Monday, June 23, 2014

አቡጊዳ – በሺሆች የሚቆጠሩ ከወለጋ «አማራን አንፈልግም» ተብለው ተፈናቀለ- ኦህዴዶች ፈርተው ነው ይላሉ

June23/2014
የአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ አማርኛዉ ክፍል ባቀረበው ዘገባ በሺሆች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ኢትዮጵያዉያን ከቅያቸው እንደተፈናቀሉ ታወቀ። ከምዕራብ ወለጋ ጊምቢና ቀለም የተፈናቀሉ ወገኖች፣ ሲሆን፣ «ተባረርን ቤት ንብረታችን ወደመ፣ ተቃጠለ» ሲሉ የደረሰባቸውን ሰቆቃ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በዝርዝር ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የክልሉ ባለስልጣናት ዜጎች መፈናቀላቸውን ያመኑ ሲሆን፣ «ተገደው ሳይሆን ፈርተው ነው የሄዱት» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሕወሃት/ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ የዘረጋው የዘር ፖለቲካ በብሄረሰቦች እና በብሄረሰቦች መካከል መከፋፈልና መፈራራትን እንዲመጣ ያደረገ መሆኑ የገለጹት በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ «ዜጎች በአገራቸው መኖር ካስፈራቸው የተዘራው ጥላቻ ምን ያህል ሥር እንደሰደደ የሚያሳይ ነው» ሲሉ ሁሉም ዜጎች፣ ሕዝብን ከሕዝብ ሊያጨራርስና የሩዋንዳ አይነት እልቂት ሊያመጣ ከሚችል ዘረኝነት አጥብቆ መወጋት እንዳለበት ይናገራሉ።
በሕዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት ፣ በቀለም ወለጋ ዞን 97% የየሚሆኑ ነዋሪዎች አንደኛ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ እንደሆነ ያስረዱት እኝሁ ተንታኝ፣ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የዘገበው አይነት የዘር ማጽዳት ወንጀል ከቀጠለ፣ ቀለም ወለጋ ሙሉ ለሙሉ፣ የኦህደድ አክራሪዎች «አቢሲኒያዎች» ከሚሏቸው የጸዳች ልትሆን እንደምትችል ለመገመት አያስቸግርም በማለት በወለጋ የታየውን አሳዛኝ ብለዉታል።
በቅርቡ የጥላቻ ሃዉልት የሚባለው የአኖሌ ሃዉልት በሚሊዮንች ብር በሚሆን ከሕዝብ ካዝና በተገኘ ወጭ በኢሕአዴግ ተገንብቶ፣ በክልሉ አስተዳዳሪ አቶ ሙክታር ከድር መመረቁ ይታወሳል። በኦሮሚያ ሕገ መንግስትም፣ የኦሮሚያ ግዛት ባለቤት፣ ኦሮምው ብቻ እንደሆነ የተቀመጠ ሲሆን ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በኦሮሚያ እንደ ዉጭ አገር ዜጋና እንግዳ እንዲታዩ የሚያደርግ የፖለቲካ ሲስተም መዘርጋቱ በግልጽ የታወቀ ነው።

No comments: