Wednesday, June 25, 2014

የመጨረሻዉ መጀመሪያ

June 25/2014

በቅርቡ በተከታታይ አገር ቤት ዉስጥ ቅርጽና ይዘት እየያዙ የምናያቸዉና ማንም አሌ የማይላቸዉ ግዙፍ እዉነታዎች ሁሉም በአንድነት የሚጠቁሙት አይቀሬዉ የወያኔ መጨረሻ መጀመሩን ነዉ። ከዚህ ቀደም በግልጽ እንዳየነዉ ወያኔ አንድ ቦታ ሲሸነፍ ሌላ ቦታ እያሸነፈ በጉልበትም በተንኮልም የፖለቲካ የበላይነቱን እንደያዘ ከሃያ ሁለት አመት በላይ ቆይቷል። ወያኔ ለአመታት ህዝብን ያታለለባቸዉ የዉሸት ክምሮችና ህዝባዊዉን ትግል ወደ ኋላ ለመጎተት የተጠቀመባቸዉ ስልቶች ዛሬ ሁሉም ሙጥጥ ብለዉ አልቀዉበት ዬኔ ነዉ ብሎ በሚመካበት ትግራይ ዉስጥ ጭምር መግቢያና መዉጪያዉ የጠፋዉ የተከበበ አዉሬ መስሏል። በያዝነዉ የ2006 ዓም ሁለተኛዉ አጋማሽ ወያኔ ጨካኙን የአግአዚ ኃይል እዚህም እዚያም አሰማርቶ ከሚቆጣጠራቸዉ ጥቂት አደባባዮች ዉጭ እንደቀድሞዉ በግልጽ ወጥቶ ወያኔን የሚያሞግስ ወይም የወያኔን የሌለ ገድል የሚናገር ሰዉ የለም። በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የትግል ስልቶች ወያኔን የሚታገሉ ኃይሎች አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ኃይላቸዉና ቁርጠኝነታቸዉ እየጨመረ መጥቶ ወያኔ ያንን የተለመደ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዉን እዲወስድና የራሱን የመጨረሻ እሱ እራሱ ሳይወድ በግዱ እንዲያፋጥነዉ እያደረጉት ነዉ።
የአገራችንን አንድነት ሊያላሉና ኢትዮጵያ የሚለዉን ታሪካዊ ስም ከታሪክ ዉጭ ማድረግ ከሚችሉ አደገኛ የወያኔ ባህሪዮች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ዘረኝነቱና ለአገር አንድነትና ዳር ድንበር መከበር ያለዉ የግድየለሽነት ባህሪይ ነዉ። ዛሬ ወያኔ በአራቱም ማዕዘን በየቀኑ አየጨመረና እያየለ የሚሄደዉን የህዝብ ቁጣ ለማብረድና አፋፍ ላይ ለደረሰዉ ስርዐቱ ተጨማሪ ግዜ ለመግዛት የሚወስዳቸዉ እርምጃዎች ከዚሁ ከዘረኝነት ባህሪይዉ የሚመነጪ እርምጃዎች ናቸዉ። ወያኔ ዕድሜዉ ሊበረክት የሚችለዉ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነት የሚታገሉ ኃይሎች መግባባት ሲያቅታቸዉ መሆኑን ያዉቃል፤ ስለዚህም በተቻለዉ መጠን ኢትዮጵያዉያንን የሚለያዩና ግጭት ዉስጥ የሚከትቱ አጀንዳዎችን አየፈጠረ ይወረዉርልናል። ከእነዚህ አገር አጥፊ የወያኔ አጀንዳዎች ዉስጥ አንዱ ህዝብን በዘር ከፋፍሎ እርስ በርሱ እንዲጋጭ ማድረግ ነዉ። ለምሳሌ በቅርቡ ደቡብ ኢትዮጵያ ዲላ ከተማ ዉስጥ በንግዱ ህብረተሰብ ላይ የነጋዴዎችን አቅምና ትርፍ ያላገናዘበ ግብር በመጫን በአንድ በኩል ነጋዴዎቹ በዞኑ አስተዳዳሪዎች ላይ እንዲነሱ በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ የዞኑ አስተዳዳሪዎች ነጋዴዎቹን የምትሰሙን ከሆነ ስሙን አለዚያ ክልሉን ለቅቃችሁ ሂዱ የሚል አስነዋሪና የዜግነት መብትን የሚጋፋ መልስ እንዲሰጡ በመገፋፋት በጌዲኦ ብሄረሰብና በዲላና አካባቢዉ በብዛት በንግድ ስራ ላይ በተሰማራዉ የጉራጌ ማህበረሰብ መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ለማድረግ ሞክሯል። ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዉስጥም እንደዚሁ የጋምቤላ ህዝብ ከጋምቤላ ዉጭ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡትን ኢትዮጵያዉያን ክልሉ የእናንተ አይደለምና ለቅቃችሁ ዉጡ ብሎ እንዲያሰገድድ በመገፋፋት በኢትዮጵያዉያን መካከል ቂምና ጥላቻ እንዲፈጠር አድርጓል። ባለፉት አምስት አመታት ወያኔ ጋምቤላ ዉስጥ ገበሬዉን እያፈናቀለ መሬቱን ለዉጭና ለአገር ዉስጥ በተለይ ለትግራይ ባለኃብቶች በርካሽ ዋጋ ማስረከቡ የሚታወስ ነዉ። ይህ ባዕዳንን ጋምቤላ ላይ እያሰፈረ ኑና እረሱ እያለ የሚለምን ነዉረኛ አገዛዝ ነዉ ዛሬ ኢትዮጵያዉያንን ከጋምቤላ ዉጡ እያለ የሚያሰገድደዉ።
ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን ያክል እንደተጠላ ለማወቅ ባለፈዉ ቅዳሜ መድረክ አዋሳ ዉስጥ የጠራዉን የተቃዉሞ ሰልፍ መመልከቱ ይበቃል። የአዋሳና የአካባቢዉ ህዝብ በዚህ መድረክ በጠራዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ የተገኘዉ ፌዴራል ፖሊስ፤ የክልሉ ፖሊስና የአገዛዙ ካድሬዎች በእያንዳንዱ ሰላማዊ ሰልፍኛ ላይ ያወርዱት የነበረዉን ዛቻ፤ ማስፌራሪያና ና የስድብ ናዳ ከምንም በለመቁጠር ነዉ። በዕለቱ የአካባቢዉን ሰላምና የሰልፈኛዉን ደህንነት አስጠብቃለሁ ብሎ በአዋሳ አደባባዮች ላይ የተሰማራዉ የወያኔ የፖሊስ ኃይል በህግ የተሰጠዉን ኃላፉነት ትቶ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር እርምጃዎች ሲወስድ ታይቷል።
ወያኔ ብሶቱን አይቼ 17 ዐመት ታገልኩልት የሚለዉና ዛሬም እወክለዋለሁ ብሎ የሚነግረን ክልል ቢኖር የትግራይ ክልል ነዉ። ዛሬ ትግራይ ዉስጥም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሞቱት ለዚህ አይደለም ብለዉ ብረት አንስተዉ ወያኔን አምርረዉ የሚታገሉ የትግራይ ወጣቶች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነዉ። አስራ ሰባት አመት ሙሉ በወያኔ የማይጨበጥ ተስፋ ተታልሎ በከንቱ ህይወቱን የገበረዉ የትግራይ ወጣት ዛሬ እዉነቱ ገብቶት ወያኔን በትግራይ ህዝብ ስም መነገድህን አቁም እያለዉ ነዉ። በቅርቡ በመቀሌና በአካባቢዋ የታየዉ ከፍተኛ ፀረ ወያኔ እንቅስቃሴ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወያኔ ለዚህ የሸተተ ስርአቱ ዕድሜ ለመግዛት ቢፍጨረጨርም “ከወደቁ በኋላ መራገጥ ለመላላጥ” ካልሆነ በቀር ካሁን በኋላ ወያኔዎች በስልጣን ላይ መቆየት ቀርቶ የዘረፉትን ኃብት የሚያሸሹበት ግዜም ልንሰጣቸዉ አይገባም።
የወያኔ ጠመንጃና የሚቆጣጠራቸዉ የአፈና ተቋሞች አላናግር ወይም አላስተነፍስ እያሉት እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ስለተገደደ ነዉ እንጂ አመጸኞቹ የወያኔ መሪዎች ለተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ታገልንለት ብለዉ በስሙ ለሚነግዱት የትግራይ ህዝብ በፍጹም የማይበጁ ፀረ አገር ኃይሎች መሆናቸዉን የትግራይ ህዝብ ካወቀ ቆይቷል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የትግራይ ህዝብም በቃ በስሜም አትነግዱ ወንድሞቼንና እህቶቼንም አትበድሉ ብሎ ደጋግሞ እየነገራቸዉ ነዉ። ዛሬ ብዙ የትግራይ ወጣቶች እዚያ የዛሬ ሰላሳና ሰላሳ አምስት አመት አባቶቻቸዉ የታገሉበት ጫካ ዉስጥ ገብተዉ እነሱም በተራቸዉ የዛሬዉን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በጠመንጃ ጭምር በመፋለም ላይ ይገኛሉ። ወያኔ የመጨረሻ መደበቂያዬ ይሆነኛል ብሎ ይተማመንበት የነበረዉ የትግራይ ክልል ዛሬ ግልጽ በሆነ መልኩ የወያኔን መጨረሻ ለማየት የሚቸኩሉ ጀግኖች ክልል እየሆነ ነዉ።
የትግራይ ጫካዎችን ጨምሮ ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች “ጨርቅ” ብለዉ ያንኳሰሱትን የኢትዮጵያ ባንዲራ በክብር አንግበዉ ከቋጥኝ ቋጥኝ የሚዘልሉት የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አርበኞች ወገንን የሚያኮሩ ዘረኞቹን የወያኔ መሪዎች ደግሞ ምነዉ ባልጀመርነዉ የሚያሰኙ የአገርና የወገን አለኝታ ሆነዋል። ዛሬ ወያኔ የትግራይን ምድር የእግር መረማመጃ እስኪጠፋ ድረስ በወታደርና በታንክ ያጠረዉ ይህንኑ በትግራይ ወጣቶች የተገነባ ህዝባዊ የነጻነት ኃይል ስለፈራ ነዉ። አምባገነኖቸ በደም የሚቀባበሉት የተፈጥሮ ባህሪያቸዉ ሆኖ ነዉ እንጂ የታንክና የወታደር ጋጋታ ህዝባዊ ኃይልን የሚያቆም ቢሆን ኖሮ እነሱ ዛሬ ሚኒልክ ቤ/መንግስት ዉስጥ ገብተዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ሊረግጡ ቀርቶ ከተፈጠሩበት ደደቢት በረሃ ስንዝር ሳይራመዱ የእሳት እራት ሆነዉ ይቀሩ ነበር። ወያኔ ዛሬ በምድርና በአየር የታጠቀዉ መሰሪያና ሰራዊት ደርግ ከታጠቀዉ መሳሪያና ከነበረዉ ወታደራዊ ብቃት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፤ ሆኖም ለነጻነቱ ቆርጦ የቆመን ህዝብ የሚገታ ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ሰለሌለ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ አግኝቶ ደርግን መደምሰስ ችሏል። የዛሬዉ አምባገነን ወያኔም ዕድል ከደርግ የተለየ አይደለም። ወያኔ ያሰኘዉን ያክል ቢታጠቅ፤ ያሻዉን ያክል የድንበር አካባቢዎችን በታንክና በወታደር ብዛት ቢያጥር . . . . ደፋርና ጭስ መዉጪያ አያጣምና የወያኔ መሸነፍና መደምሰስ ጉዳይ ቀን እስኪያልፍ ያለፋል ካልሆነ በቀር ያለቀለት ጉዳይ ነዉ።
ደርግ ስልጣን በያዘባቸዉ የመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ዉስጥ ወታደራዊ አገዛዝ አንቀበልም ብለዉ ደርግን መግቢያና መዉጪያ ካሳጡት የህብረተሰብ ክፍሎች ዉስጥ ትልቁን ሚና የተጫዉተዉ ወጣቱ ትዉልድ ነበር። ይህ ወጣት ትዉልድ በኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል ዉስጥ ምን ግዜም ቢሆን ትዝታዉ የማይደበዝዝ አኩሪ የመስዋዕትነት ትግል ያካሄደና ያለምንም ፍርሃት ዉድ ህይወቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነት መከበር አሳልፎ የሰጠ ጀግና ትዉልድ ነዉ። ዛሬም አዲስ አበባ፤ አዋሳ፤ ባህርዳር፤ ጅማ፤ አምቦ ጊምቢና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተማዎች የሚኖረዉ ወጣት እኔም አገሬም አብረን ከምንጠፋ እኔ ሞቼ አገሬን አኖራለሁ በሚል ኢትዮጵያዊ እልህ ተነሳስቶ የወያኔን የመጨረሻ እያፋጠነ ነዉ። የወያኔን እገድልሃለሁና አጅ እቆርጣለሁ የሚል ዛቻ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ በብዕራቸዉ ህዝብን እያስተማሩ ቃሊቲ ከገቡት ጀግኖች ጀምሮ ከተማ ዉስጥ ከወያኔ ጋር መኖር በቃኝ ብለዉ ጠመንጃቸዉን ተሸክመዉ ጫካ እስከገቡት ቆራጥ አርበኞች ድረስ ኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤዋን ለማብሰር የተዘጋጁ እልፍ አዕላፋት ጀግኖች አሏት።
በገጠሪቱ ኢትዮጵያም መሬቱን ተቀምቶ የተሰደደዉ ወጣት ልክ እንደ ከተማዉ ወጣት በወያኔ ላይ አምርሮ ዱር ቤቴ ብሎ ጫካ ከገባ ቆይቷል። አባቶቹና አያቶቹ ያቆዩለትን መሬት በወያኔ የተቀማዉ የጋምቤላ ገበሬ መሬቴን አለዚያም ህይወቴን ብሎ ወያኔን ማንቀጥቀጥ ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። የሰሊጥ ማዕከል የሆነዉን ለምለም መሬቱን በወያኔ የተቀማዉና ዛሬም የአባቶቹን አጽም የተሸከመዉን መሬት ለባዕዳን ለመስጠት የሚዶለትበት የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ በወያኔ ላይ ጥርስ ከመንከስ አልፎ ቃታ መሳብ ጀምሯል። እነዚህ ከትግራይ እስከ ጋምቤላ ከጋምቤላ እስከ ጎንደር በአራቱም ማዕዘናት የሚታዩ ህዝባዊ አመጾች የሚያሳዩን አንድ ትልቅ ነገር አለ፤እሱም ወያኔ በህዝብ የተጠላ ብቻ ሳይሆን ህዝብ አንቅሮ የተፋዉ ከቆሻሻም ቆሻሻ መሆኑን ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘረኝነት በጉልህ ከሚታይባቸዉና በዘረኝነት ፖሊሲ ላይ ተመስርተዉ ከተዋቀሩ አገራዊ ተቋሞች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የመከላከያ ተቋም ነዉ። የኢዮጵያ መከላከያ ተቋም በተለይ ዋናዉን የዉግያና አገርን የመከላከል ስራ የሚሰራዉ የሰራዊቱ ክፍል የተሰባሰበዉ ከመላዉ የአገሪቱ ክፍሎች ቢሆንም ይህ ተቋም ሁለት ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑና ሆን ተብለዉ የጎደሉ ጉድለቶች አሉበት።አንደኛዉ ጉድለት ሠራዊቱን በተለያየ ደረጃ ከሚመሩና ከሚያዝዙ ወታደራዊ መኮንኖች ዉስጥ ከ95% በላይ የአንድ ዘር ተወላጆች መሆናቸዉ ሲሆን ሁለተኛዉ ትልቅ ጉድለት ደግሞ በኢትዮጵያ ሠራዊት ዉስጥ አግአዚ የሚባል የአዉሬዎች ክምችት የሚገኝበት አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገሩና ከአንድ ክልል የመጡ ተዋጊዎች ያሉበት ሠራዊት መኖሩ ነዉ። የአገሬን አንድነትና ዳር ድንበር አስከብራለሁ ብሎ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰበዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዘር ተከፋፍሎ የወያኔ መጠቀሚያ መሆን ሰልችቶታል።በተለይ ይህ ሰራዊት ብዛቱን በሚመጥን ቁጥር የመሪነትና የአዛዥነት ቦታ ስለማይሰጠዉ ሁል ግዜ በሚንቁትና በሚያንቋሽሹት የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች መመራት አንገሽግሾታል። ዛሬ በየበረሃዉ ለሚገኙት የነጻነት አርበኞች እባካችሁ እንገናኝና አገራችንን አንድ ላይ ሆነን ነጻ እናዉጣ የሚል የትግል ጥሪ በተደጋጋሚ የሚመጣዉ ከዚሁ በዘረኝነት አለንጋ ከሚገረፈዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነዉ። ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ በተለይ ባለፉትሦስት አመታት በኢትዮጵያ ሠራዊት ዉስጥ ትልቁ የመወያያ አርዕስት አንዴት አድርገን የነጻነት እበኞችን እንቀላቀል የሚለዉ ጥያቄ ነዉ። በሠራዊቱ ዉስጥ ሆኖ በዚህ አርዕስት ላይ የማይወያይ የሰራዊቱ አባል ቢኖር እንደ ዘይትና ዉኃ ቅልቅል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ ባዕድ አካል ሆኖ የሚታየዉ አዉሬዉ የአግአዚ ሠራዊት ብቻ ነዉ። አግአዚ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሳይሆን በኢትዮጵያ ሰራዊት ዉስጥ እንደ እንክርዳድ የበቀለ ፍጹም ባዕድና ጨካኝ የሆነ የወያኔ መገልገያ ነዉ።
ከዚህ በላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነዉ ወጣቱ፤ ገበሬዉ፤ ነጋዴዉ፤ ከተሜዉና ወታደሩ ሁሉም ወያኔን የሚቃወም ብቻ ሳይሆን ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን ለመደምሰስ የተዘጋጁ `ኃይሎች ናቸዉ። ባለፈዉ ግንቦት ወር ወያኔ ዘረኝነትንና ሙሰኝነትን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከለበትን ሃያ ሦስተኛ አመት ሲያከብር የኢትዮጵያ ህዝብ የተዋርድንበትን ቀን አናከብርም ብሎ ወያኔ የራሱን በዐል ብቻዉን አክብሮ ዉሏል። ከዚህ በተጨማሪ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዉያን ይህንን የባርነት ቀን እንደገና ሲከበር ማየት አንደማይፈልጉ በይፋ ተናግረዋል። በእርግጥም ካሁን በኋላ ወያኔ ግንቦት ሃያን ብቻዉንም ቢሆን እንዲያከብር መፍቀድ የለብንም። ደግሞም ወደድንም ጠላን ወይም አወቅን አላወቅን ወያኔ ግንቦት ሃያን የሚያከብረዉ ብቻ ሳይሆን እንዳሰኘዉ ረግጦ የሚገዛን እኛ አሜን ብለን ስለፈቀድንለት ብቻ ነዉ። ህዝብ በአንድ ድምጽ አልገዛም ብሎ አለመገዛቱን የሚያሳይ እርምጃ መዉሰድ ቢጀምር አይደለም በዐል ማክበር ወያኔዎች ሰኞ ያደሩበት ሚኒልክ ቤ/መንግስት ዉስጥ ማክሰኞ ማምሸትም አይችሉም ነበር።
መሬት አልባዉ የኢትዮጵያ ገበሬ ወያኔ እስካለ ድረስ ልጆቼን ብሎ ስለወደፊቱ ማሰብ ቀርቶ የዕለት ጉርሱን የማግኘት ዋስትናም የለዉም። ነጋዴዉም እንደዚሁ ነዉ። ለወያኔ ሙሰኞች ካላጎበደደና ግማሽ ትርፉን ለእነሱ ካልገበረ ነግዶ መኖር ቀርቶ በልቶ ማደር የማይችልበት ግዜ እየመጣ ነዉ። ከተሜዉ ኢትዮጵያዊስ ቢሆን እስከመቼ ነዉ ሰላማዊ ልጆቹ ከጉያዉ እየተጎተቱ ሽብርተኞች ተብለዉ ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸዉ ቃሊቲ ሲገቡ የሚመለከተዉ? እስከመቼ ነዉ ዬት ገቡ ተብለዉ አድራሻቸዉ የጠፋ ልጆቹ መንገድና ህንጻ ሲሰራ የጅምላ መቃብራቸዉ በግሬደር እየተቆፈረ ሲወጣ የሚመለከተዉ? ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የወጡት የመከላከያና ፖሊስ ሠራዊት አባላት እስከመቼ ነዉ እነሱ እራሳቸዉ በወያኔ ዘረኝነት እየተለበለቡ ለወያኔ ዕድሜ መራዘም ሲሉ ወንድሞቻቸዉንናነ እህቶቻቸዉን የሚገርፉትና የሚያዋርዱት?
ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ገዳማትን የእርሻ ቦታ አድርጓቸዋል፤ የእምነት ተቋሞችን የክፋቱ መሠረት አድርጓቸዋል፡ ምሁራንን ደግሞ አገራቸዉን ጥለዉ እንዲሰደዱ አድርጓል። ባጠቃላይ ወያኔ ያልበደለዉ፤ ያላሳቀቀዉ ወይም ተስፋዉን ያላጨለመበት የህብረተስብ ክፍል የለም። የገበሬዉ፤ የከተሜዉ፤ የነጋዴዉ፤ የወታደሩ ፤ የወጣቱና የምሁሩ ጠላት ወያኔ መሆኑን ካወቅን ዉለን አድረናል፤ ታዲያ ለምንድነዉ ይህንን የጋራ ጠላት በገራ የማናስወግደዉ? ከዛሬ በኋላ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በሚቆይባት በእያንዳንዷ ቀን የእኛ ስቃይና መከራ መብዛቱ ብቻ ሳይሆን ጥፋቱም የኛ መሆኑን አጥብቀን ልንረዳ ይገባል። ወያኔ እንደሆነ ቀንበር ለመሸከም የተመቻቸ ትከሻ ካገኘ ምን ግዜም ቢሆን ከመግዛት፤ ከማሰርና ከመግደል ወደ ኋላ አይልም። አልገዛም፤ አልታሰርም ወይም አትገድሉኝም ብሎ በወያኔ ላይ መነሳት የዚህ ትዉልድ ኢትዮጵያዉያን ሀላፊነት ነዉ፤ ይህ ሀላፊነት ደግም በህብረት ቆመን ለአንድ አላማ በአንድነት ከታገልን በቀላሉ ልንወጣዉ የምንችለዉ ሀላፊነት ነዉ። ሰለዚህ የዛሬም ጥሪ እንደትናንቱ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወያኔን ለማስወገድ ሀላፊነቱን ይወጣ የሚል ነዉ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!




    No comments: