Sunday, June 15, 2014

የቴዲ አፍሮ በውዝግብ ያልተገባ ዝና ክብር ወይስ ውዝግባዊ መንፈስ

June 15/2014
ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ወደ ሙዚቃው ዓለም ተቀላቅሎ ወደ ዝና ማማ መውጣት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መነጋገሪያ ከመሆን ያመለጠ አርቲስት አይደለም፡፡ በ1993 ዓ.ም ማብቂያ ላይ ባወጣው የመጀመሪያ ‹አቦጊዳ› አልበሙ የሙዚቃ አድማጩን ጆሮ ለመቆጣጠር የቻለው ቴዲ አፍሮ በወቅቱ በአለቤ ሾው ፕሮግራም ላይ በእንግድነት ቀርቦ ‹25 ዓመቴ ቢሆንም ፍቅረኛ ገና አልያዝኩም › ባለ ማግስት የከተማው ወጣት ሴቶች አይን ማረፊያ ሆኖ ነበር፡፡ ከዚሁ ይፋ ካልወጣ የሴቶች አደን ጋር ተያይዞ የመጀመሪያውን ውዝግብ አስተናገደ፡፡ ‹በሴት ልጅ ጡት ላይ ፊርማ ፈርሟል› በሚል ተሰራጨው ወሬ ከከተማ ወሬነት አልፎ የአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ገበያ መጥሪያና ማሻሻጪያ ሆኖ ነበር፡፡‹የተባለውን ነገር አላደረኩም፤ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ኩሩዎች ናቸው፡፡ ይህንን ነገር እንዳደርግ አይጠይቁኝም ፤ እኔም አላደረኩትም› ብሎ በወቅቱ ለታተመችው ቅፅ 1 ቁጥር 1 ቁም ነገር መፅሔት ላይ ቢናገርም አድናቂዎቹን ከማሳመን በቀር የወሬ ማጣፈጫነቱን አላስቀረውም ነበር፡፡
TeddyAfro_NYC-12
ቴዲ አፍሮ የመጀመሪያ ውዝግቡን በዚሁ መልኩ ለመቋመጨት ጥረት ቢያደርግም ከዚሁ አልበሙ በፊት በሰራው የመጀመሪያ ካሴቱ ሳቢያ ለሌላ ውዝግብ የተዳረገው ብዙም ሳይቆይ ነው፡፡ የመጀመሪያ ካሴቱን ሳያወጣ ለዓመታት አስቀምጦት የነበረው ቮይስ ሙዚቃ ቤት የአቦጊዳ አልበሙ የአድማጭን ጆሮ መቆጣጠር ተመልክቶ አዲሱን አልበም ለገበያ ያቀረበው ወዲያውኑ ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያም ‹የአቦጊዳን አልበም ሽያጭ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለበሁበት ደረጃ ፈፅሞ የማይመጥን› ያለውን ከዓመታት በፊት የተሰራውን ካሴት ‹ሳያስፈቅደኝ መልቀቅ የለበትም› በሚል ሌላ ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ተፈጠረው ውዝግብ መሀል ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ገብቶ በሽምግልና ጉዳዩን እንዲፈታ እስኪያደርግ ድረስ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ መነጋገሪያ ነበር፡፡
ቴዲ በሙዚቃ ስራው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ህይወቱና በሚያደርጋቸው ቃለ ምልልሶቹ ዝናውን ከፍ እያለ ቢመጣም ምርጫ 97 ተከትሎ ገበያ ላይ በዋለሁ ሶስተኛ ‹ጃ ያስተሰርያል› አልበሙ ሳቢያ ውዝግቡ ከግለሰብ ወደ መንግስት ዞሮ ነበር፡፡ ይፋዊ በሆነ መንገድ መንግስት ተቃውሞውን ባይገልፅም ዘፈኑ በማንኛውም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ላይ እንዳይተላለፍ ከመከልከል ጀምሮ ለጉዳዩ ሌላ ፓለቲካዊ መልክ በመስጠት የውዝግቡን ጡዘት እንዳከረረው እናስታውሳለን፡፡ ከምርጫው ጋር የተያያዘው ውጥረት ቀስ እያለ ቢረግብም ከመንግስት ጋር ያለው ውዝግበ ከአንድ ዘፈን ወደ ሶስት አድጎ ከ‹ካብ ዳህላክና› እና ‹ሼ መንደፈርን› ጨምሮ ታይቷል፡፡ መንግስት በወቅቱ ከነበረው ፖለቲካዊ ራስ ምታት ተረጋግቶ ሚሊኒየሙን ለመቀበል ሽር ጉድ በሚልበት ወቅት ቴዲ አሁንም የህዝቡን የልብ ትርታ ያዳመጠ ‹አበባ አየሽ ሆይ› የተሰኘውን ተወዳጅ ባህላዊ ዜማ ለእርቅ አውሎት ብቅ አለ፡፡ ከፓለቲካ እስረኞች መፈታት ጋር ተያይዞ የእርቅ መንፈሱ በሁሉም ሙዚቃ አድማጭ ጆሮ ማንቃጨል ቢጀምርም መንግስት ግን ዘፈኑን ዘወትር በየሚዲያው ላይ ሲለቀቅ ሁኔታውን በዝምታ ከመመልከት ውጪ ‹ሆ በል ከበሮ ሆ በል አንተ ማሲንቆ ስታይ ሰው ታርቆ› በሚለው ስንኝ ከህዝቡ ጋር እስክስታ ለመውረድ ሳይችል ቀርቷል፡፡የቴዲ አፍሮ የእርቅ መንፈስ ሚሊኒየሙን ብቻ ሳይሆን ባህር ማዶ ተሻግሮ ለመዝፈንና ለማስጨፈር ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ከሚሊኒየሙ ጋር ታኮ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ቢዮንሴ ኖውልስ በቴዲ አፍሮ ‹አበባ አየሽ ሆይ› ዜማ ወገቧን ይዛ ስትጨርፍር ታይታለች፡፡
ቴዲ በዘፈኑ የሀገሩን ልጆች አልፎ የውጪ ሰዎችን ማማለል ቢችልም ከመንግስት ጋር የገባው ውዝግብ ከዚህ ቀደም ከግለሰቦች ጋር እንዳለው አይነት ተራ የሚባል አልነበረምና ወደ እስር ቤት የሚገባበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በብዙዎቹ አድናቂዎቹ ዘንድ አሁንም ድረስ እንደሚታመነው ‹ቴዲ አፍሮ በመኪና ሰው ገጭቶ አምልጧ› የሚለውን የአቃቤ ህግ ክስ ለመቀበል ዳግም መወለድ የሚያስፈልጋቸው ይመስላል፡፡ ‹ደጉ ይበልጣል› የተባለውን የ18 ዓመት የጎዳና ተዳዳሪ ገጭቶ ስለመግደሉና ስለማምለጡ በወቅቱ መነጋገሪያ የነበረው ክስ ከብዙ የፍርድ ቤት ቀጠሮና ምልልስ በኋለ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ሲቋጭ ‹ቴዲ እንደ በፊቱ ተወዳጅ ሥራዎቹን ይሰጠን ይሆን ›የሚል ጥርጣሬ መኖሩ አልቀረም፡፡ የፈጠራ ስራ ችግር የሌለበት ቴዲ ከእስር ቤት በወጣ በሶስተኛው ወር ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኮንሰርት በማዘጋጀት ገቢውን በልመና ሥራ ላይ ለተሰማሩ ወገኖች ማቋቋሚያ አደረገ፡፡ በዚህ ኮንሰርት ላይም ያገኘውን ከአንድ ሚሊየንም ብር በላይ ገንዘብም ለኤልሻዳይ የበጎ አድራጎት ማህበር አስረከበ፡፡
ከሚያወጣቸው አልበሞች ጋር ተያይዞ ውዝግብ የማያጣው ቴዲ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋርም ውዝግብ ውስጥ መግባቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከዘፈኖች መመሳሰል ጋር በተያያዘ በሰይፉ ፕሮግራም ላይ በቀረበ ዘገባ ሳቢያ ጉዳዩ በስምምነት እስኪፈታ ድረስ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ ቴዲ የሌሎቹን ያህል አይሁን እንጂ ከረዥም ጊዜ ማናጀሩ አዲስ ገሠሠ ጋርም ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የተለያዩ ሲሆን በተደጋጋሚ ተሰርቀው በወጡ ነጠላ ዜማዎቹ ሳቢያም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የቴዲ አራተኛ ካሴትም ውዝግብ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ‹ጥቁር ሰው› በሚል ርዕስ ያወጣው አልበም ከፍተኛ የሙዚቃ ችሎታውን ያሳየበትና አዳዲስ የአዘፋፈን ስልቶችን ያካተተበት ሥራው ቢሆንም ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ፓለቲካዎ አቋም ጋር ተያይዞ ተቃውሞ የገጠመው ወዲያውኑ ነበር፡፡ ጉዳዩ ከታሪክ አንፃር መታየት ያለበትና የአድዋ ጀግኖችን ለመዘከር በሚል የተሰራ ሙዚቃ እንደሆነ የተለያዩ ሰዎች የየራሳቸውን አስተያየት በማከል በየመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ለመከራከር መሞክሩም ፓለቲካዊ መልክ የተሰጠውን ውዝግብ ለማብረድ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ከዚህ ውዝግብ ቀጣይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ‹ወደ ፍቅር ጉዞ› የሚል ስያሜ የተሰጠው የሙዚቃ ኮንሰርትም በበደሌ ቢራ ስፖንሰር አድራጊነት ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች በመጓዝ ለማሳየት ፕሮግራም ቢዘረጋም ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ጋር ተያይዞ ‹ሰጠ› በተባለ ቃለ ምልልስ ሳቢያ በደሌ ቢራ ኮንሰርቱን ሰርዞታል፡፡ በደሌ ኮንሰርቱን ለመሰረዝ ምክንያት የሆነው ቴዲ ሰጠ በተባለው ቃለ ምልልስ ሳቢያ የተቆጡ ወገኖች ‹በደሌ ቢራን እንዳይጠጡ!› የሚል የቅስቀሳ ዘመቻ በመጀመራቸው እንደሆነና ከንግድ ስራ አንፃር ኮንሰርቱን መሰረዝ አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ ቴዲ የተባለውን ቃለ ምልልስ እንዳልሰጠ፤ ይልቁንም በመፅሔቱ የተፈጠረ ተራ ስህተት እንደሆነ ገልጾ ለመከራከር ቢሞክርም ሰሚ
ያገኘ አይመስልም፡፡ ጉዳዩ ስር እየሰደደ የመምጣቱ አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚወደሰደውም የዘመቻው ቀስቃሾች የቴዲን ኮንሰርት በማሰረዝ ብቻ ሳይገቱ ሌላም የመልስ ምት መሰጠት እንዳለበት የሚያሳስቡ ቅስቀሳዎች ተጠናክረው በመሰጠታቸው የጥቁር ሰው ተነፃፃሪ ተቃራኒ ነጠላ ዘፈን በአንድ አርቲስት
ተሰርቶ ተለቋል፡፡
ይህ የውዝግብ አዙሪት ባልተቋጨበት ሁኔታ ኮካ ኮላ ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በየሀገሩ ከሚያሰራቸው አርቲስቶች መሀከል አንዱ አድርጎ ቴዲን እንደመረጠው ተሰማ፡፡ቴዲም ከሶስት ወራት በላይ በአዲስ አበባና በኬኒያ እየተመላለሰ የሙዚቃ ስራውን ሰርቶ ቢያጠናቅቅም ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ ተነግሯል፡፡ በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ብራዚል እየተካሄደ የሚገኘውን የዘንድሮውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት በማድረግ እንደተለመደው ግዙፍ የቢዝነስ ተቋም የሆነው ኮካ ኮላ በተለያዩ ድምጻውያን ሙዚቃዎችን አዘጋጅቶ ራሱን እያስተዋወቀ ነው፡፡ ሙዚቃዎቹ የተሰሩት በብዙ ዓይነት ቋንቋዎችና ከተለያዩ ሀገራት በተውጣጡ ድምጻውያን ሲሆን የተቀረጹት በኮካኮላ ስቱዲዮ /Coke Studio/ ነው፡፡ ከ30 በላይ ከሚሆኑ ሀገራት የተመረጡ ድምጻዊያን የሠሩት የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አፊሲያላዊ የኮካ ኮላ ሙዚቃ ‹‹The world Is our›› /አለም የኛ ናት/ የሚል ርዕስ አለው፡፡ ይሄንን ሙዚቃ በድምፅ ለመስራት ከተመረጡት በርካታ ዘፋኞች መካከል ኢትዮጵያዊው ቴዲ አፍሮ ይገኝበታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 መገባደጃ አካባቢ ቴዲ ለሙዚቃ ኮንሠርት ወደ ኳታር ባቀናበት ወቅት ከኮካ ኮላ ካምፓኒ ስልክ ተደውሎ በዓለም ዋንጫው ሙዚቃ ላይ እንዲሳተፍ ተጠየቀ፡፡ በዚህ መሠረት ከሌሎች አፍሪካውያን ድምጻውያን ጋር በጋራ ካቀነቀነው ዘፈን በተጨማሪ በአማርኛ ቋንቋ የተሰራና በግሉ የተሳተፈበት ሙዚቃ በኮካ ኮላ ስቱዲዮ መቀረጹ ተነገረ፡፡ ሙዚቃውም በ2014 የመጀመሪያ ወራት ላይ ለህዝብ እንደሚቀርብ ተገልጾ ነበር፡፡ ይሁንና በተባለበት ጊዜ የቴዲ አፍሮ ዘፈን አልተለቀቀም፡፡
tedddyበሌሎች ሀገራት ድምጻውያን የተሰሩ ዘፈኖች ግን በይፋ ተለቀው እየተደመጡ ይገኛሉ፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የተሰራው የቴዲ ዘፈን ግን መዘግየቱ ሳያንስ በቅርቡ ደግሞ ሙዚቃው ከነአካቴው ከስቱዲዮ እንደማይወጣ ተሰማ፡፡ ይህን ተከትሎ ቴዲ አፍሮ በድረገጹ ላይ ወጣ በተባለ ጽሁፍ ድርጊቱን ኮነነ፡፡ የኮካ ኮላ ካምፓኒ ድርጊት ‹‹ሀገራችን ያዋረደ›› ጭምር መሆኑን በመግለጽ ጉዳዩን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚከታተለው ገለጸ፡፡ የኮካ ኮላ ዘመቻ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሚታወቀው ኮካ ኮላ በዓለም ላይ 200 ከሚበልጡ ሀገሮች ውስጥ ፋብሪካውን ተክሎ በቀን ከ1.7 ቢሊዮን በላይ የሚሆን ጠርሙስ ኮካ ይሸጣል፡፡ መመረት የተጀመረበትን 128 ኛ ዓመት በማክበር ላይ ያለው ኮካ ኮላ ካለፈው ጥር አንስቶ እስከ መጋቢት ባለው ሶስት ወራት ብቻ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አትርፏል፡፡ ኮካ ኮላ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ተቃውሞዎች ገጥመውት የሚያውቁ ሲሆን ሁሉንም በማይበገረው የገንዘብ ሀይሉ አሸናፊነቱን አረጋግጦ ነው የተወጣው፡፡ ከአረብ እስራኤሎች ጦርነት በኋላ በአረቡ ዓለም በታየው የፀረ እስራኤል ዘመቻ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአብዛኛዎቹ አረብ ሀገራት ኮካ ኮላን ባለመጠጣት ለፍልስጤሞች ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ጥረዋል፡፡ አረቦቹ ኮካ ኮላን ባለመጠጣት ብቻ ሳይወሰኑ ፊታቸውን ወደ ፔፕሲ አዙረዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ይህ ዘመቻ የኮካ ኮላን ገበያ የሚፈታተንና ከገበያ የሚያስወጣ ስላልነበረ በማስታወቂያው ላይ ባፈሰሰው ከፍተኛ በጀት የዓለማችን ቀዳሚ ለስላሳ መጠጥነቱን አስከብሮ ለመቆየት ችሏል፡፡ እ.እ.አ በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይም የህንድ ገበሬዎች ኮካ ኮላ ለማሳችን የሚያስፈልገንን ውሃ ተሸማብን በማለት ኮካ ኮላን ባለመጠጣት ተቃውሟቸውን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በዓመት 11 ቢሊዮን ዶላር ለማስታወቂያ ብቻ የሚያወጣው ኮካ ኮላ ንፁህ የመጠጥ ውሃን በማውጣትና ዙሪያ ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች የሚመድበውን ማህበራዊ በጀት ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር በማሳደግ ራሱን ከህንድ አርሶ አደሮች ዘመቻ ተከላክሏል፡፡
የኮካ ኮላ የአቀማመም ምስጢር ድብቅነቱን ተከትሎ ሱስ አስያዥ ቅመም እንዳለውና ለጤናም አደገኛ ስለመሆኑ የተወራበት ጊዜ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶም ሰዎችን ሱስ የሚያሲይዝ የኮኬይን ቅመም እንዳለው ሲነገር ኮካ ኮላ ግን ይህ መሰረተ ቢስ ወሬ ነው ሲል አስተባብሏል፡፡ያም ሆኖ ኮካ ኮላ አሁንም
ድረስ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ተወዳጅ መጠጥ ቢሆንም እንደ ሰሜን ኮሪያ በርማና ኩባ አይነት ሀገሮች ኮካ ኮላ ፋብሪካ በሀገሮቻቸው እንዲቋቋም ያልፈቀዱ ሀገራት ናቸው፡፡እ.ኤ.አ በግንቦት 8 ቀን 1886 በአትላንታ ጆርጂያ ለራስ ምታት መድሃኒት ይሆናል ብሎ መድሃኒት ቀማሚው ጆን ኤስ ቴምበር ከካካዋ ፍሬ በሶዳ ውሃ በጥብጦ ያዘጋጀው ኮካ ኮላ የተባለው መጠጥ ይኸው ዛሬ በመላው ዓለም ይጠጣል፡፡ በወቅቱ ድካምንና ራስ ምታትን እንዲሁም ድብርትንና የወንዶችን የወሲብ ፍላጎት ያነሳሳል በሚል የተቀመመው ኮካ ኮላ በአዲስ መልኩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ምስጢራዊነቱን ጠብቆ መመረት ከጀመረ እነሆ ዘንድሮ 120 ዓመታት ሆኖታል፡፡
ዘመቻ ‹‹ኮካ አትጠጡ››የድምጻዊው አድናቂዎችና በሁኔታው ስሜታችን ተነክቷል ያሉ ሰዎች በማህበራዊ ድረገፆች አማካኝነት በኮካ ኮላ ካምፓኒ ላይ መቀየማቸውን የሚያሳዩ ምስሎችንና ጽሁፎችን ለጠፉ፡፡ የካምፓኒውን ምርቶች ባለመጠጣት ተቃውሞአቸውን ለማሰማት ዛቱ፡፡ በተግባር ጉዳዩ ለመፈጸሙ
ማረጋገጫ ባናገኝም በቴዲና በኮካ ኮላ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ አበሳጭቷቸው ከኮካ ምርቶች የታቀቡ ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ግን አያዳግትም፡፡ በተለይ በማህበራዊ ገፆች ላይ በተደጋጋሚ ሲጻፍ የነበረውን ‹‹ፀረ-ኮካ›› ዘመቻ የቅስቀሳ መልዕክቶች ስንመለት የተባለው ድርጊት መጨረሻው የት ነው እንድንል ይገፋናል፡፡ የሙዚቃው አለመለቀቅ ‹‹ሀገራችን ከመናቅ›› የመጣ ነው ከሚል ሀሳብ ጋር አያይዞ ድምፃዊው ቅሬታውን መግለጹ ተቃውሞውን እንዲደምቅ አድርጎታል፡፡ በቴዲ አፍሮ የግል ድረገጽ ላይ ወጣ የተባለው መግለጫ እንዲህ ይላል፡፡‹‹ስለ ዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ቅጂ ሙዚቃ
የተሰጠ መግለጫ ባለፉት ወራቶች ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም ‹‹ቴዲ አፍሮ›› ከኮካ ኮላ እና በስፋት ሲወራ ከከረመው የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ቅጂ ሙዚቃ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ያለንን አቋም እንድንገልፅ ሚርፍልን ጥያቄዎች ምክኒያት ከፍተኛ ጫና ሲደረግብን ቆይተናል፡፡ በበኩላችን በተገባው የውል ስምምነት ላይ ግንኙነቱን ሚጥራዊነት ለመጠበቅ ቃል ኪዳን የገባ እና ማክበር የነበረብን ቢሆንም ቅሉ የቴዲ አፍሮ እና የኮካ ግንኙነት ወሬ እንዴት አፈትልኮ ወጥቶ ህዝብ እንዲያውቀወው እንደቻለ ቢያስገርመንም አሁን ለመገንዘብ እንደቻልነው የቴዲ ከኮካ ጋር ያለው ግንኙነት ኢትዮፒካል ንክ
በተሰኘ የሀገር ውስጥ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ የመዝኛ ፕሮግራም አዘጋጆች አማካኝነት ያወጀው እና በሚያስገርም ሁኔታ ለኮካ የቲቪ ሥራም አድናቆቱን በመስጠት ያረጋገጠው የኮካ ኮላ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ብራንድ ሥራ አስኪያጅ የሆነው አቶ ምስክር ሙሉጌታ መሆኑን መረዳት ችለናል፡፡
ያለጥርጥር በኮካ ኮላ ስም ቴዲ አፍሮ ለኮካ የቴሌቪዥን ስራ በማገናኘት እና በዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ቅጂ ሙዚቃ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ተነሳሽነቱን የወሰደው የብራንዱ ሥራ አስኪያጅ ነበር፡፡ እኛም ጥያቄን ውድ አገራችንን በመላው የዓም ዋንጫ ተመልካቾች ዘንድ አዎንታዊ ገፅታ የትኩረት እይታ ስር የሚያውላት በመሆኑ እና በዚህ በጉጉት በሚጠበቀው ታላቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት ከንዋኔ ግዙፍ ቁጥር ያለው የዓለም ህዝብ ዘንድ የአገራችንን እና የህዝባችንን መልካም ገፆች ለማሳየት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ከተሟጠጠ በኋላ ነበር፡፡በመጨረሻም ምንም እንኳን በጉዳዩ ጭብጥ ዙሪያ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ስለተያዘው አቋም የተወሰነ መግባባት ላይ መድረስ ቴሌኮንፈረንስ የሚመለከታቸው ወገኖች እንደሚገኙበት ቃል ተገብቶበት የተዘጋጀ ቢሆንም ውይይቱ ሙያዊ በሆነ መልኩ ያልተዘጋጀ፣ ግልፅነት የጎደለው፣ አለመግባባት እንዳይከሰት ለማድረግ የጋራ መፍትሔ ለመሻት ሳይሆን ቅንነት በጎደለው መልኩ የኛን ሐሳብ ለመረዳት ነበር፡፡ ቴሌኮንፈረንሱ ሆነ ተብሎ ህጋዊ ወኪል የሆነውን ሥራ አስኪያጃችንን በጭብጦቹ ላይ ለመወያየት እንዳይሳተፍ በማግለል መካሄዱ በራሱ ሂደቱ በቅን ልቦና ላይ ያለተመሰረተ መሆኑ ግልፅ ማስረጃ ነው፡፡ በመሆኑም የአርቲስቱ አድናቂ ለሆኑት ኢትዮጵያዊያን እና የውጪ አገር ዜጎች በሙሉ ከኮካ ኮላ ጋር የነበረንን ግንኙነት ያቋረጥን መሆናችንን ለመግለፅ መገደዳችን እያዘንን ስንገልፅ የዓለም ዋንጫ እስከሚከፈትበት ዕለት ድረስ ኮካ ኮላ የወሰደውን እርምጃ በድጋሚ እንዲያጤነው ያደርግ ዘንድ በተደጋጋሚ ጥሪያችንን ስናቀርብ ብሔራዊ ጠርዝ ባለው እና በውድ አገራችን፤ በህዝባችን እና አድናቂዎቻችን ላይ ጭምር የተቃጣውን የፈሪ እና ሀገር ወዳድነት የጎደለው አሳፋሪ የክህደት እና ክብር የሚያጎድፈውን ተግባር ግን ይቅር ላለማለት ወስነናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አስከመጨረሻው ዕለት ድረስ ኮካ ኮላ የተጠናቀቀውን ሥራ እንዲያሰራጨው እና እንዲለቀው ግፊት ማድረጋችንን እንደምንቀጥልበት ለአድናቂዎቻችን እያረጋገጥን ከዚህ ጎን ለጎንም ከሁኔታዎች ጋር አግባብነት ያላቸው ሰላማዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የሁለቱንም ወገኖች ገፅታን እና ጥቅምን የሚጎዳ ማናቸውም ውዝግብ በማስቀረት በአድናቂዎቻችን የተጣሉብንን አደራ መተማመን እና እምነት ለመመለስ የሚያስችል እርምጃ የምንወስድ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡›› ቢቀር ምን ይቀርበታል? ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ከኮካ ኮላ የቀረበለትን ጥያቄ በደስታ ተቀብሎ የዓለም
ዋንጫውን የኢትዮጵያ ቅጂ ሙዚቃ ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ በሚገኘው የኮካ ኮላ ስቱዲዮ ተቀርጿል፡፡ ታድያስ መጽሔት ከአሜሪካ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ሙዚቃው እንደማይለቀቅ ከተነገረ በኋላም ኮካ ለድምጻዊው ተገቢውን የካሳ ክፍያ ለመፈጸም መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ የተቀረፀው ሙዚቃ ንብረትነቱ የኔ ብቻ ነው የሚለው ግዙፉ የለስላሳ መጠጥ ካምፓኒ ለጊዜው ዘፈኑ ባይለቀቅም ለድምፃዊው ግን ተገቢውን ነገር እናደርጋለን የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ከተመለከትነው ቴዲ ሙዚቃው ባለመለቀቁ ምንም አይቀርበትም ማለት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ድምጻዊው ከሚያገኘው ገንዘብ ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም ፊት የምትታወቅበትን ዕድል አጥታለች፡፡ ቴዲም ቢሆን የደከመበት ሙዚቃ ከስቱዲዮ አለመውጣቱ ምቾት ይነሳዋል፡፡ ለምን ብሎ መጠየቁም ተገቢ መሆኑን የብዙዎቹ አድናቂዎች ሀሳብ ነው፡፡
‹‹ሾላ በድፍን››
ኮካ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ራሱን ለማስተዋወቅ የሚረዱ ሙዚቃዎች ሲያዘጋጅ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ደቡብ አፍሪካ ላይ ለተከናወነው የዓለም ዋንጫ ‹‹waving Flag›› በሚል ርዕስ ሶማሊያዊው ድምጻዊ ኬናንን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ድምፃውያን አሰርቷል፡፡
በወቅቱ ይህ ሙዚቃ ተወዳጅ እንደነበር ይታወሳል፡፡የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር አጋር የሆነው ኮካ ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ የሚሆን ሙዚቃ በራሱ ስቱዲዮ መቅረጽ የጀመረው ባለፈው ዓመት ነበር፡፡ ሳምባ በሚባለው የብራዚሎች ባህላዊ የሙዚቃ ስልት የተሰራው ‹‹The World Is Our›› የተሰኘው ሙዚቃ በተለያዩ ሀገራት ሙዚቀኞችና በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል፡፡ የዚህ ሙዚቃ ዋና አቀንቃኝ በትውልድ ብራዚላዊ በዜግነት ደግሞ አሜሪካዊ የሆነው ዴቪድ ኮሬይ ሲሆን ካለፈው መስከረም ጀምሮ ከ90 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ተዘዋውሮ ሙዚቃውን መድረክ ላይ ተጫውቷል፡፡
በዲቪድ ኮሬይ በዋናነት የተሰራው ይህ የኮካ ኮላ ሙዚቃ በሌሎች ሀገራት ድምጻውያን በተለያዩ ቋንቋዎች ተቀርጾ ለጆሮ በቅቷል፡፡ ከስቱዲዮ ያልወጣው የቴዲ አፍሮ ብቻ ነው፡፡ ለምን? እስካሁን መልስ የለውም፡፡ የኮካ ኮላ ሰዎች ከአትላንታ ሰጡት በተባለው መግለጫና ቴዲ አፍሮ በድረ ገፁ ባሰፈረው ጽሁፍ ሙዚቃው ስላለመለቀቁ እንጅ በምን ምክንያት እንደሆን አይጠቅሱም፡፡ ነገሩ ‹‹ሾላ በድፍን›› ሆኗል፡፡ ስለዚህ ከሁሉም ነገር በፊት ሙዚቃው ያልተለቀቀው በምን ምክንያት ነው? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
‹ኮካ ሀገሪቷን ደፍሯል?›
ቴዲ አፍሮ በርካታ አድናቂዎች ካሏቸው አትዮጵያዊያን የሙዚቃ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለኮካ ኮላ ሙዚቃ ሊሠራ ነው ተብሎ ሲነገር እንደ አንድ በሀገር ኩራት ተቆጥሮ በመገናኛ ብዙሀን ሲዘወርለት ነበር፡፡ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ተጠግቶ ከነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ጋር ተነጻጽሮ ሲቀርብ ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ የሚወክለው›› የሚል መንደርደሪያ ከስሙ በፊት መጠቀስ ጀምሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሙዚቃው አለመለቀቁ በዚያ ሁሉ ሙቀት ላይ በረዶ እንደመጨመር ነው፡፡ ለዚያምነው በማህበራዊ ድረገፆች ‹‹ኮካ ኮላ አትጠጡ›› የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በብዛት ብቅ ማለታቸው፡፡ ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያን ወክሎ ከተጋዘበና ሙዚቃው በስቱዲዮ ከተቀረጸ በኋላ እዚያው ታፍኖ መቅረቱ ‹‹ክብረ ነክ›› መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡ ‹‹ሀገር ተደፍራለች›› የሚሉ ሀሳቦች በስፋት እየተነሱ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ መንግስት እጁንእንዲያስገባ የጠየቁም ነበሩ፡፡ ጉዳዩ ግን የሁለት አካላት ስምምነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ሀገራዊ አጀንዳ ለመሆን ግን አይበቃም፡፡ ተራ የቢዝነስ ስምምነትና ከዚያ ጋር ተያይዞ የተከሰተ የውል መፍረስ ነው የሚሉም ወገኖች አሉ፡፡
ኮካ ኮላ እንደአንድ የንግድ ተቋም ከድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ጋር የስራ ስምምነት አድርጓል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ተፈጻሚ ያልሆኑ ነገሮች ካሉ ቴዲ አፍሮ ህጋዊ ጥያቄ ማንሳት ይችላል፡፡ ይሄን ለማድረግም ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ እንዴት ተሠራ?ኮካ ኮላ ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሙዚቃ መሪ ድምጻዊ አድርጎ የመረጠው ዴቪድ ኮሬይን ነው፡፡ ይህ ድምጻዊ ከተለያዩ ሀገራት ድምፃዊያን ጋር የየሀገራቱን ቋንቋ በመጠቀም በጋራ ሙዚቃውን ሰርቷል፡፡ ከ30 በላይ ከሚሆኑ ድምጻውያን ጋር በዚያው ቁጥር ልክ አንዱን ሙዚቃ ደጋግሞ ተጫውቷል፡፡ ይሄን ዕድል ካገኙ ድምፃዊያን መካከል ቴዲ አፍሮ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቅጅ የሆነውን ሙዚቃ ዴቪድ ኮሬይና ቴዲ በጋራ ቀርፀዋል፡፡ ኮካ ኮላ በተለያዩ ሀገራት የሙዚቃ ስቱዲዮዎች አሉት፡፡ የቴዲ አፍሮና የሌሎች አፍሪካውያን ድምጻዊያን ሙዚቃ የተቀረፀው ናይሮቢ በሚኘው የኮካ ኮላ ስቱዲዮ ሲሆን ጉዳዩን የሚከታተለውና የሚያስፈጽመው ደግሞ ማንዳላ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ ጣቢያው ግን ሙዚቃውን ‹የውሀ ሽታ› አደረገው፡፡መጨረሻው ምን ይሆን?
ለዚህ ጥያቴ ምላሽ መስጠት ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ሙዚቃው ከስቱዲዮ እንዳይወጣ የተደረገበትን ምክንያት አለማወቃችን ከግምት ያለፈ እንዳንናገር ያስገድደናል፡፡ኮካ ኮላ ትልቅ የንግድ ስም ነው፡፡ በሀገራችን በብዛት ከሚዘወተሩ የለስላሳ መጠጦች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ድምጻዊ ቴዲ
አፍሮ ደግሞ ብዙ አድናቂዎች ካሏቸው የሙዚቃ ሰዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ኮካ ኮላ በገበያው ላይ የሚደርስበትን ተጽዕኖ በመፍራት ችግሩን እልባት ይሰጠዋል ብለን መገመት እንችል ይሆናል፡፡በማህበራዊ ድረገፆች ‹‹ፀረ ኮካ›› ዘመቻ የጀመሩ የቴዲ አድናቂዎች የካምፓኒውን ስም ሊጎዱ የሚችሉ ሀተታዎችንም ደጋግመው እያስነበቡ ነው፡፡ ኮካ ለጤና ጠንቅ የሆነ ንጥረ ነገሮች እንዳሉት በመግለጽና የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ያልተለቀቀው ካምፓኒው ለኢትዮጵያ ካለው ንቀት የተነሳ መሆኑን በመዘርዘር አድማ እየቀሰቀሱ ነው፡፡
ይህን ስንመለከት ካምፓኒው በኢትዮጵያ ያለውን ተቀባይነት ላለማጣትና ስሙን ለመጠበቅ ሲል ‹የታፈነውን ሙዚቃ› ሊለቀው ይችላል፡፡

No comments: