ ሙሴ ሰሙ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ደውዬ እውነት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ እንዲያውም፣ አቶ ሙሼ የተደረገው ነገር አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ በነገው ዕለት በግል መኪናቸው ቅስቀሳ ለማድረግ ማቀዳቸውን አጽንኦት ሰጥተው ነግረውኛል፡፡
እንዲሁም፣ በዛሬው ዕለት በእነሀብታሙ አያሌው የክስ መዝገብ አንድነት ፓርቲ ላቀረበው አቤቱታ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በአራዳ ፍርድ ቤት ለማድመጥ በችሎት ተገኝተው የነበሩ ስድስት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባላት (ዳንኤል ፈይሳ፣ አብነት ረጋሳ፣ ጥላዬ ታረቀኝ፣ ፋሲካ አዱኛ፣ ብርሀኑ ይግለጡና መሰለ አድማሴ) በደህነት ሃይሎች ተይዘው በቶዮታ ደብል ጋቢና ኮድ 3-50559 መኪና ወደ ማዕከላዊ መወሰዳቸውን የፍኖተ ነፃነት የማዕከላዊ ምንጮች ገልጸው ነበር፡፡ ከሰዓታት በኋላም የታሰሩት የፓርቲው አባላት ተፈትዋል፡፡
እስያዊቷ ሀገር ማሌዥያ፣ የመንገደኛ አውሮፕሏኖቿ አንዴ ሲሰወሩ፣ አንዴ ሲከሰከሱና በሮኬት ሚሳይል ሲመቱ ዛሬም ድረስ ደርሰዋል፡፡ በዛሬው ዕለት እንኳን ከሆላንድ አመስተርዳም ወደ ማሌዥያ ኩዋላላምፑር ሲጓዝ የነበረ ቦይንግ 777 የመንገደኞች አውሮፕላን በሮኬት ሚሳይል ተመትቶ (በራሽያ መሆኑ እየተነገረ ነው) በዩክሬን ግዛት በመከስከስ 295 ሰዎች አልቀዋል፡፡ 
በሀገራችን ደግሞ ሁሉን ዓቀፍ የእስር እርምጃ በመንግሥታችን እየተወሰደ መመልከቱ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ነው፣ በርዕሴ ‹‹የዘንድሮ እስር ‹‹ጸበል ቅመሱ›› ሁነብኝ ጃል!›› በማለት የገለጽኩት፡፡
ወዳጄ ዳዊት ሰለሞንም “Ethiopia the land of prisoners” (ኢትዮጵያ የእስረኞች ምድር) የሚል መልዕክት ከአምስት ሰዓታቶች በፊት በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሮ ተመልክቻለሁ፡፡ ማሌዥያ በአውሮፕላን አሳዛኝ አደጋ ጣጣ በዓለም ስትታወቅ እኛ ደግሞ ዜጎችን በገፍ መማሰር እንታወቅ?!
እኔ ደጋግሜ ብያለሁ፣ እስር መፍትሄ አይደለም፡፡ ዜጎችን ማሰር ብዙ የማይገርምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ መንግስታችን ሆይ! ዜጎችን የማሰር ጉዞውን በአንክሮ አስብበት! አሊያ… ከባድ ነው! መዘዝ አለው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! —

No comments: