Friday, June 27, 2014

በመቀሌ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃዉሞ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ ነው

June 26/2014

ሰኔ ቅዳሜ 21 ቀን ፣ በመቀሌ ከተማ የተቃዉሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተጠራ፣ የአረና አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታ ገለጹ። ሰልፉ በከተማዋ አስተዳደር እውቅና እንዳገኘ የገለጹት አቶ አብርሃ፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ከተሞች እንደታየው የመቀሌ ሕዝብ የሕወሃት ደጋፊ እንዳልሆነ የሚያሳይበት አጋጣሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።
«የትግራይ ህዝብ እስካሁን ድረስ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ ተነፍጎ ይገኛል። በአላማጣ፣ ኲሓ፣ አይናለም፣ መቐለ (ገፊሕ ገረብ)፣ ሓውዜን፣ ዓዲግራት ወዘተ ዜጎች ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ መክረው በፌደራል ፖሊስ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል። ስለዚህ ቅዳሜ ጥዋት ሰለማዊ ሰልፍ የሚጀመርበት ታሪካዊ ቀን ይሆናል። በመቐለ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ የተፈቀደ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ይደረጋል ማለት ነው» ያሉት አቶ አብርሃ ለሰላማዊ ሰልፍ አስተዳደሩ እውቅና መስጠቱ በራሱ ትልቅ ነገር እንደሆነ ገልጸዋል።
ሰልፉ ቅዳሜ ጥዋት በ3:00 ሰዓት ከአደባባይ ዘስላሴ (ባዛር) ተነስቶ በሓውዜን አደባባይ አልፎ ሮማናት አደባባይ አቋርጦ አብርሃ ካስትል ሆቴል ከደረሰ በኋላ ወደ ናሽናል ሆቴል ታጥፎ በጤና ጣብያ በኩል ላዕለዋይ ፍርድቤት ደርሶ ሮማናት አደባባይ ላይ በ 6፡00 ሰዓት ይጠናቀቃል።
ዉስጡን ዉስጡን ቅስቀሳ የተጀመረ ሲሆን፣ የአደባባይ ቅስቀሳ ነገ አርብ ቀን ሰኔ 20፣ ፖሊሶች ካላስተጓጎሉ እንደሚደረግም ታወቋል።
ከአንድ አመት በፊት በሚሊዮኖች ድምጽ፡ለነጻነት መርህ ሥር በመቀሌ ከተማ የአንድነት ፓርቲ ሰልፍ ጠርቶ እንደነበረ ይታወቃል። በወቅቱ አስተዳደሩ አስፈላጊዉን እውቅና ሰጥቶ ፣ በመቀሌ የአንድነት አባላት በአደባባይ ቅስቀሳ ካደረጉ በኋላ፣ ሰልፉ ነገ ሊደረግ ዛሬ ማታ፣ የአመራር አባላትን በሙሉ እንዲታሰሩና ለሰልፉ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች/መኪናዎች እንዲታገቱ በመደረጋቸው፣ ሰልፉ መስተጓገሉ ይታወቃል።

No comments: